“መንሹ በእጁ ነው፤ ...... "
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!
“መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውን ያጠራዋል” ማቴ 3:12
በምህረቱ ባለጠጋ የሆነ ጌታ እግዚአብሔር የመጨረሻውን ፍርዱን ከመግለጡ በፊት የንስሐ ዕድል መስጠት ልማዱ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ከኖኅና ከሰዶም ሰዎች ገጠመኝ ከነነዌም ታሪክ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ የተመለሱ ድነዋል፤ በልባቸው ጥንካሬ ጸንተው በክፋት የቀጠሉ ጠፍተዋል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ከላይ የተጠቀሱትን ታሪኮች እንደማሳያ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ የሰማው የለም እንጂ፡፡ ማቴ 12፡41፤ ማቴ 24፡38፤ ሉቃ 17፡28-32
አውድማውን ያጠራ ዘንድ መንሹን የያዘው ከመገለጡ በፊት ቤተ አይሁድ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ሄደው ነበር፡፡ ዕለት ተዕለት ጌታ እግዚአብሔርን በከንፈራቸው ምህረትንና በረከትን በሥራቸው ግን ፍርድንና ጥፋትን እየለመኑት ነበር፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነው እርሱ ግን አባቱን በግፍ ያስገደሉበትን ብላቴና ለበቀል ሳይሆን ወደ ምህረት ጮኾ እንዲጠራቸው ላከው፡፡ በምድረ በዳ (አበው በትርጓሜ ምድረ በዳ የተባለ የአይሁድ ልቡን ነው፡፡ ምድረ በዳ ውሃ ልምላሜ እንደሌለበት የአይሁድ ልቡናም ከሃይማኖት ከምግባር የተራቆተ ነበር ይላሉ፡፡ ስም፣ ሥርዓትና ምልክት ብቻ ቀርቶላቸው ነበር፡፡ ዛሬም በእኛ ዘንድ ያለው ክርስትና ስም፣ ሥርዓትና ምልክት ብቻ ቀርቶልን በፍቅር ከሆን ሃይማኖትና ምግባር ጠፍ ሆነናል) የተገለጠው ሰባኪም በትምህርቱ የነበሩበትን ሁኔታ ገልጦ አሳያቸው፡፡ ትምህርት መስታወት ነው፡፡ መስታወት ፊታችን ላይ ያለብንን አደፍ ጉድፍ ገልጦ ቢያሳይ እንጂ እንዳያፀዳ ትምህርትም በራሱ ድኅነት አያመጣም፤ ነውርን ገልጦ ያሳያል እንጂ፡፡ ሰምቶ መመለስ ለእያንዳንዱ የተተወ ምርጫ ነው፡፡ ትምህርቱም በሦስቱ መደብ ተለይቶ የቀረበ ነበር፡፡ ለቤተ ክህነቱ፣ በመንግሥት አስተዳደር ለነበሩና ለሕዝቡ፡፡
ከሕዝቡ እንጀምርና በደረጃ ወደ ላይ እየወጣን ለመመልከት እንሞክር፡፡ ሕዝቡ የዮሐንስን ትምህርት ሰምተው ምን እናድርግ? ሲሉ የመከራቸው “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው ይስጥ፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያካፍል” በማለት ነው፡፡ በዚህ ንግግሩ ሕዝቡ የነበረበትን ሁኔታ ገልጾታል፡፡ ሰው ከመረዳዳትና ከመተዛዘን ይልቅ ሁሉ በግለኝነት መንፈስ የሰከረበት፤ ሀብት በማከማቸት የታወረበት፤ ለወገን መራራት እንደ ሞኝነት የተቆጠረበት፤ ተካፍሎ መብላት በነበር የቀረበት፤ በልጦ መታየትና በወንድም ላይ መኩራት መለያ የሆነበት ዘመነ እኪት ነበር፡፡ ቤተ አይሁድ የኖሩበት የአባቶቻቸው ባህል ይኸውም መተዛዘን፣ መረዳዳት፣ መተባበር ከመካከላቸው ጠፍቶ በምትኩ በተደጋጋሚ በባርነት የገዟቸው የአህዛብ ልማድ አማሰናቸው፡
፡ በይበልጥ የሄለናውያን(Helenistic) የአመለካከትና የአኗኗር ዘይቤ ከፍተኛ ተጽዕኖ የማንነት ግራ መጋባት ትግል ውስጥ ዘፈቃቸው፡፡ የጥንቱን የአይሁድ ባህል እንዳይጠፋ በሚቀኑና በአዲሱ ልማደ አህዛብ በተጠመቁ መካከል ልዩነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሰፋ ነበር፡፡ ይህም በአንድ አሳብ ተስማምቶና ተረዳድቶ ከመኖር ይልቅ በልዩነት ለመነታረክ ምክንያት ሆነ፡፡ እንኳን በጠላቶቻቸው ላይ ድል ሊያገኙ ቀርቶ እርስ በርሳቸው በጠላትነት አንዱ በሌላው ላይ ተነሱ፡፡ ዛሬ በእኛም የሚታይ ቤተ አይሁድ ጥፋታቸው በቀረበበት ጊዜ ያሳዩ የነበረው ጠባይ ነው፡፡ ቀድሞ እንታወቅባቸው የነበሩ አባቶቻችን በሰላምና በበረከት እንዲኖሩ ያስቻሏቸው አብሮ በመተሳሰብና በመተዛዘን መኖር ከእኛ ርቋል፡፡ ከስግብግብነታችን ብዛት አማራጭ በማይቀርብላቸው የጤናና የትምህርት ጉዳይ ላይ እንኳ ወገናችንን እንዘርፋለን፡፡ በሰው ጤናና ነገ ሀገር በሚረከቡ ሕጻናት ሕይወት ላይ ከመነገድ የከፋ ኅሊና ቢስነትና የሥነ ምግባር ዝቅጠት የለም፡፡ ኢትዮጵያውያን አሁን ባለንበት ማንነት ዓይናችንን ቀና አድርገን ከጌታ እግዚአብሔር ዘንድ ምህረትንና በበረከት የተሞሉ ዘመናትን ለመለመን የሚያበቃ የሞራል ብቃት የለንም፡
፡ ምህረት የሚሰጠው በራሳቸው ላይ ሊደረግባቸው የማይወዱትን በሌላው ላይ ለማያደርጉና ምህረት ለተገባቸው ነው፡፡ ለግፈኛ ምህረት ማድረግ በክፉ ሥራህ ግፋበት እንደማለት ነው፡፡ አሁን የሚያድነን ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት ወዘተ .
. . አይደለም፤ ግፍ መሥራትን ማቆም እንጂ፡፡ ግፍ እየሠሩ ጾምና ጸሎት በጌታ እግዚአብሔር ላይ መዘበት ነው፡፡
በሀገር አስተዳደር ረገድ ደግሞ የሮም መንግሥት ሕግንና የሠለጠነ የአስተዳደር ዘይቤን ሽፋን በማድረግ ብዙ ግፍ ይፈፅም ነበር፡፡ ዛሬ ብዙ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ያልቻሉ የዓለም ሀገራትን በዲሞክራሲና በሰብዐዊ መብት ሽፋን ሴራን እየደበቁ የማድቀቅና የማንነት ክስረት ውስጥ የመክተት አካሄድ ዛሬ የመጣ ሳይሆን ከቀድሞ የተወረሰ ነው፡፡ ዛሬም እኛ በግልፅና በሥውር ማን እንደሚገዛን የታወቀ ነው፡፡ ዛሬ ያሉ መንግሥታት ታላላቅ ግፍ የሚፈጽሙ የሕገ መንግሥትን፣ የዲሞክራሲንና የሰብዓዊ መብቶችን ድንጋጌ ጭምብል አጥልቀው ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን ክቡር ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት ተመርቶ እንዲህ ገልጿቸዋል፡፡
ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል፤
በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤
እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፤ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ፤
በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም፤ ጉሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው በምላሳቸው ሸነገሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤
አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቷል፤ ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፤ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤
እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም፡፡
በኢትዮጵያም ዛሬ በዲሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ሽፋን ለእውነት በቆሙ ላይ ብዙ ግፍ ይፈጸማል፡፡ አንድ ሀገር ሕግ ካለው ሕግን ማክበር ያለበት ሕዝቡ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ እኛ ባሥልጣናት አረዳድ ግን የእነርሱ ግዴታ ሕግን ማስከበር እንጂ ሕግ ማክበር አይደለም፡፡ የመንግሥት ሹመኞች በየደረጃቸውና እንደየአቅማቸው ሕግን ሲጥሱ ጠያቂ የለባቸውም፡፡ ለመጠየቅ የግድ ከሥልጣናቸው መውረድ አለባቸው፡፡ ተጠያቂነትን ስለሚፈሩትና ውጤቱንም ስለሚያውቁ ሥልጣን ለእነርሱ ሕዝብ ማገልገያ ሳይሆን የደኅንነታቸው ዋስትና ነው፡፡ በሁሉ ላይ የሠለጠነው እውነተኛው ፈራጅ አውድማውን ሊያጠራ በፍርድ ሲገለጥ ግን ሕጋችሁም፣ ሥልጣናችሁም ሆነ የሽንገላ አንደበታችሁ መደበቂያ አይሆኗችሁም፡፡ ልዑሉ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ፈርዖንንና ናቡከደነፆርን አልጠቅስም፡፡ ትናንት አጠገባችሁ የነበሩና ዛሬ የሌሉትን ማየት በቂ ነው፡፡ ማየት ከቻላችሁ!!! እያንዳንዱ ሸፍጥ ግፍ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ነገ በሌላው ይቅርና በራሳችሁ ልጆችና የልጅ ልጆች ሳይቀር የተናቃችሁ፣ የተጠላችሁና የምትረገሙ ትሆናላችሁ፡፡ ነገ መልስ መስጠት ለሕሊናዬ ነው የምሠራው ብላችሁ እንደ መመፃደቅ ቀላል አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያን ያደቀቀው ሕዝቡን የደኅንነት ሥጋት ላይ የጣለውና እግዚአብሔርም የተፀየፈው ባልተገራ ኅሊናችሁ ላይ መደገፋችሁን ነው፡፡
በቤተ አይሁድ በመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ላይ የተቀመጡትም ሠርቶ ለማደር ደፋ ቀና የሚለውን ለፍቶ አደር ከተፈቀደው በላይ ቀረጥ እየጫኑ ያስጨንቁት ነበር፡፡ በዚህም ነው ዮሐንስ ቀራጮችን “ከተፈቀደላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ” ሲል የገሰፃቸው፡፡ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ግን ለመናገር የሚያስጨንቅ ነው፡፡ በመጽሐፍ “ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ አያውቁምን?” ተብሎ እንደ ተጻፈ በዚህ የከበሩ ሁሉ በቁም ሳሉ ጭንቀትና ደዌ ሲሞቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚበላቸው ናቸው፡፡ ቢፈጥንም ወይ ቢዘገይም በችግር ከደረቀ ሰውነቱ የሚወጣ የደሃ ዕንባ መልስ ማግኘቱ አይቀርም፡፡
ሕዝብ ለመጠበቅ ቃል ኪዳን የፈጸሙ ወታደሮችም የደመወዛቸውን ማነስ ለማካካስ ሰውን መማለጃ ለመቀበል በሀሰት እየከሰሱ ያስጨንቁ ነበር፡፡ የታመነው ሰባኪ ጭፍሮች ሲጠይቁት “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሀሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ” በማለት ያለ ፍርሃት በደላቸውን ነግሯቸዋል፡፡ በሀገራችን የሕግ መከበር የሌለው ሕግ ስለ ሌለ ሳይሆን ሕግ አስፈጻሚ አካላት በተለያየ ምክንያት (ሙስና፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቡድን፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ ወዘተ .
. .) ስለሚሸረሽሩት ነው፡፡ ብልሹ ሕግ አስፈጻሚዎች ባሉበት እንኳን የሰዎችን ቀርቶ ፍፁም ንፁህ የሆነውን ሕገ እግዚአብሔርን ማስፈጸም እጅግ ከባድ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ መምከር፣ መገሠፅና ማስተካከል ያለበት የቤተ ክህነቱም በተመሳሳይ ነቅዞ ነበር፡፡ ሥርዓት ደንጋጊና ሕግ አስፈፃሚ የሆነ አካል ራሱ የእግዚአብሔርን ሕግ ከናቀ የጥፋት ሥር ይሆናል፡፡ ከውድቀት (ከጥፋት) በፊት በአይሁድ መካከል የታየ የመጀመሪያ ምልክት ከፍተኛ የሆነ መከፋፈል ነበር፡፡ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያን፣ ኤሴያዊያን፣ ቀነናውያን ወዘተ . . . ተብለው በቡድን ተከፋፍለዋል፡፡ አንዱ ከአንዱ ጋር አይተባበርም ነበር፡፡ ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንንም ይኸው የመከፋፈል ምች የመለያየት ዋግ መቷቸዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ”አይሁዳዊ ግሪካዊ የለም ሴት ወንድ ጌታ ሎሌ የለም ሁሉ በክርስቶስ አንድ ሆኗል” የሚለው ተረስቶ በዘር መሳሳብ ሰልጥኖብና፡፡ መከፋፈል መለያየት ደግሞ የውድቀት ዋዜማ መሆኑ የታመነ ነው፡፡
ሁለተኛው ምልክት ቤተ መቅደሱን የንግድ ማዕከል ማድረጋቸው ነበር፡፡ የቤተመቅደሱ አገልጋዮችም የእስራኤልን አምላክ አንደ አባቶቻቸው በፍቅርና በቅንዓት ከማገልገል ይልቅ በጥቅም ታውረው፤ ቤተ መቅደሱንም በሀብት መክበሪያ አድርገውት ነበር፡፡ ይህ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን እያታየ ያለ ምልክት ነው፡፡ አገልጋዮች ምንደኞችና ላልተገባ ጥቅም ተላልፈን የተሰጠን ሆነናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በገቢ ራሷን መቻሏን የሚጠላ ማንም ባይኖርም በፋይናንስ ከመጠንከር በላይ ግን በእምነት፣ በጸሎት፣ በመንፈስ፣ በእውነት፣ በሕይወት፣ በተጋድሎ ወዘተ … መጠንከር ይጠበቅበታል፡፡ ዓለምን፣ የጨለማ አበጋዞችንና መልዕክተኞቻቸውን ድል እየነሳች እዚህ የደረሰች በእርሱ ነውና፡፡ ባሏት ይዞታዎች ላይም መገንባት ያለባት ለሰው አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ እድገት የሚጠቅም ተቋም እንጂ ሀብት ለማከማቸት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የቤተ መቅደሱ ባለቤት አይሁድን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፣ እናንተ የሌቦችና የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት” ቢላቸውም በምህረት የተገለጠ ተግሳፁን ናቁ፡፡ እኛም የአይሁድ ወራሾች ሆነን መቅደሱን አቃለናል ተግሣፁንም ንቀናል፡፡
ሶስተኛው ምልክት የመኳንንትን ሥልጣን በመፍራት እውነትን አለመግለጥ ነበር፡፡ ሄሮድስ የወንድሙን ሚስት እስከ ማግባት ኃጢአት ሲሠራ ባህታዊው ዮሐንስ እንጂ ቤተ ክህነቱ ትንፍሽ አላለም፡፡ በዘመኑ የነበረው የአይሁድ ቤተ ክህነት ዘማውያን ባለሥልጣናትን የሚታገሥ ለድሆች የሚራራ ድውያንን የሚፈውስ ንጹሑን ጌታ ግን የሚከስ ነበር፡፡ ለምድራዊ ገዥዎች እጅ የሰጠች ቤተ ክህነት ተቀንዮቷ ለምድራዊ ጌታ ስለሆነ ሰማያዊውን አደራ ለመፈጸም አቅም አይኖራትም፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ተገልጣ ታየች እንጂ ከዓለም አይደለችም፡፡ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ እንጂ ነገ ወደ አፈርነት ከሚቀየሩ ዕቡይ ምድራዊ ገዦች ጋር ኅብረትም የላትም፡፡ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡
አራተኛው ምልክት የእግዚአብሔር ባላደራዎች የነበሩት ካህናትና የሕግ መምህራን ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ በእውነትና በቁርጠኝነት ከመሥራት ይልቅ የልብሳቸውን ዘርፍ በማስረዘምና አሸንክታብ በማብዛት መንፈሳዊ ለመምሰል መሞከራቸው ነው፡፡ የነበሩበትን ግብዝነት ጌታችን ገልፆ ነግሯቸው ነበር፤ ግን አልተመለሱም (ማቴ 23 ተመልከት)፡፡ ካህናተ ሀዲስን ከፈሪሳዊያን እርሾ ተጠበቁ አለን፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው በተከለከልነው እርሾ ቦክተን ማዕዳችንን የኮመጠጠ ሞላነው፡፡
አምስተኛው ምልክት በቤተ ክህነቱና በመናንያኑ መካከል የነበረው መቃቃር ነው፡፡ ኤሴያውያን በሚል መጠሪያ የሚታወቁት መናንያን በቤተ መቅደስ የሚፈፀመውን ነውር ከመጠየፋቸው የተነሳ ግንኙነታቸውን ጨርሰው አቋርጠው በዮርዳኖስ በረሃ ተከተው ይኖሩ ነበር፡፡ ጌታችን በበረሃ የጾመው በቤተ መቅደስም ያስተማረው ሁለቱንም አገልግሎት ባርኮ ሊሰጥ ነው፡፡ በዘመናት ቤተ ክርስቲያን የተጠበቀችውም በመናንያን ጸሎትና በመምህራን ትጋት ነው፡፡ ዛሬ ግን ገዳማውያኑ ቤተ ክህነቱን እንደ ዓለማዊ ቆጥረው ቤተ ክህነቱም መናንያኑን ማማከርን ችላ ብሎት የተናጠል ጉዞውን ተያይዘነዋል፡፡ ሁለቱን አስተሳሰሯቸው ያለ መዋቅር እንጂ መንፈስ እንዳልሆነ በግልፅ እየታየ ነው፡፡
ስድስተኛው ምልክት ሢመት ነው፡፡ በሕገ ኦሪት መሰረት የሚሾም አንድ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ቤተ አይሁድ ግን ቤተ መቅደሱ ላይ ሥርዓት ጥሰው ሕግ አፍርሰው አንዱ ሊቀ ካህናት ሳይሞት ሌላ ሾመው ሀናና ቀያፋ በተባሉ በሁለት ሊቃነ ካህናት ይመሩ ነበር፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሊኖራት የሚገባ ፓትርያርክ አንድ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ግን የሆነውና እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ነው አውድማን ሊያጠራ መንሽ የያዘው የተገለጠው፡፡
ዮሐንስ መጥምቅ በአውድማው ላይ ሥልጣን ያለውን መምጣት የገለፀው እንዲህ ሲል ነው፡፡ “እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፡፡ እላችኋለሁና ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሳለት ለእግዚአብሔር ይቻለዋል፡፡ አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቃጥቷል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ . . . መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል፡፡”
አንባቢው ያስተውል! በአይሁድ ሕዝብ፣ ገዥዎችና ቤተ ክህነት ዘንድ ይፈፀም የነበረው ጌታ እግዚአብሔርን የሚሳዝን በደል በልዑሉ ቁጣ ለመጠረግ ዋዜማ ነበር፡፡ እኒህ ሁሉ በእኛ መካካል መፈፀማቸውን ያስተዋለ ጥፋት በደጃችን እንደ ቀረበ ይወቅ፡፡ የእግዚአብሔር አውድማ ኢትዮጵያ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ ካልተገኘብን በአይሁድ የደረሰ እንደሚደርስብን የማያጠራጥር ነው፡፡ አውድማው ይጠራ ዘንድ ግድ ነው፡፡ እኛ እንዲህ ነን! የነእንትና ዘር ነን! አንፈርስም . . . አንጠፋም በሚል ፉከራ እርስ በርስ በመደላለል የምንኖርበት ሰዓት አብቅቷል፡፡ አሁን ባለ መንሹ ቆሟል፤
ምሳርም በዛፍ ሥር ተቃጥቷል፤ መቆረጥ ያለበት ሁሉ ይቆረጣል፡፡ ልዑሉን በመፍራት የሚኖሩ ግን ከፀጉራቸው አንዲት አትወድቅም፡፡ ለእነርሱ ሞትም ሆነ ሕይወት ለክብር ይሆናል!
ስልክ ይጠራል
ቀሲስ፡- ጤና ይስጥልኝ… እንዴት ከረሙ?
መልስ፡- እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን! በደህና ሰነበቱ ወይ ቀሲስ? ቀሲስ፡- ክብር ይግባው! ደህና ነኝ!
(መሀሉ አይነገርም)
ስንብት
ቀሲስ፡- እንግዲህ ጌታ እግዚአብሔር ምህረቱን እንዲያቀርብ መዓቱን እንዲያርቅ ጸልዩልን? መልስ፡- ዘመነ ዮሐንስን በደኅና ካለፍን ምንም አንሆን አይዟችሁ!
ቀሲስ፡- ዘመነ ሉቃስ ማለትዎ ነው?
መልስ፡- ኧኸ . . . ሉቃስማ አለፈ ዮሐንስን ነው እንጂ!
ቀሲስ፡- ኧረ እባካችሁ እኛ እኮ በጭንቅ አለቅን፡፡ እናንተ ሚስት ልጅ ውላጅ የለ ምንም አያሳስባችሁ፡፡ እኛ ግን እዚህ በጭንቀት አለቅን፡፡
መልስ፡- አዬ እሱን እንኳ ተውት የሚጨነቅ ማን እንደሆነ ባለቤቱ ያውቃል፡፡ ለማንኛውም ዘመነ ላህም አልፎ የሚተካው ዘመነ ንስር ስለሆነ እንደ ንስርነቱ የሚለቀመውን ለቅሞ ሰላም ይሆናል አይዟችሁ!
ቀሲስ፡- እንግዲያው ከሚለቀሙት እንዳንሆን በጸሎታችሁ አስቡን?
መልስ፡- ደግ ዛዲያ ምን ይዘን ኖሯል? አይዟችሁ! ጸሎተ አበው ይጠብቃችሁ! ቀሲስ፡- አሜን!!!
“ለእኔም ዘመኑ ቀርቧልና የዚህን መጽሐፍ . . . ቃል በማኅተም አትዝጋው፡፡ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፤ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፤ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅን ያድርግ፤ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ”
በአዲስ ዓመት መልካም አዲስ ሕይወት!
ተጻፈ ኅሊናቸው ላልተቀሰፈ በጳጉሜን 2011 ዓ.ም ቀሲስ ታምራት ውቤ