Login
Main menu

...በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ብፁዕ ነው፡፡ መዝ ፩፡፩

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

      በክፉዎች ምክር ያልሄደ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ ብፁዕ ነው፡፡ መዝ ፩፡፩

በመዝሙረ ዳዊት የተመሰገኑ ጠባይዓትንና አካሄዶችን አመለካከቶችንና ተግባራትን “ብፁዕ” በሚል የውዳሴ ቃል እያጀበ ተቀኝቶ እናገኛለን፡፡

ብፁዕ የሚለው ቃል “በፅዐ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የሚወጣ ሲሆን የተደነቀ የተመሰገነ ንዑድ ክቡር የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡

ከላይ በተቀመጠው ጥቅስ ክቡር ዳዊት ሦስት አንድን ሰው ወደ ጥፋት የሚወስዱ ጉዳዩችን አንስቶ ከእነርሱ በተቃራኒ የሚገኝ ቢኖር ንዑድ ክቡር ነው ይለናል፡፡

ቀዳሚው በክፉዎች ምክር ያልሄደ ብፁዕ(ምስጉን) ነው ይላል፡፡ ምክር አንድን ሰው ክፉውን ጠባይዕ እንዲተው መልካሙን ደግሞ እንዲያፀና አስነዋሪ ተግባር የበጀ መስሎት የሚኖር ካለ እንዲመለስ፤ የተወደደ ሥራ ለመሥራት መንገድ የጠፋውንም ለማመላከት የሚለገስ የፍቅር የበጎነት መግለጫ ነው፡፡ ሰው የሚመክረው የሚያፈቅረውንና የሚጠነቀቅለትን ነውና፡፡

የገንዘብ ልግስና ራቁት ይሸፍን ረሃብ ያስታግስ ይሆን እነጂ ከክፉ ጠባይ ሊመልስ አይችልም፡፡ ቀና መንገድም አያመለክትም ገንዘብ፡፡ ጊዜያዊ ምክር ግን ቀዋሚ ስጦታ ነው፡፡

በተቃራኒው ክፉ ምክር ደግሞ ሰውን በነፍስ በሥጋ በአሁኑም ሆነ በዘላለማዊው ዓለም ሊያጠፋው ይችላል፡፡የክፉ ምክር መዝገቡ ክፉ ልብ ነው፡፡ ጌታም በወንጌል ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ሊያፈራ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ሊያፈራ እንደማይችል አስተምሯል፡፡ ጨምሮም ሰውን የሚያረክሱ ክፉ አሳቦች ሁሉ መዝገባቸው ክፉ ልብ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል ማቴ 7፤ ማቴ 15፡፡ በመሆኑም ምክር ሁሉ እንደ መካሪው ማንነት ይወሰናል፡፡ በሕይወት ጉዞ ሰው ክፉም መልካም መካሪ ሊገጥመው ቢችልም በዚያ ተምስርቶ በሚሠራው ሥራ ወይም በሚገልጠው ጠባይ የሚወደሰውም ሆነ የሚነወረው ፤የሚሸለመውም ሆነ የሚቀጣው ራሱ ነው፡፡

ንጉስ ዳዊት በቃሉ ክፉ መካሮች እነዳሉ ከገለጠ በኋላ ብፁዕ የሚባለው ግን በነዚያ ምክር ፈቅዶም ሆነ ተታሎ ያልሄደ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ታሪክ በክፉ ምክር የተጎዱ የብዙ ሰዎችን የሕይወት ተሞክሮ በዋቢነት ዘግቦ ይዟል፡፡

. የእናታችን ሔዋን በምክረ ከይሲ መመራት በራሷም ሆነ በዘሯ በመከራ ለመጎብኘታቸውና በሞት ለመዳኘታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ መካሪ ምክሩን የሚጀምረው ጉዳያችንን /ምሥጢራችንን/ ከመስማት ነውና በመጀመሪያ ለማን ምን መንገር እንዳለብን ማስተዋል ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የሔዋንና የአዳም በደል/ኃጢአት/ ባህርያዊ ያይደለ በክፉ ምክር ተታለው የፈፀሙት ቢሆንም ከመቀጣት አልዳኑም፡፡ ወደ ቀደመ ክብራቸው የተመለሱ በልጅ ሞት ተክሰው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስለ ወላጅ በደል የልጅ ሞት ምን ያህል ይከብድ፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው በወላጆች ጥፋት ልጆች በቀደምት በደል ደኅርት መቀጣታቸው፡፡

ሔዋን እንደ ርዕስ ተነስቶ ምክርና ማስጠንቀቂያ ባልተሠጠበት ጉዳይ ላይ ቢሆን ኖሮ የሳተች ባልፈረድንባት ነበር፡፡ ነገር ግን መልካምነቱን የምታውቀው የአባትነት ድምፁን የለመደችው በእጁ ከመፍጠር አንስቶ ሁሉ እድትገዛ የሠጣት ጌታ እግዚአብሔር የመከራትን ምክር ማንነቱን በማታውቀው ለእርሷ ሕይወት ምንም አስተፅኦ ባልነበረው ባዕድ (እንግዳ) በአንዲት ቅፅበት ንግግር የብዙ ዓመቱን የፍቅር ግንኙነት ማቃለሏ ጭምር በብዙ ያስወቅሷታል፡፡

በመሆኑም ሲጀምር መካሪም ማን መሆኑን ሲቀጥልም ምክሩ በጉዳዩ ላይ አስቀድመን ከሰማናቸው አስተያየቶችም ሆነ ማስጠንቀቂያዎች ጋር ያለውም ተዛምዶ ወይም ተቃርኖ ፈትነን መጓዝ ከኛ የሚጠበቅ ዓይነተኛ ተግባር ነው፡፡ ሰው የሚያስበው የሚናገረው የሚወስነው የሚሰራው ወዘተ ለራሱ ብቻ አይደለም ውጤቱም በራሱ ብቻ አይቆምም፡፡ ላለፈ ትውልድ ታሪክ ለሚመጣውም ደኅንነት ትልቅ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡ የኛ ሕይወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የብዙዎች ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክር እንዲሁም ተግባር ውጤት ነው፡፡ የኛም ተጽእኖ በሌሎች ላይ እንዲሁ ነው፡፡ በእኛ የአካልም ሆነ የመንፈስ አብራክና ማህፀን ውስጥ ብዙ ልጆች ሳይሆን ትውልዶች አሉ፡፡ ዛሬ በክፉ ምክር ስተን የምንፈፅመው ተግባር በርካታ ትውልድን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በመልካም ምክር ተመስርተን የምንሰራው ሥራም ለትውልደ ትውልድ ጥቅም ይውላል፡፡ ብዙዎቹም ይታነፁበታል፡፡ ስለነቢዩ ዳዊት ልጆችም እንዲህ ተጻፈ፡፡

ለ. የንጉስ ዳዊት የበኩር ልጅ አምኖን በአባቱ በኩል እህቱ የሆነችውን ትዕማርን በማፍቀሩ ምክንያት ትካዜ በዛበት፡፡ እህል የማይበላ ከመሰሎቹም ጋር የማይጫወት ስሜቱን እያሰታመመ የሚቆዝም ሆነ፡፡ ይህን የተመለከተ ኢዮናዳብ የተባለ ጓደኛውም የንጉሱ ልጅ በምን ምክንያት ደስታ እንደራቀው በጠየቀው ጊዜ በውስጡ ያለውን እረፍት የነሳውን ስሜቱን ተረከለት፡፡ የኢዩናዳብ ምክርም “ታምሜያለሁ ብለህ ተኛ ንጉሱ ልጆቹን ይወዳልና ሊያይህ ይመጣል በዛን ጊዜ ትዕማር ከእጇ እንድበላ ወደኔ ትመጣ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን ብለህ ጠይቀው በዛን ጊዜ የወደድከውን ትፈፅማለህ” የሚል ነበር፡፡ አምኖን እንደተመከረው አደረገ ትዕማርም ባባቷ በንጉስ ዳዊት ወንደምሽ ታሟልና ተንከባከቢው የሚል መልእክት ደረሳት፡፡ ትዕማር የሚበላው ልታቀርብለት ወደ እልፍኙ ስትገባ ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንደ ግድ አላት ትዕማር “ወንድሜ ሆይ አይሆንም እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባም እና አታሳፍረኝ ይህን ነውረኛ ሥራ አታድርግ እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምቴዎች እንዳንዱ ትሆናለህ፡፡ እንግዲህስ ለንጉሱ ንገረው እኔንም አይነሳህም ” 2ሳሙ 13፡1-ፍፃሜ በማለት የመከረችውን አልሰማትም፡፡ ከክብር አሳነሳት የንጉስ ዳዊትን፣ የራሱን፣ የትዕማርና ባጠቃላይ ለቤተሰቡና ለእስራኤል ኃፍረት የሆነ ነውርን ፈፀመ፡፡ በዚህ ሳያበቃ ወትሮም ዝሙት በፍቅር ለምድ ተጀቡና ቀርባው ነበርና ሲያልፍለት ከቀደመው የከፋ በደል ፈጸመ፡፡ መጽሐፍ አምኖን ትዕማርን “ቀድሞ ከወደዳት ውድ ይልቅ ኋላ የጠላት ጥል በለጠ” እንዲል በጉልበት ካስነወራት ከክብርም ካሳነሳት በኋላ በታላቅ ውርደት ከቤቱ አስወጥቶ አባረራት፡፡

ክርስቲያኖች የዝሙት መልኳ እነሆ ይህን ይመስላል፡፡ ፊት ታጣድፋለች መብልና እንቅልፍ በመንሳት እረፍት አሳጥጣ ታስጨንቃለች፡፡ ኅሊናችን በትክክል እንዳያስብ በስሜት ግርዶሽ ታጨልመዋለች፡፡ በዚህ ላይ ለዝሙት የሚያበረታታ የሚፋፋ ክፉ መካሪ ሲያጋጥም መጨረሻዋ መራር ይሆናል፡፡

በዝሙት በተወጠረ ኅሊና ዘንድ ፍቅር አትታወቅም፣ትዕግስትም ሥፍራ የላትም፣ራስን መግዛት ምውት ናት፡፡ በመተቃቀፍ ውስጥ ፍቅር የለችም ጊዜያዊ ስሜት እንጂ፡፡ አንዱን የእንዱን አካል ማክበር አይታሰብም ተራ መጠቀሚያ አድርጎ ከመቁጠር በቀር፡፡

እህቶች ሆይ በክፉ ኅሊና ከሚያደባ በልዝብ ምላስ ከሚሸነግል በመጎምዥት ዓይን ከሚያይ ተጠንቀቁ፡፡ በማን እልፍኝ እንደተገኛችኁም አስተውሉ፡፡

ትዕማር በንፅህና ሙሽራዋን የምትጠብቅ የክርስቲያን ነፍስ ትወክላለች፡፡ ድንግልና በሥጋ ላለ ንጽህና ማሳያ ነውና፡፡ አምኖን የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ይህች ዓለም እኛን በሥጋ ፍቃድ አጥምዳ በኃጢአት እስክትጥለን ድረስ ዕረፍት የላትም ክብራችንን ከጣልን በኋላ ግን ትከፋብናለች፡፡ ኢዩናዳብ የዲያብሎስ ምሳሌ ነው የዚህ ሁሉ ሴራ አቀናባሪ ነውና፡፡ በዓለም ከሚሠራው ኃጢአት፣ተንኰል፣ክፋት፣ዝሙት፣ጥላቻ መከዳዳት ወዘተ…ጀርባ ያለው ክፉው የዲያብሎስ ምክር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

ብዙዎች ወደ ዓለም እልፍኝ በክብር ገብተው በውርደት፤በሳቅ ገብተው በለቅሶ፤በዕልልታ ገብተው በዋይታ፤በሙላት ገብተው በጉድለት ወጥተዋል፡፡ አምኖን “እኅቴ” እያለ ይነጋገራት እንዳልነበር ፈቃዱን ከፈጸመ በኋላ “ይህቺን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት” በማለት ጭካኔውን ገልጿል፡፡ ዲያብሎስ ማንንም በክቡር ማማ ላይ ሲያወጣ በመልካም ሲያነጋግር ለእኔ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው ብሎ ካሰበ የመጨረሻው የሞኝነት እርከን ላይ መቆሙን ይወቅ፡፡ ከዝንብ ማር እንደማይገኝ ከዲያብሎስም ርኅራኄን አትጠብቅ፡፡እርሱ ፍቅርን ማወቅም መፈጸምም የሚሻ ፍጥረት አይደለም፡፡

ትዕማርም የንጉስ ልጆች ደናግላኑ የሚለብሱትን ብዙ ኅብር ያለውን ልብሷን ቀዳ በራሷ ላይ አመድ ነስንሳ እጅዋንም ራሷ ላይ ጭና እያለቀሰች ሄደች፡፡

በብዙ ኅብር ያጌጠ ልብስ የተባለ በብዙ ሀብታት(ጸጋዎች) የከበረ በንጉስ ልጅ ማዕረግ የተደነቀ ተፈጥሯችንን ያመለክታል፡፡ በክፉ ምክር ግን ይህ ሁሉ ይጠፋል፡፡

ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት መበለት ሆና ተቀመጠች አምኖንም ከሁለት ዓመት በኋላ በአበሴሎም የቂም ሰይፍ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡

. አምኖን በእህቱ ላይ በሠራው በደል የተበቀለው አቤሴሎም በተራው እስራኤል በተሰበሰቡት በፀሐይ ፊት አባቱ ንጉስ ዳዊትን ለማዋረድ ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ፡፡ ይህን ታላቅ ኃጢአት ያለ ኃፍረት ይፈጸም ዘንድ ያነሳሳው ክፉ መካሪው አኪጦፌል ነበር፡፡ እርሱም በተራው ክፉ አሟሟት መጨረሻው ሆነ፡፡

እኒህ ሁሉ ታሪኮች የሚያሳዩን በክፉዎች ምክር መሄድ ለገሚሱ የሕይወት ምሬት ለተከታዩም መራር ፍጻሜ እንደሚያስተከትል ነው፡፡

ክቡር ዳዊት ንጉሱ ሳኦል ነፍሱን ሲሻ ካንዴም ሁለቴ ለመግደል የሚያሰችለው አጋጣሚ ቢመቻችለትና ዙራውያውን ያሉ መካሪዎችም እጁን እንዲያነሳ ቢጎተጉቱትም “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄንን አላነሳም እንደ ቅንነቴ ይመልስልኛል” በማለት ክፉ ምክራቸውን አልተቀበለም በዚህም “እንደ ልቤ” እስከ መባል በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ አግኝቷል፡፡

ማጠቃለያ፡- ምክር ሰምቶ ለሚፈጽማት መልካም መሆኗ አሌ የማይባል ሀቅ ቢሆንም የምክሩን ዓይነት ግን ከእነዚህ ሕግጋት ጋር የማይጣረስ መሆኑን ማስተዋል ያሰፈልጋል፡፡

፩. የተፈጥሮ ሕግ፡- የተደነቀው ተፈጥሯችን ያለ ሕግ አልተሠራም፡፡ በዙሪያው ካሉ ሌሎች ፍጡራን ጋር በኅብረት እንዲኖር የሚያደርገው የመደጋገፍና የድኅንነት ሕገጋት አሉ፡፡ በአጠቃለይ በግላዊ ተፈጥሯችን ላይም ሆነ ከሌሎች ጋር በሚያስተሳስረን የተፈጥሮ ቀመር ጋር የሚጋጭ ምክርና ተግባር በዚህ ምድር ያለንን ቆይታ ያዛባዋል፡፡ ተፈጥሮን በሠራት ዘንድን ያስጠይቀናል፡፡ ዛሬ በሥልጣኔ ወይም በነጻነት ስም ከተፈጥሮ ባህርይ ውጪ የሚፈጸሙ ብዙ አስነዋሪ ተግባራት እንደ መልካም የመብት ጥያቄ በየመድረኩ ሲነሱና የወራዙትን ሕሊና በሚማርክ መልኩ ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ዘመናዊው ሚዲያ የማኅበረሱቡን የሥነ-ምግባር ዕሴቶች ጠብቆ የማቆየትና ለትውልድ የማስተላለፍ ሚናውን ዘንግቶ ንግድ ላይ ያተኮረ በመሆኑም ለወጣቶቹ ሕይወት ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ተቀርጿል፡፡ ዛሬ ዋጋ እያሰከፈለን ያለው የዚህ ሁል ድምር ውጤት ነው፡፡

፪. የማኅበረሰብ ሕግ፡- ማንኘውም ሰው ማንነቱ ተቀርፆ የሚመጣው በዚህ እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ የመጠበቅና ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ከማኅበረሰብ መገለል ወይም አንደ ሥርዓት አልባ መቆጠር ከዚህ በተቃራኒው ከመሆን  የሚመጣ ነው፡፡

. አምላካዊ ሕግ፡ የተፈጥሮም ሆነ የማኅበረስብ  ሕግ ወይም ሌላ ሕገጋት መነሻቸው አምላካዊ ሕግ ነው፡፡ እንደ ክርስቲያን የምንሰማው ምክር ሁሉ የሚመዘነው ከዚህ አንፀር ነው፡፡ ከአምላካዊው ሕግ በተቃራኒ የሚቀርብ ምንጩ ከክፉ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ የአምላክ ሕግ የአምላክ ምክር ለሁሉ እርምጃችን ሚዛን ነው፡፡

ሰው ይህንን ሁሉ በማስተዋል በክፉዎች ምክር ከመጓዝ ቢቆጠብ በሥጋውም ሆነ በነፍሱ ደኅንነቱ በዙሪያው ላሉ መሰሎቹና በተፈጥሮ ለሚዛመዱት ሁሉ የደስታና የሰላም ምንጭ ይሆናል፡፡ ትናንትን በፀፀት ዛሬን በኃፍረትና በንዴት ነገንም በፍርሃት የሚያስተናግድ ሕይወትም አይኖረውም፡፡ ስኬታማ ሕይወት ይሏል ይህ ነው፡፡

ይቆየን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

ሕዳር ፳፻፮ ዓ.ም

Read more...

በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ብርታትና ድካም፣ ማግኘትና ማጣት፣ስኬትና ውደቀት፣ ሰላምና ሁከት፣ ጤናና ህመም ሲፈራረቁብን ከረምን፡፡ የመጡትን በመቀበል ደስታና እንደየ ሥራቸው የተጠበቀላቸውን ለመቀበል በሞት ወደ ጌታ የሄዱትን በመሸኘት በሀዘን ስሜታችን ሲቆስልና ሲፈወስ ሲያር እና ሲታደስ ባጅተን አዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ላደረሰን አምላካችን ሸክላ ሕይወታችን ጥላ መሆኑን ዘንግተን ዛሬም እንደ አምና አዲሱን ዓመት በአሮጌ መንፈስ ለመቀበል ለተቃረብን ሁሉ የጌታ መንፈስ ቅዱስ መልዕክት እነሆ፡፡

‹‹በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› ሉቃ 13፡6-9

በአንድ ወቅት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በማስተማር ላይ ሳለ ጲላጦስ በመሠዊያው ላይ በሰይፉ አርዶ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለደባለቀው ሰዎች ዘግናኝ ፍጻሜ ሊነግሩት ጀመሩ፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ሰዎችና በሰሊሆም ግንቡ ተንዶባቸው የሞቱ ሰዎች ሁሉ ከእናንተ ይልቅ ኃጢአት የሠሩ ይመስላችኋል፤ ንስሓ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ በማለት አስጠንቅቋል፡፡

ተፈጥሮአዊ በሆነ ሁኔታም ሆነ አሰቃቂ በሆኑ ሰው ሠራሽ አደጋዎች ብዙ ሰዎችን ከኋላችን ትተን ጽድቅና ኃጢአት ከሚፈራረቁበት መሬት ሥር ቀብረን እኛ ቆመናል ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ነገርግን አዚህ የመደረሳችን ምስጢር እኛ ከእነርሱ ተሽለን መገኘታችን ይሆን?

ጌታችን ለጥቆ በወይኑ እርሻ ተተክላ ሦስት ዓመት ሙሉ ፍሬ ስላልተገኘባትና እንድትቆረጥ ከተሰጠባት ትዕዛዝ በወይኑ አትክልተኛ ጸኑ ልመና ሰለዳነች በለስ ማለፊያ የሆነ ምሳሌ በመስጠት የእኛን እዚህ የመድረስ ምስጢር ገልጾልናል፡፡

የወይኑ ባለቤት በለሷ ሦስት ዓመት ባለማፍራቷ እንድትቆረጥ ትዕዛዝ የሠጠው በርሷ አለማፍራት ብቻ ሳይሆን ምድሩንም እያጎሳቀለች በመሆኗ ጭምር ነበር፡፡ የወይኑ አትክልተኛ ግን በጌታው ፊት ቀርቦ ዙሪያውን እስክኮተኩትላትና ፍግ እስካፈስላት በዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት ወደፊት ብታፈራ ፣መልካም ነው ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ በማለት ከመቆረጥ አድኗታል፡፡

መተርጉማን አንድ ሰው የተባለ ጌታ እግዚአብሔር፣በለስ የተበሉ ቤተ እስራኤል፣ የወይን እርሻ የተባለች ቤተመቅደስ የታነጸባት ኢየሩሳሌም፤ ሦስት ዓመት የተባለ ዘመነ መሳፍንት፣ዘመነ ነገሥት ዘመነ ካህናት መሆኑን ያትታሉ፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ተስፋ በተሰጣቸው ሕግ በተሠራላቸው በእስራኤል ዘንድ ሃይማኖት ምግባር አገኝ እንደሁ ብሎ በብሉይ መምህራን አድሮ ቢመጣ አጣባቸው፡፡

መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልን ለሌላው ክፉ አብነት ሆነው እንዳያስጎዱ አጥፋቸው ብሎ ቢናገርም ቅዱስ ሚካኤል ተራድቼ ምግባር እስካሠራቸው ታገሥ ብሎ በለመነው ልመና ለመትረፋቸው ምሳሌ ነው፡፡ በፋርስ፣በባቢሎን፣የገጠማቸው ስደት ጨርሶ አላጠፋቸውምና፡፡

አንደም አንድ ሰው የተባለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በለስ የተባሉ አይሁድ፣ ሦስት ዓመት የተባሉ ጌታ በሥጋ ተገልጦ ያስተማረው ሦስት ዓመት ነውና ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ዓይተውከክፋታቸው መመለስ መልካም ፍሬ ማፍራት ስላልቻሉ የወይኑ አትክልተኛ የተባለው መጋቤ አዲስ ቅዱስ ገብርኤልን አጥፋቸው ቢለው ምንም እንኳ በጥጦስ ቢማረኩም ፈጽሞ ከመጥፋት አማልዶ እንዳዳናቸው የሚያሳይ ነው፡፡

አንድም አንድ ሰው የተባለው ጌታ በለስ የተባልን በስሙ አምነን የተጠመቅን ክርስቲያኖች ነን፡፡ ሦስት ዓመት የተባለ የሰው የእድሜው ዘመናት ናቸው፡፡ ይኸውም ሕጻንነት፣ውርዝውናና ዕርግና ናቸው፡:፡ ጌታ በእነዚህ የእደሜ ዘመናችን ሁሉ መልካም ፍሬ አፍርተን እንገኝ ዘንድ ይጠብቅብናል፡፡ እንድም በሦስቱ ክፍላተ ጊዜያት በነግህ፣በሰርክ፣በሌሊት መልካም ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ ባለን ጊዜ ጠባቂ መልአካችንን ነፍሳችንን ከሥጋችን እንዲለይ ‹‹ቁረጣት›› ብሎ ማዘዙን ያሳያል ጠባቂ መልአኩ ግን ጌታ እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሓ እንዲሰጠን ‹‹ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት›› በማለት ይለምናል፡፡

ጠባቂ መልአኩ ‹‹ በዚች ዓመት ደግሞ›› ማለቱ ተመሳሳይ ልመና ብዙ ጊዜ ማቅረቡን ያመላከታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ልመና ቅዱሳንንና መላእክት ምን ያህል ጊዜ አቅርበውልን ሕይወታችንን ታደገዋት ይሆን?

በተጨማሪም የወይን ጠባቂው ካህናትን ይወክላል፡፡ የእምነት ፍሬ ያልታየባቸውን የስም ክርስቲያኖች ለሌሎቹ መጥፎ አርአያ እንዳይሆኑ ከምእመናን አንድነት ለይዋቸው በተባሉ ጊዜ እንደ መኮተኮት ፍግ እንደማፍስስ መክረን አስተምረን መልካም ሥራ እንድናሠራቸው ታገሰን በማለት በሚያቀርቡት ጸሎት በሚሠውት መሥዋዕት መማጸናቸውን ያመለክታል፡፡

ይቺን በለሰ ማወቅ ራስን ማወቅ ነውና ቀርቤ እመረምራት ዘንድ ወደደኩ፡፡

፩. የመጀመርያው በለሲቱ ፍሬ ለማፍራት የሚያስችላት ማንኛውም ነገር ተሟልቶላት ነበር፡፡ ሁኔታዋን በቅርበት የሚከታተል ጠባቂም ነበራት ነገር ግን ፍሬ አልተገኘባትም፡፡ እኛም መልካም ፍሬ እንድናፈራ የሚያስፈልጉን ሁሉ ተሟልተዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ቅዱሳት መጻሕፍት፣ምሳሌ የሚሆነን የቅዱሳን ሕይወት፣ካህናትና መምህራን፤ ከዚያም በላይ የቅዱሳን መላእክት እርዳታና በእኛ ውስጥ የሚሠራ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ አለ፡፡ ግን በአንዱም ተጠቅመን መንፈሳዊ ፍሬ ልናፈራ አልቻልንም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ከእኛ ፍሬ የሚጠብቀው ከእርሱ የሚጠበቅበትን ከፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ኢሳ 5፡1

፪. በለሷ ከሩቅ ሲያይዋት ልምላሜ ስለነበራት ፍሬ አይኖራትም ተብሎ አልተጠበቀም፡፡ ደረቅ ብትሆንማንም ፍሬ አይፈልግባትም ነበር፡፡ ይህ ቅጠል ወይም ልምላሜ በእኛ ሕይወት ያለ ‹‹መስሎ መታየት›› ነው፡፡ ቤተክርስቲያን በመመላለስ፣በማስቀደስ፣በሽንገላ ከንፈር፣ጉባኤ በመካፈል ወዘተ…ብቻ የተወሰነ ሕይወት ነው፡፡ ይህ የንሰሓ ፍሬን የሕይወት ለውጥን የመንፈስ መታደስን ካለመጣ በራሱ ዋጋ ሊያሰጥ አይችልም፡፡ ክርስቲያን የተባልነው ሆነን ለመገኘት ፍሬ ለማፍራት ነው፡፡ የመንፈስ(የክርስትና) ፍሬ የተባሉትም በገላትያ 5፤22 የተጠቀሱትና እነርሱን የሚመስሉ ምግባራት ናቸው፡፡

፫. የበለሷ ጌታ ከበለሷ ፍሬ ፈልጓል፡፡ አንድ ሰው ካህን ከሆነ የክህነት፣መነኩሴ ከሆነ የምንኩስና፣ሰባኪ ዘማሪ ከሆነ የአገልጋይነት፣ሰንበት ተማሪ ከሆነ የደናግላን በአጠቃላይ ክርስቲያን ከሆነ የክርስትና ፍሬ ይታይበት ዘንድ ግድ ነው፡፡ ስም ብቻ መሸከም ክብር አያሰጥም፡፡

ለምሳሌ፡- አንድ መንግሥት በሌላ ሲተካ የቀድሞው መንግሥት የጦር ጀነራሎች፣ኮሎኔሎች፣ሻለቆችወዘተ…ይኖራሉ፡፡ ሁሉ በአዲስ ሲተኩ ሥልጣናቸው ይውሰድና ስም ብቻ ተሸክመው ይቀራሉ፡፡ የሚያዙት አንድ ወታደር ሳይኖር ታሪክ ብቻ እያወሩ ሕይወታቸውን ይገፋሉ፡፡ ስሙ ሥራ ካልሠራ ለመጠሪያነት መለጠፉ ነበርኩ ከማለት ውጪ ለምን ይጠቀማል?እኛም ክርስቲያን ተብለን ታላቅ ስም የተሸከመን መጠሪያ ብቻ እንዲሆነን ወይም ያለፈ ታሪክ ለመተረክ ሳይሆን ትቆርጣታልህ ሲባል እስከመቼ?


 

እንኪያስ ፍሬ እንዲገኝብን ምን እናድርግ?

፩.ሁልጊዜ የጌታ እግዘአብሔርን ቃል በማስተዋል በማንበብ ሕይወታችንን ማሳደግ ‹‹ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስይለዋል ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል››መዝ ፩÷፪-፫

፪.ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፍጹም ሕብረት ያለው ሕይወት ለመምራት መጣር ይህም የቃሉን ትምህርትና የሕይወቱን አብነት በማየትና እርሱን ለመምሰል ራስን በማስለመድ የሚገኝ ነው፡፡ ጌታችን ሲመክረን‹‹ እውነተኛ የወይን ግንድ አኔ ነኝ ገበሬውም አባቴ ነው ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያሰወግደዋል ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ይጠራዋል… ‹‹ በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፡፡ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም፡፡ እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናነተም ቅርንጫፎች ናችሁ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፡፡ በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፡ እነርሱንም ሰብሰበው ወደ እሳት ይጥሏቸዋል ያቃጥሉአቸውማል፡፡›› ክርስቲያን ተብሎ የክርስቶስ ኢየሱስ ቃሉንና ሕይወቱን የማይከተል ቢኖር የተገነጠለ የደረቀ ወደ እሳትም ለመጣል የተዘጋጀ ቅርንጫፍ ነው፡፡ ዩሐ ፩፭÷፩-፭ችሁጫፎችውምሸለቆችትናንን፣ፍርድኩሰትን

፫.ጸሎት፡- በሥርዓተ ቅዳሴ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክብር ደሙ ለዘላለም ሕይወት ሲታደል በዜማ በሚጸለየው ጸሎት ላይ ‹‹ ሀበኒ እግበር ፍሬ ዘያሠምረከ›› እንላለን፡፡ አንተን ደስ የሚያሰኝ ፍሬ ሃይማኖት እሠራ ዘንድ ኃይል መንፈሳዊ ስጠኝ በማለት በሥጋው እና በደሙ እንማጸናለን፡፡ ይህም የተወደደና የተጋባ ጸሎት ነው፡፡

ዮሐንስ መጥምቅ ለአይሁድ‹‹ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣውቁጣ እንድትሸሹ ማን አመላከታችሁ; አንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ…›› በማለት ከገሠጸ በኋላ አብርሃም አባትአለን የሚሉት ከንቱ ትምክህት አብርሃማዊ ሃይማኖትና የመንፈሳዊ ፍሬ ካልተገኘባቸው ሥልጣነ እግዚአብሔር ከአብረሃም ልጅነት ቆርጦ እንደሚጥላቸው አስጠንቅቋቸዋል፡፡ በእኛ እንዲሁ ነው፡፡ በስሙ ክርስቲያን ተብለናል ከእመቤታችን በጸጋ ተወልደናል የቅዱሳን ቤተሰብሆነናል ካልን በእነርሱ የታየ ሕይወት ሊታይብን ግድ ነው፡፡ ካለበዚያ አንቆረጣለን፡፡

.የበለሷ ጌታ የበለሷ ፍሬ አለማፍራት ብቻ ሳይሆን ያሳሰበው ያለ ፍሬ በመቆየቷ ምድሩን ጭምር እያጎሳቆለች በመሆኑም ነው፡፡በመጀመሪያው የክርስትና ዘመናት አህዛብ ወደ ክርስትና በእጅጉ ይስባቸው የነበረ የክርስቲያኖች ስብከት ብቻ ሳይሆን ይታይባቸው የነበረው ተወዳጅ ምግባር ነበር፡፡ ክርስቲያኖች በፍቅራቸው፣በትዕግስታቸው፣በትኅትናቸው፣በታማኝነታቸው፣ሀሰትን፣ዝሙትን፣ርኩሰትን፣ፍርድ ማጉደልን፣መማለጃ(ጉቦ)መቀበልን፣ዘፈንና፣ስካርን ጠብንና ክርክርን፣ተንኮልና አድመኝነትን፣ትዕቢትንና በሌሎች ላይ መፍረድን ወዘተ… በመጥላታቸው ይታወቁ ነበር፡፡ በሰላም ሆነ በመከራ ጊዜ በማግኘትም ሆነ በማጣት፣በሞትም ሆነ በሕይወትም ፍቅራቸው የማይቀዘቅዝ ደስታቸው የማይበረዝ ነበር፡፡ ስለዚህ ብዙዎችን በሕይወት በሚገለጥ ስብከት እስከ ሞት ለታመኑት አምላክ ማርከዋል፡፡ ዛሬ ግን እኛ ክርስቲያኖች እንደሚጠበቅብን ባለመሆናችን እንኳን ከውጭ ያሉት ተማርከው ሊገቡ ከውስጥ ያሉት እየወጡ ተቸግረናል፡፡

ፍሬ አለማፍራታችን ከራሳችን አልፎ ለሌሎችም የማሰናከያ ድንጋይ ስለሚሆን ነው‹‹ቁረጣት›› የሚል ትዕዛዝ ከልዑሉ የሚወጣው፡፡ የቅዱሳን ምልጃ የመላእክትና የካህናት ጸሎት ጌታ እግዚአብሔርን ከመዓት ወደ ምህረት ከቁጣ ወደ ትዕግሥት ባይመልሰው በዚህች ደቂቃ ይህን ጹሑፍ ለማንበብ እንኳ አንበቃም ነበር፡፡

ከእኛ ቀድመው የተጠሩ ፍሬ ተገኝቶባቸው ወይም ምድሪቱን በክፋት ሥራ አጎሳቁለው እንደተጠሩ የሚያውቅ ጠሪው ብቻ ነው፡፡ እኛ ለመፍረድ እውቀቱም ሥልጣኑም የለንም፡፡

እኛ ግን የቆየነው ከሁለቱ ባንዱ ምክንያት ነው፡፡ መንፈሳዊ ፍሬ ተገኝብቶናል አልያም ‹‹ቁረጣት›› ተብሎ የመላእክቱና የቅዱሳን ምልጃ ታድጎናል፡፡ ግን ስለ እኛ በዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት ወደፊት ብታፈራ ደህና ነው ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋም ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል›› ሲል መስክሯል ባለፈው ዓመት ግብረ አህዛብን ለመፈጸም ለመዳራት፣ለስካር ለሥጋ ምኞት፣ለዘፈን፤ሀሰት ለመናገር ወዘተ… ጊዜ፣ገንዘብ፣ኃይል፣ ቁርጠኝነት፣ሕብረት ከነበረን ለሚያግደን ምክንያትም መንገድ እንዳልሰጠን ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ራስን ለመግዛት፣በወይን ጠጅ ሳይሆን በመንፈስ ለመሞላት፤ለመንፈሳዊ ምኞት፣ለዝማሬ፣ እውነትን ለመመስከር፣ለሚሰድቡን ለመጸለይ በሌሎች ላለመፍረድ ወዘተ…ጊዜ፣ገንዘብ፣ኃይል፣ቁርጠኝነት፣ሕብረት፣ምክንያትን መሰበር በእኛ ዘንድ ሊገኝ የተገባ ነው፡፡ በዚህ ከመቆረጥ እንድናለን፤ለምንኖርባት ምድር መልካም አርአያ እንሆናለን ጊዜያችን ደርሶ ብንሄድም የሕይወትን ጽዋ እነቀበላለን ከቅዱሳን ሕብረትም እንደመራለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

2006ዓ.ም.

Read more...

ስቅለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ በወልድ ስም  አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብዬ በማመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ሳያደርጉ እማር አስተምር እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና፡፡

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት አደረሳችሁ!

አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!

      ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ታላቅ ቃል የተናገረው በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም እንኳ በነቢዩ በኢሳይያስ እለተ ዓርብን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት " በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" ያለው፤ የጌታን ትዕግስቱን ሲያጠይቅ፤ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ እንጂ ለምዕመናን ጥቅም የሚሆን ቃላቶችን አልተናገረም ለማለት አይደለም፡፡

     ጌታ በመስቀል ሆኖ የተናገራቸውን ቃላት በቤተክርስቲያን "ሰባቱ አጽራሐ መስቀል" ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእኒህ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል ደግሞ ቀዳሚው(የመጀመርያው) " አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዚኢየአምሩ ይገብሩ" የሚለው ነው፡፡

ስለምን ጌታ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል በቀዳሚነት ይህን ተናገረ ቢሉ፡-

ሀ. ወደዚህ ዓለም የመጣው ለዚሁ ነውና ነው፡፡ ይኸውም ትዕዛዝን በማፍረስ ከእግዚአብሔር የተጣላውን(የራቀውን) አዳምን ካሣ ከፍሎና ቤዛ ሆኖ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ነውና ይኽንኑ መፈፀምን ከሁሉ አስቀድሞ ጌታችን ስለዚሁ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ የሚበላ ሲያቀርቡለት " እናንተ የማታውቁት የምበላው አለኝ" በማለት ሲመልስ፤ ሌላ ሰው የሚበላ ያመጣለት ሲመስላቸው ድግሞ "የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው" በማለት አስረድቷቸዋል " ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል" በሚል አስተምህሮውም ምን ያህል ለዚህች ሰዓት ዝግጁ እንደነበር አስረግጧል፡፡ ዮሐ 4፥ ፣ዮሐ 9፥

      ጌታችን የሰውን ድኅነት የመጣበትን ዕርቅ የመፈፀም ሥራ ከመደብደቡ፣ከመገረፉ፣ከመንቸንከሩ በአጠቃላይ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራም ይበልጥ ቅድሚያ ትኩረት ይሠጠው እንደነበር በዚህ እናውቃለን፡፡ ከህማሙ ይልቅ ቅድሚያ የሰጠው የሰውን ድኅነት መሆኑ በዚህ ቃል ተረጋግጧል፡፡ የመቁሰሉ የሞቱ ዓላማ ይኸው ነውና፡፡

ለ. ጠላትን መውደድን በተግባር ለማስተማር ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር " ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ ፣ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ" እንዳለ፤ ጠላቶቹ ሳለን ለወደደን ለእኛ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ለሰቃልያኑም ራርቶ ይቅርታን ለመነልን፡፡ ይህን የሚፈፅሙ ማን መሆኔን ባያውቁ ነው ሲል ይቅርታውን አበዛልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር" እንዳለ በዚህም ሰው በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ቢተላለፍ ንስሐ ከገባ ስርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኝ አስታወቀን፡፡ ለእኛም ስለይቅርታ በቃል ያስተማረንን በተግባር ፈጽሞ አብነት ሆነን እኛም እርሱን አብነት አድርገን ምን ቢበድሉን ፈጽመን ይቅር እንድንል በተግባር አሳየን ሰማዕታትም አርአያውን ተከተሉ፡፡የሐዋ.ሥራ 7፥60

. ጌታ ሌሎቹን ስድስቱን ተናግሮ ይህን ትቶ ቢሆን ኖሮ በኋላ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ወልደ ማርያም ሲሰቀል ወልደ እግዚአብሔር ተለይቶት ነበር ለሚል የስህተት ትምህርታቸው ይመቻቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመስቀል የተሰቀለው፣ መከራን በነሣው ሥጋ የተቀበለው እርሱ በመስቀሉ ላይ ሳለ በመከራው ሰዓት "አባት ሆይ" ብሎ በመጣራቱ መለኮት በለበሰው ሥጋ መከራን ተቀበለ ሞተ…ወዘተ የሚለውን እውነተኛ ትምህርት አጸና፡፡ ይህን ትቶ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" "ተጠማሁ" ወዘተ…የሚለውን ብቻ ተናግሮ ቢሆን ለስህተት ትምህርታቸው ማስረጃ ባደረጉት ነበር፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ከሥጋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳ እንዳልተለየ በዚህ አውቀን ተረዳን፡፡ዕሩቅ ብእሲ(ፍጡር) እግዚአብሔርን " አባት ሆይ" ብሎ ይጠራ ዘንድ አይቻልምና፡፡ እርሱም ተከሶ የተሰቀለበት ምክንያት ይኸው ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል" እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሐር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡" ዮሐ 5፥18

በተጨማሪም ያቺ ሰዓት የይቅርታ የምህረት እንጂ የክስና የፍርድ ሰዓት አልነበረችምና ለሰቃልያኑ እንኳ ምህረትን አደላቸው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ" እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ከቁጣም የራቀ ምህረቱም የበዛ ነው ሁልጊዜም አይቀስፍም ለዘላለምም አይቆጣም እንደ ኃጢአታችንም አላደረገብንም፤ እንደበደላችንም አልከፈለንም " እንዳለ፤ በዮሐንስ ወንጌልም " በእርሱ የሚያምን ሁለ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና፡፡" ጌታም " ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም" በማለት ያቺ የይቅርታ ሰዓት በእርሱም ሆነ ከርሱ ርቀው በኖሩ ፍጥረቶቹ በጽኑ ናፍቆት ትጠበቅ ስለነበር ነው ይቅርታውን የገለፀባት፡፡ ዮሐ 3፡16

     ለሰቃልያኑም ዕድሜ ለንስሐ ሰጣቸው፡፡ ምናልባት በጊዜ ስቅለቱ የተፈፀመውን ዓይተው ሊድኑ ለሚችሉ የመዳን ዕድልን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም የሆነውን ዓይተው ፍፁም አምላክነቱን የተረዱ ፈያታዊ ዘየማንና የጭፍሮች አለቃ የነበረው አምነው መስክረዋል፡ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እና "ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር" በማለት፡፡ ሉቃ 23፥39-43፤ ማር 15፥39

    ለሌሎቹም በስቅለቱና በሞቱ ባያምኑ ዜና ትንሣኤውን ሲሰሙ ምናልባት አምነው ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ 40 ዘመን ታገሣቸው፡፡ ይህም የይቅርታውን ስፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ተጠቅመውበታል፡፡ ያልተጠቀሙበት ግን በ70 ዘመን ጥጦስን አስነስቶ ቀጥቷቸዋል፡፡


 

        ጌታ " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" በሚለው ቃሉ በመስቀሉ ላይ" ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ ጌታ በልደቱ ተፈጥሯችንን፣ በጥምቀቱ ጥምቀትን፣ በፆሙ ፆምን፣ጸልዮ ጸሎትን አንዳች ሳይኖረው ኑሮ መንኖ ጥሪትን፣የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ትህትናን፣ታግሦ ትዕግስትን፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሰማዕትነትን ወዘተ…ፍፁም እንዳደረጋቸው ይቅር ብሎም ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ እርሱ በዚያ ሰዓት የፈፀመው የይቅርታ ሥራ ተከታይ ተቀፅላ የማያስፈልገው የማይደገም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው፡፡

      የአዳም በደል(ኃጢአት) ፍፁም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትን የሠራው ከባህርዩ አንቅቶ ሳይሆን በዲያብሎስ ተታሎ ነውና፡፡ የዲያብሎስና የአዳም በደል ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የኃጢአት የስህተት የሐሰት ሁሉ ነቅዑ ዲያቢሎስ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ዲያብሎስን "…እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ  የሐሰትም አባት ነውና" በማለት የክፋት ሁሉ ምንጩ መነሻው ዲያብሎስ እንደሆነ መስክሮበታል፡፡ ሰው ከዲያብሎስ ያልተማረው ከራሱ አንቅቶ የሠራው ወደፊትም የሚሠራው ኃጢአት የለም አይኖርምም፡፡ ዮሐ 8፡፡  ጌታ የተንኮል ምክሩን እስኪያፈርስበት ድረስ የዲያብሎስ ጥረትም ይኸው ነበር፡፡ ሰውን አዘቅት ውስጥና፤ አምላኩንና የቀደመን መልኩን(ክብሩን) በመርሳት በድንቁርና ጨለማ ተውጦ በመዳኑም ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር ቅዱስ እግዚአብሔርም አዳምን እንደ ዲያብሎስ ይህስ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ከሚጨምር በቀር የቀደመ ሕይወቱ ናፍቆት አይደለም የመዳን ምኞት የሌለው ነው በማለት ከማዳኑ ቸል እንዲለው ተመኝቶ ነበር፡፡

      ምንም እንኳ በመጽሐፍ "በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም " ቢባልም በየዘመናቱ የአዳምን ዘር ወክለው የድኅነትን ምኞትና ተስፋ አንግበው በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት የሚታዩ ቅዱሳን አልጠፉም፡፡ መዝ 13፡ 1-3

     ይልቁንም ዲያብሎስ በአዳም ዘር ውስጥ ከርሱ ባህርይ ከምትገኝ ንጽህት ዘር ተወልዶ እንደሚያድነው የሰጠው ተስፋ፤ያቺ ንጽህት ዘርም እንደ ሚያበራ ንፁህ ዕንቁ በአበው አካልና ባህርይ ውስጥ ስትፋለስ መምጣቷ ኃጢአት በአዳም ላይ ባህርያዊ እንዳይሆንና ዲያብሎስም የተመኘው እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ" ተፈፀመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል"(የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ) ያለው እኛም "ምክሀ ዘመድነ" ምክንያተ ድኂን (የባህርያችን መመኪያ የድኅነታችን ምክንያት) የምንላት፡፡

    በመሆኑም ፈፅሞ በበደል ከእግዚአብሔር የይቅርታ ድንበር ውጪ ያልሆነውን አዳምን የበደለው በምክረ ከይሲ ተታሎ እንጂ ከባህርይ አንቅቶ እንዳልሆነ ጌታ ሲመሰክርለት " የሚሠሩትን አያውቁምና" አለ፡፡ አውቆ አጥፊ እና በስህተት የሚበድል እኩል አይሆንምና በዲያብሎስ ቅጣት ለአዳም ድኅነት ተፈረደ፡፡ አንድም

      አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ፍፃሜውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልዓ" እንዳለ፣ ዲያብሎስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን እንዳያስተውሉ ቢጋርድባቸው ነው እንጂ፤ ኃጢአት ምን ፍዳ እንደሚያመጣባቸው ፈፅመው ጠንቅቀው ቢረዱ አሁን የሚሠሩትን አይሠሩትም ነበር ሲል ነው:: ዛሬም ጊዜ እንኳ ሰው ይህን ቢያውቅ ዘላለማዊው ቅጣትም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ቢረዳ ዛሬ የሚሠራውን ባልሠራው ነበር፡፡ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑ በራሱ እጅግ አስጨናቂ ነውና፡፡ ቅዱሳን ኃጢአትን ብቻ ያይደለ በዓለም ያለ ግብርን ሁሉ እንደ ምናምን ቆጥረው እርግፍ አድርገው ትተው በፍፁም ኃይላቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸውና በፍፁም ልባቸው ጌታን የሚከተሉ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትንና ምረረ ገሃነምን በመረዳታቸው ነው፡፡

      ጌታ በመስቀል በነበረባት በዚያች ሰዓት ራሱን ፍፁም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት፤ ዘላለማዊ ካህን (አስታራቂ) እና ይቅር ባይ(ታራቂ) በመሆን አቀረበ፡፡

      አዳም ከፈጣሪ ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ጸጋው በመገፈፉ ጠባዩ በማደፉና ባህርይው በመጎስቆሉ የተነሳ ይኸው በዘሩ ተጋብቶ የጠብን ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ሊገኝ አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉ በኃጢአት ስለተያዘና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው እርቅን ማምጣት አልቻለም፡፡ከአዳም ጀምሮ የነበሩ  ታላላቅ አበው፣ከሙሴ ጀምሮ የተነሱ ነቢያት ከአሮን አንስቶ የነበሩ ካህናትና ከእያሱ ኋላ የተነሱ መሣፍንት ዳዊትንም የተከተሉ ነገሥት በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት መሥዋዕት ኃጢአትን በደልን ማራቅ ህዝቡንም ከህዝቡ ማስታረቅ አልቻሉም ነበር፡፡

     በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ስለህዝቡ ኃጢአት መስዋዕትና ምልጃ ከማቅረባቸው በፊት ስለራሳቸው ኃጢአት መስዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ ድኅነት ጊዜያዊ እርቅ ከማምጣት ያለፈ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እነርሱም ህዝቡን እንደጥላ(ምሳሌ) በነበረችው ድንኳንና የኦሪት ሥርዓት ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተከትሏቸው ይወርዱ ነበር፡፡ እነርሱም የበለጠ ሊያድናቸው ወደሚችል በብርቱ ጸሎትና ምልጃ ይቃትቱ ነበር፡፡ " አንሥዕ ኃይለከ ወነአ አድኀነነ"(ኃይልህን ግለጥና መጥተህ አድነን) እያሉ በዘመናቸው ሁሉ ይጮኹ ነበር፡፡

    ከዚያም በላይ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ድረስ በኩላብ ተቸንክረው በመጋዝ ተተርትረው ደማቸው ቢፈስም ለዓለም አይደለም ለራሳቸውም ቤዛ መሆን አልቻለም የኒህ ሁሉ ደም ይካሰስ ይፈራረድ እንደሆን እንጂ ይቅርታን ሰላምን ሕይወትን አንድነትን አላመጣም፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ "እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡ጽድቁንም እንደ ጥሩር ለበሰ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ…" እንዳለ የተፈረደውን ፍርድ ሊያስቀር የሚችል እንደሌለ ባወቀ ራሱ ወደዚህ ዓለም መጣ ሥጋንም ለብሶ ተገለጠ፡፡    ኢሳ 59፡ 15-17

     ጌታ ዓለሙን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ሲገለጥ ክህነቱ(የማስታረቅ አገልግሎቱ) ከብሉይ ኪዳን ካህናት በእጅጉ የራቀና የመጠቀ ነበር፡፡

፩. የብሉይ ካህናት መሥዋዕት ሲያቀርቡ መጀመርያ ለራሳቸው ቀጥሎ ለህዝቡ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለ ኃጢአት ያለ ነውር ስለተገለጠ  ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሲናገር " ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ዕብ 5፥5-4

፪. የብሉይ ካህን በዘር ጨምሮም በቅዱስ ቅባት ተቀብቶ የክህነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ሰያሜ ካህናት የሆነው ጌታ ግን ከማንም አልተቀበለውም፡፡ ስለ እርሱ እንደተባለ" አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ" ሿሚ የለበትም፡፡ዕብ 5፥5-6

፫. የብሉይ ካህን ጊዜአዊ እርቅን የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሊያሰጥ የሚችል የፍየልና የኮርማዎች ደም ያቀርብ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሥጋን ነፍስን ደመ ነፍስን የሚቀድስ ክቡር ደሙን አፍስሶና ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ አስታረቀን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ" የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ፤ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?" በማለት ገልፆታል፡፡ ዕብ9፥13-14 

     ጨምሮም "…የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ "መስዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ፡፡በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተፃፈ አምላኬ ሆይ ፍቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ" ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትና ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደህግ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህ ላደርግ መጥቻለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም ፊተኛውን ይሽራል በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡" በዚህም ቃል በግልፅ ቃል መሥዋዕተ ኦሪት ተሽሮ መስዋዕተ ሐዲስ እንደተተካ ይህ የሆነበት ምክንያትም የኃጢአት ሥርየት ማምጣት አለመቻሉና መለኮታዊውንም ፍርድ አለማርካቱ መሆኑን አትቷል፡፡ዕብ 10፥4-10

     የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የእውነተኛይቱ ምሳሌ በምትሆን ቅድስተ ቅዱሳን በዕለትና በዓመት ኃጢአትን ሊያስወግዱ የማይችሉበትን መስዋዕቶች ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ምሳሌይቱ ሳይሆን አማናዊ ወደሆነችው ቅድስት አንድን መስዋዕት አንድ ጊዜ አቅርቦ ኃጢአትን በማስወገድ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "… ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሰዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ  ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሺር አንድ ጊዜ ተገልጦአል…" ጨምሮም  " ሊቀ ካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡" በማለት ጽፏል፡፡ዕብ 9፥24-28፤ ዕብ 10፥11-12

      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የማስታረቅ አገልግሎቱን በራሱ ብቻ አላስቀረውም ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደራሴው በመሆን በእርሱ ተገብተው በሚሠውት የእርሱ ሥጋና ደም በእምነት ለሚቀርቡ ሁሉ ጊዜአዊ ያይደለ ዘላለማዊ ድኅነትን ፍፁም ይቅርታን ለምዕመናን ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ"…ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤ በደላቸውም አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ " በማለት የአዲስ ኪዳን ካህናት ከብሉይ ካህናት ምን ያህል የሚበልጥ የክህነትን ክብር እንደተቀዳጁ ጽፏል፡፡ 2ቆሮ 5፥18-21

     ከላይ በተብራራው ላይ መሥዋዕቱ እርሱ መሥዋዕቱን አቅራቢውም እራሱ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ ሌላው በዚሁ የምናየው ነጥብ ተወካፌ መሥዋዕቱ እርሱ ራሱ መሆኑንም ነው፡፡ በአዳም የሞትን ፍርድ የፈረደበት እርሱ፤የይቀርታን የድኅነትን ቃል " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቀር በላቸው" በማለት አወጀልን፡፡ በዚህ ቃል የጠብ ግድግዳ ፈረሰ የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ለሰው ዘር ፍፁም ካሣ ተክሶ አዳምም ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም" እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው" ብሏል፡፡ አክሎም " እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግደግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡" በማለት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንዴት እንደታረቀን አስተምሯል፡፡ኤፌ 2፥13-16፤ቆላ 2፥13-15

     በአዲስ ሥርዓት በሆነ ደሙ ላጠበን ከበደላችንም ሁሉ ላነፃን ይቀርታውንና ምህረቱን ላበዛልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም መቼም መች ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!

ይቆየን!

ጥር 2005 ዓ.ም

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 

Read more...

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ