እስረኞቹ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!
በተኛበት የዋሻ እስር ቤት ቅዝቃዜ ሰውነቱ ደንዝዟል ለእርሱ ብቻ በሚሰማው ቃል ግን መንፈሱ ግሏል፡፡ አካሉ በደረሰበት እንግልት ደቋል ልቡ ግን እንደ ዓለት ፀንቷል፡፡ የመንፈስ ልጆቹ ዓይን ውስጥ ያየው አንተ ከሌለህ ምን እንሆናለን? የሚለው ጭንቀት የማያንቀላፋ እረኛ የራሳቸውን ፀጉር እንኳ ቆጥሮ የሚያውቅ ጠባቂ እንዳላቸው ካለመረዳት የመጣ እንደሆነ በመረዳቱ የፀናውን እውነት እንደሚገባው አልገለጥኩላቸው ይሆን? ሲል ላፍታ አሰበ፡፡ ከተቀመጠበት በውኃ የላቆጠ የእስር ቤት ወለል ላይ ተነስቶ የእስር ቤቱን ዘብ ለልጆቹ መልዕክት የሚጽፍበት ብዕርና ክርታስ እንዲሰጠው በትኁት ድምጽ ለመነው፡፡ በጭካኔ የደደረው የሮማ ወታደር ልብ በማያውቀው ምክንያት በእስረኛው ላይ መጨከን ተሳነው፡፡ ትንሽ እልፍ ብሎ ከተቀመጠው ጠረጴዛ ላይ ብዕርና ክርታሱን እንዲሁም ቁራሽ ዳቦ አቀበለው፡፡ ኅብስቱን እንደ ተቀበለ እጆቹ እየተንቀጠቀጡ እንባ ባቀረሩ ዓይኖቹ ዘቡን ተመለከተው፡፡ ዘቡ ምን የሚያስከፋ ነገር እንዳደረገ በመደናገር ትኩር ብሎ እስረኛውን ሲያጠናው በዕድሜና በእንግልት ከደከመ ልሳን የሚያስደንቅ ጥንካሬ ያለው ቃል መፍለቅ ጀመረ፡፡
እኛ አስራ ሁለታችን፣ እናቱና ከገሊላ ጀምሮ የተከተሉት ሴቶች አብረን አጠገቡ ጉብታው ላይ ተቀምጠናል ሕዝቡ ግን ታቹን ሜዳውን ሞልቶታል፤ በግምት የአምስት ገበያ ሕዝብ ይሆናል፡፡ ከፊልጶስና ከእንድርያስ ጋር ጥቂት ቃላት ከተነጋገሩ በኋላ “ይበቃል” ሲላቸውና እርስ በርስ ግራ በመጋባት ሲተያዩ ተመለከትኳቸው፡፡ ወዲያው ጌታችን ፊልጶስ አጠገቡ በዕንቅብ ያስቀመጠውን አምስት ኅብስትና ሁለት ዓሣ ይዞ አሻቅቦ ወደ ሰማይ ዐየና ባረከ፤ ቆርሶም ለሁላችን ሰጠን፤ እኛም ለሌላው እንዲሁ፡፡ የሆነው ሁሉ ልንገነዘበው ከምንችለው በላይ ስለ ሆነብን የጎረስነውን እንኳ መዋጥ አቅቶን ሁላችን ዓይን ዓይኑን በማየት ደንዝዘን ቆምን፡፡ ሕዝቡ በታላቅ ደስታና መደነቅ ተይዞ ከበረከቱ ይሳተፋል፡፡ በዚያ ጫጫታ መካከል “ከሰማይ የወረደ እውነተኛ የሕይወት ኅብስት እኔ ነኝ፤ የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ ግን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋገረ እንጂ ሞትን አያይም” ብሎ በመንፈሱ ቃተተ፡፡ የሚነግረን ቃል ሕይወትና መንፈስ ስለነበር እንዳልገባን ተረድቶናል፡፡ ቃሉን ለመረዳት በራሱ ከላይ ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ለካስ ለዚያ ኖሯል በሌላ ጊዜ “ብዙ የምነግራችሁ ነገር ነበረኝ ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን ሁሉን ያስታውቃችኋል” ያለን፡፡
ተላልፎ በተሰጠባት በዚያች ሌሊትም በመካከላችን ቆሞ ኅብስቱን አነስቶ ባረከ “እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው ሁላችሁ ከእርሱ ብሉ፣ ደግሞም ወይኑን አንስቶ አመሰገነ ሁላችሁ ከዚህ ጠጡ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ይህን በምታደርጉ ጊዜም ሞቴንና ትንሣኤዬን ታስባላችሁ” አለን፡፡ አሁንም አንተ ኅብስቱን ስትሠጠኝ ከእርሱ ጋር የነበረኝ ጊዜ ትዝ ስላለኝ ነው እንጂ ያንተ በጎነት እንከን ኖሮበት ስላይደለ ቅር አትሰኝ አለው እስረኛው፡፡ የእስረኞቹ ዘብ በሰማው ተደንቆ “እንዲህ በእያንዳንዷ የሀሳብ ልውውጥና ድርጊት ልታስቡት፣ በፍቅሩ ልትቃጠሉና በናፍቆቱ ልትንገበገቡ የቻላችሁ ምን ዓይነት ጌታ ቢሆን ነው? በእያንዳንዱ የኑሮ ሂደት እርሱን እያሰባችሁ በሲቃ መሞላትስ ሕመምና ድካም አይሆንባችሁም? ሕይወታችሁንስ በትካዜ የተሞላ አያደርገውም?” ሲል በመደነቅ እስረኛውን ጠየቀው፡፡ ይህን ሁሉ ለማብራራት ጊዜ ያጥርብኛል፡፡ ይህን ለመረዳት ከእርሱ ጋር ሰው ዓየር ስቦ የሚያስወጣበትን ያህል ቅፅበት ቢኖርህ እመኝ ነበር፡፡ ምሥጢሩ ግን እርሱን በማወቅ፤ ሕይወትና ደስታ የሚለውንም ሐሳብ በምትተረጉምበት መንገድ ይፈታል፡፡ ስሜት ከቃላት በላይ ነው፡፡ ስሜትን መኖር እንጂ ለሌሎች ማጋራት እጅግ ከባድ ነው፤ በውስጡ ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ለማንኛውም አንተ ይቺን የመጨረሻ ኑዛዜዬን ለልጆቼ ልታደርስልኝ ፈቃድህ ከሆነና እኛ የምንኖረውን ለመኖር ድፍረቱ ካለህ እኛ የቀመስነውን መቅመስ ትችላለህ፡፡ ስለ እኛ ግን በአጭሩ ለማስረዳት በክርስቶስ ወንድማችን የሆነ ጳውሎስ የጻፈውን ላሰማህ፡፡ እንዲህ ይላል “ ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም፣ በንጽህና፣ በእውቀት፣ በትዕግስት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ ግብዝነት በሌለው ፍቅር፣ በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኃይል፣ ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ፣ በክብርና በውርደት፣ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፡፡ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወት ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እንደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው ” ፡፡ በሌላ ሥፍራም “ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፡፡ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡ የኢየሱስም ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሳ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን፡፡ . . . ስለዚህም አንታክትም! ነገር ግን የውጪው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፡፡ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው” ይላል፡፡ ወንድሜ ሆይ አሁን ፍቀድልኝና ኑዛዜዬን ልጻፍ ከዚያ ፈቃድህ ከሆነ ብርሃንን ታያለህ ብሎ እስረኛው ወደ ሥፍራው ተመለሰ፡፡ የእስረኞቹ ዘብ ፈዞ እየተመለከተ እስረኛው የተቀበለውን ኅብስት በዕድሜ ለጋና ቁጡ የሆነ ሁሉን ለሚያመናጭቅ በነፍስ መግደል ለታሠረ ሌላ እስረኛ ሠጠው፡፡ በለዘበ አንደበትም ገና ብዙ ሥራ ይጠብቅሀል፤ አትሞትም፡፡ ከዚህ ስትወጣ ግን የእግዚአብሔርን ቸርነትና እኔም የነገርኩህን አትርሳ፡፡
፪
በጭቃ የላቆጠ እጁን ልብሱ ላይና እርስ በእርሱ በማሻሸት ካላቀቀ በኋላ ዓይኖቹን በዋሻው የላይኛው ክፍል ላይ ሰክቶ በመንፈሱ ቃተተ፡፡ “የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፤ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት መጻተኞች ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ! እውነትን ስላወቃችሁና ሕይወት ስለተገለጠላችሁ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ፡፡ ይልቁን የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ በመጠን ኖራችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ ማንም የሚናገር ቢኖን እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን እግዚአብሔር በሚሠጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፡፡ ትጸልዩ ዘንድ በመጠን ኑሩ ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፡፡ በእኔ ከእናንተ መለየት በልባችሁ ብዙ ፍርሃት እንደገባ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አይዞአችሁ በአንዳች አትሸበሩ፡፡ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ በዓለም ያለን ወንድሞቻችሁ ሁሉ ያን መከራ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፡፡ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፡፡ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ፡፡ እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል፡፡ ሞት ወደ ወገኖቻችን ለመሰብሰብ የምንጓዘወው መንገድ እንጂ መለያየት አይደለም፡፡ እኔም በአካል ብለያችሁም በመንፈስ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡ በማንም አትፍረዱ፤ በመከራ ታገሱ፤ መልካም ለማድረግ አትለግሙ፤ ቃሉ በምልዐት ይኑርባችሁ፤ በእምነት ጽኑ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና፤ ሁልጊዜም በዚህ ማደሪያዬ ሳለሁ በማሳሰቤ ላነቃችሁ የሚገባኝ ይመስለኛል፡፡ ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ፡፡ በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ፤ በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ለእርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፡፡ አሜን!” ፡፡
ክርታሱን ጠቅልሎ ለእስረኞቹ ጠባቂ ሲያቀብለው ድካም የተለየው፣ ተስፋ መቁረጥ የሸሸው፣ ሞት የሚፈራው፣ ፍርሃት ያልደፈረው ይህ ሽማግሌ ምን ቢያውቅ ነው? ሲል ተገረመ፡፡ ቅድም የነገረውን አስገራሚ ቃላት የጻፈውን ጳውሎስ የሚባለውን ሰው የት ሊያገኘውና ናዝራውያን ስለሚሞቱለት ስለ እርሱ ማወቅ እንዴት እንደሚችል ሊጠይቀው ሲል ከውጪ ስምዖን ጴጥሮስ የሚባለውን እስረኛ አውጡት ሲል ተሰማ፡፡
የእስረኞቹ አለቃ ውስጥ ከነበሩት ዘቦች ሁለት አስከትሎ ሽማግሌውን እስረኛ የሚሰቀልበትን አሸክመው ይዘውት ሄዱ፡፡ በመንገድ ላይ ሳለም በግራና በቀኝ ላሉት “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም የተመለከትነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፡፡ ሕይወት ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፤ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፡፡ እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንዲመጣላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንዲልክላችሁ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመኑ፡፡ ኃጢአታችሁም ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም፡፡ መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመኑ” እያለ በታላቅ ድምጽ ይጮኽ ነበር፡፡
የመሰቀያው ቦታ ሲደርስ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ “ጌታ ሆይ ይቅርታህን ከጥብርያዶስ ሞገድ ይልቅ ገዝፎ በሰማሁባት ቅጽበት፤ ወጣት ሳለህ በገዛ ፈቃድህ ታጥቀህ ወደ ምትፈልገው ትሄዳለህ በሸመገልህ ጊዜ ግን እጆችህን ትዘረጋለህ የማታውቀው ያስታጥቅሀል ወደ ማትወደውም ይወስድሀል በማለት በምን ዓይነት ሞት እንደማከብርህ የነገርከኝ ቃል እነሆ ደረሰ፡፡ ጌታ ሆይ አንተን ማወቅ የጥበብ ሁሉ ጫፍ ነው፤ አንተን ማመን ክብር ሁሉ የማይተካከለው ማዕረግ ነው፤ ስላንተ መከራን መቀበል ሽልማት ሞትም ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ደካማ ሰውነታችን ስላንተ ከዚህም በላይ እንድንሆን የሚፈለግ ቢሆንና ብንሆን እንኳ የፍቅርህን መጠን ሊገልጽልን አይችልም፡፡ ልንሆን የማንችለውን እንድንሆን ስላስቻልከንና ካንተ ጋር እንነግስ ዘንድ ፈቃድህ ስለሆነ እናመሰግንሃለን!!!”
ጸሎቱን እንደ ጨረሰ መስቀሉ ላይ ሊቸነክሩት ሊያስተኙት ሲሞክሩ የእስረኞቹን ዘብ በዓይኖቹ እየተማጸነ ታገላቸው፡፡ ወታደሮቹ ሲታገሉት የእስረኞቹ ዘብ ላለመሞት ግብግብ እንዳልገጠመ ተረድቶት ወደ ሽማግሌው በመቅረብ በትኅትና ምን እንደሚፈልግ ጠየቀው፡፡ በዕንባ በራሱ ዓይኖቹ የእስረኞቹን ዘብ እየተመለከተ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ “አ..አ…አ…አይሆንም እ…እኔ እ…እ…እንደ ጌ…ጌ…ጌ…ጌታዬ ወደ ላ…ላይ ልሰ…ቀል አ..ይ..ገ..ባ..ኝ..ም፤ ኃ..ጢ…አ…ተ..ኛ… ነ…ኝ ….ቁ..ል..ቁ..ል ስ…ቀ…ሉ..ኝ” ሲል ተማጸነ፡፡ የእስረኞቹ ዘብ ብቻ ሳይሆን ወታደሮቹ ጭምር በሽማግሌው ጥያቄ ግራ ተጋብተው ፈዘዋል፡፡ ሽማግሌው ግን ውትወታውን ስላላቆመ የእስረኞቹ አለቃ ፈቃዱን እንዲፈጽሙለት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ሽማግሌው ወደ ምንጣፉ ለመተኛት እንደሚቸኩል ሰው ተጣድፎ መስቀሉ ላይ ተኛ፡፡ ሲቸነክሩት ትንሽ ካሰማው የጣዕር ድምጽ ውጪ ምንም የተለየ ነገር አልታየበትም፤ ይልቁን በሀሳብ ርቆ የሚቆዝም ይመስል ነበር፡፡
መስቀሉን ካቆሙት በኋላ የእስረኞቹ ዘብ አጠገብ ካለ ቋጥኝ ላይ ዐረፍ ብሎ መጨረሻውን ይጠባበቅ ጀመር፡፡ ሽማግሌው ግን በመስቀሉ ላይ እንኳን ቁልቁል ተሰቅሎ እስከ ሞት ስለተከተለው ጌታው በፍጹም ግለት ይመሰክር ነበር፡፡ ብዙ ቢናገርም ትንፋሹ በደከመበት ሰዓት የተናገራቸው ጥቂት ቃላት ውስጡን ሰርስረው ገቡ፡፡ “አትፍሯቸው! ሥጋን መግደል የሚችሉትን ነፍሳችሁን ግን ምንም ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሯቸው፤ ይልቁንስ ሥጋንና ነፍስን በአንድ አድርጎ ውደ ገሃነም ሊጥል የሚችለውን እርሱን ፍሩት፡፡ በሚታየውም ሆነ በማይታየው ላይ ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት፤ በጊዜም ሆነ ከጊዜ ውጭ የሠለጠነውን እርሱን ፍሩት፤ በሞትና በሲዖል ላይ ሥልጣን ያለውን እርሱን ፍሩት ፡፡ አስቀድማችሁ በቃሉ ለዚህ ዓለም ሳትሞቱ ስለ ቃሉ ትሞቱ ዘንድ አይቻላችሁምና ትጉ” ሲል ሰማው፡፡ የእስረኞቹ ዘብ እርሱ ከተነፈሰ የሽማግሌውን እስትንፋስ የሚነጥቀው ያህል በጭንቅ እየተነፈሰ “እባክህን ስለ ሕይወት ቃል እንደሚገባኝ አውቅ ዘንድ ያ ጳውሎስ የሚባለው ሰው የሚኖርበትን አመልክተኝ” ሲል ተማጸነው፡፡ ሽማግሌውም ፈገግ ብሎ በጭንቅላቱ ወደ አንድ አቅጣጫ አመለከተው፡፡ ወታደሮች አንድን ከትከሻው ጎብደድ ራሱ ገባ ያለ ሰው በሰይፍ ሊቀሉ ከትከሻው ልብሱን እያራቆቱት ተመለከተ፡፡ ያኛው እስረኛ ወደ መገደያው እንደመጣ ሽማግሌውን ትኩር ብሎ ሲመለከተው እንደነበር ያስተታወሰው አሁን ነው፡፡ አንዳች የሚግባቡበት ምሥጢር እንዳለ አስተዋለ፡፡ በመካከል እስረኛው በታላቅ ድምጽ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሃብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? ብሎ ቃሉን ሳይጨርስ የወታደሩ ሰይፍ አንገቱን ከትከሻው ለየው፡፡
የእስረኞቹ ዘብ የሆነውን አይቶ ቁልቁል ወደ ተሰቀለው ሽማግሌ ዘወር ሲል በሚቃትት የደስታ ድምጽ “ስላንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ካሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞትም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን መላዕክትም ቢሆኑ ግዛትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን ኃይላትም ቢሆኑ ከፍታም ቢሆን ዝቅታም ቢሆን ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቻለው” በማለት ያኛው እስረኛ የጀመረውን ሽማግሌው ሲጨርሰው ሰማው፡፡ ቁልቁል የተሰቀለው ሽማግሌ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ሲናገር እና ነፍሱን ሲሰጥ የእስረኞቹ ዘብ በሀዘን እና በቁጭት ሰውነቱ ተወጣጥሮ መዳፉን ሲጨብጥ በቀኝ እጁ መዳፍ ውስጥ የሆነ ነገር እንዳለ ታወቀው፡፡ የሽማግሌው የመጨረሻ ኑዛዜ የተጻፈበት ክርታስ ነበር፡፡
የበጉ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ በረከት ይደርብን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
ቀሲስ ታምራት ውቤ 2011 ዓ.ም