ሆሣዕና
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሆሣዕና፡- በዚህ ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ቀን እናስባለን፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከጌታችን ፱ቱ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ከሌሊት ጀምሮ በታላቅ መንፈሣዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በሌሊቱና በዑደቱ ሥርዓት ላይ ብቻ ከዘጠኝ ያላነሱ ምስባኮች ስለሚደርሱ ሁሉን መተርጐምን ለጊዜው ታግሠን የትኞቹ እንደሆኑ እንድናውቅ ብቻ ማመላከቻ እንሰጣለን፡፡
ምስባክ፡-መዝ፹፥፫፤መዝ፻፲፯፥፳፮፤መዝ፻፳፩፥፩፤መዝ፻፵፯፥፩፤መዝ፻፲፯፥፳፯፤መዝ፱፥፲፩፤መዝ ፰፥፪፤መዝ፵፱፥፩፤መዝ፷፯፥፴፬
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ አራቱም ወንጌላውያን ተባብረው ጽፈውታል፡፡ በማቴ 21፥1-17፤በማር11፥1-10፤ሉቃ19፥29-38፤በዮሐ12፥12-19 በመሆኑም አንዱ ወንጌላዊ የመዘገበውን ብቻ የጽሑፋችን መነሻ ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ወንጌላት መዳሰስን መርጠናል፡፡
ጌታችን ራሱን ለዓለም ገልጦ ማስተማር ከጀመረ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይኽ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚሁም ጊዜ ቤዛነትን ፈጽሟል፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በአህያናበውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈፀም ነው፡፡
ትንቢቱ “ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ትን.ዘካ 9፥9
ምሳሌውም፡- በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመነ ጸብዕ(ጦርነት) መምጣቱን ለማመልከት በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታዩ፤ ዘመነ ሰላም መምጣቱን ለማመልከት ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ለአራተኛ ጊዜ የመጣው በደሙ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በመካከላችን ፍፁም ሰላምን(ዕርቅን) ለማድረግ ነውና ይህንኑ ሲያመለክት ነው፡፡ በመከራዬ፣ደሜን በማፍሰሴ፣በስቅለቴ፣በሞቴ ሰላም የሚሆንላችሁ ጊዜ ቀርቧል ሲለን ነው፡፡
“ፈትታችሁ አምጡልኝ ለጌታ ያስፈልጉታል”
ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ወደምትባል መንደር ሲደርስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ሲልክ የሰጣቸው ትዕዛዝ ነው፡፡ የታሠሩ አህያና የአህያይቱን ግልገል ሲያገኙ የሚያደርጉትንና ለሚጠይቋቸው የሚሠጡት መልስ፡፡
ነባቢት ነፍስ ያለችው ሰውም ሆነ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታት መታሠርን አይወዱም፡፡ምክንያቱም በተፈጥሮ ያገኙትን የመንቀሳቀስ መብት ይፃረራልና ነው፡፡መታሠር ነፃነትን፣ መታሠር ፈቃድን ይጋፋል፡፡ እኒያ እንስሳት የታሠሩበት የራሱ ምክንያት ይኖራል፡፡ እንስሳት እንዳይጠፉ፣ሌባ እንዳይሠርቃቸው ወይም የሚያጠፉት ነገር ሲኖር እንዳይደርሱበት ለማድረግ ይታሠራሉ ወይም በሌላ አነጋገር ነፃነታቸው ይገደባል፡፡
ሰውንም እንደአስፈላጊነቱ ከጥፋት ለመጠበቅ በሕግና በደንቦች ይታሠራል፡፡ አስተዋይ የሆነ በኅሊና ህግ ይጠበቃል፡፡ እኒህን ሁሉ ያልተጠቀመባቸው በቦታ እንዲገደብ ያደረጋል፡፡በሰው ላይ በጫና ሳይሆን በስምምነት የሚወጡ አብዛኛዎቹ ሕጎች ነፃነቱን አይነጥቁትም፡፡ በኅሊናው ሕግ የሚመራ ግን በአፍአ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ከሚኖርበት ሙግት ነፃ ስለሚሆን ፍፁም ሰላም ይኖረዋል፡፡ ከራሱ ከመሰሎቹ፣ከተፈጥሮና ከኒህ ሁሉ ገዢ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ህብረት፣ስምምነት፣ፍቅር፣አንድነት ይኖረዋል፡፡
ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ሲልክ “ ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱን መተርጉማን ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት(ከኃጢአት ማሠርያ) የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሠ ለማጠየቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ተመልከት)
ከእስራታቸው ተፈትተው ለጌታ ያስፈልጉታል እንደተባለ ጌታ ተቀመጠባቸው፡፡
- አዳምና ዘሩ ከሞት እስራት ነፃ ወጥተው የትንሣኤ ጌታ የሆነው የእርሱ ማደርያ ሆኑ፡፡
-አዳምና ዘሩ ሞትን ከሚያስከትል የሕግ እስራት ተለቀው፤ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ላወረደው አምላክ ዙፋን ሆኑ፡፡ በኦሪት የተሠጡን ትዕዛዛት ደገኛ ነበሩ፡፡ በማናቸውም ምክንያት እነዚያን ትዕዛዛት የሚተላለፍ ቢኖር ቅጣቱ በሞት ይፈፀማል፡፡ ይህም ሰውን ከሕጉ መልካምነት ይልቅ የቅጣቱን ክፋት እያሰበ በባርነት መንፈስ እንዲኖር አድርጎታል፡፡
ሰውም የእግዚአብሔርን አሳብ መረዳት ስላልቻለ ግንኙነታቸውን በፍርሃትና በሕግ ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሰብረው መውጣት የቻሉ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ሕጉን መተላለፍ በድንጋይ መወገርና በእሳት መቃጠልን ሳይሆን ከፍቅሩ መለየትን እንደሚያስከትል አስተማረ፡፡ አሁን ሕጉን የምንጠብቀው የሞት ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን የአባታችንን ፍቅር ላለማጣት ነው፡፡ ሕጎቹ አልተሻሩም ቀድሞም ደገኛ ሕግ ነበሩና፡፡ ጌታችን ያሻሻለው እኛ ለሕግጋቱ ያለንን ግንዛቤ ነው፡፡ ሕጉን የምንፈፅምበትን መንፈስ ነው በውስጣችን ያደሰው፡፡ሕጉ በፍቅር ይጠብቀናል እኛም ሕጉን በፍቅር እንፈፅማለን፡፡ የአዲስ ኪዳን መንፈስ የወንጌል የምስራች ይኸው ነው፡፡ ዮሐ 14፥15፣ዮሐ15፥9-11 ሮሜ 7፥1-20
ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “እግዚአብሔርን ስንወድ ትዕዛዛቱን ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድበዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፡፡ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” 1ዮሐ 5፥2-4
ፈታችሁ አምጡልኝ በማለቱ የእስር ሠንሰለታችን ተቆረጠ፡፡ ሞት በሰው ላይ የሠለጠነው ኃጢአትን ምክንያት አድርጎ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ዓለምን የገዛው ኃጢአትንና ሞትን መውጊያው በማድረግ ነበር፡፡ ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋህዶ ኃጢአትን ባለመስራት ኃጢአትን፤ በሥጋ ሞቶ በመነሣት ሞትን፤በደመሰሰ ጊዜ የዲያብሎስ ግዛት ፈረሰ፡፡ ምክንያት የሚያደርግ ኃጢአትን ነበርና ጌታችን ግን “የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች የለውም” በማለቱ የሰው ልጅ ለባርነት ምክንያት የሆነው የኃጢአት መርዝ እንደተወገዱለት አረጋገጠልን፡፡ ይህን የተናገረ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የሚጠራ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ዮሐ14፥30፤1ቆሮ 15፥54-57
ይህ ብቻ ያይደለ በጸሎት በተመስጦ ከዚህ ዓለም ጭንቅና ፈተና፤በፆምና በተጋድሎ ከፍትወታትና ከእኩያት፤እውነትን በማወቅ ከወግና ከልማድ ትብታብ መፈታትን አደለን፡፡ ጥንትም ሰው የተፈጠረ በገዢነት መንፈስ እንጂ በተገዢነት ሁኔታ አልነበረም፡፡ሰው ሁሉን ይገዛል እርሱ የሚገዛው ግን ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛትም ነፃነት ነው፡፡ ለጌታ እግዚአብሔር ከመገዛት በራቅን ቁጥር ራሳችንን መግዛት አቃተንና ከእንስሳት እንኳ በግብር አንሰን እስክንታይ ተዋረድን፡፡ ሕግጋት ይመሩን ይደግፉን ዘንድ ቢሰጡንም ለመፈፀም አቅም አጣን፡፡ በመሆኑም ሕግጋቱ ኃጢአታችንን እየገለጡ እንደገና ዕዳ ሆኑብን፡፡ ቅ.ጳውሎስ “ነገር ግን በህግ ባይሆን ኃጢአትን ባለወቅሁም ነበር” እንዳለ ሮሜ 7፥9-10
ጌታችን ሰውነታችንን በወደዳትና በተዋሀዳት ጊዜ ከጸጋው ብዛት የተነሣ ከሕግ በላይ አደረግን፡፡ ከጌታችን ጋር ፍፁም ህብረት ያደረጉ ሁሉ ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋው በታች ይሆኑ ዘንድ ተባለላቸው፡፡ በሕግ ቢኖሩም ሕግ እንዳለባቸው አያስቡም በጸጋው ይደነቃሉ እንጂ፡፡
ይህ ሁሉ ነፃ የመሆን የመፈታት ማሳያ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ ነው “በነፃነት እንድንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን” ያለው፡፡ ሮሜ 3፥21-31፤ሮሜ 6፥12-19፤ገላ 5-1
አስተውሉ “ፈትታችሁ ልቀቋቸው” አላለም “ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁም ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ”አለ እንጂ፡፡ ከኃጢአት፣ከዓለም፣ከምኞት፣ከወግና ከልማድ ወዘተ…መፈታትን ወደርሱ ቀርበን ማደርያው ለመሆን ከእርሱ ጋር ለመሆን እንጂ ልንባዝን አይደለም፡፡
ወደ ሕይወታችን የተላኩ ካህናት ከእስራት የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡የሚፈቱን ወደ ጌታችን ለማቅረብ ነው፡፡ ከጌታችን ጋር የምንዋሃደውም ቅዱስ ሥጋውንና ክብሩ ደሙን በመቀበል ነው፡፡ ማንም በራሱ ሥልጣን ከኃጢአት እስራት መፈታት አይችልም፡፡ በራሴ ወደ ጌታ እቀርባለሁ በማለት የድፍረት ቃል መናገርም የተገባ አይደለም፡፡ እነሆ ሂዱ በማለት የሚፈቱንን የመንግስቱን ካህናት ልኳል፡፡ እነርሱም ከኃጢአት የምንፈታበትን ትምህርት ሥርዓት ጸሎትና ሥልጣን ይዘው እንፈታ ዘንድ ይጋብዙናል፡፡ ለምን? ለሚል መልሳቸው ለጌታ ታስፈልጉታላችሁ! ነው፡፡ ማቴ 18፥18፤ዮሐ 20፥23
ሰው ሆይ የተሰጠህን ክብር ተመልከት፡፡ ፍጡር ሳይኖር በፈጣሪነቱ፤ተገዢ ሳይኖር በአምላክነቱ፣ አመስጋኝ ሳይኖር በአኰቴቱቅድመ ዓለም ነግሦ ለሚኖር፤እልፍ አእላፋት ወትልፊት አእላፋት መላእክት፤የሚታየውና የማይታየው ሁሉ ለሚገዛለት ለእርሱ ታስፈልጉታላችሁ መባላችን እንዴት ያለ ክብር ነው?፡፡ ፈጣሪነቱ በእኛ ታወቀ አንል ከእኛ ይልቅ ብዙ ፍጥረት ተዘርግቷል፤ያለእኛ ተገዢነት ጌትነቱ አይሟላም እንዳንል ሳንፈጠርም በጌትነቱ ኑሯል፤ ታዲያ “ለጌታ ያስፈልጉታል”መባላችን ስለ ምንድር ነው?/ቅዳሴ ዲዮስቆርስ/
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ልዑሉ ሲናገር “የእኛ ሕዝብህ መሆን ላንተ አያስፈልግህም ያንተ ጌትነት ለእኛ ያስፈልገናል እንጂ፤የእኛ ልጅነት ላንተ አይጠቅምህም ያንተ አባትነት ለእኛ ይጠቅመናል እንጂ” በማለት ገልፆታል፡፡ አባትነቱ በእኛ ልጅነት አይደነቅም፤ጌትነቱም በእኛ ተገዢነት አይከብርም፡፡ ዛዲያ “ታስፈልጉኛላችሁ” መባሉ ስለምንድር ነው?
እንመርምረው ዘንድ አይቻለንም! መልስ እናገኝለት ዘንድም ቅጥነተ አእምሯችን አይወስነውም! እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለ ርኅራኄስ እንደምን ያለ ርኅራኄ ነው ብለን ከማድነቅ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?/ ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ/
ጌታ ሆይ ልትፈልገን መጥተሃልና፤ታስፈልጉኛለችሁ ብለህም በክብር ጠርተኸናልና፤በአፈ አበው ቀደምት፣በልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት፣ጻድቃን ወሰማዕታት፣አእሩግ ወሕፃናት፤በአኰቴተ መላእክት ወሊቃናት እናመሰግንሃለን፡፡ ምስጋናና ክብር ኃይልና ባለጠግነት ጌትነትም በመታረዱ ለፈለገን ለበጉና ለአባቱ ለመንፈስ ቅዱስም ይገባል መቼም መች ለዘላለሙ አሜን! ራዕይ 4፥6-14
ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ ይመጣል
ለጽዮን ንጉሷ እንዲሚመጣ በአፈ ነቢያት ተነግሯታል፡፡ የሚመጣው ግን እንደነ ሰሎሞን በዝሆን ጥርስ በብርና በወርቅ ባጌጠ፤በሀምራዊ ግምጃ በተሸፈነ ሠረገላ ሳይሆን በአህያና በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ የዋህ ሆኖ ነው፡፡
የዋህ የሚለው ኀዳጌ በቀል መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጌታችን የመጣው አንገተ ደንዳና ወደ ሆነ የነቢያቱንና የካህናቱን ደም ወዳፈሰሰ ሕጉንም በወግና በልማድ ወደ አፈረሰ ሕዝብ ነው፡፡ መጻሕፍቱን የነቢያቱንም ቃል ያነባሉ ለመቀበል ግን አይፈልጉም፡፡ ምንም እንኳ ሰይፈ በቀል በእጁ ቢሆንና ፍርድ ቢገባቸውም ሰው የመሆኑ ዓላማ ሁሉን ለማዳን እንጂ በአንድ ስንኳ ለመፍረድ ስላልሆነ በየዋህነት ተገለጠ፡፡ የነቢያትን ደም ባፈሰሰ እጃቸው የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ በመስቀል ሰቅለው ጽዋቸውን ቢሞሉም “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለቱ የምህረት እንጂ የበቀል ጊዜ አለመሆኑን አሳያቸው፡፡ የምህረት የይቅርታ ጊዜ አለ፤ከወዳጆቹ ከነቢያት ጀምሮ ላፈሰሱት ደም የበቀል ጊዜ ደግሞ ይኖራል፡፡ ዮሐ 3፥16፤ማቴ21፥33-46፤ማቴ 23፥29-36
“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው”
ሆሣዕና በዕብራውያን ቋንቋ “አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” የሚል ትርጉም አንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ሆሣዕና የሚለው ቃል ሰው ሲደነቅ ወይም ሲደሰት ከሚያወጣው ድምፅ ጋር በማመሳሰል በሌላ ቋንቋ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው እንደማይቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱም ትርጓሜ አይጣላም፡፡
አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው ቢሉ ጉዞው ወደ መስቀል ነበርና እውነተኛ መድኃኒትም እርሱ ነውና የተገባ ምስጋና ነው፡፡
ቃለ አንክሮ ቃለ ትፍስሕት ነው ቢሉም በዚያ የተሰበሰቡ አብዛኞቹ ያደረገውን ተዐምራቶች እያወሱ ይመሰክሩም ስለነበር፡፡ አንድም ከነበረው የአቀባበል ሁኔታ አንድም እንደ ኢትዮጵያ ሊቃውንት ትርጓሜ የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት ይታይ ነበርና አድናቆቱ የተገባ ነው፡፡
ሆሣዕና እያሉ የሚያመስግኑት ሁሉ“የዳዊት ልጅ” እና “ጌታ” ብለው ጠርተውታል፡፡ በዚህም የዳዊት ልጅ በማለታቸው ፍፁም ሰው መሆኑን አንድም“እግዚአብሔር ማለ አይፀፀትም ከወገብህ ከሚወጣ ከዘርህ በዙፋንህ አኖራለሁ” የተባለው ትንቢት መፈፀሙን ያጠይቃል፡፡አይሁድም በገዛ አፋቸው ክርስቶስ ማነው? ብሎ ሲጠይቃቸው የዳዊት ልጅ ነው ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ አሁን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ላለማመን ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ 2ሳሙ7፥12-14፤ማቴ22፥41-46
በ“ጌታ” ስም የሚመጣ ማለት እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሎ የሚመጣ የተባረከ ነው ብለዋል፡፡ አይሁድ “YHWH” የሚለውን በአብዛኛው የሥነ-መለኮት ሊቃውንት “ያህዌ” የሚል ግምት የሚሠጠውን በኮሬብ ለሙሴ የተገለጠ ስመ አምላክ ለመጥራት ሰለማይደፍሩ “Adonai” ወይም “ጌታ” በሚል ቀይረውታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጌታ የሚለው ቅፅል በቀጥታ ለእስራኤል አምላክ የሚነገር በመሆኑ “በጌታ ስም” “የሚመጣ” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ገልፀዋል፡፡ ማቴ 22፥41-46
ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በዕለተ ሆሣዕና ይመሰክሩ የነበሩ መጻሕፍት አንብበው ከሊቃውንት አፍ ተምረው ትንቢት የተረጎሙ ሱባዔ የቆጠሩ አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጭምር ነበሩ፡፡ አይሁድንም ይበልጥ ያስቆጣው ህፃናቱ ያመሰገኑበት መንፈስ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ተዐምር ነውና፡፡
ምንጊዜም ንፁህ ምስጋና ፣ ንፁህ ጸሎት፣ንፁህ መሥዋዕት፣ንፁህ ልቡና፣ ንፁህ አገልግሎት ይበልጡንንፁህ ሕይወት አጋንንትን፣ ክፍዎችን፣ ተንሎለኞችን፣ ተረፈ አይሁድን፣መናፍቃንን፣ አረማውያንን ያስቆጣል፡፡ ይህ እንዲቋረጥ የማያኖሩት እንቅፋት የማይፈፅሙት ድርጊት አይኖርም፡፡ ንጹሐ ባህርይ ከሆነው ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ በንፁህ ህይወት የኖሩ በንፁህ አገልግሎት የፀኑ ሁሉ ተገፍተዋል ተዋርደዋል፤ለሞትም ወደ መታረጃቸው ተነድተዋል፡፡ ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ንፁህ ሁን በዓለም ወደ ኋላ ትቀራለህ ትዋረድማለህ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ግን ትቀድማለህ ትከብርማለህ፡፡ ማቴ 14፥1-4 ዮሐ15፥18-21
ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁሉ ይዘው የተቀበሉት የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ወደ መስቀል የሚወጣ ለድል ነውና፡፡ ይህ ሁሉ የሰው አቀባበልና ምስጋና ጌታችንን ለአመል ከዓላማው አላዘናጋውም፤ ለመጣባት ለዚያች ሰዓት አዘጋጀው እንጂ፡፡ አድናቆት ሊያጅበን ምስጋና ሊነጠፍልን ይችላል፤ዓላማችን ምን መሆኑን ግን ልንረሳ አይገባንም፡፡ ከሰዎች ክብርን ብንቀበል ከእግዚአብሔር ከሆነው ክብር ከተጣልን ምን ይጠቅመናል፡፡ ሊጠቀምብህ የሚፈልግ ያወድስሃል ሊጠቅምህ የቆረጠ ግን ይገሥፅሃል፡፡ ወዳጀህን መምረጥ ያንተ ድርሻ ነው፡፡
የአይሁድ ሊቃናት እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻለችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል“ ይባባሉ ነበር፡፡ ቅንዐት ጥላቻን ይወልዳል ጥላቻ ደግሞ ሞትን፡፡ ጌታችን እንደቃሉ ወደ ትክክለኛዋ ሰዓት ቢመጣም በቁሙ ሲታይ ግን የሆሣዕና ትዕይንት በአይሁድ ሊቃናት ላይ ያሳደረው ቅንዐትና ቁጣ በሞቱ ላይ እንዲቆርጡ በከፍተኛ ሁኔታ አነሣስቷቸዋል፡፡እርሱ ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንደ ሰዓቱ ደርሶአል፡፡እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ብትሞትም ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች”በማለት በሞቱ ይበልጡ ብዙዎችን እንደሚያድንና ወደ ራሱ እንደሚስብ ነግሯቸዋል፡፡
የእግዚአብሔር መንግስት ከጥንት ጀምሮ የሚጋፏት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን ከመጨመር ልዑለ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከመከተል አላስቆሙትም፡፡ ገና በሃይማኖቱ ጠንክሮ እየቆመ በኅሊና ትንሣኤ ኃጢአትን ድል አድርጎ እየዘመረ ይከተለዋል፡፡ የታመነ መሪ ነውና፡፡“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ መከተል ማለት በግብር መምሰል በአርአያነቱ መጽናት ነው፡፡ በህይወታችን በኑሮአችን ከመሰልነው በሞቱ እንመስለዋለን በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን፡፡ ክርስትና ማለት ቅሉ ይኸው ነውና፡፡ የበዓሉ ጌታ ቸርነቱ ይደረግልን! ማቴ11፥12፤ዮሐ10፥1-18፤ሮሜ 6፥5
ይቆየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት