በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!
ትውልዱ ከእመቤታችን ምን ይማራል?
መግቢያ
‹‹ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ›› በማለት አባ ሕርያቆስ በእመቤታችን ስም(ለእመቤታችን) በደረሰው የቁርባን ምስጋናው ስለ እመቤታችን ንጽሕናና ቅድስና፤ አካላዊቃልን በሥጋ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ለመውለድ መብቃት እንደቻለች፤ የአበው ተስፋ የነቢያትም ትንቢትና ምሳሌ በእርሱዋ እንዴት እንደተፈጸመ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል፡፡ ሊፈጽመውግን አልቻለም፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጐሥዐ ልብየ… ልቤ በጎ ነገርን አፈለቀ እኔ የንጉሥን ሥራ እናገራለሁ››፤ ብሎ ቅድመ ዓለም ያለ ፍጡራን አምላክ፣ ያለ ተገዢ ጌታ፣ ያለ ሎላልት ንጉሥ የሆነ፤ ድህረ ዓለም በማኅፀነ ማርያም በተዋህዶ ኋላም በመስቀል የነገሠ የእግዚአብሔርን ሥራ እናገራለሁ ብሎ ቢጀምር ሊፈጽመው እንዳልቻለ የአባ ሕርያቆስም እንዲሁ ነው፡፡መዝ 44፥1
ስለ ምሥጢረ ሥላሴ(ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ልዩ ሦስትነት) በቅጥነተ ኅሊና ሊመረምሩ የወደዱ ብዙ ሊቃውንት፤ስለ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ፍጹም ሰው መሆን የማይወሰነው መወሰኑ ርቀትን ከግዘፍ፣ኃይልን ከድካም፣ባዕልነትን ከንድየት፣ሕያውነትን ከመዋቲነት ፍጹም በሆነ ተዋሕዶ ሳይቀላቀሉ ሳይለያዩ ሳይጠፋፉ አንድ ማድረግ፤ ጉምቱ ጉምቱ መንፈሳውያን ሊቃውንት ጠንቅቀው ሊጽፉ የሞከሩ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ይህን ማድረግ ሳይቻላቸው ድካማቸው ስዒን በወለደው አንክሮ ተደምድሟል፡፡
የጌታ እግዚብሔርን ባሕርይ የመድኃኒታችንንም ሰው የመሆን ምሥጢር ጠንቅቆ ፈፅሞ መናገር እንዳይቻል፤ የአብ ሙሽራ የወልድ ማደሪያ የመንፈስ ቅዱስ ንጽሕት አዳራሽ ስለሆነች ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በእርሷ ስለተደረገ ነገርና ስለ ክብሯ ጠንቅቆ ፈጽሞ መናገር አይቻልም፡፡
‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር›› እንዳለ ነብዩ ዳዊት የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተከበረ(ድንቅ) ነገር ይባላል ሲል ነው፡፡ቃሉ ቃለ አንክሮ ነው፡፡‹‹ድንቅ›› የሚለው ቃለ አንክሮ ከአእምሮአችን በላይ ለሆነ የተከተተ መግለጫ ልንሰጠው ለማንችለው ጉዳይ የምንጠቀምበት ነው፡፡እመቤታችን ብሥራተ መልአኩን ከተቀበለች በኋላ ‹‹እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዐቢያተ››አብ ቢሉ በልጁ ወልድ ቢሉ በሥልጣኑ ምድራዊ ባይደለ ሰማያዊ፤ ተፈጥሯዊ ባይደለ አምላካዊ፤ ጊዜያዊ ያይደለ ዘላለማዊ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል ብላ መስክራለች፡፡መዝ 86፥3 ፤ሉቃ 1፥49
እንዚራ መንፈስ ቅዱስ የተባለ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ስለ እመቤታችን በጻፈው ድርሰቱ በብዙ ሕብረ አምሳል እየመሰለ ሲያወድሳት ቢቆይም የእርሷን ክብርና ገናናነት ተናግሮ መፈጸም እንደማይቻል ከተረዳው በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሰውነቱ‹‹መኑ ዘይክል ነቢበ ዕበየኪ ወአልቦ ዘይመስል ኪያኪ›› ትርጉም ‹‹ክብርሽን ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማነው? አንቺን የሚመስልሽ የለምና››ሲል መልካም ነገርን አፍልቋል፡፡
የምሥጋና አባቱ(መምህሩ)ነቢዩ ዳዊት ስለ ጌታ እግዚአብሔር‹‹መኑ ይመስለከ እምነ አማልክት እግዚኦ›› ‹‹አቤቱ ከአማልክት አንተን የሚመስልህ ማነው?›› ብሎ የልዑሉን ገናናነት እንደተናገረ፤ ከአማልክት የሚተካከለው ያይደለ የሚቀርበው፤የሚቀርበው ያይደለ የሚመስለው የሌለ የልዑሉ ዙፋን፤እርሱን በማኅፀኗ ተሸክማ በሥጋ ወልዳ ዓለማትን በረቂቅ በግዘፍ የሚመግበውን ጡቶቿን አጥብታ ያሳደገች የእርሷንም ክብር ገናንነት መናገር አይቻልም ሲል በምሥጢር መስሎታል፡፡ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ
ጨምሮም ‹‹ዕበያ ለድንግል ኢይትከሀል ለተነግሮ እስመ እግዚእ ኀረያ›› የድንግል ክብሯ ጠንቅቆ ይነገር ዘንድ አይቻልም ጌታ መርጧታልና፡፡አብ ቢሉ ለልጁ ማደርያ እንድትሆን ወልድ ቢሉ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ ሰው ይሆን ዘንድ መርጧታልና፡፡ መምረጡንም ቅድመ ሥጋዌ ቢሉ በነቢያት ትንቢት፤ ጊዜ ሥጋዌ ቢሉ በመልአክ ብሥራት፤ ድኅረ ሥጋዌ ቢሉ ሥጋን ነስቶ በመታየት፣ በሐዋርያት ትምህርት፣ በሊቃውንት መጻሕፍት አስረድቶናል፡፡ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ምዕመናን፤ እንዲሁም በእምነት በቀኖና የሚመስሏቸው ሌሎች የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ዳዊት በመዝሙሩ‹‹ወዘሕጎ ያነብብ መዐልተ ወሌሊተ ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ፤እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቈፅላኒ ኢይትነገፍ›› እንዳለ የነቢያትን ትንቢት፣የሐዋርያትን ትምህርት፣ የሊቃውንትን የትርጓሜ ድርሳናት፣ ከንፁሕ ምንጭ ስለ አምላካቸው ታላቅነት፤ ስለ እመቤታችንም ንፅሕና ቅድስና ክብርና አማላጅነት ሲጠጡ በመኖራቸው ልምላሜ ነፍስ ሳይለያቸው ሥራ ሊሠሩ በተሰጣቸው ጊዜ የንስሐ ፍሬ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት በትሩፋት ላይ ትሩፋት እየጨመሩ የእርሷን ጸጋ ክንፈ ረድዔት በማድረግ እንደ ንስር በመንፈሳዊ ሕይወትና እውቀት ሲመጥቁ ይታያሉ፡፡መዝ 1፥2-3
ክርስቲያን ለመባልና የልጅነትን ክብር ለማግኘት የቻልነው አካላዊ ቃል ከእመቤታችን ተወልዶ የቤዛነትን ሥራ በመፈጸም ዓለምን ካዳነ በኋላ ነው፡፡‹‹በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው›› እንዲል፡፡ ወረደ ተወለደ መከራን ተቀበለ ተሰቀለ ሞተ ተነሣዐረገ ዳግመኛ በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ይመጣል ብሎ ሥጋን ተዋሕዶ በፈፀመው ሥራና ስመ ሥጋዌውን ስመ ሥርየት ስመ ድኅነት ነው በማለት ማመን ነው፡፡ይህ ሁሉ የተፈፀመ ከእርሷ በነሳው ሥጋ ነው ብሎ የሚያምን በነገረ ድኅነት ውስጥ ያለውን የእመቤታችንን ሱታፌ መገንዘብ አይሳነውም፡፡
በኦሪት ጽላት ያደረበት(የተቀመጠበት)ታቦት በሚታይ ገንዘብ የእስራኤል ዘሥጋ የአምልኮታቸው ማዕከል ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ቃሉን የሚያሰማቸው በታቦቱ ላይ በመገለፅ ነበር፡፡ እስራኤል ታቦቱን ይዘው ባህር ተከፍሎላቸው ቅጥር ፈርሶላቸው ጠላት ጠፍቶላቸው ምደረ ርስት ከነዓንን ወርሰዋል፡፡ታቦት የእመቤታችን ጽላት የጌታ ምሳሌ መሆኑ በብዙ መተርጉማን የተብራራ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነትና የእመቤታችንን ምልጃ ማዕከል አድርጋ አምልኮዋን ትፈጽማለች፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የጌታችንን መወለድ በልባቸው ይዘው ያመኑ፤ በአፋቸውም የእርሱን አምላክነት የእርሷን ወላዲተ አምላክነት የመሰከሩ ምዕመናን በጥምቀት በሚገኝ ልጅነት ጥቅመ ኃጢአት ፈርሶላቸው ዲያብሎስን ድል ነስተው ርስት መንግሥተ ሰማያትን ለመውረሳቸው ምሳሌ ነበር፡፡
ቅድስት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያምን አልቦ (ያገለለ) ክርስትና የለም፡፡በዚህ የተቃኘ ትምህርትም ከአባቶቻችን ከሐዋርያትና ከሊቃውንት የተገኘም አይደለም፡፡ ወንጌላውያኑም እመቤታችን በወንጌል በነገረ ድኅነት የነበራትን ሱታፌ በግልጽ ጽፈውታል፤ከጽንስ እስከ በዓለ ጵራቅሊጦስ፡፡ ጌታችን ካረገ በኋላ እንኳ ሐዋርያት እርሷን እንደ ታቦት በመካከላቸው አድርገው ይጸልዩ ነበረ ፡፡ጸሐፊው‹‹የኢየሱስም እናት በመካከላቸው ነበረች›› ብሎ የጻፈ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
ጌታችን ልጅነትን የምናገኝበትን ሥርዓተ ጥምቀት አስቀድሞ በግብር ፈፅሞ ምሳሌ በመሆን ኋላ በቃሉ ከውኃና ከመንፈስቅዱስ ካልተወለዳችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ልትገቡ አይቻላችሁም እንዳለ፤ በመስቀሉ ላይ በዮሐንስ አማካኝነት በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ‹‹እነኋት እናትህ›› ‹‹እነሆ ልጅሽ›› ብሎ በቃሉ እናት አድርጎ ከመስጠቱ በፊት ከእርሷ በመወለዱ ልጆቿ አድርጎናል፡፡ ሊቃውንትም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ በመሆኑ እኛን በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች አደረገን ‹‹ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ. . .›› እንዲል፤ ከድንግሊቱም ተወለዶ የድንግሊቱ ልጆች አደረገን ብለው አመስጥረውታል፡፡የዮሐንስ አፈወርቅ የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ማቴ1፥25-ፍጻሜ
ጌታ ቅድመ ዓለም አካል ዘእምአካል ባህርይ ዘእምባህርይ ከአብ እንደተወለደ፤ ድኅረ ዓለም ደግሞ ከእመቤታችን ፍጹም የሰውን ባህርይ በመያዝ በግዘፍ አካል ነስቶ ተወልዷል፡፡‹‹ንሕነሰ አባላቲሁ ለክርስቶስ››እኛ የክርስቶስ ብልቶቹ(አካሉ)ነን እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ በምሥጢር የክርስቶስ አካሉ የምንባል ክርስቲያኖች ሁሉ ከእርሷ ተወልደናል፤ እናትነቷም ተሰጥቶናል፡፡ ‹‹እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ›› ‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል ከእርሷ ሰው ተወልዷልና›› እንዳለ ክቡር ዳዊት ከአዳም በሥጋ የተወለደ ሁሉ እንደሞተ፤ ከእርሱ(ከክርስቶስ) በመንፈስ የሚወለድ ሁሉ ለዘላለም በሕይወት እንዲኖር ከእርሷ ተወልዷልና፤ ሰው እመቤታችንን ጸወነ ሥጋ ጸወነ ነፍስ(የነፍሳችንና የሥጋችን መጠጊያ መጽናኛ) እናታችን ሲላት ይኖራል ሲል የተናገረው ሁሉ በዚህ ተፈጽሟል፡፡1ቆሮ6፥15፤1ቆሮ12፥12-27፤መዝ86፥5
እመቤታችን በክርስትና ካላት ቦታ በትንሹ ይህ ካልን በልጇ አምነን ክርስቲያን የተባልን ሁላችን ከእናትነቷ ምን ተምረናል? በወንጌል ከተገለጠው የእመቤታችን ሕይወት ምን ወስደናል? በእርግጥስ እንደ እናትነቷ የእኛ የክርስትና ሕይወት ለእርሷ ደስታ የሚሆን ነውን? የሚለውን ማንሳት ያስፈልገናል፡፡
ይህንን እንድናነሳ ያስገደደን በአብዛኛው ስለ እርሷ በማስተማር እንጂ ከእርሷ ፍጹም ልዩና የተቀደሰ ሕይወት ስንማር አንታይምና ነው፡፡ከእመቤታችን ሕይወት ልንወርስ የሚገቡንን አርአያ ቅድስና (መልካም ነገሮች) መንፈስ ቅዱስ በዘመናት በሊቃውንት አንደበት በቅዱሳን ሕይወት አድሮ እንዳስተማረን ሁሉ ከእርሱ የተቀበልነውን እንዲሁ እናቀብላለን፡፡
1ኛ. ትህትና፡- በእመቤታችን ሕይወት የምናየው በቃላት ከመገለጽ በላይ የሆነ ትኅትና ነው፡፡ ሊቃውንት ወትሮም እመቤታችን መጽሐፈ ኢሳይያስን ስታነብ‹‹እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙን አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች›› ብሎ ከተናገረው ብትደርስ እኔ በሆንኩ አላለችምከዚች ድንግል ደርሼ ወጥቼ ወርጄ ባገለገልኳት አለች እንጂ፡፡ ኢሳ7፥14
ዛሬ ክብርን ሁሉ የከፍታ ወንበርን ሁሉ ለራሱ የሚመኝ እንጂ ለሀገር ለቤተክርስቲያን እንዲህ የሚሠራ ተነስቶ እኔ አገልጋዩ ሆኜ ባለፍኩ የሚል ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ይህን የእመቤታችንን የትኅትና ሕይወት ማስተዋል ያስፈልገናል፡፡ተመርጠው ለክብር የሆኑትንም ስናይ ቀርቦ ማገልገል እንጂ መተቸት ለውጥ አያመጣም፡፡ ዛሬ ሁላችን የምንጨነቅ ሌላውን ስለመለወጥ እንጂ ስለራሳችን መለወጥ አይደለም፡፡
የእመቤታችን ትኅትና በመልአኩ ብስራትም ተገልጸ_ል፡፡ ያንቺ ጽንስ እንደ ሌሎች ሴቶች አይደለም ካንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ባላት ሰዓት‹‹እነሆ የጌታ አገልጋዩ (ገረዱ)እንደ ቃልህ ይሁንልኝ›› በማለቷ ታውቋል፡፡ እናቱ ትሆኛለሽ ሲላት ለልጇ አገልጋዩ መሆንዋን በመግለጽ ነበር ትኅትናዋን ያሳየች፡፡
ጌታ በመስቀል ሳለ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ››ለእመቤታችንም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› ብሎ ሲያረካክባቸው፤ ከጌታ ጋር ኖሬ ከአገልጋይ፣ ከመምህር ጋር ኖሬ ከደቀመዝሙር፤ ከፈጣሪ ጋር ኖሬ ከፍጡር አላለችም ዮሐንስ ወደ ቤቱ ሲወስዳት በትኅትና ተቀበለች እንጂ፡፡ ስንቶቻችን ይሆን ከታናናሾቻችን ጋር እነርሱን መስለን መኖር የምንችል? ከታላላቆች ጋርማ ማንነታችንን ሸጠን ክብራችንን ጥለን እምነታችንን ሰውተን አንገታችንን እንደከዘራ ቆልምመን መኖርን እናውቅበታለን፡፡ ለፍርፋሪ ስንል!!!
2ኛ.ሃይማኖት፡- ከወላዲተ አምላክ ማርያም አንዱ የተማርነው ሃይማኖት ነው፡፡ከእርሷ በፊት ያልሆነ ከተፈጥሮ ሥርዓት የተለየ ያለወንድ ዘር መጽነስ እና በድንግልና መውለድ በመልአኩ ሲነገራትና ይህ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ሲላት ፈቃዷን በሃይማኖት ገልጣለች፡፡ ፍጹም እምነት ማለትም ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ማመን ነው፡፡
በቃና ዘገሊላ ሠርግ ለልጇ የወይን ጠጅ ማለቁን ከነገረችው በኋላ ላገልጋዮች በፍጹም እምነት የሚላችሁን አድርጉ ብላቸዋለች፡፡ በዚያ ደቂቃ ለዚያ ሁሉ ሠርገኛ የሚሆን ወይን ከየት ያመጣል? ምን መፍትሄ ሊኖር ይችላል?የመሳሰሉት የጥርጥር ሀሳቦች በእርሷ ዘንድ አልነበሩም፡፡ ሁሉን ቻይ መሆኑን ከቀድሞም አውቃና አምና ትኖር ነበርና፡፡
ዛሬ ያለውንየዓለም አካሄድ በእምነት ካልሆነ ማሸነፍ አይቻልም፡፡ከተስፋ መቁረጥ የተነሳ ጨለማው የማያልፍ ደመናው የማይገፍ የሚመስላቸው ብዙዎች ይኖራሉ፡፡ እምነት ማለት በእግዚአብሔር ኃይል የማይቻለው ይቻላል ይሆን የማይመስለው ይሆናል ብሎ ማመን ነው፡፡ የተፈጥሮ ህግ፣ አመክንዮ ወዘተ… እዚህ ቦታ የላቸውም፡፡ የእርሱ ሥራ ከዚህ ሁሉ በላይ ነውና፡፡
3ኛ. ፍጹም ታዛዥነት፡- እመቤታችን ፈቃዷ ሁሉ ለልጇ የተሰጠ ነበር፡፡ ከእርሱ የተለየ ሀሳብ ወይም ፈቃድ አልነበራትም፡፡ ራሷን ፈጽማ ለእግዚአብሔር ያስገዛች ብላቴና ስለነበረች የመልአኩን ብሥራት የተቀበለችው የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጸም ራሷን በመስጠት ነው፡፡ ከቀደምት ነቢያት እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ሲልካቸው ሲጠራቸው ምክንያት በማንሳት ወደኋላ ለማለት የሞከሩ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ለሚጠራን አገልግሎት መሠማራት ክብር እንደሆነ ሁሉ ታላቅ ሸክምና ኃላፊነትም ነው፡፡ እመቤታችን ለእናትነት ስትመረጥ ታላቅ ክብር መሆኑ ቢታወቅም ‹‹በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል›› እስኪባል የደረሰ ታላቅ ኃላፊነትም ነበር፡፡ በፍጹም ታዛዥነትም እስከ ፍጻሜ ኃላፊነቷን ተወጥታለች፡፡ በመጨረሻም በመስቀል ላይ ሳለ በፈቃዱ ወደ እርሱ እስኪወስዳት ድረስ በዮሐንስ ዘንድ እንድትኖር ሲነግራት በጊዜው ወድቆባት የነበረ ነፍስን የሚወጋ ሀዘን ለቃሉ ያላትን ታዛዥነት አልለወጠውም፡፡
4ኛ.ጥበብ መንፈሳዊ፡- እመ አምላክ ብሥራተ መልአክን በተቀበለችበት ወቅት ቅዱስ ገብርኤልን ትጠይቀው የነበሩ ጥያቄዎች ፍጹም ጥበብ መንፈሳዊ የተሞሉነበሩ፡፡ ከጉባዔ ያልዋሉ ምሥጢር ያላደላደሉ የመጽሐፍ ቅዱስ የከንፈር ወዳጆች የእመቤታችንን ጥያቄዎች የጥርጥር ያለማመን አድርገው ሲያቀርቡ እነሆ እንሰማቸዋለን፤እኒህ የወንጌሉ ምሥጢር የተከደነባቸው ናቸው፡፡እመቤታችን የጠየቀቻቸው ጥያቄዎች የተገቡና ነገረ ሥጋዌን የበለጠ እንዲብራራ ያደረጉ ናቸው፡፡ እመቤታችን ጥያቄዎቹን ባትጠይቅ ኖሮ፡-
ሀ. ከእርሷ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ
ለ. በድንግልናና ያለወንድ ዘር የተጸነሰና የሚወለድ መሆኑ
ሐ. ለአበው በተሰጠው ተስፋና በትንቢተ ነቢያት መሠረት የዳዊት ዘር መሆኑና የያዕቆብን ወገን ለዘላለም የሚገዛ መሆኑ፡
መ. ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ መወለዱ በግብረ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ
ሠ. አብ ሊያፀናት ወልድ ለተዋሕዶ(ሥጋን ለመንሳት)መንፈስ ቅዱስ ሊከፍል ሊያዋሕድ እንደሚያድሩባት ተለይቶ ባልታወቀ ነበር
ረ. የሚወለደው ሕጻን ስሙ ኢየሱስ እንደሚባልና ሕዝቡን ሁሉ ከኃጢአት ከመርገም ከፍዳ የሚያድናቸው መሆኑ
ሰ. ራሷ እመቤታችን በንጽሕናና በቅድስናዋ ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የከበረች መሆኗ
ሸ. ነቢየ ልዑል ዐርኩ ለመርዓዊ የተባለ የዮሐንስ መጥምቅ በእግዚአብሔር ድንቅ ተዐምራት ከዘካርያስና ከኤልሣቤጥ መፀነስ፤ኤልሳቤጥ በብፅዐት ብትሰውረውም የተገለጠ በእመቤታችን ጥያቄ ነው፡፡
ብዙ ጠይቀን ጥቂት መልስ ለማናገኝ ለእኛ የጥያቄ አቀራረብን አቅል(ሥርዓት) እንረዳበት ዘንድ ታላቅ ትምህርት ነው፡፡በአግባቡ ያልቀረበ ጥያቄ መልስ አይኖረውምና፡፡
5ኛ. መናፍስትን መመርመር፡-‹‹መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ››እንዲል፤እመቤታችን መልአኩ ተገልጦ የምስጋና ሰላምታ ባቀረበላት ጊዜ ወዲያውኑ አልተቀበለችውም፡፡መተርጉማን‹‹እናቴሔዋንን ያሳተ ሰይጣን…››ብላ አሰበች እንዲሉ ዛሬ ትንቢት ተናጋሪ፣ ራዕይ ተመልካችና ሕልም ሀላሚ በበዛበት ጊዜ፤ ብዙዎቻችንም በመናፍስት አሠራር የሚሆነውን ሳንመረምር በምናያቸው ድንቃ ድንቆች የሰዎችን እውነተኛነትና ቅድስና በምንመዝንበት ሰዓት ከተወዳጇ እናታችን እንዲህ ያለውን የመጠበቅ ጥንቃቄ ልንማር ያስፈልጋል፡፡1ዮሐ4፥1
6.ጭምትነት፡-እመቤታችን እንዴት ባለ ጭምትነት በንጽሕና በቅድስና እንዳደገች አባ ሕርያቆስ ሲናገር ‹‹ ኦ ድንግል አኮ በተላህዮ ዘልሕቂ ከመ አዋልደ ዕብራውያን እለ ያገዝፋ ክሣዶን አላ በቅድስና ወበንጽሕ ውስተ ቤተ መቅደስ ነበርኪ›› ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም በንጽሕና በቅድስና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ በማለት ገልጿል፡፡ ከቅዱስ ገብርኤል ከኤልሳቤጥና ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር በነበራት ጊዜ፤ ስምኦን አረጋዊ ጌታን ባቀፈውና ትንቢት በተናገረበት፤ በአሥራ ሁለት ዓመቱም በቤተ መቅደስ በጠፋባቸው ወቅት፤ እንዲሁም በጊዜ ስቅለቱ በደረሰባት ሀዘን ወዘተ…ጭምትነቷ በሚያስደንቅ ሁኔታ ታይቷል፡፡በእያንዳንዱ ሁኔታ የምታደርገው እንቅስቃሴም ሆነ ንግግር ፍጹም ጸጋን የተላበሰ ነበር፡፡ጥያቄዋ፣ ሰላምታዋ፣ ቅሬታዋንም ሆነ ሀዘኗን ትገልፅበት የነበረበት መንገድ በፍጹም ጭምትነት የተጌጠ ነበር፡፡ በመልአኩ እንደተነገራት በኤልሳቤጥም እንደተመሰከረላት የእስራኤል ተስፋ ከእርሷ እንደሚወለድ የታወቀ ቢሆንም ቸኩላ ይህን ምስጢር ለማንም አልገለጠችም፡፡ እርሱ በሚፈቅደው መንገድ ራሱን እስኪገልጥ በጭምትነት ጠበቀች እንጂ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያን ሴቶች ሊመክር የሚገባውን ሲነግረው ‹‹…ሴቶች ጭምቶች፣የማያሙ፣ልከኞች፣በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባቸዋል›› ብሎታል፡፡ 1ኛ ጢሞ3÷11 ቅምጥሊቱ ሴት ግን በሕይወቷ ሳለች የሞተች ናትና፡፡1ኛ ጢሞ5፥8 የክርስቲያን ሴቶች በሥራቸውም ሆነ በአነጋገራቸው በአለባበሳቸውም ሆነ በአካሄዳቸው ራሳቸውን በጭምትነት እንዲገልጹ ከእመቤታችን በላይ አርአያ ሊሆን የሚችል አይሰጣቸውም፡፡
7. ማኅበራዊ ሕይወት፡- እመብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያም የኤልሳቤጥንመጽነስ ከመልአኩ እንደሰማች ፈጥና ነው ወደ ኤልሳቤጥ የሄደችው፡፡ ያቺ እግዚአብሔርን በመፍራት የምትኖር የካህን ሚስት ስእለቷ ተሰምቶ በመልአክብሥራት ወንድ ልጅ መጽነሷን ስትሰማ ደስታዋን ለመካፈል አልዘገየችም፡፡ በሰው ሀዘን ተደስቶ በባልንጀራው ደስታ የሚከፋ በበዛበት በዚህ ክፉ ዓለም የእርሷን አርአያ መከተል ምንኛ መቀደስ ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ከሚያዝኑም ጋር አልቅሱ››ያለው የሰውን ስሜት በቅንነት መካፈልክርስቲያናዊ ምግባር በመሆኑ ነው፡፡ሮሜ 12፥15፤ ሉቃ 1፥57-65
ከእግዚአብሔር የሆነን ነገር ደግሞ የሰዎቹን ደስታ ከመካፈል ባለፈ ማድነቅ ይገባል፡፡ለኤልሳቤጥ ከእግዚአብሔር እንደሆነው ሁሉ ለሕዝቡ ጥቅም ከእግዚአብሔር የሆነ ስጦታ(ጸጋ) የተሰጣቸው ስንመለከት
ሀ. እግዚአብሔር በእነርሱ አድሮ ስለሠራው ድንቅ ሥራ
ለ.እግዚአብሔር በእርነሱ አድሮ ሕዝቡን ስለመጥቀሙ
ሐ.በዘመናችንም ዓይኖቻችን የእርሱን ድንቅ ሥራ በማየታቸው ልንደሰት ይገባናል፡፡ ከእግዚአብሔር በሆነ ጸጋ መቅናት፤ሰዎቹ ለሚሠሩትም ሥራ እንቅፋት መሆን ከእግዚአብሔር ጠላቶች ጋር መሰለፍ ነው፡፡
8. ድንግልና፡- የእመቤታችን ድንግልና፡-
ሀ. በሥጋ በኅሊና በመሆኑ( ድንግል በኅሊናኪ ወድንግል በሥጋኪ) እንዲል
ለ.ሕዋሳቶቿ በሙሉ የተጠበቁ መሆናቸው ማለት የኃጢአት መግቢያ ከሆኑት ከርዕይ ከሰሚዕ ከገሢሥ ከአጼንዎ የተጠበቀች መሆኗ( ከማየት፣ከመስማት፣ከመዳሰስ፣ከማሽተት)
ሐ.ቅድመ ጸኒስ ጊዜ ጸኒስ ድኅረ ጸኒስ ፤ቅድመ ወሊድ ጊዜ ወሊድ ድኅረ ወሊድ ድንግልናዋ ለቅጽበት ያልተለወጠ መሆኑ(ድንግልናዋ እናት በመሆኗ ያልተለወጠ መሆኑ)ልዩ ያደርጋታል፡፡ይህ ለሌሎች ሴቶች አይቻልምና‹‹ከሴቶች ተለይተሸ››ያሰኛት ቅሉ አንዱ ይህ ነው፡፡
በተፈጥሮ ሥርዓት አንዲት ሴት ሙሽራዋን እስክታገኝ(እስኪመጣ)ራሷን በመግዛት እንደምትጠብቅ፤ ያ ካልሆነ ግን ከክብር እንደምታንስ በመንፈሳዊው ሕይወትም ነፍሳችንን በኃጢአት ከክብር ከማነስ ጠብቀን ድንግልና የተባለ ልጅነታችንን በሃይማኖት በምግባርሙሽራችን የሆነው ክርስቶስ እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡
ለእርሱ ለክርስቶስ የሸለመች ሙሽራ ሆነን እንዴት ባለ የነፍስ ቅድስና መጠበቅ እንዳለብን የተሰጠችን ሕያው ምሳሌ ደግሞ እመቤታችን ነች፡፡ በእርሷ በአካል ያደረ በእኛ በጸጋ ያድርብናልና፡፡የዮሐ.ራዕ 21፥2
9.ጸሎት፡- እመቤታችን የመልአኩን ብሥራት የኤልሳቤጥንና የዮሐንስን ምሥክርነት ከተቀበለች በኋላ የተናገረችው ጸሎት በዘመናት በአላውያን ነገሥታት በአረማውያን እንዲሁም በመናፍቃን የተነሣባትን የጥፋት ማዕበል ለመሻገር ለቤተክርስቲያን ጉልበት የሆነ ነው፡፡ጸሎቷም ምን ያህል በቅዱሳት መጽሐፍት እውቀት የበለጸገ የልዑሉንም ሥራ በማስተዋል የከበረ መሆኑ ተገልጦ የሚታይ ነው፡፡ ፍጹም በነፍሷ ለእግዚአብሔር ያላትን ክብር፣ ትኁታኑን የማይረሳ መሆኑን፤ ቅድስናውን፣ እውነተኛ ፈራጅ መሆኑን፣ለሚፈሩት የሰጣቸውን ቃል ኪዳን የማይረሳና ምህረቱም ለልጅ ልጅ መሆኑን የገለጠ ነው፡፡በከንፈር እግዚአብሔርን የሚያከብሩና በነፍሳቸው ልዑሉን የሚፈሩ የጸሎታቸው ልዩነት ለማነጻጸር ከሚቻል በላይ ነው፡፡ ጸሎተ ማርያም ዛሬም ድረስ በቤተክርስቲያን ለካህናት ሞገስ ለሕሙማን ፈውስ፤ ለሀገር ሰላም ለርኁባን ምግብ፤ለመምህራን ጽናት ለደቀመዛሙርት እውቀት የሆናቸው ለዚህ ነው፡፡ሐዋርያትም በጸሎታቸው ወቅት እርሷን ይዘው መጸለያቸው የጸሎታቸው ምላሽ ይፈጥን ዘንድ ነው፡፡የእርሷ ጸሎት ተሰሚ ጉዳይ ፈጻሚ መሆኑን በቃና ሠርግ በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡ ‹‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም››ብላ ለልጇ ከነገረችው በኋላ ድጋሚ መጠየቅ አላስፈለጋትም ‹‹የሚላችሁን አድርጉ›› አለች እንጂ፡፡ ደራሲ‹‹አልቦ ጸሎት ወአልቦ ትንባሌ እንበሌኪ ድንግል ዘየዐርግ ሉዐሌ››ያለ ይህን ማስተዋል በመቻሉ ነው፡፡በመሆኑም እመቤታችንን ሳትይዝ ጸሎት ልመና አቀርባለሁ የምትል ቤተክስቲያን ብትኖር እርሷ ሐዋርያት የሰበሰቧት ቤተክርስቲያን አለመሆኗ በዚህ ይታወቃል፡፡
0. ምስጋና፡- እመቤታችን በእርሷ ላይ ይሆን ዘንድ ልዑሉ የፈቀደው ከሆነ በኋላ ይህን የተረዱ እነ ኤልሳቤጥ በተፀውዖ ስሟ ማርያም ብለው መጥራታቸውን እንደማይገባ ድፍረት አድርገውስለቆጠሩት፤ የእርሷም ከቤታቸው ጣሪያ በታች መግባት የተገባቸው እንዳልሆነ ስለተረዱት‹‹የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?››በማለት ክብሯን ገልጠው መሰከሩ፡፡እመቤታችን ጌታን ፀንሳ ከወለደች በኋላ በወንጌል እንዲሁ ‹‹ማርያም›› ተብላ ስትጠራ አናገኝም፡፡ወንጌላውያኑ ሁሉ ‹‹የሕጻኑ እናት›› ‹‹የኢየሱስ እናት›› ‹‹ሴቲቱ››እያሉ ሲጠርዋት ነው የምናየው፡፡ ሁሉም መጠሪያዎች የነቢያትን ትንቢት መፈጸም የሚያሳዩና የሥጋዌን ምሥጢር ያዘሉ ናቸውና፡፡ይህን የተረዱ ሊቃውንት‹‹እመ አምላክ፣ ወላዲተ አምላክ፣እመ ብርሃን ወዘተ…››እያሉ መጥራቻቸው ወንጌላውያንን አብነት አድርገውነገረ ሥጋዌን ለመግለጽና ክብሯን ለመመስከር ነው፡፡
እመቤታችን በኤልሳቤጥ ቤት የሆነውን ካየች በኋላ‹‹ለእኔ(በእኔ)ታላቅ ሥራን አድርጓልና ስሙም ቅዱስ ነው›› ስትል አመስግናለች፡፡ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስብሎ ማመስገን በዓለመ መላእክት የተለመደ ነው፡፡የመላእክት እህት የሆነች እመቤታችንም ከነፍሷ የሆነ ምስጋናዋን በዚሁ ሰማያዊ በሆነ ምስጋና ገልጻለች፡፡ ይህም ከመላእክት ጋር የነበራትን የምስጋና ኅብረት ያሳያል፡፡ከዚህም በግላችንም ሆነ ለፍጥረተ ዓለም ለተደረገው የእግዚአብሔር የቸርነቱ ሥራ ማመስገን የተገባ መሆኑን ለሁላችን ትምህርት ትታልናለች፡፡
እመቤታችን ፈጣሪዋናአምላኳ እንዲሁም ልጇ የሆነውን እርሱን ማመስገን ብቻ ሳይሆን፤በእርሷ ላይ በተደረገው ድንቅ ነገር ትውልድ ሁሉ ሲያመሰግኗት ሲያደንቋት እንደሚኖሩም ገልጻለች፡፡በዚህም የተነሳ እውነተኛዋ የሐዋርያት ቤተክርስቲያን ልዑል እግዚአብሔርን ከማመስገን ለጥቃ እመቤታችንን በውዳሴ በቅዳሴ በማንሳት ታመሰግናለች፡፡ ልጆቿም በነገር ሁሉ በንጽሕናና በቅድስና በማጌጥ እናታቸውን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲመስሉ ታስተምራለች፡፡ ቤተክርስቲያን በማኅሌቱ በቅዳሴው በሰዐታቱ በስብከቱና በትምህርቱ ሁሉ ደጋግማ እመቤታችንን የማንሳቷ ምስጢር በንጽሕናና በቅድስናዋ አብነት በመሆን በአማላጅነቷም ፍጹምነት ወደ እግዚአብሄር እቅፍ የምታደርሰን በመሆኗ ነው፡፡
ከጥንት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ትክክለኛ ዶግማ ቀኖናና ትውፊት እንዳይበረዝ እንዳይከለስ በማስተማር ጠብቃ ማቆየቷ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ከማንም በላይ ሐዋርያት ከጌታችን የተቀበሉት የጥንታዊውና የእውነተኛው ክርስትና የታመነችባለ አደራ ቤተ መዘክር ያደርጋታል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!
እንኳን ለጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሰላም አደረሰን!
ቀሲስ ታምራት ውቤ
ነሐሴ 2007 ዓ.ም