ኒቆዲሞስ
መድኃኒታችን “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ” በማለት በእግዚአብሔርና በምዕመናን ዘንድ የሚደረገውን የአዲስ ኪዳን ማሠሪያ ውል ነግሮታል፡፡ምሥጢሩም ከአእምሮው በላይ መሆኑ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በሚል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ ምሥጢራት ምስጢር መባለቸው ቅሉ ከሰው አእምሮ በላይ በመሆናቸው እንጂ የተሸሸገ ነገር ኖሯቸው አይደለም፡፡
በምሥጢረ ጥምቀት ሰው በካህኑ እጅ ጸሎት ተደርጎ ሲጠመቅ የሚታይ አገልግሎት ይፈፀማል በቅዱስ ቅባትም(ሜሮን) ይታተማል፡፡ በዚህ ወቅት በሚታይ አገልግሎት(ሥርዓት) የማይታይ ጸጋን እናገኛለን ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅነት ነው፡፡
ከእግዚአብሔር መወለዳችንን በምን እናውቃለን ቢሉ በእምነት ነው፡፡ በሥጋ የወለዱንን በእምነት እንደተቀበልን መንፈሳዊውም ይኸው ነው፡፡ ወላጅ መውለዱን ያውቃል ልጅ መወለዱን ያምናል፡፡
በእናቱ ማኅፀን ያለ ተወልዶ ካልሆነ በቀር የዚህን ዓለም ብርሃን ማየት አይችልም፡፡ወላጆቹን ዘመዶቹን ሁሉ ማወቅ መገናኘት አይሆንለትም፡፡ እኛም በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለድን የእግዚአብሔርን መንግስት ብርሃን ማየት አይቻለንም፡፡እንደ ወላጅ ሥሉስ ቅዱስን እንደ ዘመድ የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑ ቅዱሳንን መገናኘት አይሆንልንም፡፡ መወለድ ወደዚህ ዓለም መግቢያ በር እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ለመንፈሳዊው ዓለም(ለእግዚአብሔር መንግሥት) መግቢያ በር ነው፡፡
ጌታችን ይኽን ምሥጢር በነፋስም ምሳሌ ቢነግረው ሊረዳው ስላልቻለ “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታቸንን አትቀበሉትም፡፡ ስለ ምድራዊው ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” የሚል ተግሣፅ ተነግሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ በአእምሮው ሊገነዘበው ያልቻለን ነገር ለማመን አለመፈለጉን ጌታ አውቆበታል ሃይማኖት ግን ከሥጋዊ ደማዊ አእምሮ እጅግ የራቀና የረቀቀ ምሥጢር ስለሆነ ከእውቀቱ ማነስ የተነሣ ከማመን እንዳይዘገይ የተሠነዘረ ተግሣፅ ነው፡፡
በልዑል እግዚአብሔር ባህርይና በሀልዎቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም በሃይማኖት የሚፈፀሙ ምሥጢራትና ተዐምራቶች ሁሉ ከአእምሮ በላይ ናቸው፡፡ በእኔ የእውቀት ልክ ስላልሆኑ አልቀበልም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ይህን የሚል የራሱን ሁኔታ ጭምር መካድ ውስጥ ይገባልና፡፡ ምክንያቱ የሰው ተፈጥሮና ማንነት በራሱ ከሰው አእምሮ በላይ ነውና፡፡
- ለኒቆዲሞስ የነፋስን ምድራዊ ምሳሌ አቅርቦ ሲያስረዳው ስላልገባው ከነፋስ ይልቅ ረቂቅ የሆነ የመንፈስን ነገር ቢነግረው እንደማያምን አስረግጦለታል፡፡ አንድም
በምድር የሚፈፀመውን የጥምቀት ሥርዓት አምነህ መቀበል ካልቻልክ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊና መንፈሣዊ ልደት አምነህ መቀበል እንዴት ይቻልሃል? ሲለው ነው፡፡ አንድም በአፈ ነቢያት በቃለ መፅሐፍት የተነገረውን በኅቱም ድንግልና የሆነ ምድራዊ ልደቴን ብነግራችሁ ካላመናችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያለመቀዳደም ያለመበላለጥ የሆነ ሰማያዊ ልደቴን ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ሲል ነው፡፡
ለጥቆም “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ ማንም የለም፤እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት የሚነግረው ሁሉ እንደነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በሚል ከባህርይ እውቀት ባልመነጨ ሁኔታ ሳይሆን በባህርዩ የሚያውቀውን በጌትነቱ ያዘጋጀውን መሆኑን ነግሮታል፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ንግግር ሲጀምር “…እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለት ወደ እስራኤል በተለያየ ጊዜ እንደሚላኩ ነቢያት ወይም መምህራን ቆጥሮት ነበርና ለዚያ የተሠጠ መልስ ነው፡፡ እኔ ነቢይ ወይም መምህር ብቻ ያይደለሁ የነቢያት ጌታ የመምህራን እውቀት ነኝ፡፡ እነርሱ በሰሙት ቃል በተገለጠላቸው ራዕይ ይናገራሉ እኔ ግን የሰማያት ምሥጢር ባለቤት እንደመሆኔ በባህርይ እውቀት እነግርሃለው፡፡ አንድም
ከሰማያት(ከልዕልና) በፈቃዱ ሰውን ለማዳን የወረደ፤ኋላም ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞ በሥልጣኑ በክብር ወደ ሰማይ የሚወጣ ከእኔ በቀር የለም ሲለው ነው፡፡ በውሱን አካል ቢገለጥም ምሉዕነቱ እንዳልተለወጠ ያጠይቃል፡፡ ውሱን የሰው አካል ምሉዕ ሆነ፤ምሉዕ(የማይወስነው) መለኮት በሥጋ ተወሰነ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ቦታውን ሳይለቅ ምድር ደርሶ ጨለማን እንደሚገልጥ፤በልቡና ያለም ሀሳብ ከልብ ሳይለይ በቃል በጹሑፍ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥም እንዲሁ ነው፡፡
አያይዞ “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” በማለት ተናገረ፡፡ ኒቆዲሞስ በአጭር ቆይታ የአዲስ ኪዳን መልክ ምን እንደሚመስል ተስሎለታል ሁለቱ ቁልፍ ነገሮች በጥምቀት የእግዚአብሔር መንግስት ዜግነት የሚገኝበትንና፤በጌታችን ሞት የዓለም ድኅነት የሚፈፀም መሆኑን ገለጠለት፡፡
ጌታችን እንደሚሞትና ሞቱም በምን ዓይነት መንገድ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጥ የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡ የሞቱም ዓላማ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መሆኑን ጭምር አስረዳው፡፡
ወገኖቼ እነሆ የክርስትና መልክ፡- በክርስትና ምንጊዜም ማመንን መከራ፣ጥምቀትን ሞት፣ሞትን ትንሣኤ ይከተለዋል፡፡ ይህ ከሌለ መንገዱ ላይ አይደለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀትን ምንነት ሲገልጥ “…ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?... ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡” ብሎታል፡፡ በግልጥ በስሙ የተጠመቅን በሞቱ ልንመስለው ቃልኪዳን ገብተናል፡፡ በሞቱ ያልመሰሉት በትንሣኤው አይመስሉትምና፡፡ሮሜ 6፥1-23፤ቈላ 2፥8-15
በጥምቀት ለኃጢአት እንሞታለን፣አሮጌው ሰውነታችንን እንሰቅላለን፣በሕግ ከሚመጣ እርግማን ነፃ እንወጣለን፡፡ በአንፃሩ በሕይወት እንኖራለን፣አዲሱን ሰው እንለብሳለን፣ከጸጋው በታች እንሆናለን፡፡
ቤተክርስቲያን ለዚያ ነው ወዲያው እንደተጠመቅን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በማቀበል ሞቱን እንድናስብና በሞቱ መተባበራችንን እንድናትም የምታደርገን፡፡ ያልተጠመቀ የጌታን ሥጋውን ደሙን መቀበል እንደማይችል ሁሉ ተጠምቆም የጌታችን ሥጋና ደም ሳይቀበል የሚሄድ ክርስቲያን ሆኗል ልንል አንችልም፡፡ ሊነጣጠሉ አይችሉምና፡፡
ይህንኑ ለማመስጠር ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለጥምቀት ሲነግረው ከቆየ በኋላ አከታትሎም ስለ ስቅለቱ የነገረው፡፡ ለጥምቀታችን የሆነው ማየ ገቦና ለቁርባናችን የሆነ ደሙ የፈሰሰ በመስቀል ላይ በስቅለቱ ጊዜ ነውና፡፡ ከአዳም ጎን ሙሽራው ሔዋን እንደተገኘች ከዳግማዊው አዳም ከክርስቶስም ጎን ሙሽራው ቤተክርስቲያን ተገኘች፡፡ ዮሐ 19፥33-35
ክርስቲያኖች ሆይ በወላጆቻችን ክንድ በዮርዳኖስ ለመጠመቅ ስንቀርብ ተቀብሎን ልጅነትን ሰጥቶናል፡፡ ቀጥሎ የሚጠብቀን የቀራንዮ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ቀራንዮ የሚኬደው ግን በራስ ጽናትና በፍፁም እምነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተጠምቂያለሁ ብቻ ብለን የምንቆመው ለዚህ ነው፡፡ ክርስቶስን በፍፁም ኑሯችን ልንመስለው ግድ ነው፡፡ እኛን መስሎ የተገለጠ እርሱን በመምሰል እንከብር ዘንድ ነውና፡፡
ወገኖች ሆይ የአንድ ሰው በጨለማ ወደ ጌታችን መሔድ ለስንቶች በሕይወት ብርሃን የሚሆን መንገድ እንደገለጠ ተመልከቱ፡፡ የአንድ ሰውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያደርገው የልብ ግንኙነት ለዓለም ጥቅም እንደሚሆን አስተውሉ፡፡
በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት በክህደት፤ጽድቃችንን በኃጢአት፣ንፅሕናችንን በርኵሰት ሳናጎድፍ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሠጠች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይደግፈን! አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!