ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ሰባት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
መግቢያ፡ በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!
ሌላው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነቱን ከገለፀባቸው ባህርያት አንዱ ኃጢአትን የማስተሰረይ(ይቅር የማለት) ሥልጣኑ ነው፡፡
በመጽሐፍ እንደተፃፈ ኃጢአትን ማስተሰረይ ብቸኛ የቅዱስ እግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡ በማር.ወን 2፥ 5፡- ላይ ሽባውን ሰው እንዲፈውስላቸው በአልጋ አድርገውና የቤቱን ክዳን ነቅለው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ሲያቀርቡት አንተ ሰው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ነበር ያለው፡፡ በዚያ የነበሩ አይሁድም "ይህ ሰው በርግጥ ይሳደባል ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ማን ይችላል?" በማለት ሲያጉረመርሙ ጌታችን ግን "የሰው ልጅ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው እንዲያውቁ አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ሽባውንም ፈውሶታል፡፡ እዚህ ላይ"የሰው ልጅ" እያለ ጌታ የሚጠራው ራሱን እንደሆነ አስተውል፡፡
ኃጢአት የሚሠራ ሰው በዋናነት የሚበድለው ቅዱስ እግዚአብሔርን ነው፡፡ ምክንያቱም፡
1. ሕጉን ይተላለፋል አድርግ የተባለውን ሲያስቀር አታድርግ የተባለውንም ሲያደርግ የአግዚአብሔርን ሕግ ማቃለሉ አይደለምን?፡፡ ለልዑል እግዚአብሔር ፍቅርና ክብር እንዳለን የሚታወቅበት ብቸኛ መንገድ በቃሉ(በሕጉ) ታዛዥ ሆነን መገኘት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ዓመፀኞች ነን፤ ዓመፃ ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአትንም የሚያደርግ ከእግዚአብሔር አልተወለደም፤እግዚአብሔርንም አያውቀውም፡፡ 1ዮሐ 2
2. እግዚአብሔርን የሚበድለው የፈጠረውን ፍጥረት በማሳዘኑ ነው፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር የፍጡራኑ በደልና ሥቃይ የሚሰማው አምላክ ነው፡፡ ገዢያችን አባታችን ነውና፡፡ የግዛቱ መደፈርና የህዝቡ በጦርም ሆነ በምርኮ መንገላታት ንጉስን ከዙፋኑ አውርዶ ከቤተመንግስቱ አስወጥቶ ጦርነት እንደሚያስከትተው፤የሚስቱ የልጆቹ መጠቃት የአባትን ቁጣ ቀስቅሶ ለበቀል አንደሚያነሣሣው ለልዑል እግዚአብሔርም የፍጡራኑ መበደል አንዲሁ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ከአካላችን አንዱ ብልት ላይ የሚደርስ አደጋ ህማሙ ነፍሳችን እንደሚሠማት ለጌታ እግዚአብሔርም በፍጡራኑ ላይ የሚደርስ ጥቃት እንዲሁ ነው፡፡
በመሆኑም ሰው ኃጢአት ሠርቶ ባልንጀራውን ቢበድል ይቅርታን ማግኘት ያለበት ከተበዳዩ ብቻ ሳይሆን በዋናነት ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ምሳሌ፡- አንድ ሰው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ብላቴናን በግዳጅ ቢደርስባት ጥቃቱ(በደሉ) የእርሷ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ፣ የማኅበረሰቡና የመንግስት ጭምር ነው፡፡ ምንም እንኳ በዳዩ ሽማግሌ ልኮ ካሣ ከፍሎ ከተበዳይዋም ሆነ ከቤተሰቧ ይቅርታን ቢያገኝ የሀገሪቱን ሕግ በመተላለፉና በአንዲት ንፁህ ዜጋ ላይ ወንጀል በመፈፀሙ በመንግስት ሕግ ከመጠየቅ አይድንም፡፡ ማኅበረሰቡም ይህ ሰው ነገ ሊያደርሰው የሚችለው ተመሳሳይ በደል ሊታረም የሚችልበትን መንገድ ከመጠየቅ ችላ አይልም፡፡ ስለዚህ ያ ሰው ፍፁም ይቅርታን አግኝቻለሁ ብሎ በሰላም መኖር የሚችለው ከግል ተበዳይዋ፣ ከቤተሰቧ፣ ከማኅበረሰቡና ከመንግስት ይቅርታ ሲደረግለት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለምም ይኸው ነው፡፡ ሰው የግል ተበዳይን ብቻ ሳይሆን ቅዱስ እግዚአብሔርን ፍፁም ይቅርታ በሚጠይቅ ሰዓት ስርየትን ያገኛል፡፡ የአባቱን ሀብት ያባከነው ወጣት ወደቤቱ ሲመለስ ለአባቱ "በሰማይና በምድር ፊት በድያለሁ" ያለው ለዚህ ነው፡፡ በምድር ወላጅ አባቱን በሰማይ ያለ ፈጣሪውን በድሏልና፡፡ሉቃ 15
ስለዚህ በዚህ አግባብ ፍፁም የኃጢአት ይቅርታን ሊሠጥ የሚችል ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዳዊት " ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ አጥንቶቼ ሁሉ የተቀደሰ ስሙን ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን አመስግኚ፤ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል ከደዌሽ ሁሉ የሚፈውስሽ…"
በማለት የይቅር ባይነት ሥልጣን የቅዱስ እግዚአብሔር መሆኑን ይገልፃል፡፡ ጨምሮም…ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ" እንዲሁም "አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ አቤቱ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና" በማለት ያስረግጣል፡፡መዝ 31፥1-5፣ መዝ102፥1-14፣መዝ 129(130)፥3
ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን የጌታ እግዚአብሔር መሆኑ ከታወቀ ኢየሱስ ክርስቶስ "ኃጢአትህ(ሽ) ተሰረየችልህ(ሽ)" ማለቱ እርሱ አምላክ(እግዚአብሔር) ለመሆኑ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡
ሉቃ7፥48፡- ሽቱ የቀባችውን ሴት በቃሉ "ኃጢአትሽ ተሰረዮልሻል በሰላም ሂጂ" ብሎ ሲያሰናብታት በዚያ የነበሩ "ኃጢአትን ስንኳ የሚያስተሠርይ ይህ ማነው? እስከማለት ተገርመዋል፡፡
ሉቃ23፥43፡- በመስቀል ላይ ሳለ በቀኙ የተሰቀለ ወንበዴ በሰማይና በምደር የተፈፀሙ ተዓምራቶችን አይቶ "በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" ብሎ ላቀረበው የይቅርታ ልመና" ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ" በማለት የይቅርታ ባለቤት መሆኑን አሳይቷል፡፡
ሉቃ24፥46፡-"…ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤በስሙም ንስሐና የኃጢአት ሥርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአህዛብ ሁሉ ይሰበካል"፡፡ ልናስተውል የሚገባን በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በዓለም ሃይማኖቶች ታሪክ ንስሐና የኃጢአት ሥርየት በስሙ የሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ በቡድሐም፣ ሆነ በክሪሽና በዘራስተርም ሆነ በመሐመድ የለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም በቀደምት አበው ሆነ በነቢያት፣ በነገስታት ከጌታም በኋላ በተነሱ በሐዋርያት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ስም የኃጢአት ሥርየት አልተሰበከም፡፡ ሁሉ በእርሱ ከኃጢአት ነፁ ለዚሁም ምስክር ሆኑ እንጂ፡፡
የሐዋ.ሥራ 2፥37-38፡- ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ጰራቅሊጦስ የሰበከውን የሰሙ ልባቸው የተነካ ሰዎች ምን እናድርግ ? ብለው በጠየቁ ሰዓት የተሰጣቸው መልስ "ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሠረይ ዘንድ በጌታ በእየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" የሚል ነው፡፡
1ዮሐ1፥1-10፡- ያየነውን እንመሠክራለን ያለ ዩሐንስ ወንጌላዊ " …ኃጢአት የለብንም ብንል ውሸተኞች ነን … የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል…በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነ ጻድቅ ነው፡፡" በማለት የኃጢአትን ይቅርታ እንዴት እንደሆነ ጽፎልናል፡፡
ኃጢአትን ይቅር የሚል በደልን የሚደመስስ ለሚወዱትም መንግሥቱን የሚያወርስ ጌትነቱ በሁሉ ላይ የሆነ በመጨረሻው ዘመን ግን የባርያን መልክ ይዞ የተገለጠ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ነው፡፡ ስለ ኀጢአታችን ብዙ ልንፆም፣ በፀፀት ልናለቅስ፣ በርካታ ምፅዋት ልንሠጥና በድካም እስክንዝል ልንሰግድ እንችላለን ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ይቅርታውን ደጅ የምንጠናበት መንገድ እንጂ በራሱ ፍፁም ሆኖ ይቅርታን የሚያስገኝ አይደለም፡፡ ይቅርታን ለማግኘት ለኃጢአታችን መስዋዕት ሆኖ የቀረበ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን ልንበላ ክቡር ደሙንም ልንጠጣ የግድ ያስፈልገናል፡፡
መጽሐፍ "ያለ ደም ሥርየት የለም" እንዲል ጌታም በቃሉ "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ህይወት አለው፡፡ ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም"፡፡ እንዲል ዕብ፣ዮሐ 6፥53
ጸሎት፡- ቅዱስ አምላክ ሆይ አናመስግንሀለን፡፡ ከቸርነትህ ገናናነት የተነሣ ሥጋህንና ክቡር ደምህን ለህይወት ለመድኃኒት እንዲሆነኝ ሰጥተኸኛል፡፡ ይህም በሕይወት ዘመኔ የተቀበልኩት በዋጋ የማይተመን እኔን የመውደደህ ስጦታ ነው፡፡ ቸር ሰውን ወዳጅ ሆይ ወደ ሕይወት መድኃኒት እንዳልቀርብ ዲያብሎስ በብዙ የምክኒያት ሰንሰለቶች አስሮኛልና ፍታኝ፡፡ ምክንያትን ቆርጬ የምጥልበትን ኃይል አድለኝ፡፡ በእኔም ዘንድ መኖርያህን ታደርግ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን!አሜን!
አቡነ ዘበሰማያት
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!