Login
Main menu

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

“ንግር ወኢተአርምም!”

                                                  የሐዋ.ሥራ 18፡9

 

ሰሞኑን እመቤታችን ‘የአዳምን የጎሰቆለ ባሕርይ’ ነው የያዘችው ብሎ ከተናገረ አንድ ወንድማችን ጋር የተደረገ የቃላት ምልልስን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ጉዳዩ አሳስቧቸው አጋሩኝ። ከውይይቱ የተገነዘብሁት ነገር መልስ ይሰጥበት የነበረው የጥያቄውን ዐውድ በተረዳ መንገድ አለመሆኑን ነው። ውይይቱ በአብዛኛው ያተኮረው ስለ ጥንተ አብሶ፣ ስለ መርገም፣ ስለ ጎሰቆለ ባሕርይ እንጂ ይህ ባሕርይ እንዴት ታደሠ? እግዚአብሔር የአዳምን የጎሰቆለ ባሕርይ ለማደስ ወደ ቀደመ ክብሩም ለመመለስ ምን አደረገ? የሚለውን ከነገረ ድኅነት አንጻር አልነበረም።

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው እንዲህ ዓይነት ጠንከር ያሉ ዶግማ ነክ ጉዳዮች ላይ መወያየት ለቤተ ክርስቲያን አዲስ አይደለም። የነበረ ያለና ወደ ፊትም የሚኖር ነው። አሁን ያሉ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ጉዳዩ ላይ አጥጋቢ ምላሽ በማቅረብ ሁሉን ወደ ቦታው መመለስ ይጠበቅባቸዋል። እኔም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ የራሴን ጥያቄና ሀሳብ ከዚህ እንደሚከተለው ለማሳየት እሞክራለሁ።

 

፩. ከብዙኀን እንደ ሰማሁት ‘የባሕርይ መጎስቆልን’ ከኃጠአተኝነትና ከጥንተ አብሶ ጋር ሲያገናኙት ነበር። ይህ አንዱ ጥያቄውን በሚገባ ላለመመለስ የጋረደን ስህተት ነው። ምክንያቱም የባሕርይ መጎስቆል የኃጢአት ውጤት እንጂ ኃጢአት አይደለም። አትናቴዎስ ሐዋርያዊ እንደ ጻፈው እንኳን እመቤታችን ካሣ ከመፈጸሙ በፊት የነበሩ ሕጻናትና እንደ ነቢዩ ኤርምያስና መጥምቁ ዮሐንስ ያሉትም ምንም እንኳ የጎሰቆለውን የአዳም ባሕርይ ቢይዙም ኃጢአት እንዳልሠሩ ይታመናል። ስለዚህ የጎሰቆለ ባሕርይ ይዘናል ማለት የግድ ኃጢአት አለብን ማለት አይደለም። ኃጢአት ፈቃድና ሱታፌ ያለበት ሲሆን የባሕርይ መጎስቆል ግን የአዳም ዘር በመሆናችን የመጣብን ነው። አንድ መረዳት ያለብን ነገር የሰው በደል እንደ መላእክት በደል አይደለም። እያንዳንዳቸው የበደሉ መላእክት በዲያብሎስ የደረሰ የደረሰባቸው ከእርሱ በዘር ስለ ተከፈሉ ሳይሆን በክህደትና በበደል ስለ መሰሉት ሲሆን እኛ ግን ውጤቱን የተቀበልን ከአንዱ ከአዳም ባሕርይ ተካፋዮች ስለሆንን ነው። እመቤታችንንም የአዳምን የጎሰቆለ ባሕርይ ይዛለች ማለት የግድ በደል ተገኝቶባታል ወደሚል አይሰድም። ታዲያ የጎሰቆለ ባሕርይ ምን ማለት ነው? Early Christian Doctrines: by J.N.D. KELLY: Rev. edi. Page 345-346

 

 

፪. የጎሰቆለ ባሕርይ ማለት የግድ ከሞት ጋር ብቻ መያያዝም የለበትም። መራብ፣ መጠማት፣ ድካም፣ መታመም፣ ድንቁርና፣ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ እርጅና፣ ሞትና ወደ ኃጢአት ማዘንበልን የመሳሰሉትን ሁሉ የሚያካትት ነው። ብዙዎች የእመቤታችን በሞት ውስጥ ማለፍ ከባሕርይ መጎስቆል ጋር አይገናኝም ምክንያቱም አዳም ከመበደሉ በፊትም የማይሞት ሆኖ አልተፈጠረምና በማለት ሲከራከሩ ታዝቤአለሁ። አዳም ከመበደሉ በፊት ሞትን ሊያስናግድ የሚችል ባሕርይ ነበረው ማለትና ሞት ሠለጠነበት ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በምሳሌ ለማስረዳት ሁላችንም ወንጀል ከሠራን ልንታሰር በምንችልበት ሁኔታ መኖርና ወንጀል ሠርቶ መታሠር እጅግ የተራራቁ ነገሮች ናቸው። ከበደል በፊት ሞት ሊያስተናግድ (possibility) የሚችል ባሕርይ ሲሆን ከበደል በኋላ ያለው ባሕርዩ ግን ለሞት የሚገዛ ባሕርይ ነው። “. . . የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። 1 ቆሮ 15፡27  ነገር ግን የእመቤታችን ሞት ካሣ ከተፈጸመ በኋላ ስለሆነ ከባሕርይ ጉስቁልና ጋር ሳይሆን (ይህ እንኳን ለእርሷ በጌታችን ቤዛነት ላመኑ ሁሉ አይቀጸልም) በኵረ ትንሣኤ የሆነውን እርሱን ለመምሰል ከምናልፍበት ሂደት ጋር የሚገናኝ ነው። ሰሞኑን አንድ ሊቅ ባጋሩን ጽሑፍ በአዳም በደል የተቀበልናቸው መርገሞችና ውጤቶች ሁሉ በክርስቶስ ሞት ወዲያው ስላልተሻሩና አሁንም እናቶቻችን በምጥ ስለሚወልዱ የወደቀውን የአዳም ባሕርይ ይዘዋል ማለት አይቻልም። ይህ ከሆነ ክርስቶስ ከመርገም ከፍሎ ያስቀረው አለ ያሰኝብናል ላሉት ቅዱስ ጳውሎስ መልስ ሲሰጥ “አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኵራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአልና። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኵራት ነው . . .” ይለናል። 1 ቆሮ 15፡20-23 ስለዚህ ከመርገም ከፍሎ ማስቀረት ሳይሆን ድኅነት ሂደት (process) ስለሆነ ነው።

ሌሎችም በጥር 21 የእመቤታችን ዕረፍት ላይ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፤ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ” የሚለውን ይዘው የእመቤታችን መሞቷ ያስደንቃል የተባለ መጀመሪያውኑ የጎሰቆለ ባሕርይ ስላልያዘች ነው በማለት ሞግተዋል። ነገር ግን እዚያው ላይ “እፎኑ እመ አምላክ በከየት ደንጊጻ፤ ከመ ኵሉ ሰብእ ሞት ሶበ ሐወጻ” የሚለውን እንዴት ያዩታል። በእርግጥ ሊቁ ሊል የፈለገው ሌሎች ሰዎች ሞት መጣ ቢሏቸው መደንገጣቸው ከገቢር ቢነጹ ከነቢብ ስለማይነጹ፤ ከገቢር ከነቢብ ቢነጹ ከሀልዮ ስለማይነጹ ነው። እርሷ ግን ሥርጉት በቅድስና ሆና ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ለማለት እንጂ ከባሕርይ መጎስቆል ጋር የሚገናኝ አይደለም። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ በመነሻዬ የባሕርይ ጉስቁልና ከሞት ጋር ብቻ ለምን ይያያዛል? ያልሁት ሌሎችስ ከበደል በፊት በነበረው የአዳም ባሕርይ ያልነበሩ ነገሮች በእመቤታችን ላይ አልነበሩምን? እርሷ የነበራት ሥጋ የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚደክም፣ የሚፈራ፣ የሚጨነቅ፣ ወዘተ. . . አልነበረምን? “ምክሀ ዘመድነ” የምንል በጎሰቆለ ባሕርያችን ያለ በደል በመገኘቷ ነው። ይህን ባሕርይ አልያዘችም ማለት በቀጥታ ባንናገረውም ‘ኃይል አርያማዊት’ ናት ወደሚሉት በምሥጢር መቅረብ ይመስለኛል። ሌላ አነጋገር ስለሌለው ነው ባሕርይ እያልን የምናነሣው። ምክንያቱም ኃጢአት የአዳምን ባሕርይ ጨርሶ አላጠፋውም፤ አጎሰቆለው (disfigured) አደረገው እንጂ።       

፫. ‘የጎሰቆለ ባሕርይን’ በተመለከተ የተሻለ መረዳት ላይ ለመድረስ አመቺው መንገድ ጉዳዩን ከነገረ ድኅነት አንጻር ማየት ነው። ምክንያቱም ነገረ ማርያም የነገረ ሥጋዌና የነገረ ድኅነት አካል ነውና። በነገረ ድኅነት ደግሞ ልናነሣው የሚገባን የመጀመሪያው ጥያቄ ‘አካላዊ ቃል ሰው ይሆን ዘንድ ለምን ፈቀደ?’ የሚለው ነው። ‘ፈቀደ’ የሚለው ቁልፍ ምሥጢር ያለው ነው። ምን ለመሆን? የማንን ባሕርይ ለመያዝ ነው የፈቀደው? ይህን ጥያቄ ማስቀደም የፈለግሁ እርሱ ለመሆንና ለማድረግ የፈቀደውን እኛ ለመናገር ሲከብደን ስላየሁ ነው። እንደ እውነቱ ሰው ሆነ (በየትኛውም መንገድ) ማለት፤ ተሰደበ፣ ተዘበተበት፣ ተተፋበት፣ ተገረፈ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ፣ ተቀበረ እና የመሳሰሉትን ማለትም እኮ ይከብዳል። ግን ፈቅዶ ስላደረገው ለመናገር አናፍርም፤ አንሳቀቅም። ቅዱስ ጳውሎስ “በወንጌል አላፍርም” ማለቱ እኮ ከላይ ያለውን ሲገልጽ ነው። ሮሜ 1፡16

ስለዚህ እርሱ የጎሰቆለን ባሕርይ ለማደስ ያጣነውን ክብር ለመመለስ እስከ መጣ ድረስ የተዋሐደው የጎሰቆለ ባሕርይን ነው ማለት ለምን ስህተት ይሆናል? የጎሰቆለውን ካልተዋሐደውስ ያደሰው እንዴት ነው? ደሙን ያፈሰሰ ጊዜ ካልን ማዳኑን በዕለተ ዓርብ ብቻ መወሰን ይሆንና ሌላ ጎራ ውስጥ ይከተናል። በመሆኑም ትክክል የሚሆነው ያለ ተዋሕዶ ድኅነት አልተፈጸመም! ድኅነት የጀመረውም ጌታ ደመ ጽጌ ከፍሎ በማኅፀነ ማርያም ባሕርያችንን ሲዋሐድ ነው። በማኅፀን አካላዊ ቃል ባሕርያችንን ባሕርዩ አካላችንን አካሉ ሲያደርግ ‘ጊዜ ተዋሕዶ’ የጎሰቆለ ባሕርያችንን አድሶታል። የሚለብሰውን ሥጋ በመፍጠርና በመዋሐድ መካከል መቀዳደም እንደሌለ እንዲሁ ‘ጊዜ ተዋሕዶ’ በመፍጠር በመዋሐድና እንዲሁም በማዳን መካከል መቀዳደም የለም። በጊዜ ተዋሕዶ ድኅነት ያስፈልገው ጎስቍል የነበረ የአዳምን ሥጋ በተዋሕዶ መድኃኒት አደረገው። አንባቢ ያስተውል ‘ቅድመ ተዋሕዶ’ ጉስቁል የነበረውን ሥጋ ቢዋሐድም ‘በጊዜ ተዋሕዶ’ ከጎስቁልናው አድሶ ያደፈ ጠባዩን ፈውሶ ጸጋውን መልሶለታል። ቀድሞውኑ የተዋሐደው ሊያድሰው፣ ሊያከብረው ነውና። በኪዳን “ዘተውህበ ለሙስና ዘትካት ብእሴ ወሐደስኮ በዘኢይማስን” እንዲል። ለጥፋት የተሰጠ የቀደመ ሰው የአዳም ባሕርዩን ባሕርይህ አካሉን አካልህ አድርገህ ዳግም እንዳይጠፋ አድርገህ አደስከው ሲል። በዚህ ላይ የጎሰቆለውን ከያዘማ የአዳም መርገም አለበት ልንል ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል። ግን እንዲህ አይደለም! ቅዱስ ቄርሎስ እንዳስረዳው አካላዊ ቃል ሥጋን ሲዋሐድ በሥጋ ላይ የነበረ መርገም ወይም ጉስቁልና አልደረሰበትም። ይህም የዛገ ብረትን እሳት ቢዋሐደው እሳቱ ከዝገቱ ጋር ሳይዋሀድ ዝገቱን ከብረቱ ላይ እንደሚያጠፋው ነው በማለት ድንቅ በሆነ ሁኔታ ገልጾታል። ስለዚህ የክርስቶስ አካል ጉስቍል ነው አይባልም፤ የጎሰቆለውን ባሕርይ ተዋሐደ እንጂ።  

ሌሎችም በቅዳሴ ማርያም “ስፍሖ ገብረ ዘእምጥንተ ሥጋሁ ለአዳም” የሚለውን ይዘው ከበደል በፊት በገነት የነበረውን ሥጋ ለማለት ነው ይላሉ። ይህን ካልን ‘የጎሰቆለ ባሕርዩን አደሰው’ የምንል ምኑን ይዘን ነው? ዘእምጥንተ ሥጋሁ ማለት አዲስ ሥጋ ይዞ አልወረደም/አልተገለጠም ማለት እንጂ ያልጎሰቆለ ባሕርዩን ነው የነሣው ለማለት አያስኬድም። እዚያው ላይ “ሶበሰ ኢለብሰ ሥጋ እምኢያድኃነ አላ ውስተ ከርሠ ድንግል ለብሶ ለዘአበሰ” በማለት የለበሰው የበደለውን ቢሆንም ጊዜ ተዋሕዶ ግን አንጽቶታል ማለት ያስኬዳል። የጎሰቆለው የአዳም ባሕርይ በእመቤታችን ነጽቶ (ታድሶ ያላሉበት ምክንያት ግልጽ ነው) ተገኝቷልና ይላል። ነጽቶ የሚለው ምንም ምን በደል ስላልተገኘባት ነው። ታድሶ ቢል የጌታ መምጣት ታዲያ ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄ ያስነሣልና።

በተጨማሪም ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ “ያልነሣውን አላዳነውም” እንዲል ካልነሣው እንዴት አዳነው/አደሰው ብለን እንናገራለን? ጌታችን ይህን ሁሉ ለመሆንና በዚህ ውስጥ ስለ እኛ ፍቅር ሲል ለማለፍ ፈቃዱ ከሆነ ለምን ይህን ሆንህ ለማለት እኛ ማን ነን? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን የትሕትና ሥራ ሲናገር “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፤ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፤ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” እንዳለ፤ ለመሆኑ በዚህ የተጠቀሰው ሁሉ ለእርሱ ባሕርይ የሚስማማ ነበርን? ፊልጵ. 2፡6 ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “ሞተ ዘኢይመውት. . .” ካለ በኋላ ጌታችን የደረሰበትና ለእኛ ሲል የሆነው ከአእምሮው በላይ ሆኖበት “ኦ ትሕትና ዘመጠነዝ ትህትና፤ ኦ ትዕግሥት ዘመጠነዝ ትዕግሥት፤ ኦ ሂሩት ዘመጠነዝ ሂሩት፤ ኦ ፍቅር ዘመጠነዝ ፍቅር አፍቅሮተ ሰብእ፤ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት” ያለው። ይህን ይሆን ዘንድ ከፈቀደ የእኛን ጉስቁል ባሕርይ ነሣ/ተዋሐደ ማለት ምኑ ይከብዳል? ከሆነውና ከደረሰበት የትኛው ይበልጥ ይሆን?

ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው ሰውን ለማዳን ነው ካልንና እመቤታችንን መጀመሪያውኑ የያዘችው የጎሰቆለ ባሕርይ አይደለም ካልን በክርስቶስ የማዳን ሥራ ላይ exceptions/exclusion እያስቀመጥን አይደለምን? መምህሩ ከፍሎ የተወው መርገም እንዳሉ በማዳኑም ከፍሎ የተወው ሰው አለ ልንል ይሆን? ይህማ አንድ ጊዜ ከአንድ የእስልምና ምሁር ጋር በአዳም ድኅነት ላይ ስንነጋገር ‘ውጣ ብሎ ያስወጣው አላህ ግባ ብሎ ቢያስገባው ማን ጠያቂ አለበት’ እንዳሉኝ ሊሆን፤ ድኅነተ ዓለምም ጥበበ እግዚአብሔር የተገለጸበት ምሥጢር ከመሆን ይልቅ ተረት (fairytale) ወደ መሆን ሊወርድ ነው።

ማጠቃለያ፡

ከላይ የገለጽሁትን ሁሉ ጥያቄያዊ ጽሑፍ በቅን ልቡና ተረድቶ የሚጸናውን አጽንቶ የሚቃናውን አቅንቶ ምላሽ ለሚሰጠኝ በፍጹም ደስታ ተቀብዬ ምሥጢሩ እስኪደላደልልኝ ድረስ በውይይቱ እቀጥላለው። በሃይማኖት መሀል ሠፋሪ መሆን አይቻልም። ካወቁ ያወቁትን እውነት መመለስ እንጂ በፍቅርና በሌሎችም ሽፋን ስህተትን ማለፍ ተገቢ አይመስለኝም። አዲስ ስህተትም ሆነ የኖረ ስህተት ካለ ይታረም ዘንድ ግድ ነው። በሰው ዘንድ ያለንን መልካም ስምና ተቀባይነት ላለማጣት የሚደረግ መሀል ሠፋሪነት ግን ውጤቱ መልካም አይሆንም። ጌታችን “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብርን የምትቀባበሉ ከአንዱ ከእግዚአብሔር የሆነውን ክብር የማትፈልጉ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?” ያለ የራሱን ስምና ክብር የሚጠብቅ የእውነት መንገድ አስተማሪ ሊሆን ስለማይችል ነው። ማስታረቅ መሸምገል መልካም መሆኑን ማናችንም አንስተውም። ግን ማስታረቅ እንደ መልከ ጼዴቅ እውነት ፈርዶ መሆን አለበት። ካለበለዚያ እርቅ ብቻውን ለሃይማኖታዊ ጉዳይ መፍትሔ አይሆንም። ዮሐ. 5፡44 

መጠየቅ ሁሉ ተጠራጣሪ ካስባለ፤ ጥያቄ ሁሉም ኑፋቄ ከሆነ ወደ ፊት የሚመጣውን ትውልድ እንዴት ይዘነው ልንሻገር ነው? ጥያቄ ደግሞ ሰው ያልገባውን ለመረዳት ሲመላለስበት የኖረ መንገድ መሆኑ ይታወቃል። ይህ በጌታችንም በሐዋርያትም በሊቃውንትም ዘመን የነበረ ልማድ መሆኑን መካድ አይቻልም። ለምሳሌ ጌታችን ለአይሁድ ስለ እርሱ እንዲረዱ ለማድረግ ነገሩን የጀመረ በጥያቄ ነው። “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው” እንዲል። እነርሱም የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም እንኪያስ ዳዊት፡- ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል? በማለት፤ እነርሱ የቻሉትን ቢመልሱም በጥልቀት እንዲያስቡና ወደ እውነቱ እንዲደርሱ ሊያደርጋቸው በሚያስችል ሁኔታ ውይይቱን ቋጭቶታል። ማቴ 22፡41-46 የማይጠይቅ ትውልድ እንደማፍራት ያለ መካንነት ለእኔ አይታየኝም!

አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ ለተነሣው ጥያቄ መልስ አለኝ የሚል ይመልስ፤ ካልደረስንበትም አልደረስሁበትም ማለት ነውር አይደለም። ስንጠየቅ የማንመልስ ወይም ሲነገረን የማንቀበል ከሆነ ግን ጌታ እንዳለው “ብነግራችሁ አታምኑም ብጠይቅም አትመልሱልኝም . . .” ይሆናል። ሉቃ 22፡68

ከላይ በርዕሱ “ተናገር ዝም አትበል” ያልሁ ቤተ ክርስቲያን አሳድጋኛለች የሚል ሁሉ ስለ ስሙና በሰው ዘንድ ስላለው ተቀባይነት ሳይጨነቅ እውነታውን እንዲናገር ለማሳሰብ ነው። ሰው ምን ያደርስብኛል ብሎ መፍራት በከተማይቱ/በተስፋይቱ ያሉ ብዙዎች እውነትን ባለ ማወቅ እንዲሰናከሉ መፍረድ አይደለምን? “እውነት አርነት ያወጣችኋል” እንደ ተባለ እውነትን ባለ መናገር ሐሰትን ማጽደቅ ወይም እውነትን መቅበር ሁለቱም አንድ ቀን ተወቃሽነትን ማስከተሉ አይቀርም። የሐዋ.ሥራ 18፡9-10፤ ዮሐ 8፡32

ንባብ ብቻ ሳይሆን ትርጓሜ፤ ትርጓሜ ብቻ ሳይሆን ምሥጢር በምትመግብ ቤተ ክርስቲያን ያሳደገን የአባቶቻችን አምላክ ክብር ምስጋና ይግባው፤ አሜን!

በቀሲስ ታምራት ውቤ                 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ