ስቅለት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ በወልድ ስም አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብዬ በማመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ሳያደርጉ እማር አስተምር እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና፡፡
እንኳን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት አደረሳችሁ!
አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ታላቅ ቃል የተናገረው በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም እንኳ በነቢዩ በኢሳይያስ እለተ ዓርብን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት " በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" ያለው፤ የጌታን ትዕግስቱን ሲያጠይቅ፤ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ እንጂ ለምዕመናን ጥቅም የሚሆን ቃላቶችን አልተናገረም ለማለት አይደለም፡፡
ጌታ በመስቀል ሆኖ የተናገራቸውን ቃላት በቤተክርስቲያን "ሰባቱ አጽራሐ መስቀል" ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእኒህ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል ደግሞ ቀዳሚው(የመጀመርያው) " አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዚኢየአምሩ ይገብሩ" የሚለው ነው፡፡
ስለምን ጌታ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል በቀዳሚነት ይህን ተናገረ ቢሉ፡-
ሀ. ወደዚህ ዓለም የመጣው ለዚሁ ነውና ነው፡፡ ይኸውም ትዕዛዝን በማፍረስ ከእግዚአብሔር የተጣላውን(የራቀውን) አዳምን ካሣ ከፍሎና ቤዛ ሆኖ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ነውና ይኽንኑ መፈፀምን ከሁሉ አስቀድሞ ጌታችን ስለዚሁ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ የሚበላ ሲያቀርቡለት " እናንተ የማታውቁት የምበላው አለኝ" በማለት ሲመልስ፤ ሌላ ሰው የሚበላ ያመጣለት ሲመስላቸው ድግሞ "የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው" በማለት አስረድቷቸዋል " ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል" በሚል አስተምህሮውም ምን ያህል ለዚህች ሰዓት ዝግጁ እንደነበር አስረግጧል፡፡ ዮሐ 4፥ ፣ዮሐ 9፥
ጌታችን የሰውን ድኅነት የመጣበትን ዕርቅ የመፈፀም ሥራ ከመደብደቡ፣ከመገረፉ፣ከመንቸንከሩ በአጠቃላይ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራም ይበልጥ ቅድሚያ ትኩረት ይሠጠው እንደነበር በዚህ እናውቃለን፡፡ ከህማሙ ይልቅ ቅድሚያ የሰጠው የሰውን ድኅነት መሆኑ በዚህ ቃል ተረጋግጧል፡፡ የመቁሰሉ የሞቱ ዓላማ ይኸው ነውና፡፡
ለ. ጠላትን መውደድን በተግባር ለማስተማር ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር " ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ ፣ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ" እንዳለ፤ ጠላቶቹ ሳለን ለወደደን ለእኛ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ለሰቃልያኑም ራርቶ ይቅርታን ለመነልን፡፡ ይህን የሚፈፅሙ ማን መሆኔን ባያውቁ ነው ሲል ይቅርታውን አበዛልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር" እንዳለ በዚህም ሰው በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ቢተላለፍ ንስሐ ከገባ ስርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኝ አስታወቀን፡፡ ለእኛም ስለይቅርታ በቃል ያስተማረንን በተግባር ፈጽሞ አብነት ሆነን እኛም እርሱን አብነት አድርገን ምን ቢበድሉን ፈጽመን ይቅር እንድንል በተግባር አሳየን ሰማዕታትም አርአያውን ተከተሉ፡፡የሐዋ.ሥራ 7፥60
ሐ. ጌታ ሌሎቹን ስድስቱን ተናግሮ ይህን ትቶ ቢሆን ኖሮ በኋላ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ወልደ ማርያም ሲሰቀል ወልደ እግዚአብሔር ተለይቶት ነበር ለሚል የስህተት ትምህርታቸው ይመቻቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመስቀል የተሰቀለው፣ መከራን በነሣው ሥጋ የተቀበለው እርሱ በመስቀሉ ላይ ሳለ በመከራው ሰዓት "አባት ሆይ" ብሎ በመጣራቱ መለኮት በለበሰው ሥጋ መከራን ተቀበለ ሞተ…ወዘተ የሚለውን እውነተኛ ትምህርት አጸና፡፡ ይህን ትቶ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" "ተጠማሁ" ወዘተ…የሚለውን ብቻ ተናግሮ ቢሆን ለስህተት ትምህርታቸው ማስረጃ ባደረጉት ነበር፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ከሥጋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳ እንዳልተለየ በዚህ አውቀን ተረዳን፡፡ዕሩቅ ብእሲ(ፍጡር) እግዚአብሔርን " አባት ሆይ" ብሎ ይጠራ ዘንድ አይቻልምና፡፡ እርሱም ተከሶ የተሰቀለበት ምክንያት ይኸው ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል" እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሐር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡" ዮሐ 5፥18
መ. በተጨማሪም ያቺ ሰዓት የይቅርታ የምህረት እንጂ የክስና የፍርድ ሰዓት አልነበረችምና ለሰቃልያኑ እንኳ ምህረትን አደላቸው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ" እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ከቁጣም የራቀ ምህረቱም የበዛ ነው ሁልጊዜም አይቀስፍም ለዘላለምም አይቆጣም እንደ ኃጢአታችንም አላደረገብንም፤ እንደበደላችንም አልከፈለንም " እንዳለ፤ በዮሐንስ ወንጌልም " በእርሱ የሚያምን ሁለ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና፡፡" ጌታም " ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም" በማለት ያቺ የይቅርታ ሰዓት በእርሱም ሆነ ከርሱ ርቀው በኖሩ ፍጥረቶቹ በጽኑ ናፍቆት ትጠበቅ ስለነበር ነው ይቅርታውን የገለፀባት፡፡ ዮሐ 3፡16
ለሰቃልያኑም ዕድሜ ለንስሐ ሰጣቸው፡፡ ምናልባት በጊዜ ስቅለቱ የተፈፀመውን ዓይተው ሊድኑ ለሚችሉ የመዳን ዕድልን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም የሆነውን ዓይተው ፍፁም አምላክነቱን የተረዱ ፈያታዊ ዘየማንና የጭፍሮች አለቃ የነበረው አምነው መስክረዋል፡ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እና "ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር" በማለት፡፡ ሉቃ 23፥39-43፤ ማር 15፥39
ለሌሎቹም በስቅለቱና በሞቱ ባያምኑ ዜና ትንሣኤውን ሲሰሙ ምናልባት አምነው ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ 40 ዘመን ታገሣቸው፡፡ ይህም የይቅርታውን ስፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ተጠቅመውበታል፡፡ ያልተጠቀሙበት ግን በ70 ዘመን ጥጦስን አስነስቶ ቀጥቷቸዋል፡፡