Login
Main menu

ጰራቅሊጦስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

ጰራቅሊጦስ የሚለው ቃል የጽርዕ ሲሆን ‹‹የቅርብ ረዳት፤በአጠገብ ሆኖ የሚያፅናና የሚያረጋጋ›› የሚለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ይህ መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ከተጠራባቸው ስሞች አንዱ ነው፡፡

     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለዓለም ከገለጠና ምሥጢረ መንግሥትን ሦስት ዓመት ለሐዋርያት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ጊዜው እንደደረሰ አውቆ ለሐዋርያት ከእነርሱ ተለይቶ እንደሚሔድ ነግሯቸው ነበር፡፡ በእርግጥ ሐዋርያት ተላልፎ የመሠጠቱንና የሞቱን ነገር ደጋግመው ሲሰሙት የነበረ ቢሆንም የተቆረጠው ቀን መድረሱን ሲረዱ ግን ከፍተኛ ድንጋጤ ወደቀባቸው፡፡

     በዚህ ጊዜ ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ እሔዳለሁ ስላችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል፤እኔ ካልሔድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና ያላቸው፡፡ ጌታችን የሐዋርያትን መደንገጥ ማዘንና መሸበር ሲያይ መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ የሚመጣው ሊያረጋጋቸውና ሊጽናናቸው መሆኑን አብስሯቸዋል፡፡ ያድርባችኋል በውስጣችሁም ይኖራል እርሱም ዓለም ሊቀበለውና ሊያውቀው የማይችል የእውነት መንፈስ ነው በማለትም አስረድቷቸዋል፡፡

     የክብር ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ ከተነሳ በኋላ

በ$ኛው ቀን ሲያርግ ‹‹አብ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› በማለት ተስፋን ሰጥቷቸው ሄዷል፡፡ ከአሥር ቀን በኋላም እንደ ቃሉ ተፈጽሟል፡፡ ሉቃ 24፥49

     መጀመሪያ በሐዋርያት ለጥቆም በምዕመናን ላይ መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው ስንል ሀብቱ ጸጋው ኃይሉ ማለታችን እንጂ በአካል በእነርሱ አደረ ለማለት አይደለም፡፡ያደረባቸው ሰዎች በሚያሠራቸው ሥራ ተገልጠው ይታወቃሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስየሚሠራው ሥራ የሚሰጠውም ኋይልና ጸጋ በዓለም ባለ የትኛውም ጥበብ፣ ሀብትና ሥልጣን ሊገኝ(ሊሠራ) ፈጽሞ የማይችል ነው፡፡

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ባደረባቸው ጊዜ ከብልየት ታደሱ በአዕምሮ ጎለመሱ፤ ፍሩሃን የነበሩ ጥቡዓን ሆኑ፡፡አንዲት ቋንቋ ብቻ ይናገሩ የነበሩ  ፸፩ቋንቋ ገለጠላቸው፡፡ መተርጉማን ስለምን ቋንቋው ፸፪ሆነቢሉ በጊዜው በዓለም ይነገር የነበረ ቋንቋ(ልሳን) ይኸው ነበርና ለዓለም ሁሉ ወንጌል መንግሥትን ይገልጡ ዘንድ ፈቃዱ መሆኑን ሊያጠይቅ ነው ይላሉ፡፡ የሐዋ.ሥራ 2፥1-ፍጻሜ

     ከዚህም በተጨማሪ መጻሕፍትን ከገበታ እስከ ገበታ አወቁ ምሥጢር ተገለጠላቸው፤ ትንቢተ ነቢያትን እነርሳቸውን መስለውና ተካክለው ተረዷቸው ተረጎሟቸው አመሰጠሯቸው፡፡ጌታችን የትምህርታቸውን(የቃላቸውን)ደገኛነትም በሚከተሏቸው የተለያዩ ምልክቶች አጸናላቸው፡፡ ያመኑትን ድውያንን ፈወሱ ሙታንን አነሱ፡፡ለወንጌል እንቅፋት የሆኑባቸውን በተግሳጽ በመቅሰፍት ከመንገድ አስወገዱ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሀብት ጸጋና ኃይል በየትኛውም ምድራዊ ኃይል፣ ሥልጣን፣ጥበብና ብልጥግና ሊገኝ የማይችል ከላይ(ከአርያም)ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ማር 16፥17፤የሐዋ.ሥራ 3-6፤የሐዋ.ሥራ 13፥7-12

     ለመግቢያ ያህል ይህን ካልን ጰራቅሊጦስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት፡-

1. መጽንዒ ወይም የሚያጸና ማለት ነው፡፡ሐዋርያት ወንጌል መንግሥትን ለመስበክ የወጡት መልእክታቸውን አሜን ወአሜን ብሎ ለመቀበል በናፍቆት ወደ ሚጠብቅ ሕዝብ አይደለም፡፡ ይልቁንም በጥላቻ በተመረዙ አይሁድና በጣዖት አምልኮ በደነዘዙ አሕዛብ መካከል ነው፡፡

     የክርስትና አስተምህሮ በወቅቱ ከነበረው የዓለም ኅብረተሰብ ባህልና አኗኗር ጋር የብርሃንና የጨለማ ያህል መራራቅ ነበረው፡፡በመሆኑም አይሁድን ሥርዓተ ኦሪትን አሕዛብን ልማደ ጣዖትን ለማስጣል ሲወጡ ብዙ ግፍንና መከራን ተቀብለዋል፡፡ጌታችን እንዳላቸው ኃይልን ሳይቀበሉ ለስብከት ወጥተው ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስ ባላደረበት ሰውነታቸው መከራ ቢያጸኑባቸው ፈጥነው ይክዱ ነበር፡፡ስለዚህ የሚመጣውን ለመቀበል መጨከን እንዲችሉ የሚያጸና መንፈስ ቅዱስ አድሮባቸዋል፡፡

     አበው መንፈስ ቅዱስ ስለምን በእሳት አምሳል ታያቸው የሚለውን ሲተረጉሙ፤በእሳት የተቃጠለ(እሳት የነካው)መሬት ለአዝርዕት ለአትክልት እንዲመች መንፈስ ቅዱስ ያደረበትም ሰውነት ለገድል ለትሩፋት የተመቸ ነው፡፡አንድም ሸክላ ሠሪ ሸክላ ሠርታ በእሳት ተኩሳ እንደምታጸናው መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ጽኑ ነውና ይላሉ፡፡

     መንፈስ ቅዱስ ባያድርባቸው ኖሮ ነቢያት በትንቢት ሐዋርያት በስብከት፣ሰማዕታት በደም ጻድቃን በገዳም ፀንተው ለመገኘት ባልተቻላቸውም ነበር፡፡

2. መንጽሒ፡-የሚያነጻ ማለት ነው፡፡ሰው ኃጢአት ሢሠራ የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስለው መልኩ ይበላሻል ባህርዩ የጎሰቁላል ጠባዩም ያድፋል፡፡በሠራነው ተጸጽተን ንስሐ ገብተንና በካህኑ የተሰጠንን ቅኖና ፈጽመን ካህኑ ከሚያደርሰው ጸሎት ጀምሮ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እስከ መቀበል ድረስ የኃጢአት ሥርየታችን የሚከናወነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

እሳት ብረት ቢሉ ዝገቱን ወርቅ ቢሉ ዕድፉን አስወግዶ የቀደመ የተፈጥሮ ባህርያቸውን እንደሚያሲዛቸው እኛም በኃጢአት ምክንያት የጠፋ መልካችን ያደፈ ጠባያችን የጎሰቆለ ባህርያችን ነጽቶና ታድሶ ወደ ክቡር(ማንነቱ)የሚመለስ በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

     እመቤታችን በተለየ አካሉ አግዚአብሔር ወልድን ጸንሳ ለመውለድ እንድትችል ጥንት በአበው ባሕሪይ በማዕከል በማኅፀነ ሐና ኋላም በሕልውና ሳለች ንፅህት አድርጎ የጠበቃት ያዘጋጃት ያበቃት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ያነጻ የከፈለ ያዋሀደ መንፈስ ቅዱስ ነው እንዲሉ ሊቃውንት፡፡

3. ናዛዚ፡- የሚያፅናና ማለት ነው፡፡ በዚህ መከራ በበዛበት ዓለም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በመልካም ሥራ በመትጋት በአብ ኅሊና ታስበው ያሉት በዚህ ዓለም በሚደርስባቸው መከራሲያዝኑና ሲተክዙ የሚያፅናናቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

     በመግቢያው እንዳየነው የሚያጽናና ስንል የቅርብ ረዳት የመንገዳችን ደጋፊ የነፍሳችንን ሲቃ አዳማጭ የማይለይ ታዳጊ ማለታችን እንጂ ተራ ደርሶ ሒያጅ አጽናኝ ማለት አይደለም፡፡በዓለም የሚወድቅብንን ሀዘንና ሰቆቃ ሁሉ ድል አንድንነሳው የሚያደርገን እርሱ የቅርብ አረጋጊ አጽናኛችን በመሆኑ ነው፡፡

     የቅዱሳን ሀዘን ራበኝ ጠማኝ ሀብት ንብረት ጠፋብኝ ወረት አነሰኝ ዘመድ ወገን ሞተብኝ ብለው አይደለም፡፡ ፍትሕ ሲጓደል ድሃ ሲበደል፤ እውነት ስትኮስስ ሀሰት ሲነግስ፤ የአዳም ዘር ፍርድ እንዳለ ዘንግቶ በኃጢአት በበደል ሲረክስ፤ ጻድቃንሲበደሉ ኃጥአን በምቾት በቅንጦት ሲደላደሉ ሲያዩ አምርረው ያዝናሉ፡፡ይልቁንም በቤተ እግዚአብሔር እውነተኞች መምህራን በግፍ ሲባረሩ መናፍቃንና ለመንጋው የማይራሩ ምንደኞች ሲከበሩ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲጣስ ሥርዓት ሲፈርስ፤ ከጽድቅ ይልቅ የግብዝነት ካባ ሲደረብ ሲመለከቱ ልባቸው በሀዘን ነፍሳቸው በምሬት ይቆስላል፡፡

     በዚህ ጊዜ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በማይመረመር ፍርዱ የደሀን ደም ሲበቀል ፍትሕን ሲተክል፤እውነትን ሲያነግስና ሀሰትን ሲደመስስ፤ በኃጢአት የከበሩ ሲዋረዱ ስለጽድቅ የተዋረዱት ሲከብሩ ፤ በኃጢአት በክህደት የተያዘውንም ሕዝብ በመጽሐፍት በመምህራን አንደበት መክሮና አስተምሮ ሲመልስ፤ በቤቱም እውነተኞቹን መምህራን አስነስቶ መናፍቃንና ምንደኞን ለይቶ አውጥቶ ሥርዓትንሲመልስ አምልኮተ እግዚአብሔር በግብዝነት ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ ሲሆን ሲመለከቱ የቅዱሳን ልባቸው ይታደሳል ነፍሳቸው ይጽናናል፡፡ ይህም በዘመናት ሁሉ የታየ በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በታሪክ መጻሕፍት የተዘገበ ነው፡፡በፍርዱ ቅዱሳንን ያጽናናል ግፈኞችን ደግሞ እንደሥራቸው ጽዋቸውን ይግታቸዋል፡፡ የእመቤታችንንና የሐና እመ ሳሙኤልን ጸሎት ልብ ይሏል፡፡ ሉቃ 1፥46-ፍጻሜ፤ 1ኛ ሳሙ 2፥1-10

 


 

4. አራኃዊየሚከፍትማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ኢየሱስን ጌታ(የሕያው እግዚብሔር ልጅ፤አምላክ ወልደ አምላክ ሊል የሚችል የለም፤ እንዳለ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተገለጠ እርሱን ዓለማትን ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ መጀመሪያውና መጨረሻው የሆነ አምላክ ብሎ ማመን በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ ከባድ ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 12፥3

     የተመሰገነው ሐዋርያ‹‹በወንጌል አላፍርም››ማለት ወረደ ተወለደ እንደ ሰው ተመላለሰ፤ ተገረፈ ተሰቀለ ሞተ ተነሳ ዐረገ ብዬ በማመንና በማስተማር አላፍርም ያለ ለዚህ ነው፡፡ሰዎች አምላክ ብለው በኅሊናቸው የሳሉትና የጌታችን ትሑት ሆኖ በመካከላችን መገለጥ በቀላሉ ለመቀበል የሚቸግር ነውና፡፡ ሮሜ 1፥16

     በሐዋርያት ሥራ ሐር ሻጭዋ ልድያ ሰለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጳውሎስ የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት ተብሎ የተጻፈ ለዚህ ነው፡፡ የሐዋ.  ሥራ 16÷14-15 የእግዚአብሄርን ቃል  ሰምተን መንፈሳዊ ፍሬ የማይታይብን ከሆነ ምክንያቱ የልብ አለመከፈት ነው፡፡ ቃሉን ሲሰማ ልቡ የተከፈተ ሰው ወዲያው ምን ላድርግ ብሎ ይጠይቃል ለንስሐም ቀጠሮ አይሰጥም ወደ ጥንት ኑሮውም አይመለስም፡፡

     መንፈሳዊ ሥራን ለመሥራት ወንጌልንም ለመስበክ ጽኑ መሻታችንን ዓይቶ ሁሉን የሚያመቻች ማሕየዊ(ሕይወትን የሚሰጥ) መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡በራዕይ ‹‹ሥራህን አውቃለሁ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም›› በማለት በፍልድልፍያ ላለች ቤተክርስቲያን አለቃ ታላቃ የወንጌል ሥራ ከፊቱ እንዳኖረለት የነገረው የልብ መሻትን አይቶ ሁሉን የሚያመቻች እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ ራዕ 3፥7-8

5. መስተፍሥሒ ማለት ደስ የሚያሰኝ ደስታን የሚመላ ማለት ነው፡፡ደስታ ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ይህ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ በመብልና በመጠጥ በመሾምና በመሸለም እንደሚገኘው ዓይነት ጊዜያዊ ደስታ ወይም በኃጢአት የሚሆን ፍርድና ሀዘን የሚከተለው ደስታ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ማለት እግዚአብሔርን በመፈለግና በመከተል፤በቅድስናው ሥፍራ ተገኝቶ በእምነት በእውነት ሆኖ በማምለክ በመድኀኒታችን የማዳን ሥራ፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ትርጉም ያለው ግንኙነት፤ ወንጌል ሲሰበክና ሰዎች ወደ ድኅነት ሲቀርቡ ወዘተ. . .እኒህንና እኒህን በመሳሰሉት ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ መንግስተ ሰማያት አዋቂዎች ነን በሚሉ ጻፎችና ፈሪሳዊያን ሳይታወቅ በመንፈሳቸው እንደሕጻናት የዋህ ለሆኑ ሐዋርያት ስለተገለጸላቸው. . . በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አደረገ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ሉቃ 10፥21

     ሌላው መሐሪና ይቅር ባይ፤ ስመ ድኅነትና ስመ ሥርዓት ስለሆነው ስሙ መከራን ለመቀበል የተገቡ ሆነው ስለተገኙ ሐዋርያት ሐሴት ያደርጉ ነበር፤ደስታ ይሉሀል በሰማዕትነት ሥቃይ ውስጥ ሆነን ራሳችንን ለክርስቶስ አሳልፈን በመስጠታችንና ከእርሱ ጋር ለመሞት ስለተመረጥን የሚሰማን ደስታ ነው፡፡ በዚህ ዓለም በመንፈስ ቅዱስ ሀሴት ስለማድረግ ካሰብን ከዚህ የሚበልጥ ደስታ የለም፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚያዘጋጅ የሚያበቃ በዓለም ከሚሆን ደስታም የሚለይ ስለሆነ ነው ጌታ መንፈስ ቅዱስ መስተፍሥሂ የተባለው፡፡ ማቴ 5፥11-12፤የሐዋ.ሥራ 5፥40-42

አንድም በዚህ ዓለም ያለን መከራ አልፈን በሃይማኖት ጸንተን በትሩፋት ሥራ ከብረን ከሥጋ ርስት ስንለይ በዘላለም ቤት የዚህን ዓለም መከራ እስክንረሳ በሚያደርስ ደስታ ያኖረናል መስተፈስሂ ይባላል፡፡ ራዕ 14፥13፤ሮሜ 8፥18

6. ከሣቲ፡-ሕይወትን የሚሰጥ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ደስ ለሚያሰኙት ወዳጆቹ ብዙ ነገር የተለያየ ምሥጢርን እንደየዐቅማቸው ይገልጥላቸዋል፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ አካላዊ ቃል ዓለምን ለማዳን ከድንግል እንደሚወለድ ለነቢያት የገለጠ በእነርሱም አድሮ ለዓለም ያስተማረ እርሱ ነው፡፡ ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረፀ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት…›› እንዲል ጸሎተ ሃይማኖት፡፡

     የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትም መንፈስ ቅዱስ ያላደረበት አእምሮ ሊረዳው አይችልም፡፡ዓለም ይህንኑ(ነገረ ሥጋዌን) በተለያየ ፍልስፍናና አስተሳሰብ ለመተንተን እየሞከረ በስህተት ገደል የሚወድቅ ለዚህ ነው፡፡ስምዖን ጴጥሮስ በፊሊጶስ ቂሣርያ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ ሲመሰክር ጌታ መልሶ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጠልህም የሰማዩ አባቴ እንጂ(አሐቲ ሥምረት መሆኑን ልብ ይሏል) በማለት የነገረው፤ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጦ የታየ ጌታችንን አምላክ ወልደ አምላክ ብሎ ማመን ለሥጋዊአእምሮ ጠጣር በመሆኑ ነው፡፡

     ሐዋርያት ምሥጢረ መንግስትን እንዲያውቁ የሙሴና የነቢያት መጻሕፍትን ሁሉ እንዲያስተውሉና እንዲተረጉሙ በአጠቃላይ ሰማያዊ የሆነውን እውቀት ሁሉ የገለጠላቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ቅ.ጳውሎስ ‹‹…እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም፡፡እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዘብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም፡፡›› ብሏል ጨምሮም ‹‹ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታወቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ››በማለት ምስጢር ገላጭ የሆነ እርሱ ብቻ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ትንቢት መናገርም ሆነ ትንቢትን መተርጎም ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ሲያስረዳ‹‹ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤በመጽሐፍ ያለው ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡ 2ጴጥ1÷20-21፤1ቆሮ2÷11-12፤ ኤፌ6÷19

ሰዎች በትዕቢት ሲያዙ ደግሞ የሚያነቡትን እንዳያስተውሉ ምሥጢርን ይሰውራል፡፡ ሐዋርያት ጌታችንን ለምን በምሳሌ እንደሚያስተምር ሲጠይቁት ‹‹ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም››ያለ ይህን ለማመልከት ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስም‹‹ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው፡፡››ብሏል፡፡በቆሮንቶስ መልእክቱም ዓለም በጥበቧና በምርምሯ እግዚአብሔርን ለማወቅ እንዳልቻለች በተብራራ ሁኔታ ተገልጿል:: ማቴ13፥10-11፤ 1ቆሮ1÷18-27፤2ቆሮ4÷3 ስለዚህ ከትዕቢተኞች ምሥጢር የሚሰውር መንፈስ ቅዱስ ለትኁታን ደግሞ ስለሚገልጥ ከሣቲ ተብሏል፡፡

7. አለባዊ ማለት ማስተዋልን የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ሰዎች ጌታ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ሳያከብሩት ሲቀሩና ኃጢአት መሥራት ሲደፋፈሩ ለማይረባ ከንቱ አእምሮ ተላልፈው ይሰጣሉ፡፡ከንቱ አእምሮ ማለት ማስተዋል የተሳነው ለመምረጥ ለመወሰን በሚሰራውም ነገር የሚጠብቀውን ውጤት(ፍርድ) ለመረዳት የተዘጋበት፤ ምክር የማይሰማና ተግሳጽ የማይቀበል ማለት ነው፡፡

     ማስተዋል የተነሳቸው ለከንቱ አእምሮ ተላልፈው የተሰጡ ሰዎች የጌታ እግዚአብሔርን መኖር ይክዳሉ በግብራቸውም ከእንስሳት አንሰው ይታያሉ፡፡‹‹ልብ እንደሌላቸው እንስሳት ሆኑ››ያለው መጽሐፉ እንደነዚህ ያሉትን ነው፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ‹‹ሂድ ይህን ሕዝብ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው›› በሚል ጠባያቸው ተገልጿል፡፡ ኢሳ 6፥9፤ሮሜ 1፥20-28

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ እውቀት በማጣት ጨለማ ላለ ሕዝብ እግዚአብሄርን የማወቅ ብርሃንን እንዲያይ ማስተዋልን ይሰጣል፡፡ዮሐንስ መጥምቅ ጌታችንን አያውቀው እንደነበርና ለእርሱም የገለጠለት መንፈስ ቅዱስ እንሆነ መስክሯል፡፡ዮሐ1÷3

ጌታችን ሐዋርያትን ብዙ ነገር ከነገራቸው በኋላ ከዚያም በላይ ሊነግራቸው ይችል እንደነበር እነርሱ ግን በነበሩበት ደረጃ ቢነግራቸው ለማስተዋል እንደማይችሉ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን እንደሚመራቸው (ማስተዋልን እንደሚሰጣቸው) እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፤‹‹የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል…ዩሐ16÷12-13 ቤተክርስቲያን በቸርነቱ እየጠበቀ በምግብናው የሚመራት ጌታ መንፈስ ቅዱስን‹‹ሀበነ እግዚኦ አዕይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ ወአዕዛንነሂ ቃለ ዘባህቲትከ ይስምዓ››ስትል በጸሎቷ ትማልላለች፡፡ዓይነ ሥጋችን ግዙፉን ዓይነ ልቡናችን ረቂቁን፤አንድም ዓይነ ሥጋችን ሥነ ፍጥረትህን በማየት ዓይነ ልቡናችን ቸርነትህን ምህረትህን መግቦትህን በማስተዋል አንተን ብቻ ማየት(ማምለክ) እንድችል፤ዕዝነ ሥጋችንና ዕዝነ ልቦናችንምሕይወት የሆነ ያንተን ቃል ብቻ መስማት ይችል ዘንድ አቤቱ ስጠን ስትል ነው፡፡

     ካለ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ጥበብን ይልቁንም መንፈሳዊ ጥበብን(ምሥጢርን) ገንዘብ አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ነው፡፡የጠቢባንን ምክር የአዋቂዎችንም ማስተዋል የሚያስረሳቸው እርሱ በትኅትና በየዋህነት ደጅ ለሚጠኑ ሁሉ ግን ማስተዋልን ይሰጣል፤ፈቃዱ እንዱሁ ነውና፡፡


 

8. መስተናግር ማለት ሃይማኖትን፣ የጥበብን ቃል፣ ምሥጢርን የሚያናግር የሚያስተረጉም ማለት ነው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሀምሳ በአይሁድ መካከል ቆሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ቢናገር በአንድ ጊዜ ስብከት ሦስት ሺ ሰዎች ማሳመን ችሏል፡፡ ይህ የሆነው ከቅዱስ ጴጥሮስ ዝግጅት ሳይሆን ‹‹ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል›› ብለው ሲያሙ ለነበሩ አይሁድ የተሰጠ የመንፈስ ቅዱስ መልስ ነበር፡፡ቅዱስ ጳውሎስ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል፡፡ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል…ለአንዱም ትንቢትን መናገር…ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር…ይሰጠዋል››ሲል የመንፈስ ቅዱስን የማናገር ኃይል አብራርቷል፡፡እንግዲህ በዋናነት መንፈስ ቅዱስን መስተናግር(የሚያናግር)ስንል፡-

ሀ. ሀብተ ትንቢትን ሰጥቶ ኃላፍያትን መጻእያትን የሚያናግር

ለ.የጠፋውን ለመመለስ የጠመመውን ለማቅናት የጥበብን ቃል የሚሰጥ(የሚያናግር)

ሐ.የሃይማኖትን ቃል ለማቅናት እውቀትን(ምሥጢር በመተርጎም) የሚናገር

መ.ለእያንዳንዱ ነገድና ሕዝብ ቋንቋውን ተናጋሪ ኅብረተሰብን መስሎና ተካክሎ መናገር ማለት ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 12፥4-11

ከዚህ የሚልቀው ደግሞ እነሆ፡-

‹‹ለእርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወስዳላችሁ፤አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁም››ማቴ 10፥18-20

ጌታችን በሰማዕትነት ሰዓት ከነገሥታቱና ከጠቢባኑ በእኛ ያለውን እውነትና ተስፋ ለማስተሐቀር እንዲሁም በሀይማኖታችን ለመዘበት ለሚያነሱት ጥያቄና ክርክር እንዳንጨነቅ በዚያኑ ሰዓት በእኛ ውስጥ ያለ ጌታ መንፈስ ቅዱስ የምንናገረውንና ተከራካሪዎቻችንን የምናሳፍርበትን ቃል እንደሚሰጠን የተናገረው ማረጋገጫ ነው፡፡

9. መስተሥርዪ፡-መንፈስ ቅዱስ መስተሥርዪ ይባላል፡፡ኃጢአትን የሚያርቅ የሚያስወግድ የሚደመስስ ማለት ነው፡፡መንፈስ ቅዱ በአርባ በሰማንያ ከተጠመቅንበትና ከሥላሴ ልጅነትን ካገኘንበት ቀን ጀምሮ በእኛ ያድራል፡፡ሃይማኖትን ካልካድን በስተቀር አይለየንም፡፡ይህን ሲያይ ነው ቅዱስጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?›› ያለው፡፡ 1ኛ ቆሮ 3፥16

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአታችንን ሊሽር በደላችንንም ሊደመስስ የመጣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አሐቲ ሥምረት ነው፡፡ኤፍሬም ሶርያዊ‹‹እስመ በፈቃዱ ወለሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኃነነ›› እንዳለ፡፡ ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ፡፡ በአባቱ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን ማለት ነው፡፡ይህቺ ሥምረት(ፈቃድ) አንዱ ቀድሞ አስቦ ለሌላው የሚገልጻት መቀዳደም መለያየት ያለባት አይደለችም አንዲት ናት አንጂ፡፡ሰው በልቡ የሚያስበው ከመንፈሱና ከቃሉ መወቀዳደም እንደሌለበት ማለት ነው፡፡በመሆኑም በሰው ልጅ መዳን ውስጥ የፈቃድ መለያየት የለምና መንፈስ ቅዱስመስተስርዪ ይባላል፡፡አንድም

     በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ምሥጢራት ሁሉ የሚፈፀሙ(የሚከብሩ)በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡በጥምቀት ለሚገኝ ሥርየተ ኃጢአት ፈጸሚው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባ ወቅት በካህኑ ላይ አድሮ የሚናዝዝ የኃጢአትንም ሥርየት የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ጌታችን ከትንሳኤው በኋላ ‹‹እፍ ብሎ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› በማለት ለሐዋርያትሥልጣነ ክህነትን ሰጥቷቿል፡፡ በዚህ ዓለም የካህናት ተግባር ሰዎች ሁሉ ስለኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታንና ሥርየትን እንዲያገኙ ማገልገል ነው፡፡በጥምቀት፣በማስተማር፣በመምከርና በመገሰፅ፣በመናዘዝ፣እንዲሁም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በማቀበል በስሙ የሆነ የኃጢአት ሥርየትን መስበክ የምሥጢረ ክህነት ዋና ተግባር ነው፡፡በመሆኑም ክህነትን ከመስጠት ጀምሮ ምሥጢራት ሁሉ የሚፈጸሙ በመንፈስ ቅዱስ በመሆኑ መስተሥርዪ ተብሏል፡፡ ዮሐ 20፥22-23

     መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በሚመጣ ጊዜ ስለ ሶስት ነገር ዓለምን እንደሚወቅስ ተናግሯል፡፡ ‹‹…እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፡፡ ስለ ኃጢአት በእኔ ስለማያምኑ፤ ስለ ጽድቅም ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው›› ዮሐ16÷8-11

     በዘመነ ሐዲስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ዓለምን ማዳኑን ከመካድ በላይ ኃጢአት የለም፡፡መንገድ ሕይወትና እውነት የተባለች በእርሱ ያለን ይህቺ ሃይማኖት ናት፡፡ሃይማኖትን መካድ ከመንፈስ ቅድስ ልጅነት የመለየት መጨረሻው ምልክት ነው፡፡

     በአንጻሩ ወረደ፣ተወለደ፣ተሰቀለ፣ሞተ፣ ተነሣ፣ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ዐረገ፣ ፣ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ብሎ ከመመስከር የበለጠ ጽድቅም የለም፡፡ ቅ.ጳውሎስ‹‹እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ለመላእክት የታየ፣በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣በክብር ያረገ››1ጢሞ3÷16 ብሎ ክርስተናን በጥቅል ያስቀመጠ ለዚህ ነው፡፡ሐዋርያት በአጽናፈ ዓለም ጻድቃን በገዳም ሰማዕታት በደም የፈጸሙት ጽድቅም ይኸው ነው፡፡ ሁሉም አምላክ ሰው ሰውም አምላክ የመሆኑ ሕያው የሕይወት ምስክሮች ናቸው፡፡

     መንፈስ ቅዱስ የዚህ ዓለም ገዢ የተባለ ዲያቢሎስ እንደተፈረደበትም አብስሯል፡፡ፍርዱ ግን በዲያብሎስ ብቻ አይደለም በክህደት በኃጢአት እርሱን በሚመስሉት ላይ ሁሉ እንጂ፡፡ዮሐንስ በወንጌሉ‹‹በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡…በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤በማያምን ግን በአንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈረዶበታል››ዮሐ3÷16-19 ብሎ የዲያብሎስን የክህደት መንገድ የመረጡ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከመንግስተ እግዚአብሔር በአፍአ የሚጣሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ዲያብሎስን በግብር በክህደት የሚመስሉት ሁሉ ፍጻሜያቸው እርሱ በሚኖርበት መኖር በእርሱ ላይ የተፈረደውንም መቀበል ነው፡፡

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይህን ሁሉ የሚሠራ እኛ ለዘላለም በሕይወት እንኖር ዘንድ ነው፡፡ ራሳችንን ለፈቃዱ ካስገዛን፤የእርሱ ማደሪያ መቅደሶች መሆናችንን አውቀን ህዋሳቶቻችንን ሁሉ በቅድስና ከጠበቅን በቅዱሳን ላይ አድሮ የሥራውን ሥራ በእኛም አድሮ ይሠራል፡፡ ሕይወትን ከሚሠጥ ከእርሱ ጋርም ለዘላለም በሕይወት እንኖራለን፡፡ሃይማኖትን ከመልካም ሥራ አስተባብረን እንድንይዝ በጌታችን በደሙ መገዛታችንንም ከንቱ እንዳናደርግ በማስተዋልም እንድንኖር ነው ቅዱስ ጳውሎስ‹‹ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ››ያለን፡፡ኤፌ3÷30 የእግዚአብሔር ልጆች የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች የመሆናችን ማረጋገጫ ማኅተማችን እርሱ ነውና፡፡

ዓለማትን የፈጠረ በነቢያት አድሮ የተናገረ በሐዋርያትም እውነትን ያስተማረ ጻድቃን ሰማእታትን ለገድል ያዘጋጀ እግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ተረክቦ ይመራልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን! ጌታ ቢፈቅድ ብንኖር በሌላ የሕይወት ቃል እስክንገናኝ የአብ ቸርነት የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ሕብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!

ግንቦት2007

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

Read more...

ሰቆቃወ አርድእት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

‹‹ሰቆቃወ አርድእት››

ዙሪያችን ለመስበር በሚያስፈራ ዝምታ ታጥሯል፡፡ ሁሉም ሲያየው ባደረውና በዋለው ትዕይንት ልቡናው ተቧጦ መንፈሱ ደቆ ሰው በመሆኑ ሳይቀር ተሳቆ በየጥጋጥጉ ተቆራምዷል፡፡ በዚያች ጠባብ ክፍል የተቀመጠ ሁሉ ብቸኛ ነው፡፡ማንም ማንንም ለማዋራት ለማፅናናትም ሆነ ሰቆቃውን ለመጋራት አቅም አልነበረውም ፡፡አልፎ አልፎ ከደረቀ ማንቁርት የሚወጣ ሳግ፤ በስቃይ ከተመታ ልብ የሚገነፍል ትንፋሽ ይሰማል፡፡

የሚያፅናና፣ የሚያበረታታ፣የሚመክር፣ አይዟችሁ የሚል የለም፡፡ ፍርሃት ከቦናል ጨለማ ወድቆብናል፡፡ነፍሳችንን ሀዘን እንደመቃብር ተስፋ መቁረጥም እንደ መርግ ተጭኗታል፡፡

ያ ቃል ነፍስን ከዓለም አሳብ ለይቶ እንደ ንስር የሚያመጥቃት፤ ያ ድምፅ ልብን በሀሴት አስክሮ ከሰማያት ደጃፍ የሚያደርሳት፤ ያ ርኅራኄ በኃጢአት የደቀቀችን ዝንቦች በጭካኔ እንደወረሩት ገጣባ ጀርባ አጋንንት የተቀራመቷትን ሰውነት የሚያሳርፋት፤ ዛሬ ካጠገባችን ርቋል፡፡

አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ፣ እወዳለሁ ንፃ. . .፣እምነትሽ አድኖሻል. . .፣እኔም አልፈርድብሽም. . .፣ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል በሰላም ሒጂ. . .፣ ዛሬ በዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል . . .የሚሉት ከአድማስ ደንጊያ የበረቱ ቃላት ትዝታቸው ብቻ ቀርቶልናል፡፡

በርጅና ምክንያት አጥንትና ጅማት ብቻ የቀራቸውን እግሮቼን ካጠፍኩበት ለመዘርጋት ስታገል አንድ ሰው ቀስ ብሎ ረዳኝ፡፡ የልብሱ ሽታ ነፍሴ የለመደችውን መዓዛ ስላስታወሰኝ እርጅና የተጫነው ሰውነቴ በሀዘን ተርገፈገፈ::ዕንባዬ ወደ ውስጤ ሰርጎ አንጀቴን ሲያቃጥለው ተሰማኝ፡፡ ዋ! ለካስ ለሚወዱት ለማዘንም(በዕንባ ዘለላዎች ፍቅርን ለመግለፅም) አቅም ያንሳል፡፡

ከነፍሴ ጥልቅ ጮኽኩ፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም ሊሰማው የማይችል ዋይታዬን፤ የሰው ጭካኔ ካስደነገጣት ነፍሴ የተጨመቀ ሰቆቃዬን ወደ አርያም ላክሁ፡፡

እረኛችን ሆይ! መንጋህ እኮ ተበተነ፡፡ በአንዲት ቀን ብትለየን ውስጣችን በሀዘን ከሰሎ ነፍሳችን በተስፋ መቁረጥ ቆስሎ እንግዳ በሆንባት ምድር እንደ ሽኮኮ በፈረሰ ግንብ ውስጥ ተቅበዝብዘን፡፡ ነፍሴ የወደደችህ ሆይ ንገረኝ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ከድንጋጤ የተነሳ ልቤ በውስጤ እንደ ሰም ቀለጠ ጉልበቶቼ ሁሉ ደከሙ፡፡ ነፍሴ እንደ ምድረ በዳ ተጠማችህ፡፡ አቤቱ እረኛዬ ሆይ! የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፡፡

ውጋት የሚያሰቃየው ደረቴ በአንድ እጄ ደግፌ ጉልበቶቼን ለመዘርጋት የረዳኝን ሰው ለማየት ከተደገፍኩበት ቀና አልኩ፡፡ አልባሌ ልብስ የለበሰ ሰው እንዳልሆነ ስዳስሰው ታውቆኛል፡፡ የክፍሉ ብርሃን ማነስና እርጅና የተጫነው ዓይኔ ማን መሆኑን ለመለየት ግን አላስቻሉኝ፡፡ማን መሆኑን ለማወቅ መጓጓቴን ስላወቀ ክፍሉ ጠርዝ ጋር የነበረውን መቅረዝ አምጥቶ አጠገባችን አኖረው፡፡አፌን ብከፍትም ቃል ማውጣት ግን አልተቻለኝም፡፡ ሁኔታዬን ስለተረዳ‹‹አባባ ናታን እኔ ነኝ የቀን ቀን ፈሪሳዊ የሌሊት ክርስቶሳዊ የሆንኩት እኔ ኒቆዲሞስ ነኝ›› አለኝ፡፡

የለበሰውን የፈሪሳውያንና የአይሁድ መምህራን ካባ ስመለከት በዚህች የታወቀች ዕለት ይህ የለበሱ ሁሉ ይፈፅሙት የነበረው ጭካኔ የእንባዬን ቀላይ ነደለው፡፡ አጥንታቸው ብቻ በቀረ ጉንጮቼ ላይ እየወረዱ ፂሜ ውስጥ ሰርገው ቀሩ በልቅሶ የሚርገፈገፍ ሰውነቴን ለማስከን ኒቆዲሞስ ትከሻዬን ጫን አድርጎ ያዘኝ በደከመ ድምፅ ‹‹ ግን ለምን. . .? ያ ሁሉ ጭካኔ ያ ሁሉ መጠን ያለፈ ጥላቻ፤ ግን ለምን. . .?በንፁሑ ላይ፡፡ ግፋቸው እየጨመረ ሲሄድ የገዛ ጭካኔያቸው ሲያስፈራቸው ጥላቻቸውን ለመሸከም ሲከብዳቸው አይቻለሁ፡፡ አባባ ናታን ‹‹ክፋት መንስዔን ጥላቻም ምክንያት አይሻም፡፡የዚህን ዓለም ጠባይዕ መመርመር አሰቻጋሪ ነው፡፡ ፍቅሩም ሆነ ጥላቻው ከእውነት ይልቅ ስሜትን የሚከተል ነው፡፡ ከሚስቀው ጋር ለመሳቅ፣ ከሚያለቅሰውም ጋር ለማንባት፣ከሚጮኸው ጋር ጮኸን ከሚፈርደው ጋር ለመፍረድ ርትዕ አያስፈልገንም፡፡ በቁጥር መብለጥ ጩኸት ማብዛት ብቻ በቂ ነው፡፡ይልቁንም የአድማውን መለከት የነፉት የአመፁን ችቦ የለኮሱት በሥልጣን ወንበር የተቀመጡ በብልጥግና የቀበጡ በሽበት የተጌጡ የሕዝብ አውራዎች ከሆኑ እውነትን ለመርገጥ ፍትህን ለመደፍጠጥ ቀላል ነው፡፡

በዚህ ሰዓት በፍርድ ወንበር የተቀመጠው ማስተዋሉን ፣ መርማሪም ጥበቡን ይደብቃል፡፡ የገዘፈውን ለማየት የጎላውን ለመስማት አቅም አይኖረውም፡፡በሁከት መካከል የዝምታን ምሥጢር መለየት፣ ከአድመኞች ወጥመድ እውነትን ማውጣት ከጨካኞች ጉያ ፍትህን ነፃ ማውጣት እስከ ዛሬ ወደ ምድር የወረደውን የዝናብ ነጠብጣብ የመቁጠር ያክል የማይሞከር ነው፡፡

የገዛ ወገኖቹ ይዞ የመጣውን ፍቅር ሊያክል ትንሽ የቀረው ጥላቻ ይዘው ተቀበሉት፡፡ ፈጥሮ የሠጣቸውን ውኃ እስኪ ነፍጉት ድረስ፡፡ አባባ ናታን‹‹ ምን እላላሁ? ነፍሴን በምክራቸው ያልጨመረ በፍርዳቸው ልቤን ያላኖረ ሰውነቴንም ከሸንጎዋቸው የለየ የእስራኤል አምላክ ይመስገን፡፡ በቅዱሱ ብላቴና ላይ ሲሸምቁ እንደ ተኩላም ሲያደቡ ዓይኖቼን እንዲያዩ የከፈተ እርሱ የተመሰገነ ይሁን››፡፡

አስፈሪውን ጸጥታ ለመስበር ድፍረታችንን ያዩ በክፍሏ ውስጥ የነበሩ ሌሎችም ቀስ እያሉ መጥተው አብረውን ተቀመጡ፡፡

የመቅረዟን መብራት በእንባዬ ግርዶሽ እያየሁ መንፈሴ ወደ ኃሙስ ሌሊት ተነጠቀ፡፡ መምህሩን ይዘውታል የሚል መርዶ ከሰሎሜ እንደሰማሁ ልቤ ጉሮሮዬ ውስጥ ተሰንቅራ ጉልበቶቼ እየተብረከረኩ ወሰዱት ወደተባለበት የቀያፋ ጊቢ ተፋጠንኩ፡፡ እዚያ ስደርስ ሐና ወደተባለው የሊቀ ካህናቱ አማት ወስደውት ኑሯል ጊቢው ጭር ብሏል፡፡

አረጋዊ መሆኔና እንደ በረሃ ዓለት ባገጠጡ የጉንጮቼ አጥንቶች ላይ የሚወርደውን ዕንባ ጨለማውና ሀጫ በረዶ የመሰለውን ፂሜ ተረዳድተው ስለሸፈኑልኝ በረኞቹ አንዳእ ሳይሉኝ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡

ከብርዱ የተነሳ እዚህም እዚያም ከሚነደው እሳት በቀር እረጭ ብሏል ምን ያህል እንደቆየሁ አላስታውስም፡፡ ብቻ ግራ ገብቶኝ ዙሪያውን ሳማትር የጩኸትና የሁካታ የስድብና የዛቻ ድምፅ እየቀረበኝ መጣ፡፡ወዲያው በገመድ የደኃሪት አስረው ወደፊትና ወደኋላ እያዳፉ ይዘወት መጡ፡፡የማየውን አምኖ መቀበል ቸገረኝ፡፡ ሀይ ባይ ከልካይ የለም ሊመታው የፈለገ ይመታዋል ሌላው ይገፈትረዋል፤ገሚሱ ምራቁን ይተፋበታል መቅረብ ያልቻለ ከሩቅ ሆኖ ይረግመዋል፡፡

የሊቀ ካህናቱ ዘቦች ከአሁኑ እርሱ በመደብደብ መድከማቸው ያስታውቃል፡፡ ወላጆቹ እንደጠፋበት ህጻን በማየው ነገር ግራ ተጋብቼ መካከል ላይ እንደቆምኩ ደርቄ ቀረሁ፡፡ ዘቦቹ ህዝቡን እኔ ካለሁበት ጥቂት ሲቀር ገታ አድርገው እርሱን ብቻ ለይተው መሀል ላይ ለበቅሎ ማሰሪያ የቆመ ግንድ ጋር ጠፍረው አሰሩት፡፡

ልብሱ ተቦጫጭቋል፡፡ መደረቢያው የለም፡፡እጆቹና እግሮቹ ተጋግጠዋል፡፡ፊቱ ለማየት በሚዘገንን ሁኔታ በደም በላብና በምራቅ ተሸፍኗል፡፡በታሰረበት ቦታ ከጉልበቱ ሸብረክ አንገቱን ዘለስ አድርጎ ከብርቱ ድካም ጋር ይታገላል፡፡ጥቂት ቆይቶ ቀና ብሎ ሲመለከተኝ አሁንም ዓይኖቹ ውስጥ የተለመደውን ርኅራኄና ፍቅር የጀመረውን ለመጨረስ የተዘጋጀ ቁርጠኝነት አየሁ፡፡ ፍርሃትም ሆነ ጭንቀት አይታይበትም፤ፍቅር ሀዘንና ርኅራኄ ግን ከዓይንኖቹ አሁንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይረጫሉ፡፡ በደምና በምራቅ ካደፈ በጡጫ ብዛትም ካባበጠ ፊቱ መካከል ዓይኖቹ በድቅድቅ ጨለማ እንዳሉ ከዋክብት ያበራሉ፡፡ሁሉን በፍቅርና በሀዘኔታ ያያል፡፡አባት ሕፃናት ልጆቹን በሚያይበት ሁኔታ ያስተውላቸዋል፡፡ሲመቱትም ሆነ ሲተፉበት ፊቱን አይሰውርም እይታውም አይቀየርም፡፡

ከሆዴ አንዳች ጥላቻ ሲገነፍል አፌንም ምሬት ሲሰማኝ ሁሉን በቁጣ ተመለከትኳቸው፡፡እርጅናዬን ድካሜን ሁሉ ረገምኩት፡፡ወይኔ በጉብዝናዬ ወራት ቢሆን የቻልኩትን ጥዬ እወድቅ ነበር፡፡እኒህን ጭራቆች እኒህን የሰው ልጅ የጭካኔው ጫፍ መገለጫዎች ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አንዳች ኃይል ቢኖረኝ ስል ተመኘሁ፡፡በቁጣና በእልህ ጉሮሮዬ አብጦ ደም ሥሬ ተወጥሮ ዘወር ስል ዓይኖቼ ዓይኖቹ ላይ አረፉ፡፡

የማውቀው መዓዛ አወደኝ፡፡እናቱ ቀኝ እጇን ልቡ ላይ ጣለ ያደረገችበት ሕፃን በግርግም ሳለ ታየኝ የእናቱን ጡት ሽቶ ሲያለቅስ እርሷም በስስት እያየችው ለፈቃዱ ስትታዘዝ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ወዲያው ደግሞ በታላቅ ዙፋን ላይ እንደታደረ በግ ሆኖ አየሁት፡፡

ከዓይኖቹ የሚወጣው ብርሃን ዓይኖቼን ሲዳስሳቸው ጥላቻና በቀል ቁጣና እልህ ከውስጤ ሲጠፋ በምትካቸው ፍቅርና ርኅራኄ ሀዘኔታም ሲሰርፅ ተሰማኝ፡፡በእርሱ ዓይን ሳያቸው እነርሱን የመጥላት አቅም አነሰኝ ፡፡ ዕይታዬ ሲፈወስ በደም የራሰ ፊቱ ሲፈካ ከአይኑም የአልማዝ ፈርጥ የሚመስሉ ዕንባዎች ሲፈሱ ተመለከትኩ፡፡ እንባው እንደታላቅ ዥረት ሲፈስ ፍጥረት ሁሉ በሀሴት ሲታደስ ይታየኛል፡፡ዕፁብ ዕፁብ ኦ የዘላለም አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የነፍሳችን ዕረፍት ይህን ፍቅር ይረዳ ዘንድ ማን ይችላል? ይህ የማይመረመር ትዕግስት ይገልጡት ዘንድ የማይደፈር ትኅትና ምን ይደንቅ?

ኅሊናዬ በሰዎች ክፋትና ጭካኔ እየታመመ በጌታ ቸርነትና ፍቅር እየተደመመ እያለ በትንሹ ረገብ ብሎ የነበረው ጩኸትና ርግማን ድጋሚ ሲፈነዳ በድንጋጤ ዞርኩ፡፡ እነሆ የመድኅን እናቱ ከዮሐንስ ጋር በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል መጣች፡፡ ግማሹ ይራገማል ግማሹ ይጮኻል እርሷ በመካከላቸው ስታልፍ ምንም ዓይነት መረበሽ አይታይባትም፡፡ ወደ ማንም አትመለከትም፡፡ዓይኗ አንድዬ ልጇን ብቻ በመፈለግ ያማትራል፡፡ የምትፈልገውን እንዳገኘት ለጥቂት ደቂቃ ባለችበት ቆማ ታስተውለው ጀመር፡፡ ቀና ብሎ ወደርሷ ሲመለከት ቀስ እያለች ወደርሱ ቀረበች፡፡ የጠራ የጨረቃ ፀዳል የሚመስለው ፊቷ ለዘላለም የሚቆም በማይመስል ዕንባ ይታረሳል፡፡ ዕንባዋ በአንገቷ ወርዶ ደረቷን አርሶታል፡፡ አትጮኽም አትወራጭም፡፡ ፊቷ ላይ ብቻ አንዴ ሀዘን አንዴ መደነቅ ሲያረብበት ግንባሯ ቅጭም ደግሞም በርኅራኄ ጥንዝል ይላል፡፡ ማንም ሊያስቆማት የሞከረ የለም፡፡ ደርሳ በዕቅፏ ልትይዘው የጎልማሳ ርምጃ ያህል ሲቀራት አንድ ዘብ አስቆማት አልተቆጣችም አልተቃወመችም ባለችበት ቆማ ዕንባ ባረገዙ ዓይኖቿ ውዷን እያየችው እጇን ዘረጋች፡፡ቁስሉን ልታጥብለት ስቃዩን ልታስታግስለት የእናትነት አንጀቷ ናፈቀ፡፡ ሀዘን አንጀቷን ሲያኝከው በልጇ የደረሰ መጎሳቆል መንፈሷን ሲያቆስለው ምጥ እንዳስጨነቃት ወላድ ሆዷን እቅፍ አድርጋ የሠራ አካላቱን በዓይኖቿ ትዳስሰዋለች፡፡

ጌታችን እናቱን ሲያያት ልቧን የሚወጋትን ሕዋሳቷን የሚቧጥጣትን የሀዘን ሰይፍ ለመቻል ትታገል ነበር፡፡የዘረጋች እጆቿን ለመያዝ እጁን ለመዘርጋት ቢሞክርም አልቻለም፡፡ብርቱ ንፋስ እንደመታው ዛፍ በሲቃ የሚናጥ ሰውነቷን እያየ አናገራት፡፡ቃል ግን አላወጣም፡፡ሁለቱ በሚተዋወቁበት በዝምታው አናገራት በጽሞና አደመጠችው ለፈቃዱም ታዘዘች ልምዷ ነውና፡፡

ዘወር ብላ የምትቆምበት ጥግ ስትፈልግ ጻዕረ ሞት መስዬ በቆምኩበት ተመለከተችኝ፡፡የብርሃን እናት ከፊቴ ስትቆም ዓይኖቿን እያየሁ ለመናገር ሞከርኩ፡፡ምላሴ ከትናጋዬ ተጣብቋል ሰውነቴ ውስጥ አንዳች ፈሳሽ የቀረ አልመሰለኝም፡፡መናገር አቅቶኝ አፌን ለመክፈት ስታገል ቀረብ ብላ እጆቼን ያዘቻቸው፡፡የሀዘን ማዕበል ሲንጠኝ ከልቅሶዬ ሳግ ጋር እየታገልኩ‹‹ለምን?ግን ለምን የብርሃን እናት ሆይ?ይህ ሁሉ በእርሱ ላይ ለምን?ምን በደል ተገኘበት?ምንስ ክፋት ታየበት?. . .መቀጠል አልቻልኩም፡፡

የብርሃን እናት‹‹እርሱ ሁሉን ያውቃል መንገዱን ይመረምር ዘንድ ማን ይችላል፡፡እንዳሰበ ይሠራል እንደፈቀደም ይፈፅማል፡፡ ነቢያት የተናገሩት የመጻህፍትም ቃል ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው፡፡ይህ ሁሉ እንደሚሆን አስቀድሞ እንደነገረን ልብ በል ናታን››አለችኝ፡፡ እርግማንን ሲሽር የበደልን ሥራ ሲቆርጥ ስለዚች ሰዓት መጥቷልና፡፡ የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ተግሳፃችንን ሊሸከም በደላችንንም ሊያስወግድ ተገልጧል፡፡የጀመረውን ይፈፅመዋልና በጽናት እንቁም አይዞህ ስትልኝ በረታሁ፡፡አጽናንተሸኛል የጌታዬ እናቱ ሆይ ብያት ሌሊቱን እንገፋ ዘንድ አንዱ ጥግ ሔደን ተቀመጥን፡፡

ለቅፅበት እንኳ ለዓኖቿ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶቿ ዕረፍት ሳትሰጥ ዕንባዋ እንደ ክረምት ዥረት እየፈሰሰ አደርን፡፡እርሱ ላይ ዱላ ባረፈ ቁጥር እያንዳንዷ ሕዋሷ ሲታመም ይታወቀኝ ነበር፡፡ ዕለተ ዓርብን መግለጽ የሚችል ምን አንደበት ነው? ልብ ይታመማል አእምሮም ይዝላል፡፡ከጠዋት አንስተው እያንገላቱ ገዥው ጊቢ ወሰዱት አንዲት ፅዋ ውኃ እንኳ እናቀብለው ዘንድ የሚፈቅድ ርኅሩኅ ልብ አላገኘንም፡፡

በዚህች ዕለት የአዳም ልጆች ጭካኔ የእርሱ ይቅር ባይነቱ ተገለጠ፡፡የገዛ ወገኖቹ ያልራሩለትን እርሱን የሮማ ወታደሮች የደም ጥማታቸው ተወጡበት፡፡

የማይሆን ሲሆንበት ሊደረግ ማይገባ ሲደረግበት ሁላችን እናቱን ከበን እናይ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ መከራው የእርሷም አካል አብሮ እንደ ጽጌረዳ ይረግፍ ነበር፡፡

መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ መንገድ ሲጀምር እዚያው እንድቀር ሁሉም ግድ አሉኝ የብርሃን እናትን ግን ለመንኳት‹‹እባክሽን በተጓዘበት መንገድ ልጓዝ የደሙን ነጠብጣብ ተከትዬ ልሂድ፡፡ ከልቤ ናፍቆት ሰንፌ እንዳልቀር በጸጋሽ ደግፊኝ፡፡ እግሮቹ የቆሙበት ሥፍራ ልድረስ፤ ማዳንህን ዓይኖቼ አይተዋልና ባሪያህን አሰናብተኝ እለው ዘንድ በመስቀሉ ሥር ልዋል፡፡

የጌታዬ እናት‹‹እርሱ ከመከተል አትድከም የሁሉን ፍጻሜ ታይ ዘንድ ልብህን አበርታ›› አለችኝ በረታሁም፡፡

እነዚያ ጨካኞች እነርሱ ራሳቸውን ችለው መውጣት የከበዳቸውን መንገድ፤ውኃ እየጠጡና እያረፉ ሲጓዙ ከእርጥብ እንጨት የተሠራ መስቀል ተሸክሞ ለሚቃትተው ለእርሱ ግን ዕረፍትን ሊሰጡት አልወደዱም፡፡ ስለ እርሱ የእኔ ልብ በውስጤ ቀለጠች፡፡ ድንገት አንዱ ፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ ፍጠን ብሎ ቢረግጠው መስቀሉን እንደተሸከመ በግንባሩ ፍግም ብሎ ወደቀ፡፡ መስቀሉ ማጅራቱን ቀጥቅጦ ከዓለቱ ጋር ስላጣበቀው ፀጥ ብሎ ሲቀር ሁላችን በዋይታ ተሞላን፡፡

ወደ ማን እንጩኽ? ዕርዳታስ ከወዴት ይመጣ ዘንድ እንጣራ?

ወታደሮቹ ሁሉ ከመሰቀሉ በፊት የሞተ መስሏቸው ተደናገጡ፡፡ አንድ ዓይን ብቻ የነበረው የወታደሮች አለቃ በቁጣ ከጮኸ በኋላ ፣መስቀሉን ያነሱለት ዘንድ አዘዘ፡፡ ገልብጠው በጀርባው ሲያንጋልሉት ዓለቱ ከቀጠቀጠው አፍና አፍንጫው የእሾኽ አክሊል ከተጎነጎነበት ራስ ቅሉም ደም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ፊቱም በደምና በአቧራ ተሸፍኖ ለማየት ተሳነው፡፡

አንዲት በነፍሷ የቆረጠች ብላቴና በወታደሮቹ መካከል አፈትልካ አጠገቡ በመድረስ መጠምጠሚያዋን ፈትታ ሰጠችው፡፡ ከመሳቀቋ የተነሳ ደፍራ ልትጠርግለት እንኳ አልቻለችም፡፡ እርሱም ፊቱ ላይ ያለውን ደሙን ጠርጎ አንዳች ነገር ካናገራት በኋላ ለመነሳት መታገል ጀመረ፡፡

ውሎአችንን የሚሰሙ በጊዜው ያልደረሱ ወይም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ያልቀረቡ ራሳቸው እስኪፈርስ ሲያለቅሱ ሳጋቸው ይሰማኛል፡፡

በመካከል አንዲት ልጅ እግር ብላቴና በደም የተታታ ጨርቅ አቅፋ እያነባች ‹‹አባባ ናታን እነሆ ጌታችን ደሙን የጠረገበት ጨርቅ፡፡ አሁን እስኪያነሱት ድረስ የሆነውን ሁሉ ለማስታወስ የሚችል አቅል አልነበረኝም፡፡ እያንዳንዷ የደም ጠብታ ከሰማይና ከምድር የገዘፈ ዋጋ አላትና ለብርሃን እናት ወይም አእማድ ለሚመስሉ ደቀመዛሙርቱ አግኝተን እስክንሰጣቸው እነሆ›› አለችኝ፡፡

ጨርቁን ስቀበላት ያቀድሞ የማውቀው መዓዛ ሲያውደኝ ይታወቀኛል፡፡ እጀቼ እየተንቀጠቀጡ ቀስ አድርጌ የደከሙ ጉልበቶቼ ላይ ስዘረጋው ለማመን የሚከብድ ትዕይንት ገጠመን፡፡ ሁላችንም አፋችንን ከፍተን ዕንባ ባቆረዘዙ ዓይኖቻችን ለረዥም ሰዓት በአድናቆት ስናስተውለው ቆየን፡፡

መከራውን እንድናስብ የደሙን ዋጋ እንድንረዳ መልእክት ትቶልናል፡፡ ልክ መልካም ሰዓሊ እንደሚሥለው ሥዕል የመከራው ሰዓት መልኩ ጨርቁ ላይ በደሙ ታትሞበታል፡፡

ብላቴናይቱ‹‹ወንድሞቼና እህቶቼ ጌታ ይህን ጨርቅ ፊቱን ጠርጎ ሲመልስልኝ፤ ዓይኖቹን ትኩር ብዬ አየኋቸው ደም ጎርሰው ለማየት እንኳ እስኪቸግረው ቢደርስም እስከመጨረሻው ለመሔድ የነበረውን ጽናት እንድረዳው አደረገኝ በቃሉም ‹‹እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች ስለ ራሳችሁ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ፡፡ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጠቶች የተባረኩ ናቸው የሚባልበት ዘመን ይመጣልና፡፡ በእርጥቡ እንጨት ይህን ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?›› አለኝ ብላ በዚያች የመከራው ወቅት እንኳ ስለ መንጋው እንጂ ስለ ራሱ እንዳልተጨነቀ የፍቅሩን ጽናት አስታወሰችን፡፡

ጥግ ላይ ግዙፍ ሰውነቱን የሀዘን እሳት እንደ ጅማት ያኮማተረው አንድ ጎልማሳ መሬቱን በእጁ እየጫረ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል ድምፁን ሳግ እያነቀው‹‹ወታደሮቹ አጠገብ ስለነበርኩ የጭካኔያቸውን መጠን አይቼዋለሁ፡፡ ከእርሱ መከራ ይልቅ የስጨንቃቸው የነበረ ከቁማራቸው ላይ ተነስተው እርሱ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ለመፈጸም ያባከኑት ጊዜ ነው፡፡ጌታ ኢየሱስ ፊቱን በጨርቅ ካበሰ በኋላ ከወደቀበት ተነስቶ መስቀሉን ለመሸከም ረዥም ጊዜ ወሰደበት፡፡አንዳቸው እንኳ መስቀሉን አንስተው ለማሸከም ርኅራኄ አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንም ቆሎ በል እያሉ ባለ ኃይላቸው በአለንጋ ይገርፉት ነበር፡፡ እያንዳንዱ ግርፋት ሲያርፍበት ከሕመሙ የተነሳ ሰውነቱ ሲንቀጠቀጥ ይታየኝ ነበር፡፡ትንሽ ፋታ እንኳ ሳይሰጡ ያጣድፉታል፡፡ ጌታ ግን መስቀሉን ሊሸከም የሚችልበት አቅም ስላልነበረው ሰውነቱን ለአለንጋችው ትቶ ተንጋለለ፡፡ያለ ህኅራኄ ሲገርፉት አለንጋው ስለሚያርፍበት ቦታ እንኳ አይጨነቁም ነበር፡፡ ሰውነቱ ደም በሚተፋ ሰምበር ተዥጎርጉሮ ደም ግባቱም ጠፋ፡፡

ቀስ ብዬ ወደ ወታደሮቹ አለቃ ስቀርብ በዚህች ምድር ላይ ለመኖር አንዳች ፍላጎት ስላልነበረኝ ሞትን በደሰታ ለማቀፍ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ምድር ለአራዊት ለመሰጠቷ ከዚያ በላይ ምስክር አላስፈለገኝም፡፡

የወታደሮቹን አለቃ‹‹ፍርዱ ሳይፈጸም እዚሁ ከሚሞትባችሁ መስቀሉን ለመሸከም እንድረዳው ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡ እርሱም በቀረች አንድ አይኑ ውስጥ ያልጠበኩት የርኅራኄ ጥላ ውልብ ብሎ ፈቀደልኝ፡፡

መስቀሉ እንኳን በድካም ለዛለና በዱላ ብዛት ለደቀቀ ቀርቶ ጤነኛ ሰው ሊሸከመው ከሚችል በላይ ክብደቱ አስጨናቂ ነበር እንዴት ቻለው?

እንደምንም መስቀሉን አንስቼ ስቆም ከክብደቱ የተነሳ ጎኔን ውጋት ቀስፎ መተንፈስ አቃተኝ፡፡ከህዝቡ መካከል ሀዘን ያደቀቃት የጌታችን እናት በትኅትና እየተራመደች ሔዳ አጠገቡ በርከክ አለች፡፡እጆቹን አንስታ ደረቷ ላይ ስታደርገው ቀና ብሎ ሲያያት እርሱን በመውለዷ ስላገኛት መከራ ፊቱ በሀዘን ተመቶ ዕንባው ኮለል እያለ ወረደ ዕንባዎቹን ቀስ ብላ በጣቷ እየጠረገች በከንፈሮቿ መጠጠቻቸው ግንባሯ ቅጭም አድርጋ ራሷን ከፍ ዝቅ እያደረገች በዓኖቿ ስታናግረው አንደምንም አንገቷን አቅፎ ተነሳ፡፡ሀዘን ያደቀቀው መከራ የሰበረው ልብ ሰይፍ ያለፈባትም ነፍስ ምን እንደምትመስል እርሷ ፊት ላይ አነበብኩኝ፡፡

እኔ በስተቀኙ ሆኜ ትከሻ ለትከሻ ገጥመን መስቀሉን ለመሸከም ክንዶቻችን ሲቆላለፉ መስቀሉ ዓለት እንደወደቀበት ቁልቁል አጠፈኝ፡፡ይህ መስቀል ከእርሱ በቀር ፍጡር ሊሸከመው የማይችል መሆኑ የገባኝ ያኔ ነበር፡፡ ለካስ የተሸከመው ዓለምን ነበር፡፡ለካስ ጫንቃው ላይ የወደቀው መለኮታዊው ፍርድ ነበር ተሸክሞ እየቃተተ ኮረብታውን የሚወጣው የሰውን ልጆች ሁሉ ሸክም ነበር፡፡

መንቀሳቀስ ሲያቅተኝ ዘወር ብዬ ተመለከትኩት ወደ እኔ ሲዞር ፊታችን ስንዝር ያህል ርቀት ነበረው፡፡በምራቅ የተበከለ ፊቱ ፍቅርን፤ደም የጎረሱ ዓይኖቹም ርኅራኄን ሲረጩ አየኋቸው፡፡

ጌታ ሆይ ለዚህ የተገባሁ አይደሉምና ይቅር በለኝ፡፡ይህን መስቀል መሸከም የሚችል መቼም መች ካንተ በቀር አይኖርም፡፡ በልቤ ቅንነት ያደረግሁትን ተመልከት፤ላግዝህ እንደማልችል ባውቀውም እስከ ፍጻሜው ግን አብሬህ ልሒድ ሸክሜ በአንተ ጫንቃ እንደኖረ መተላለፌንም እንደተሸከምክ አሁን አወቅሁ፡፡ እባክህ ጌታ ሆይ ከጌታ ጋር መስቀሉን የተሸከመ ተብዬ እቆጠር ዘንድ የታሪኬም ፍጻሜ ካንተ ጋር ይሆን ዘንድ ይቺን ብቻ ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡

ያን ጊዜ መስቀሉ የርግብ ላባ ያህል ሲቀለኝ ክፋቴ ሁሉ ግን በእርሱ ሸክም ሲሆንበት ታወቀኝ፡፡ በጸጥታ እያነባሁ እስከዚህ ያደረስከኝ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ በፊትህ ምንድር ናት?እያልኩ መጨረሻው ድረስ አብሬው ተጓዝኩ፡፡

በዓይኖቹ ትኩር ብሎ ሲያየኝ ወደ ሞት እየሄደ መሆኑን ባውቅም አልተሰናበተኝም፡፡ይልቁንም ይበልጥ ሊቀርበኝ ከርሱም ጋር ፈፅሜ ስጣበቅ ተሰማኝ፡፡

ችንካሩን ስመለከት ሰውነቴ በፍርሃት ራደ ልበሶቹን ሲገፉት መከራ ያልደረሰበት አንዳች ሰውነት አልቀረውም፡፡በጎኑና በጀርባው ያሉ አጥንቶቹ እስኪቆረጡ ድረስ ፈጠዋል፡፡ሲቸነክሩት ያሰማ የነበረው የጣዕር ድምፅ የሕይወት ዘመኔ ሲቃ እንደሚሆን ታወቀኝ፡፡ጌታ ሆይ! ለምን?ሌላ መንገድ አልነበረምን? ለምን ይህን የጭንቅ መንገድ ትመርጥ ዘንድ ፈቃድህ ሆነ?

ሆዴ ሲገላበጥ አፌን ደም ደም ሲለኝ የብርሃናት ጌታን ዕርቃን ለማየትም ስላልደፈርኩ ፊቴን ሸፈንኩ፡፡ ግን አሁንም ይታየኛል፡፡ መከራው ሊረሱት ከሚችሉት በላይ ነበርና፡፡

ጎልማሳው ይህ ሲነግረን የነበረውን መቀጠል አልቻለም ፡፡ የተመለከተው ነገር የዕድሜ ዘመኑ ሸክም የሕይወቱም እንጉርጉሮ እንደሚሆን ከእኛ የተጠራጠረ አልነበረም፡፡

የአይሁድ መምህር የሆነው ኒቆዲሞስ ‹‹ወንድሞቼ እህቶቼ የሆነውን ሁላችን ዓይተናል፡፡ጌታችን ነፍሱን በሠጠባት ሰዓት ፀሐይ ስትጨልም፣ጨረቃ ደም ስትሆን፣ ከዋክብት ሲረግፉ፣የቤተመቅደሱ መጋረጃ ሲቀደድ፣የመሬት መናወጥ ሆኖ መቃብራት ሲከፈቱና ሙታን ሲነሱ ስመለከት በመጽሐፍ የተባለው የነብያቱ ሁሉ ጩኸታቸው የአበው ተስፋቸው እንደተፈፀመ አወቅሁ፡፡ እርሱ እውነተኛው መሲሕ የሕያው አምላክ የባሕርይ ልጁ የዓለሙ ቤዛ እንደሆነ ፍጹም አመንሁ፡፡

ጲላጦስ ቤተመንግሥት ስደርስ የካህናት አለቆች የአይሁድ ሽማግሌዎች ጲላጦስ ስላደረገላቸው ምስጋና ሊያቀርቡ ተሰብስበው ነበር፡፡ሁሉም በዓይነ መዓት ተመለከቱኝ፡፡ጥርሳቸውን የሚያፋጩም ነበሩበት፡፡

ገዥውን የጌታን ሥጋውን እንዲሰጠኝ ስለምን በቁጣ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ አስቀድሜ ስለተዘጋጀሁበት ነገ ሰንበት ነው ሰንበት ከመግባቱ በፊት ሥጋው ከመስቀል መውረድ አለበት ብዬ ስናገር የአርማትየሱ ዮሴፍም ሰንበት ሊሻር አይገባም ብሎ ደገፈኝ አይሁድ ስለ ሰንበታቸው እንጂ ስለጌታ ሥጋ ግድ ያልሰጠን ስለመሰላቸው ተስማሙ፡፡

ገዥው ሥጋውን እንዲሰጡን ፈቀደ፡፡አስቀድመን ግን መሞቱን እንድናረጋግጥ ጻፈበት፡፡ለወታደሮቹ አለቃ ትዕዛዙን ስንሰጠው ጠጋ ብሎ በጦር ጎኑን ወጋው፡፡ያልተቀላቀለ ውኃና ደም ከጎኑ ሲወጣ የወታደሮቹ አለቃ ጦሩን ጥሎ በምስጋና መጮኽ ጀመረ፡፡በዚያ ቅጽበት ጠፍቶ የነበረው አንድ ዓይኑ እንደተፈወሰ ተመለከትን፡፡መስቀሉ ሥር ተንበርክኮ ‹‹መስማትንስ ድምጽህን ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ›› ብሎ ሲያመሰግን እኔም የወጉትን ያዩታል የሚለውን የመጽሐፉን ቃል እያሰብኩ ነበር፡፡

ከመስቀሉ ስናወርደው እናቱ ከእኛ ጋር አብራ በእቅፏ ተቀበለችው፡፡ እኛ የግንዘቱን ሥርዓት ስናደርስም ራሱን ጭኗ ላይ አሳርፋ ዕንባዋ ሰውነቱ ላይ እየወረደ ያለማቋረጥ የተቸነከሩትን እጆቹ ትስማቸው ነበር፡፡ሥጋውን ያሸንበትን በደም የተነከረ ጨርቅ ከእጄ ስትቀበል ዓይኖቿ ውስጥ በቃላት የማይገለፅ ምስጋና ተመለከትሁ::

ወደ መቃብሩ ከመሄዳችን በፊት መስቀሉ ላይና መስቀሉ ሥር የፈሰሰ ደሙን በመጎናጸፊያዋ አብሳ ያዘችው፡፡

መቃብሩ በጲሊጦስ ማኅተም ሲዘጋ ከዮሐንስ ጋር ቁልቁል መውረድ ጀምሩ በየጥቂት እርምጃዎቿ ዘወር እያለች መቃብሩን ታየው ነበር፡፡ ልቧ በዚያ እንደቀረ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜም ከዚያ እንደማትለይ ያያት ሁሉ በቀላሉ እርግጠኛ ይሆናል፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ‹‹ጌታ በሕይወቱ ገና ሳለ የነገረን ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ የቀረን በሦስተኛው ቀን እነሳለው ያለንን ቃል በእምነትና በተስፋ ጸንተን መጠበቅ ነው፡፡ ለቃሉ የታመነ ነውና፡፡ በዚያ ያሉ አርድእት ሁሉ በስቅለቱና በመከራው ሰቆቃ እንደተዋጡ ትንሣኤውን በተስፋ ሊጠብቁ በቃሉ ፀኑ፡፡

‹‹ እሁድ ማለዳ ››

ዜናው ሰማን፡፡መላእክት ወደ መቃብሩ ለሔዱ ሴቶች ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትሹታላችሁ? እንደተናገረው ተነሥቷል፡፡ ወደ ገሊላም ይቀድማችኋል›› እንዳሏቸው አበሰሩን፡፡

መግደላዊት ማርያም እንዳየችው እንዳናገራትም ተረከችልን፡፡ ኬፋና ዮሐንስም መግነዙንና መጠምጠሚያውን ከመቃብሩ ይዘው መጡ፡፡

ወደ ገሊላ ስንሔድ ዓርብ በሀዘን የተቃጠሉ ዓይኖቻችን ዛሬ በትንሣኤው ደስታ ያነቡ ነበር፡፡

በዝግ ቤቶቻችን ሳለን‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› የሚለውን የእረኛችንን ድምጽ ዳግመኛ መስማት በዚያ ለነበርን ሁሉ ከአእምሮ ባለይ ነበር፡፡

እንዲህ ያለ ትኅትና እንደምን ያለ ትኅትና ነው፡፡

እንዲህ ያለ ትዕግሥት እንደምን ያለ ትዕግሥት ነው፡፡

እንዲህ ያለስ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፡፡ሰውን እስከሞት መውደድህ ከማለት በቀር ሌላ ልንለው የምንችል ነገር አልነበረንም፡፡

ጌታ በተደጋጋሚ ለእኛ በታየባቸው አርባ እለታት ያውደኝ የነበረ ያ የማውቀው መዓዛ በዕለተ ዓርብ ኒቆዲሞስ ሲቀርበኝ ለምን እንዳወደኝ አሁን ተገለጠለኝ፡፡ እስከሞቱ ተከትሎታል ቅዱስ ሥጋውንም ገንዞ ለመቅበር ተመርጧል፡፡ የቅድስናው መዓዛም በእርሱ ላይ የመቅረቱ ምሥጢር ያ ነበር፡፡ ተሰብስበን በአንድነት በዳዊት ቃል አመሰገንን "በምሽት የለቅሶ ዋይታ ከበበን ሲነጋ ደግሞ ፍስሐ፤ ክፉን ባየንበት ሕማምንም በተቀበልንበት ዘመን ፋንታ ደስታ በዛልን፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን ከሠራ ከእርሱ ነውና"፡፡

 

ከነገድን ከቋንቋ ከሕዝብም ለአባቱ መንግሥት የተባገባን እንሆን ዘንድ በደሙ የዋጀን የፍጥረታት ሁሉ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባው አሜን !





ሚያዝያ 2007

ዘመነ ሉቃስ

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 



Read more...

ስለጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ክፍል ስምንት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በተለያዩ አህጉር ተበትናችሁ በቃሉ ለመኖር ለምትጋደሉ የመንፈስ ልጆቼ የተላከ ህሊናን ሁሉ የሚያልፍ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በሚል ቃለ ብሥራት ሰላምታችንን እያስቀደምንና በትንሣኤው ትንሣኤያችንን እያወጅን ሰነበትን፡፡ “በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፈንታ ደስ ይለናል፡፡” እንዳለ ነቢዩ ዳዊት ፍርድህን ከሰማንበት ቃልህ፤ ምህረትህን ፣ ይቅርታህን ፤በሞት አዋጆች ፈንታ ትንሣኤና ሕይወትን፤ከባርነት ተላቀን ነፃነትን በመቀዳጀታችን የመከራውን ዘመን አስረስተህ ደስታን ሞላኸን፡፡ ከዛሬ ፪ሺ ዓመት ገደማ የበዛልን ሥጦታህ ከአበው ወደ ውሉድ እየተላለፈ ደስታው ሳይፈዝ ስሜቱ ሳይደበዝዝ “ግበሩ በዓለ በትፍስህት” እንዲል ዛሬም እንደያኔው አከበርነው፡፡ ሰውነታችን በፆም እንዳከበረችህ በመብልም አመሰገነችህ፡፡ በድካማችን፣በትካዜያችን፣በረሃብና በጥማችን፣ በሀዘንና በዕንባችን ወራትም ትዝታችን አንተ ነበርህ፤ በደስታና በሐሤት በመብልና በመጠጥ ወራትም የአንደበታችን ቅኔ የዝማሬያችን ጉልበት አንተው ነህ፡፡

በምሴት ይደምፅ ብካይ ወበጽባህ ፍስሐ” እንዳለ ክቡር ዳዊት በጨለማ ኦሪት፣ በጨለማ ኃጢአት በጨለማ ሞትና ሲዖል በተያዝንበት ወራት አለቀስን፤ የወንጌል ብርሃን፣ የትንሣኤ ብርሃን፣ የጽድቅ ፀሐይ በወጣበት ዘመን ሐሤት እናደርጋለን፡፡ የፊትህን ብርሃን አይተናልና ቀኑን ሁሉ ደስ ይለናል፡፡ ይኸውም በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያገኘነው ዘላለማዊ ይቅርታህ ነው፡፡

ከላይ ያልነውን ሁሉ ያልነው ስለ ዐብይ ፆም ሰንበታትና ስለ ጌታችን ስቅለት ትንሽ ጽፈን ስለነበር ምነው ትንሣኤውስ? ላለመባል ነው፡፡ ትንሣኤ ካልታወጀ ካልተሰበከ ክርስትና ተብሎ ነገር የለምና፡፡ ትንሥኤውንም የማያምንና የማይሠብክ ሰውም ከመላእክት አንድነት ሊጨመር ከነቢያትና ከሐዋርያት ከጻድቃንና ከሰማዕታት ኅብረትም አንድ ሊሆን አይቻለውም፡፡ የኒህ ሁሉ መከራቸው በትንሣኤው ማመናቸው ክብራቸው ትንሣኤውን መመስከራቸው ነውና፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡፡ ሉቃ 241-8 1ቆሮ 151-ፍፃሜ

ዐብይ ፆም በነገሠባቸው ሁለት ወራት ስለጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት በተከታታይ እናቀርበው የነበረውን ትምህርታዊ ጹሑፍ በይክረም አቆይተነው ነበር፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ቀጥለን እንጽፋለን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ” ይላል፡፡ ክብር ሁለት ወገን ነው፡፡ አንዱ የባህርይ ሲሆን ሌላኛው የጸጋ ክብር ነው፡፡ ሮሜ 137

.የባህርይ ክብር የጌታ እግዚአብሔር የብቻው ነው፡፡ ማንም ማን በዚህ ሊመሰል፣ሊጠራ ሊታመንና ሊመለክ አይችልም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሿሚ የሌለበት ንጉሥ፤ አክባሪ የማይሻ ክብሩ ነው፡፡ ሌላው ፍጡር ሁሉ ቢነግሥ ቢከብር ወደው ፈቅደው ወይም ተገደው ተዋርዶ ባገኛቸው ላይ ነው፡፡ ሕዝብ ከሌለ ንጉሥ ተገዢ ሳይኖርም ገዢ አይኖርም፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ግን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ ንጉሥ ነው፡፡ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም” እንዲል ክቡር ዳዊት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው“ ከዓለም አስቀድሞ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር በመንግሥቱ በሦስትነቱ በአምላክነቱ ነበር” በማለት ገልጾታል፡፡

በዚህ ክብር ሊጠራ ሊመሰገን የሚችል አልነበረም አይኖርምም፡፡ በነቢዩ ኢሳይያስም እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም በማለት አስጠንቅቋል፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለፈጣሪ በሚገባና በሚቀርብ ክብር ምስጋና ማክበር ተገቢ ነውን? መልሱ “ይደልዋ ” ወይም “ይገባወል” ነው!

- ዮሐ 114-18….አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን…መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው ” በዚህ ቃል የእርሱ ክብር ከአባቱ ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ፍፁም አንድ አንደሆነ ተረዳን፡፡ ለፍጡር እንዲህ ይባል ዘንድ ከቶም አይቻልም፡፡

- ማቴ 1627- የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና…..የሚለውም ከላይ ያለውን የሚያጠናክር ነው፡፡

- የፈጣሪ ምስጋና ለፍጡር አንደማይሠጥ የክርስትና ጽኑዕ ሕግ ነው፡፡ በራዕየ ዮሐንስ ም 56-14 ያለው ሰማያዊ የቅዳሴ ሥርዓት ስንመለከት መንበሩን የሚሸከሙ ኪሩቤል ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ሱራፌል እልፍ አእላፋት መላእክትም በተባርዮ(እየተቀባበሉ) “…በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን!አሜን!” እያሉ ሲዘምሩ ታይተዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጡር ቢሆን በሰማያዊያን መላእክት አፍ ይህን ምስጋና ባልተቀበለም ነበር፡፡ “በጉ” የሚለው የሚወክለው እርሱን ነውና፡፡ ራሱ ጌታችን በተናገረው “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ባንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አክብረኝ” ማለቱ በቅድምና በክብር መኖሩን ያሳያል፡፡ ፍጥረት ያልነበረበት ጊዜ እንደነበርም እናውቃለንና፤ከፈጣሪ በቀር ቅደመ ፍጥረት በክብር ሊኖር የሚችል ማን ሊኖር ይችላል? ዮሐ 175

- የባህርይ ክብር ወይም አንድን ነገር የባህርይ ነው ስንል ከማንም በሥጦታ ያልተቀበልው ፍቅር ሲሆን የሚጨመርለት ከፈቃድ ሲወጣ የሚቀነስበት ያይደለ ሰጭም ሆነ ነሺ የሌለበት ማለት ነው፡፡ ፍጡራን ሁሉን የተቀበሉ ከፈጣሪ ልግስና ነው፡፡ በድካም በጥረት በዋጋ ስላላገኙት “በጸጋ(በስጦታ)” ተብሎ ይገለፃል፡፡ ከፈጣሪ የተቀበልናቸው ሥጦታዎች ሁሉ በዋጋ የማይተመኑም በመሆናቸው በጸጋ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንድም ጠይቀን ለምነን ያገኘናቸው ባለመሆናቸው ከልዑሉ ልግስና የተነሣ በጸጋ ያገኘናቸው እንደሆኑ እናምናለን፡፡

ለፍጡራን የተሠጡ ሁሉ በመታዘዝ ይጨመርላቸዋል ከፈቃድ ሲወጡ ይገፋፉታል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሰው በመሆኑ ቅድመ ዓለም ከነበረው ክብር የተቀነሰ ወይም የተጨመረ ነገር የለም፡፡ በሰዎች ዘንድ ብዙ ወርደትን መቀበሉም ፈቃዱን እንጂ በባህርዩ የጎደለበት ነገር ኖሮ አይደለም፡፡

ከትንሣኤ በኋላም የኤማሁስ መንገደኞችን ሲወቅስ “ክርስቶስ መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? ነው ያላቸው፡፡አዲስ ክብር አልተቀበለም የትህትናን ሥራ ሠርቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ገባ እንጂ፡፡ ይህም ሲባል አጥቶት(ተወስዶበት) ነበር መልሶ አገኘው ማለት አይደለም፡፡ በፈቃዱ ራሱን ዝቅ ማድረጉን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ራሱን ዝቅ ማድረጉ የፈቃድ እንጂ የባህርይ አይደለምና፡፡

በተጨማሪ እኒህን ጥቅሶቸወ ተመልክተው ያገናዘቡ፡፡

ማቴ 2531 የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፡፡

ዮሐ517-18፤ ዮሐ1030-37፤ ዮሐ148-11 1ጴጥ 4112ጴጥ 318

- የክብር ባለቤት እንደመሆኑም በአፈ መላእክት ወሰብዕ በሰማይም ሆነ በምድር ከምድርም በታች ያለ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግነዋል ለአምላክነቱም እንደሚገባ ይሰግድለታል፡፡

- ማቴ211- የጥበብ ሰዎች በቤተልሔም በእናቱ እቅፍ ሲያገኙት እጅ መንሻ በማቅረብ ሰግደዋል፡፡

- ዮሐ91-ፍፃሜ፡- ባለው ውብ ታሪክ ላይ ጌታ ዓይኑ ይበራለትን ሰው አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህ? ሲለው አምን ዘንድ እርሱ ማነው? በማለት መልሶ ጠይቆታል፡፡ ጌታም አይተኸዋል የሚያነጋግርህም እርሱ ነው ባለው ጊዜ አምናለሁ ጌታ ሆይ በማለት ሰግዶለታል፡፡

- ማቴ1433- በባህር ላይ እየተራመደ ሔዶ ወደ ታንኳዋ በገባ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ሰግደውለታል፡፡

- ብዙ ዓሣ ባጠመደ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ፤ ደሟ በቆመ ጊዜ ሴቲቱ፤ ልጁ የሞተችበት ኢያኢሮስም ለጌታችን ሰግደውለታል፡፡ ሉቃ 58፤ማር 533፤ ማር 523

- በትንሣኤው ጊዜ የገሊላ ሴቶችና ደቀመዛሙርቱ ሰግደውታል፡፡ ማቴ 289 እና 17

- ራዕ 511-14፡ አየሁም በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎችም ዙርያ የበዙ መላእክትን ድምጽ ሰማሁ ቁጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፡፡ በታለቅ ድምጽም የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋና በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ፡፡በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባህርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ፡፡በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ አራቱም እንስሶች አሜን አሉ፤ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ፡፡

በዚህ ጥቅስ ላይ እንደተመለከተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ(የእግዚአብሔር በግ) በፍጡራን ሁሉ አንደበት ተመስግኗል፡፡ ሦስት ነገሮችንም እንመለከታለን፡፡

. ምስጋናና ክብር ይገባዋል የተባለው ከዘላለም እስከ ዘላለም ነው፡፡ መነሻና መድረሻ ጥንትና ፍፃሜ የሌለው ከዘላለም እስከ ዘላለም በምስጋና በክብር ተፈርቶ የኖረ ከርሱ በቀር የለምና፡፡

. ምስጋናና ክብር የቀረበለት ከባህርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ተካክሎ ነው፡፡ ከፈጣሪ ጋር ተካክሎ(ተጫፍሮ) በአንድ ምስጋናና ክብር ሊቀርብለት የሚችል ፍጡር ደግሞ ሊኖር አይችልም፡፡

. የመከራ የስደት የረሃብ የጥም የሞት የእስራት ፍርሃት ስጋት የሌለባቸው፤እበላ እጠግብ እሾም እሸለም ብለው የማያጎበድዱ፤የልዑሉን ፈቃድ ብቻ የሚፈፅሙ ኪሩቤል ሱራፌልና አጠቃላይ መላእክት በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለበጉም መስገዳቸው አምላክነቱን ቢያውቁ አንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ፊልጵ 25-11 “…እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ…(እስከ ቁጥር 11 ይፃፍ)



የመንፈሳዊው ዓለም ነዋሪዎች መላእክት ተፈጥሯቸው ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ለመራባት፣በመድከም ለመዘንጋት፣ ለሀብት መጓጓት፣ ለመሞት ወዘተ…ተላልፎ ያልጠሠጠ፤ታናሹን ማዋረድ ለታለቁ ማጎብደድ የሌለባቸው ለአንዱና በጌትነቱ ብቸኛ ለሆነው አምላክ በፍፁም ኃይላቸውና በፍፀም አሳባቸው የሚገዙ የሚያገለግሉም ደገኛ ፍጥረት ናቸው፡፡

መላእክቱ ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ” መዝ 102(03)20፤“መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዩቹን የእሳት ነበልባል” መዝ 9011፤“አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ” ትን.ዳን 622 “በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ…መልአክን በፊትህ እሰዳለሁ…መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና“ ዘጸ 2320 ላይ የተጠቀሱ ሀሳቦች የመላእክት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያመላክታሉ፡፡ እርሱም ፈቃዱን ይፈፅም ዘንድ ለመዓትም ሆነ ለምህረት ይልካቸዋል፡፡ ስሙን ተሸክመው ስለሚሄዱ ባለሙሉ ሥልጣን ናቸው፡፡ ሉቃ 119 የጌታን ፈቃድ ይፈፅማሉ እንጂ የረሳቸው ፈቃድ የላቸውም፡፡ለሌላም አይገዙም፡፡ ዘፀ 2321

ከላይ ባየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ አሳቦች የእግዚአብሔር መላእክት የተባሉት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልእክተኞችና አገልጋዩች እንደሆኑም ተመዝግቧል፡፡

- ማር 113-…መላእክቱም አገለገሉት” ፤መላእክት አላለም መላእክቱ እንጂ፡፡

- ማቴ 1341-“የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፡፡”

- ማቴ2430-31- “…የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፡፡

መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፡፡

አንዳንዶች በራዕይ 127 ላይ የተመዘገበውን በመያዝ ሚካኤልና መላአክቱ ሰለሚል ከዚህ የተለየ ትርጉም አይሠጠውም ይላሉ፡፡ምክንያቱም ሚካኤልና መላእክቱ ማለቱ ቅዱስ ሚካኤልን የመላእክት ጌታ(የአምላክ) አያደርገውምና፡፡

በዚህ ምንባብ ሚካኤልና መላእክቱ የሚለው ቃል ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ መሆኑን ለማመልከት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ዳን 211 ከላይ የተጠቀሱትን ሁለቱን ሀሳቦች ዓይነተኛ በሆነ መንገድ የሚያስታርቃቸውና ልዩነታቸውን የሚያሳየን ከዚህ የሚከተለው ምንባብ ነው፡፡

- ዕብ 11-ፍፃሜ፡- ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመላእክት በኩል ያለውን ልዩነት ባብራራበት መልእክቱ ከመላእክትስ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ደግሞም እኔ አባት እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ያለው ከቶ ለማን ነው? ደግሞም በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ፡- የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል፡፡

የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም” ሲል ቅዱስ ሚካኤልንም ጨምሮ መሆኑ የተረዳ ነገር ነው፡፡ በኲር፣ የሰው ልጅ፣ በግ ወዘተ…ተብሎ የተጠራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና የተገባው በእግዚአብሔር ዙፋን እስኪቀመጥ የከበረ፣ መላእክት የሰገዱለትና ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኑት ፍፁም የባህርይ አምላክ ቢሆን አይደለምን? በዚህም የመላእክት ጌታ መሆኑን አወቅን፡፡

- ራዕይ 226-7- ላይ “…የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ፡፡ “የሚለውን በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር አስራ ስድስት ከተፃፋው ጋር ሲነፃፀር ኢየሱስ ክርስቶስ የመላእክት አምላክ ጌታ ፈጣሪ እንርሱም ታዛዦቹ መልእክተኞቹ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ቃሉ እንዲህ ይላል “እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንደ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ፡፡”

ይቆየን!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Read more...

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ