ዐቢይ ፆም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
እስከ ቅርቡ ጽሑፍ አነሣው የነበረውን አሳብ ተግ አድርጌ፤አዲስ የምጽፈውንም ሚያዝያ እስኪብት አቆይቼ በያዝነው የፆም ጉዳይ ላይ ልጽፍላችሁ መልካም መስሎ ታየኝ፡፡
በቀኖና ቤተክርስቲያን ከተደነገጉት ዓበይት አፅዋማት አንዱ ፆመ ኢየሱስ (ዐቢይ ፆም ወይም ሁዳዴ) አንዱ ነው፡፡ ጌታ ስለፆመው ፆመ ኢየሱስ ወይም ዐብይ ፆም፤ ሁሉ ተስተካክሎ ስለሚፆመውም “ሁዳዴ” ተብሏል፡፡ የሁዳድ እርሻን ሁሉ በህብረት እንዲሰራው በዚሁ አንፃር ነው፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እፀድቅ አይል ጻድቅ፣ እቀደስ አይል ቅዱስ፣እነፃ አይል ንፁህ፣ ኃይል መንፈሳዊ አገኝ አይል ኃይል የባህርዩ የሆነ፣ ከኃጢአት ሥርየት ለማግኘት አይል “የዓለምን ኃጢአት የሚያስተሠርይ የእግዚአብሔር በግ” የተባለለት መስተሥርዬ ኃጢአት፣ፍትወታት እኩያትን አስታግስ አይል ከድቀት በፊት የነበረ የቀዳማዊውን አዳም ክብር ይመልስ ዘንድ የተገለጠ ዳግማዊ አዳም ስለምን ፆመ? ቢሉ መልሱ እንዲህ ነው፡፡
ጌታ ሥጋን ተዋህዶ በዚህ ምድር ሳለ የሠራውን ሁሉ ሰለ ዐራት ምክንያት አድርጎታል፡፡
፩. ለቤዛ(ለካሣ) ዓለም
፪.ለአጽድቆተ ትስብዕት( ፍፁም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ)
፫.ለአቅርቦተ ሰይጣን(ሰይጣን አቅርቦ ለማሠር)
፬. ለአርአያነት ነው፡፡
ሦስቱን ጊዜ በፈቀደ እስኪገልጣቸው የፆሙን እንመልከት ተያያዥነቱ ከአራተኛው ጋር ነውና፡፡
፩. ጌታ የፆመው “ለአርአያነት” ነው፡፡ ፈጽሞ ቅሉ “ከመዝ ግበሩ”(እንዲህ አድርጉ)” ማለት የተመቸ ነውና፡፡ መልካም መምህር ተናግሮ ማስረዳት ፈፅሞ ማሳየት አርአያ ትቶ መምራት መገለጫው ነውና፡፡ ከዚህ የወጣ መምርነት የለም፡፡ በአፍ ብቻ ቢለፈልፉ ኪያስፈርድ በቀር ረብ ጥቅም አይገኝበትም፡፡ ስለጌታችን ግን ቅዱስ ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና” ሲል ገልፆታል፡፡ ይህም ጹሞ ጹሙ፣ጸልዮ ጸልዩ፣ ታግሦ ታገሡ፣ አፍቅሮ ተፋቀሩ… ወዘተ፡ ማለቱ አይደለምን? 1ጴጥ 2፥21
፪. ጌታችን የመጣ ኦሪትንና ነቢያትን ሊፈፅም ነውና ትንቢታቸውን ፈጽሞ ኑሯቸውን ኑሮ የነቢያቱን እውነተኛነት አተመ፡፡ ክቡደ መዝራዕት ሙሴ በሲና ኤልያስም በቀርሜሎስ ሌሎችም ዓበይትና ደቂቀ ነቢያት ፆምን አብዝተው ይፆሙ ነበርና “ተቸግረው ወይንም የማያስበላና የማያስጠጣ ጋኔን አድሮባቸው ሳይሆን ከፈጣሪያቸው ኃይል መንፈሳዊን የተቀበሉበት አምላካዊ ምስጢራትን ያዩበት ረቂቀ መንገድ መሆኑን ለማስረገጥ ጌታም ፆሞታል፡፡ በዚህም የነቢያቱን ፆማቸውን አተመ መንገዳቸውንም አፀደቀ፡፡ ማቴ 5፥17 ማቴ 11፥18
፫. አጋንንትን ፍትወታት እኩያትን ድል የምንነሣበትን ኃይል መንፈሣዊ እንዴት እንድናገኝ ሲያመለክተን ፆመ ፡፡ ጌታን በፆሙ ወቅት ዲያቢሎስ በስስት ቢመጣበት በትዕግስት፣በፍቅረ ነዋይ ቢመጣበት በጸሊዓ ነዋይ፣ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና ድል ነስቶታል፡፡ በዚህም ከዲያቢሎስም ሆነ ከባህርያችን የሚመጡብንን ፈተናዎች እንዴት ባለ መንፈሳዊ ጥበብ እንደምናሸነፍ ገልፆልናል መንፈሳዊው ትጥቅና የጦር አሠላለፍ መልኩ ይህ ነው፡፡ በድካም ውስጥ ያለ ኃይል፡፡ ጥበብ በዚህ አለ ልብ ያለው ልብ ይበል! 2ቆሮ 10፥2-5
፬. መምራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፆሙን በምድረ በዳ አደረገው፡፡ ይህም ህሊናችንን ከምግብና ከመጠጥ በሥጋ ከሚሆንም ተድላ ደስታ ሀሳብ ሁሉ ለዩት ሲለን ነው፡፡ መዓዛ መባልዕቱን በአጼንዎ ህሊና እያሸተቱ ፤ የማዕዱን ዓይነት በዓይነ ህሊና እየላሱ መፆም “ቁጭት” እንደሆን እንጂ ፆም አይሆንም፡፡ በፆም የምንማረው አምላካዊ ታላቅ ምሥጢር “ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር” ነውና፡፡ በዚህ ወቅት ሰውነት(ነፍስና ሥጋ) ከመብል ከመጠጥ ርቆ በመንፈስ ሠረገላ መጥቆ የእግዚአብሔር መንግሥቱንና ጽድቁን በመመኘት ሀሴት ያደርጋል፡፡ ጊዜው ላመሉ ሲደርስ ለቁመተ ሥጋ ያህል ያለ ሀሳብ ብዛት ያስተናግዱታል፡፡ ስለ እንጀራ ብቻ የሚያስብ ከዲያቢሎስ ስለፆም፣ ስለጸሎት ስለተጋድሎ የሚያስብ ከክርስቶስ መሆኑ በገዳመ ቆሮንቶስ ተለይቷል፡፡
ጌታችን ምድረ በዳውን ለመናንያን ባርኮ ሠጣቸው ይህ ባይሆን ቅሉ ምድራውያን መላእክት የበረሃ ከዋክብት የተባሉ አበው ባልተገኙም ነበር፡፡ እነርሱም በዓለም ያለ መብል መጠጥ ሹመት ባለጠግነት ሳያምራቸው በፆም በጸሎት ጽሙዳን ሆነው ባለቤቱን እርሱን መስለው ኖሩ በመንግስቱም ባለሟሎች ይሆኑ ዘንድ ተገባቸው፡፡
እንስሳትም ሆኑ አራዊት ከተወለዱባት ደቂቃ ጀምረው የሚያስቡ ስለ ምግባቸው(ሆዳቸው) ነው፡፡ ያለፈ ታሪክ አይጠይቁም ከእነርሱ በፊት የነበሩት በምን ተጠቀሙ በምንስ ተጎዱ ብለው አይመረምሩም፡፡ ለወደፊትም ፈጣሪያችን የሚደሠትበት የበጀ ሥራ እንሥራ ብለው አይጨነቁም፡፡ እንግዲህ ሰውም ነጋ ጠባ ስለሆዱ ብቻ የሚያስብ ከሆነና ያለፈን መርምሮ ለወደፊቱ ተምሮ የማይኖር ከሆነ ከእንስሳት በምን ይለያል? ልጆቹም በምግበ ሥጋ ብቻ የሚያሳድግ ቤተሰብ ሥራው እንስሳት ከማርባት በምን ይሻላል?
ወደ ሕይወት መድኃኒት እንቀርብበት ዘንድ ቀድሶ የሠጠንን ፆም እንደተለመደው ያይደለ እንደሚገባው ፆመን ዋጋ የምናገኝበት ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱን ደጅ እየጠናን በዐቢይ ፆም ውስጥ ሰለምናሳልፋቸው(ሰለምናከብራቸው) ሰንበታት በድርበቡ እንመልከት፡፡
በዓቢይ ፆም ውስጥ የሚገኙ ተሰዓቱ ሰንበታት የተለያየ ስያሜ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው...
፩.ዘወረደ፡- በሌላ ስሙ ፆመ ሕርቃል በማለት ይታወቃል፡፡ ንጉሥ ሕርቃል/Heraklis/ በፋርስ ንጉሥ መከራ የፀናባቸውን ክርስቲያኖች ነፃ ለማውጣት ሲዘምት በፆም በጸሎት እንዲያስቡት በመጠየቁና ዘመቻውም በስኬት ሰለተጠናቀቀ ያን ለማዘከር ይፆማል፡፡
በዋናነት ግን ዘወረደ በተባለው ሳምንት የምናስበው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት መውረድና በሥጋ መገለጥ ነው፡፡ በዚህ ዕለት የሚሰበከው ምስባክና የሚነበበው ወንጌል እንደሚከተለው ነው፡፡
ምስባክ፡- ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት
ወተሐሰዩ ሎቱ በረዓድ
አፅንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዓዕ እግዚአብሐር መዝ ፪፥፲፩
ምክር፡- ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ የመከረን ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ”ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ” አለ የተገባ ነውና፡፡ በሌላው ዝርዝር ሳንገባ የመግደልም ሆነ የማዳን ፈርዶ ሲዖል የማውረድም ሆነ ይቅር ብሎ ለዘላለም ደስ ማሰኘት የልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡ እኔ እገድላለሁ አድንማለሁ፤እቀስፋለሁም ይቅርም እላለሁ ከእጄ የሚያድን የለም ጨምሮም እርሱን ፍሩት ነፍስንና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሃነም ሊያጠፉ የሚችለውን ተብሎ ተጽፏል፡፡ ዘዳ 32፥39፣ማቴ 10፥28
ፍርሃት የልቡና ድንጋፄ የናላ ረዓድ የጉልበት ነው፡፡ ለጌታ እግዚአብሔር በፍርሃትና በረዓድ ሆናችሁ በመገዛታችሁ ደስ ይበላችሁ፡፡ አንድም ኃይል ከጉልበት ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ በፆም በጸሎት በስግደት በውስጥ(በልብ) በአፍአ(በጉልበት) እየተገዛችሁ ኃይል ሥጋዊን በማድከማችሁ ደስ ይበላችሁ እርሱ ኃይል መንፈሳዊን ያድላችኋልና፡፡ “ኃይሌ በድካም ይፈፀማልና” ጸጋዬ ይበቃሃል እንዲል፡፡ 2ቆሮ12፥9
የጌታ እግዚአብሔር ቁጣ በላያችሁ እንዳይሆን ጥበብ መንፈሳዊን አጽንታችሁ ያዙ፡፡ ጥበብ መንፈሣዊ የተባለውም ፈሪሃ እግዚአብሔር፣አምልኮ ሠናይ፣ጸሊዓ እኩይ፣ተፋቅሮ፣ትህትና ጾም ጸሎት ምፅዋት ወዘተ… እና ከከርሠ መጻሕፍት ከከናፍረ ሊቃውንት የሚገኝ ምክር ሁሉ ነው፡፡ አንድም ጥበብ የተባለ ጌታችን ነው፡፡ አጽንታችሁ ያዙ አለ በእርሱ ማመንን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣቱንና እርሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የማያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ አያመልጥም፡፡ በአድስ ኪዳን ታላቁ ኃጢአት በእግዚአብሔር ልጅ አለማመን ነው፡፡ ዩሐ 3፥16-21 ፣ ዩሐ16፥7-11፣1ዩሐ 5፥10-12፣ 1ዩሐ4-2 ተመልከት በእርሱ ማመን ማለትም ወረደ ተወለደ ተሰቀለ ሞተ ተነሣ ዐረገ ዳግም ይመጣል ብቻ ብሎ መናገር ሳይሆን ለምን ወረደ? ተወለደ? ለማንስ ተሰቅሎ ሞተ? በትንሣኤውስ ምን አገኘን? እኔስ የትንሣኤው በርሃን(ድል) ተካፈይ ነኝ ወይ? ወዘተ----እያሉ በውሳጣዊ ህሊና በማስተንተን በህይወት መግለጥ ነው፡፡ ይህ ሁሉ በእኛ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ካላመጣ ስመን ብቻ ክርስቲያን ተብሎ መሸከም ከፍርድ አያስጥልም፡፡
የሚነበበው ወንጌል ዩሐ 3፥10-24
በዚህ ምንባብ ውስጥ ያለውን ተዝቆ የማያልቅ ምስጢር ለጊዜው ታግሠን በሁለት ነጥቦች ላይ እናተኩር፡፡
፩. የሰማያዊው ልደት ምሥጢር ምስክርነት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ በስሙ ያመንን የእኛ ሰማያዊ ልደት ምሥጢር የተገለጠው በጌታችን ምድራዊ ልደት ነው፡፡ እርሱ ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ያለ አባት ተወልዶ ቅድም ዓለም ያለእናት ከአብ የተወለደውን ሰማያዊ ልደት ገለፅልን፡፡ ጌታችን በኒቆዲሞስ በተናገረው ቃል ላይ “ስለምድራዊ ነገር ስነግራችሁ ያለመናችሁ ስለሰማያዊው ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ? ሲል ምድራውያን ስለሆናችሁ ስለእናንተ ሰማያዊ ልደት ስነግራችሁ ያለመናችሁ ከዓለም አስቀድሞ ስለሆነ ስለእኔ ልደት ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ ሲል ነው? አንድም ሰለምድራዊ ልደቴ ስነግራችሁ ካለመናችሁ ስለሰማያዊው ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ? ሲል ነው፡፡
ሰማያዊውን ምሥጢር ሊገልጥ የተገለጠ ብቸኛው ከሰማይ የወረደው በሰማይም ያለው እርሱ ነው፡፡ በዚህ ቃሉም በሥጋ ቢወሰንም ምሉዕ ሰፋሕ ከመሆን እንዳልተለወጠ አስረዳ ምስክርነቱ ግን አልታመነም፡፡ ኢሳያስም“ ምስክርነታችንን ማን አመነ?“ ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ያየነውንና የሰማነውን እውነት መመስከር ግድ ነው፡፡ ይኸውም ህይወት ተገለጠ ዓይተንማል ሰምተንማል ሕይወት እንዲበዛላችሁ በእርሱ ፍቅር ኑሩ ብሎ መመስከር ነው፡፡ በምስክርነታችን በሰዎች ዘንድ አክራሪ፣ ሥራ ፈት ወይም ሌላ እነደሆንን ተቆጥረን መላገጃ ልንሆን እንችላለን፡፡ ክብራችንም ይኸው ነው፡፡
፪.የእግዚአብሔር ፈቃድ በልጁ መገለጥ:- የጌታ እግዚአብሔር የዘመናት ዕቅድ ሁሉ ይድኑ የክብሩም ወራሾች ይሆኑ ዘንድ ነው፡፡ ይህም በአንድያ ልጁ ሞት ተረጋገጠ፡፡ ይህን ፍቅር ለመግለጥ ልብ ይደክማል፣አእምሮ በአንከሮ የሸነፋል፣አንደበት በዝምታ ይታሠራል፣ቃለትም ይፈራሉ፡፡ የባርባሮስ ጥልቀት የሰማያትም ምጥቀት የረቂቁም ሆነ የግዙፉ ዓለም ስፋት ይህን ፍቅር ሊሸከመው ሊገልፀው አይችልም ምትክ ከሌለው ልጅ በላይ ጠላትን መውደድ በአብ ዘንድ፤ከራስ በላይ ጠላትን መውደድ በልጁ ዘንድ ምን ይደንቅ? በወንጀለኛ ተገብቶ ካሣ ሞትን ወስዶ ህይወትን ማደል እኔም በአባቶቼ መንፈስ ጌታ ሆይ እጠይቅሃለው ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ከሌሎች ይልቅ እስከዚህ ትደርስለት ዘንድ ሰው የመሆን ምሥጢር ምንድር ነው?
*በዘወረደ በትህትና ወርደን በመንፈስ መጥቀን የምናስበው ይሔን ነው!
፪. ቅድስት፡- በዚህ ዕለት የሚነበቡት ምንባባት የቅድስና ህይወት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ስለመሆኑና እኛም እንዴት መኖር እንዳለብን የምንመካከርበት ነው፡፡
ምስባክ፡- እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ
አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤የሚል ነው፡፡ መዝ ፺፭፡፭
ሲተረጎም፡- እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ
ሃይማኖትና ምግባር በፊቱ ነው
ቅድስናና ታላቅ ምስጋናም በመቅደሱ ውስጥ ማለት ነው፡፡
-እውነት ነው ከእርሱ በቀር ሰማያትን የሠራ በክብርም ያስጌጣቸው የለም፡፡ የተሠሩትም ለጥቅማችን ነው፡፡ ለፍጡራን መኖሪያና(እርሱ ባወቀ) ለብርሃናት መመላለሻ ከመሆንም ባለፈ የቃሉን ብርታት የክብሩን ገናንነት የሚመሰክሩ ኃይላት ናቸው፡፡“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ“ እንዲል ዳዊት፡፡ የልዑል እግዚአብሔርን ታላቅነት በጥቂቱ እንኳ ለመረዳት ብትሻ በሌሊት በጠፈር ሰምይ እንደስንዴ የተዘሩትን ከዋክብት ተመልከት፡፡ መዝ 18፥1
በህዋሳይንስ known Universe(የታወቀ ዓለም(ህዋ)) እና Unknown Universe(ያልተደረሰበት ዓለም(ህዋ)) የሚባል አለ፡፡ በታወቀው ዓለም(ህዋ) ከመቶ ቢልዩን በላይ የሆኑ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከእንዚያ አንዱ የእኛይቱ ያለችበት ጋላክሲ ሚልክዌይ ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ጋላክሲ ብቻ ከ300-500 ቢሊዮን የሚደርሱ ከዋክብት እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከመቶ ቢልዮን በላይ ባሉ ጋለክሲዎች ስንት ከዋክብት ሊኖር እንደሚችል ገምት ለዚያውም በታወቀው(በተደረሰበት) ህዋ (Known Universe)፡፡ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ትችሉ እንደሆነ የሰማይ ከዋክብትን ቁጠሩ፤እርሱ ግን ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድ ስንኳ አይታጣውም፡፡ኢዩብ 38-39፣ ኢሳ 40፥18-26፤መዝ
ልብ በል እኒህ ሁሉ ሰማያትን፣ለማሰብ እንኳ የሚከብዱን ግዙፍ ዓለማት በልዑሉ ዘንድ ግን እፍኝ እንኳ አይሞሉም፡፡ ለዚህ ነው ኤሊሁም“ እነሆ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤እኛም አናውቀውም“ ቅዱስ አጲፋንስዩስም “ከሰማነው በላይ ግሩም ነህ፤ከተነገረንም በላይ ድንቅ ነህ“ በማለት በአንክሮ የቃተቱት፡፡ ኢዩብ 36፥26 ቅዳሴ ኤጲፋንዩስ
-ገናንነቱን እንዲህ ነው ብለን ልንናገረው የማንችለው አምላክ ሃይማኖት ምግባር በፊቱ ነው ይህ ማለት የሰው ሁሉ ሃይማኖትና ምግባር በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ የሚሠወረው የለም ሲል ነው፡፡ አንድም ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብረው በቅድስና በምስጋና በመቅደሱ ፀንተው የሚኖሩ በፊቱ በክብር ናቸው ሲል ነው፡፡ አንድም በሃይማኖት በምግባር የጸኑ ሰዎች የእግዚአብሔር መቅደስ የሆነ ሰውነታቸው በቅድስናና በክብር ምስጋና የተጌጠ ነው፡፡
ሃይማኖትና ምግባር እንደነፍስና ሥጋ የተዋሃዱ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ነፍስ እንዳለው የሚታወቀው የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋውን ስታንቀሳቅሰው ነው፡፡ እርሷ ባትታይም በሥራዋ ሀልዎቷ ይታወቃል፡፡ ሃይማኖትም የሚታይ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ ሃይማኖት የሚታይ የሚዳሰሰው በምግባር ግዘፍ ሲነሣ ነው፡፡ ፆም ደግሞ የትሩፋት መግቢያ በር ነው፡፡ የአንዲት ሃይማኖት ተከታይ የሆነም በራሱ ፍልስፍና መጓዝ አይገባውም፡፡ ይልቁን የቤተክርስቲያኒቱን ቀኖና በመጠበቅና በመፈፀም ሃይማኖቱን በምግባር ይገልፃል እንጂ ፡፡ ያዕ 2፥14-26
የሚነበበው ወንጌል ማቴ፮፥፮-፳፬
ምንባቡን አንዱት ኃይለ ቃልን ማዕከል አድርገን እንመልከተው፡፡
-እንግድህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ ጨለማው እንዴት ይበረታ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ኃይለ ቃል እንደ ማሠሪያ ነው የተጠቀመው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ለነፍስ ብርሃንነት የሚጠቅሙ ዋና ነገሮችን አስተምሯል፤፤ ምፅዋት ፆምና ጸሎት ዛሬ ስለሆዳቸው አብዝተው በሚጨነቁ ሰዎች እንደሚነሣው ፆም ያስፍጋል አያስፈልግም? መቼ እንፁም? ከምን እንፁም? ወዘተ… ዓይነት ጥያቄዎችን በጌታ ጊዜ አልተንሡም፡፡
ጸሎት ምፅዋት አስፈላጊነታቸው እንደማያጠያይቅ ሁሉ ፆምም አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ ስለሆነ በምን ዓይነት መንፈሣዊ ይዘት መፆም እንዳለብን ብቻ ነው መመሪያ የተሠጠን፡፡
ፆምን ስንፆም ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንድናሟላ ተነግሮናል፡፡
፩. ለታይታ እንዳናደርገው፡፡ ሰው ጦመኛ መሆናችን ቢያውቅ ከማድነቅ ባለፈ ዋጋ አይሠጠንም የጦማችንን መስዋዕት በረሃብ እሳት ተቀብሎ ዋጋ የሚሠጠን በስውር የሚያየን የሰማይ አባታቸን ብቻ ነው፡፡ ለሚጦሙ ለሚፀልዩና ምፅዋትን ለሚወዱ ሰዎች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በተደጋጋሚ የሰማይ አባታችሁ ዋጋችሁን በግልጥ ይከፍላችኋል በማለት ከቅዱስ እግዚአብሔር ጋር ያለቸውን ሕብረት አረጋግጧል፡፡ ጦምን የሚነቅፉ ህብረታቸው ከማን ጋር ይሆን? እኒህን ድንጋይ ዳቦ እንዲሆኑ በል ከሚል ጋር ወይስ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በማለት ድል ከነሣ ጋር?
፪.በጦማችን ወቅት ለሌሎች መራራትን ስንጦም ለምግባችን ይውል የነበረውን ገንዘብ በከርሠ ነዳያን ውስጥ ከማኖር ይልቅ የጦሙ ወራት ሲያልቅ ለመጠቀም በሚል ብናኖረው ጦማችን ረብ ጥቅም አይኖረውም፡፡ እኛ ወደን ፈቅደን ከምግበ ሥጋ ስንከለከል ሳይወዱ በምግብ እጦት የሚጨነቁትን ማሰብ የክርስትና ግዴታ ነው፡፡
ሰውነታችን ከምግብ ሊከለል ነፍሳችን ከስስት፣ከፍቅረ ነዋይ፣ከጭካኔ፣ከትዕቢት ወዘተ…ካልጦመች እየተገዛን ያለነው ለገንዘብ(በቁሙ) እና በገንዘብ ተገዝቶ ሆድን ለሚሞላ ምግብ እንጂ ለእግዚአብሔር አይሆንም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት እንደማይቻል በፆምና ለስስት፣ለምፅዋትና ለፍቅረነዋይ፣ለትህትናና ለትዕቢት ወዘተ…ባንዴ ማደር አይቻልም፡፡
ይህን ከመከረ በኋላ ጌታችን ዓይን የሰውነት ብርሃን መሆኗን፤ዓይን ታማሚ ከሆነች ሰውነት ሁሉ እንደሚጨልም አይነተኛ ምሳሌ ከተናገረ በኋላ፤የሰውነት ብርሃን የምትሆን ነፍስም በመስገብገብ በግብዝነት በሀኬተኛነት ጉድፍ ከተበላሸች የከፋ ጨላማ እንደሚሆንብን አስጠንቅቋል፡፡ ነፍስ ብሩህ የምትሆነው ጦምን ጸሎትን ምፅዋትን ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ተዘክሮተ ሞትን አፅንታ ስትይዝ ነው፡፡ ነፍስ በቅድስና ብርሃን ካጌጠች የነፍስ ለሥጋ የሥጋ ቅድስና በአፍአ ላለው ሁሉ ይተርፋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን የህይወታችን ብርሃን ይጨልማል፡፡ ለሥጋ ብርሃን ሕይወት የምትሆነው ነፍስ እንደሆነች፤ለነፍስ ብርሃኗ ሕይወቷ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሥጋ ነፍስ ስትለየው ይሞታል፡ነፍስ ደግሞ ጌታ እግዚአብሔር ሲለያት ትሞታለች፡፡
፫. ምኩራብ፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ወደ ምኩራብ አይሁድ ገብቶ ገበያውን እንደፈታ በቤተክርስቲያን የምናስታውስብት ነው፡፡
ምስባክ-እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዓኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕለየ
ወቀዳዕክዋ በጾም ለነፍስየ
ትርጉም፤-የቤትህ ቅንዐት እንደ አሳት በላኝ
አንተን የተገዳደሩህ ተግዳሮት በእኔ ላይ ደረሰ
ነፍሴን በፆም ቀጣኋት መዝ ፷፰፥፱
ለጊዜው ለይሁዳ መቃቢስ ፍፃሜው ለጌታ የተነገረ ነው፡፡ በመቃቢስ ጊዜ አንጥያኮስ በቤተመቅደሱ አምልኮ ፀሀይ አግብቶ እሪያ ሰውቶ ነበርና፤መቃቢስ ያንን አጥፍቶ ለቤተመቅደሱ መከበርና መቀደስ የቀናውን ቅንዓት ያመለክታል፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ላይ በስህተትም ሆነ በድፍረት የሚቀርብ ተግዳሮት በቅዱሳንም ይደርሳል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ባህርዩ ደርሶ የሚገዳደር የለም እርሱ ነገሥታት የማይነሣሡበት መኳንንትም የማያሰጉት ንጉሠ ነገሥት ነው፡፡ ነገር ግን የአምልኮቱ መገለጫ በሆኑ ሥፍራዎች(ቤተመቅደስ) ታቦታት፣ንዋያተ ቅዱሳት፣በዓላትና ሥርዓቶች እንዲሁም እርሱ የላካቸውን ቅዱሳን መግፋት መገዳደር ጌታ እግዚአብሔርን መገዳደር ነው፡፡ መጽሐፈ መቃብያን፣ትን.ዳን 5፥1-ፍፃሜ፣ መዝ104(5)፥14-15፣ ዘኁ 12፥1ፍፃሜ፣ማቴ 10፥40፤1ሳሙ 4-6
በክርስትና ስንኖር መጠንቀቅ ያለብን ልዑል አምላክ በሠራልን ሕግና ሥርዓት ለመሔድ ነው፡፡ እኛ ሕግ ሐጋጊዎች ሥርዓተ ደንጋጊዎች አይደለንም፡፡ በቤተክርስቲያንም ከሰው የሆነ ሥርዓት የለም፡፡ በጥምቀቱ በቁርባኑ በቅዳሴው በማሕሌቱ በጸሎት በፆም በበዓል አከባበር ሥርዓቱ ሁሉ በጥንቃቄ መጓዜ እንጂ "ምናለበት" በሚል የቸልታ መንፈስ፣ወይም በራስ ሕግ መመራት ከጸጋው ይለያል በመቅሠፍት ያስጎበኛል፡፡ ለመሆኑ ራስህ በሠራኸው ሕግና ሥርዓት በቤተእግዚአብሔር ልኑር የምትል አንተ ማነህ? ይህን ሥርዓት ለቤቱ ከሠራ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ትወዳደር ዘንድስ ምንደር ነህ? የአባቶቻችን ህግና ሥርዓት የምትንቅስ ከእነርሱ የተሻልክ ሆነህ ተገኝተህ ነውን? እንደ እውነቱ የራስህን እንኳ ህይወት በህግና በሥርዓት መምራት ያልቻልክ፤እፈፅመዋለሁ ብለህ ቃል የገባኸውን ለመፈፀም በምክንያት ልምሾ ሆነህ የታሠርክ አንተ እንደምን የእግዚአብሔርን ቤት ህግ ለመተቸት የተሻለ ህግም ለማውጣት ትደፍራለህ?
የቤቱ፣የሥርዓቱ፣የአምልኮቱ፣የቅዱሳኑ፣ቅንዓት እንደ እሳት በሚበላው በሠራዊት ጌታ ፊት ድርሻህን እወቅ፡፡ ደርሻህ በተደነገገልህ ህግ በተሠራልህ ሥርዓት ፀንተህ መኖር ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግዳሮት ነው፡፡ አመድና ትቢያ መሆንህን አስብ!!
ሥጋ የነፍስ መሣሪያ ነው፡፡ መልካምም ክፉም ትፈፅምበታለች፡፡ ነፍስ ከተለየቸው ሥጋ ሀዘን፣ደስታ፣ፀፀት፣ህመም፣ሀፍረት፣ትዕቢት ሌላም ሌላም ስሜቶች አይኖሩትም በድን ነው፡፡ ሥጋ ሲጦም ረሃብ ሲሠማ ስሜቱን ነፍስና ሥጋ ይጋሩታል፡፡ ዳዊት ነፍሴን በፆም አስመረርኳት(ቀጣኋት) ያለው ለዚህ ነው፡፡ አስተውል ነቢዩ ፆምን ለነፍስ እንጂ ለሥጋ አልሠጠም መሪዋ አንቀሳቃሿ ተጠቃሚዋ እርሷ ናትና፡፡ ነፍስ አልቦ ፆም የለም፡፡ ስለዚህ በፆም ነፍሳችንን እንቅጣ እንጂ በዓለም ድንቃ ድንቅ፣በወዘበሬታ፣በሥራ በመወጠር የረሃብ ስሜታችንን ለማጥፋት(ለመርሳት)አንሞክር፡፡ እኛ የረሳነውን(ትኩረት የነፈግነውን) እርሱ ይቀበል ዘንድ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ተረቱስ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይሸከመውም አይደል፡፡ ከረሃብ ስሜታችን ጋር በመቆየት ፆማችንን ማስባረክ ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡
ወንጌል ዮሐንስ ም፪፥፲፪—፳፭
ጌታ ኢየሱስ ራሱን ከገለጠ በኋላ ወደኢየሩሳሌም ሲወጣ የመጀመርያው ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ከቤተመቅደስ አስወጥቷቸዋል ሁለቴም ተግዳሮት ገጥሞታል፡፡ በዚህ ቀንና በዕለተ ሆሣዕና በቤተመቅደሱ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሰዱቃውያን ብዙ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚዎች ስለነበሩ ድርጊቱን ከመቃወም ይልቅ ያበረታቱ ነበር፡፡ የአንድ አገር መንግስት በሌላ አገር ግዛት ውስጥ የዜጎቹን ደኅንነት የሚከታተልበት ጉዳያቸውን የሚከታተልበት ወደራሱ አገር ለሚገቡ ሌሎች ዜጎች ፈቃድ የሚሠጥበት(ቪዛ) ቆንስላ(Embassy) እንደሚኖረው፤ቤተመቅደስም የሰዎች ነፃ ፈቃድ በሰለጠነበት ዓለም የምትገኝ የሰማያዊው መንግስት ቆንስላ(Embassy) ናት፡፡ የዜጎቿን መንፈሳዊ ድኅነት በጸሎት በትምህርት በመከራ ትጠብቃለች፤ አዲስ ለሚመጡት በጥምቀት የሰማያዊ ዜግነት ፈቃድ ትሠጣለች፡፡ ይህንንም በባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴዎች ካህናት ታስፈፅማለች፡፡ የቤተመቅደስም የካህናትም አገልግሎት ይኸው ነው፡፡ ከዚህ ከወጣ ቤተመቅድሱንም በአሠራር ቅርፁ ብቻ ካህናቱንም በአለባበስ ካህናት ለማለት ይቸግረናል። በአውሮፓ በአሜሪካ ወደሙዝየምነት የተቀየሩ አብያተ መቅደሶች አንዳሉ እንሰማለን በአሠራር ቅርፃቸው ብቻ ግን አሁንም ቤተመቅደስ ብለን አንጠራቸውም፡፡ በትያትር በፊልም ካህናት መስለው የክህነት ልብስ ለብሰው የተወኑትም የእውነት ካህናት ናቸው ብለን አንወስድም የታላቁ ሰማዕት የአቡነ ጴጥሮስ ተውኔት አብራር አብዶ(ሙስሊም) መተወኑን የምናሰወታውሰው ነው፡፡ ስለዚህ ቤተመቅደስና ክህነት የይዘት አንጂ የቅርፅ የውስጥ እንጂ የአፍኣ አይደለም፡፡
ጌታ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ድርጊት በመፈፀም ቤተመቅደሱን ሊያጠራው ወደ ዓላማው ሊመልሰው ፈቃደ ተቀባይ ስላላገኘ የተፈታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ጌታ ቤተመቅደሱን በተደጋጋሚ “ያባቴ ቤት” ብሎ ይጠራው ነበር በመጨረሻ ግን እሱን ባለማመን አምጸው ሲፀኑ “ቤታችሁ” ብሎታል፡፡ ክርስቶስ የሌለበት የእግዙአብሔር መቅደስ የለምና፡፡ሉቃ19፣ ማቴ 23፤ አንድም
በቤተመቅደሱ የነበሩት እንስሳት ለተለያየ ዓይነት መሥዋዕት የሚቀርቡ ነበሩ፡፡ የአዲስኪዳን መሥዋዕት እና ሊቀካህናት የሆነው መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተመቅደሱ እንስሳቱንና ርግቦችን ማስወጣቱ መሥዋዕተ ኦሪት መሻሯን፤ ካህናተ ብሉይን መቃወሙም ለአዲስ ስርዓት የአዲስ ኪዳን ካህናት ይሾም ዘንድ እንዳለው ያጠይቃል፡፡
በዚህ ወቅት ጌታ የተጠየቀው ይህን ለማድረግ ስላለው ሥልጣን ምልክት እንዲያሳይ ነበር፡፡ እርሱም ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን አነሣዋለሁ ብሏቸዋል፡፡ አስተውል እሠራዋለሁ አላለም አነሣዋለሁ እንጂ፡፡ በዚህም የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ገለጠ፡፡ (የትንሣኤውን ምስጢር በጊዜው ጊዜ እናመጣዋለን)
በገለጠው ቃል ውስጥ ግን የሰውን አካል እንዴት ባለ ክብር እንዳከበረው አስታወቀ ቅዱስ እግዚአብሔር ቃሉን ከድንጋይ ድላት ይልቅ በልባችን ላይ ሊጽፍ፤በሸራ ድንኳንም ሆነ በድንጋይ፣በዕብነበረድ፣ በወርቅ፣ ከሚሠራ ቤተመቅደስም ከምናመልከው ይልቅ በሰውነታችን መቅደስ ብናከብረው ይወዳል፡፡
አባቶቻችን ወደ ሲና ተራራ ወጥተው ቃሉን የሕዝቡ ልብ አምሳል በሆነው በድንጋይ ድላት ይዘው ወረዱ፤በአዲስ ኪዳን ወደ ቀራንዮ ተራራ ወጥተን ቃሉን ፍቅሩን ቃልኪዳኑን በልባችን ጽላት ተሸክመን ወረድን፡፡
በተለያየ ዘመን የተሠሩት ቤተ መቅደሶች የመፍረስ ግዳጅ ደረሠባቸው፡፡ አሁን ግን ክፉዎች ደርሰው ሊያፈርሱት በማይችሉት መቅደስ ላይ ይመለክ ዘንድ የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነ፡፡ ይኸውም የምዕመናን ሰውነት ነው፡፡ የማይጠፋ ዘላለማዊ ሕያው ቤተመቅደስ የሰው ልጅ፡፡
በዚህች ዕለት ቤተክርስቲያን ልጆቿን ራሳቸውን ህያውና ቅዱስ መሥዋዕት፣ዘላለማዊ መቅደስ አድርገው እንዲያቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ ትለምናለች፡፡ በእንዴት ያለ ክብር እንዳከበረን አስተውሉ፡፡ የኃያሉ ንጉስ የዘላለማዊው አምላክ መቅደስ የቅዱስ መንፈሱም ማደርያ እንሆን ዘንድ የተመረጥን እኛ ማን ነን? ከልባችን ከሕሊናችን ከሥጋችን ላይ የዓለምን ሸቀጥ ማራገፍ ዛሬ ይጠበቅብናል፡፡
ሥጋችን በክርስቶስ መዓዛ ከብሯል፣በቅዱስ ቅባቱ ወዝቷል፣ በንፅህና ልብስ አጊጧልና ሌላ አያስፈልገውም። ንፅኅናህን ባለመጠበቅ ግን ለሰዎች ምሬት ሁን እያልን አይደለም በፈቲው ጦር ሌሎችን ወግቶ ለመጣል ሁሉን ወደራስ ስቦ ለመደነቅ የተዘጋጀ መንፈስህን ለማውገዝ እንጂ፡፡ የነፍስ ክርፋት በሽቶ፤የሥጋ ርኩሰት በልብስ አይሠወርምና፡፡
፬ መፃጉዕ፤- በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕሙማንን ስለመጎብኘቱና ከብዙ ዘመን ጀምሮ በደዌ ተይዞ የኖረ ሰውን ስለማዳኑ ይተርካል፡፡
ምስባክ፡- እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ
ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምጸዌሁ
አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሀለኒ፡፡
ትርጉም፡- በሕማሙ አልጋ ሳል እግዚአብሔር ይረዳዋል
ከደዌውም ምንጣፉን ሁሉ ይመልስለታል
አቤቱ እኔ ይቅር በለኝ አልሁ
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ ብዙ ጥልቅ ነገሮችን ያነሣል አበው በአጭሩ ሲገልፁት መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አፍ አድሮ ያልተናገረው ነገር የለም ይላሉ፡፡ በቤተክርስቲያን ብርቱ ጸሎት ተደርጎ የሚታመነውም ለዚሁ ነው፡፡
ነጠላ ትርጉሙን ስናየው ለድኆች የሚራራ ሰው ከሚገጥመው ችግር እንዴት እንደሚታደገው የሚናገር ነው፡፡ ቢታመም ይረዳዋል ፈውስንም ልኮለት የደዌ ሽታ ያለበትን ምንጣፉን ሁሉ የጤና መዓዛ በሚያውደው ምንጣፍ ይለውጥለታል፡፡ በምንጣፉ እያለ የእግዚአብሔርን ይቅርታ ደጅ ጠንቷልና፡፡
አንድም፡-አንደ ኢዮብ ያለ ጻድቅ በዲያብሎስ ተንኮል በሕመም በቁስል ተመትቶ በአልጋው ቢተኛ እግዚአብሐር ይረዳዋል አለ ያስችለዋል፡ ያስታግሠዋል ሲል ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ሃይማኖቱን ተመልክቶም ከደዌው ይፈውሰዋል፡፡ የደዌ ሽታ ያለበትን ምንጣፍ ለውጦ በጤና በሀሴት የሚተኛበት ምንጣፍ ይሠጠዋል፡፡ ኢዩብ በድያለሁ ይቅር በለኝ ከማለት ውጪ ክፉ አልተገኘበትምና፡፡
አንድም፡-አዳም ባለመታዘዝ ደዌ ተይዞ ሳለ እግዚአብሔር ወልድ አካሉን አካል ባህርዩን ባህርይ አድርጎ“ ነሣዓ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ”እንዲል ታሞና ካሣ ክሶ ይረዳዋል ማለት ያድነዋል፡፡ በኃጢአት መርዝ ታሞ የተኛበት አልጋም ጠረኑ መልካም አልነበረም፡፡ ሰው በጽኑ ደዌ ተይዞ ሲተኛ ከሰውነቱ በሚወጣ የተለያየ ፈሳሽ የአልጋው ምንጣፍ እንደሚበላሽ፤ጠረኑም እንደሚከፋ አዳም በበደለ ገዜ መዓዛ እግዚአብሔር ተለየው ጸጋው ራቀው በፍትወታትና እኩያት በኃጢአትና በርኩሰት መዓዛ ቅድስናው ተበላሸ፡፡
በመሆኑም ያደፈ ጠባዩን የጎሰቆለ ባህርዩን አድሶ ቀድሞ ወደተፈጠረበት አርአያ እግዚአብሔር ሊመልሰው እሱኑ(አዳምን) ሆነ፡፡ ሰው በመሆኑም በኃጢአት፣በርኩሰት፣በሞት በመቃብር፣በመፍረስ በመበስበስ በሲዖል ምንጣፍ ላይ ወድቆ አቤቱ ይቅር በለኝ ይል የነበረ አዳምን በንፅህና በቅደስና አስጊጦ ሞትን መፍረስና መበስበስን በትንሣኤ ድል ሽሮና በህያውነት አክብሮ የቀደመ ምንጣፉን መለሰለት ይህችውም“ልጅነት“ ናት፡፡
የነፍስ ጤናም በዚህ ይታወቃል፡፡ ሰው በደዌ ካልተያዘ በቀር ጥንካሬ ደስታ ሰላም እንደማይለዩት፤ ነፍሱ በመልካም ሁኔታ ያለች ሰው መንፈሳዊ ህይወቱ፣ጸሎቱ ፆሙ ወዘተ…ጥንካሬና ትጋት ያልተለየው፣ሁልጊዜ ከመንፈስ ቅዱስ በሆነ ደስታ የተሞላና፤ከህሊናው፤አንስቶ ህዋሳቱ ሁሉ በእግዚአብሔር ሰላም የታጠረ ነው፡፡ ኃጥአን ግን እንዲህ አይደሉም፡፡
ወንጌል ዘዩሐንስ ፭፥፩—፩፲ በወንጌሉ የተጠቀሰው ታሪክ ዩሐንስ ከጠቀሳቸው ሰባት የጌታችን ታላላቅ ተዓምራቶች አንዱ ነው፡፡ እጅግ መሳጭና ዕምቅ ምሥጢራትን ያቀፈ ነው፡፡ የተወሰኑ ነጥቦች ለማየት ያክል፡፡
፩.በታሪኩ ውስጥ አምላካዊ ድኂንና(direct salivation) ምክንያታዊ ድኂን(Indirect salivation) መሳ ለመሳ ሢሠሩ እናያለን በአንድም በሌላም መንገድ መናገርም ሆነ መሥራት ፈቃዱ የሆነ አምላክ ዋናው ዓላማው ሰውን ማዳን ነውና፡፡
በቤተሳይዳ የነበሩ ህሙማን የእግዚአብሔር መልዓክ በሚያንቀሳቅሰው ውኃ(ጸበል) ይፈወሱ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይህ ምክንያታዊ ድኂን ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር በታቦቱ፣በመስቀሉ፣በጸበሉ፣በእምነቱ፣ በገድላቱ፣ በቅዱሳኑ ወ.ዘ.ተ…አድሮ የሚሰጠው ድኅነት ከዚህ የሚመደብ ነው፡፡
በሌላ አንፃር ጌታ ራሱ“እወዳለሁ ንፃ” ተነሣና አልጋህን ተሸክመኅ ተመላለስ“ እያለ በቃሉ መልሶ በእጁ ዳሶ የሠጠው ድኅነት አምላካዊ ድኅነት ይባላል፡፡ ይልቁንም በቀራንዮ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ጸዋትዎ መከራን ታግሦ የሰጠን ድኅነት በማንም ፍጡር ሊፈፀም ያልቻለና የማይችል አምላካዊ ድኂን ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ምዕመናን የሁለቱም መንገድ ተጠቃሚዎች የሆኑትም ለዚህ ነው፡፡
፪.“ሰው የለኝም” የምትለዋ በወንጌሉ የተጠቀሰች ቃል መፃጉዕ በምን ዓይነት ቀቢፀ ተስፋ ውስጥ እንደነበር ታሳያለች፡፡ በኃያሉ በእግዚአብሔር የፈውስ ሥፍራ ተኝቶ በተስፋ ይጠብቅ የነበረው የሰውን እርዳታ ነበር ጌታም ሲያናግረው ጎልማሳነቱን ዓይቶ ተስፋ ያደረገው ይህንኑ ነበር፡፡ ተስፋ ያደረጋቸው ሰዎች ግን ሠላሳ ስምንት ዓመት አልደረሱለትም፡፡ ሀብት ሥልጣን ጉልበት ወዘተ… ባላቸው ሰዎች የተመኩ ፍፃሜውን አይተዋል፡፡ ሌላው ይቅርና በሰው ፍቅር እንኳ ፍፁም ተስፋ አይጣልም፡፡ የሰው ፍቅር ከአቅምና ከፍቃድ ጋር የተገናኘ ነውና፡፡ በመንገድ ወድቀው ወይም ራቁታቸውን ላይ ታች ሲባዝኑ የምናያቸው የአካልና የአዕምሮ ህሙማን ከሰው ያልተፈጠሩ ሆነው አይደለም፡፡ ችግራቸው ከሰው የፍቅር አቅም በላይ ሆኖ አንጂ፡፡
ፍቅሩ በአቅም ውሱንነት ፈቃዱ በመሰልቸት የማይዳፈን እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ ምንኛ መልካም ነው፡፡ ክቡር ዳዊት “እናትና አባቴ ረሱኝ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” ለእኛ ያለውን ውዴታ ይገልፅልናል፡፡ ጨምሮም “ሴት ከማኀፀንዋ ለወጣው ልጅ አስከማትራራ ትረሣ ይሆናል እኔ ግን አልረሣችሁም” የሚል ለርኅራኄው በእኛ ጨካኝ ህሊና መስፈርት ልናበጅለት የማንችለው አባት ነው፡፡ በእርሱ ታመኑ! መዝ ኢሳ49፥14-16
፫.ለሰው ልጅ የእግዚአብሔር ምህረት የተቋረጠበት ጊዜ የለም፡፡ ከህሊና በላይ የሆነው ርኅራኀሄው ምንግዜም ህዝቡን ይጎበኛል፡፡ ብንተወው አይተወንም እኛ ፈጣሪነቱን ብንክድ እንኳ እርሱ ፍጡራኑ መሆናችንን አይክድም፡፡ አምላካዊ መጎብኘት መቼና እንዴት እንደሚሆን የሚያውቀው ጌታ እግዚአብሔርና እርሱ በመንፈሱ ያመለከታቸው ብቻ ናቸው፡፡
መፃጉዕ የተጎበኘው ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ይህ ለመፃጉዕ የዘገየ ለጌታ እግዚአብሔር ግን ትክክለኛው ሰዓት ነበር፡፡ መፃጉዕ መጎብኘቱን ይጠብቅ የነበረው መልዓኩ ውኃውን ሲያናውጠው በነበረው ሂደት እንጂ አምላክ በአካል አጠገቤ ቆሞ በቃሉ አዝዞ ይፈውሰኛል የሚል እምነቱ አይደለም ሀሳቡ አልነበረውም፡፡ የሆነው ግን እንዲህ ነበር አንድ መልከመልካም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ፍፁም ጤነኛ ጠንካራ የሚመስል ድንገት በመፃጉዕ አልጋ አጠገብ ቆመ፡፡ የተለየ የሚጠይቀው ዘመድ አልነበረውም፤የተጠቁት ሁሉ ዘመዶቹ ነበሩ፡፡ መፃጉዕ የተረጋጋና ፍጹም የሚመስጥ “ልትድን ትወዳለህ?“ የሚል ቃል ወደሰማበት ሲዞር የተመለከተው ነው፡፡ መልሱ ሰው የለኝም ነበር፡፡እዚህ ቦታ መጥቶ ከወደቀ እንዲህ ቀርቦ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ከዚህ ጎልማሳ በቀር መኖሩን ማስታወስ አልቻለም፡፡ የሚያዋራውም ሰው ናፍቋል ብሶቱን ተነፈሰ፡፡ ቀጥሎ የተሰማው ቃል ግን አጥንቱን ሲያበረታው፣ ጡንቻውን ሲያፀናው፣ ጅማቱን ሲፈታው፣ ድካሙን ሲያነቃው እርሱም ሊገነዘበው በማይችል ፍጥነት እመር ብሎ ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ መዝለል ጀመረ፡፡
ይህን ያደረገለትን ከሞት እንኳ ከከፋ ኑሮ ውስጥ ትንሣኤ የሰጠውን ማን መሆኑን ለማሰተዋል ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ብቻ ተጓዘ ነጎደ…
ሰው ይኸው ነው ካደረገለት ይልቅ ለተደረገለት፤ከሠጠው ይልቅ ለተሰጠው ነገር የበለጠ ክብርና ትኩረት ይሰጣል፡፡
ሥጋው እንጂ ህሊናው አካሉ እንጂ መንፈሱ ያልተፈወሰው መፃጉዕ በአይሁድ ጥያቄ ደስታው ሲቋረጥ ነው ማን እንደፈወሰው እንኳ ለማስታወስ የሞከረው፡፡ የጎበኘው ግን ካጠገቡ ርቋል፡፡ መልሶ ሲያገኘውም የተያዘበትን ትብታብ ስላየ የሚብስ እንዳያገኝህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ” አለው፡፡ በዚህም ደዌው ቀድሞም በኃጢአት ምክንያት እንዳገኘው ወደፊትም መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገው አመለከተው፡፡ ግን አልተጠቀመበትም ሂዶ በሰንበት የፈወሰው ኢየሱስ መሆኑን ተናገረ፡፡ ልብ በሉ“መሰከረ” አላለም“ተናገረ“ እንጂ፡፡ ስለዚህ ስሙ መፃጉዕ መሆኑ የተገባ ሆነ ከደዌ ሥጋ እንጂ ከደዌ ነፍስ አልተፈወሰምና፡፡
ወንድሞቼ ክርስቲያኖች መጎብኘታችን ለሚበልጠው እንዲሆን ጸልዩ፡፡ ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምናደርገው ግንኙነት በሥጋ ጉዳይ(Agenda) ላይ ብቻ የተመሠረተ ከሆነ ምን ይጠቅመናል? መጎብኘታችን በነፍስ በሥጋ እንዲሆን ጸልዩ! የመጎብኘታችንን ወራት ማስተዋል እንድንችል ጸልዩ ሲጎበኘን እርሱ መሆኑን ማወቅ እንድንችል ጸልዩ! በቀራንዮ ኮረብታ እጆቹን መስቀል ላይ ሲዘረጋ ሁላችንን ጎበኘን “ልትድን ትወዳለህን” እያለ በውኃ ጥም በደረቀ አንደበቱ ላቀረበልን ግብዣ መልሳችን ምን ይሆን?
፬.ጌታችን ከቃሉ እንደምንረዳው አምላክነቱን የገለፀው በቃሉ(በትምህርቱ) ብቻ ሳይሆን በሥራው ጭምር ነው፡፡ መፃጉዕን ከፈወሰው በኋላ ከአይሁድ ለቀረበለት ጥያቄ የሠጠው መልስ “አባቴ እስከዛሬ ይሠራል፤እኔም ደግሞ እሠራለሁ” የሚል ነው፡፡
የእኛም ክርስትና ቃል ከግብር መስማማት ያስፈልገዋል፡፡ እንግዲህ ምን እንላለን ታላቅ የሆነ ስም ተሸክመናል፡፡ በዚህ ዓለም ሰዎች ሊጠሩበት የሚችሉ ከዚህ የሚልቅ ስም የለም ስሙ ቃል ከግብር ተስማምቶ ካልተገለጠ ከራስ አልፎ ለሌሎች መዘበቻ ከመሆን አያልፍም፡፡ ነን ስላልን ብቻ መሆን አንችልም፡፡
ታለቁ ምሥጢር፡- መፃጉዕ የአዳምና የዘሩ ምሳሌ ነው፡፡ አዳም በኃጢአት ደዌ ተጠቅቶ ወደቀ ይህ የኃጢአት ደዌ ከክብደቱ የተነሣ ማንም ሊያርቅለት አልቻለም፡፡ ዘመኑ ሲርቅ የሰዎች ቀቢፀ ተስፋ እየጨመረ ወርጄ ተወልጄ አድናችኋለው የሚለው አምላካዊ ቃል ኪዳን እየተዘነጋ በብዙ ሰው ሰራሽ ምልከታዎች ከል ለበሰ፡፡ በጣም ጥቂቶች ትንቢት እየተረጎሙ ሱባዔ እየቆጠሩ ተቀመጡ፡፡ በመካከላቸው ሲገለጥም እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ስላልሆነ ሊያውቁትም ሊቀበሉትም አልቻሉም፡፡ተቆራምደው ከተኙበት የውርስ ኃጢአት ምንጣፍ ባለመታዘዝ ከመጣባቸው የኃጢአት ደዌ ፈውሷቸው ሲሔድ አላወቁትም፡፡ አምላክነቱን በቃልም በሥራም እያሳያቸው ሌላ የሚያድን ይጠብቃሉ፡፡ ሐሳዊ መሲህ ሲገለጥም እርሱን የመቀበላችው ስህተት የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ ኢሳ 59፥16፤ዮሐ 1፥10-12
አዳነን“ከዚህ የባሰ እንዳያገኛችሁ ዳግመኛ ኃጢአትን አትስሩ” ብሎንም ዐረገ፡፡ ምክንያቱም አዳም ቢስት ወርጄ ተወልጄ አድንሃለው በሚል ተስፋ የቀደመ ርስቱን አግኝቷል፡፡ የህያው እግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነቱን ፈጣሪነቱን አዳኝነቱን ጌትነቱን የማያምኑ ግን የድኅነት ተስፋ የላቸውም፡፡ የአዳም ቅጣት በዘመን ተገድቧል በእግዚአብሔር ልጅ የማያምኑ ግን ዘላለማዊ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ የሚብስ የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ዮሐ3፥16፤21፤ዮሐ16፥7-11
ይቅጥላል ....
ውስብሐት ለእግዚአብሔር!

