- Published in ትምህርቶች በጽሁፍ
ኒቆዲሞስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ኒቆዲሞስ፡- ጌታችን ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ መምህር ጋር የነበረውን ቆይታ የምናስብበት ሰንበት ነው፡፡
ምስባክ፡- ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመጻ በላዕሌየ
ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለእመሕያው፡፡
ትርጉም፡- ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ
ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፡፡
- ክቡር ዳዊት ከንጉሡ ሳዖል ጋር በነበረው ጠብ የተናገረው ነው፡፡ ምንም እንኳ ሳዖል ቢከፋብኝም ካንዴም ሁለቴ በእጄ ጥለኽው ፈተንኸኝ፡፡ እኔ ግን እንደሆነብኝ ልሁንበት እንዳደረገብኝ ላድርግበት የሚል ክፋትን፣ ቂም፣ በቀልን በልቤ አላገኘኸብኝም፡፡ በአፌም እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም ከማለት በቀር ጠላትህን በእጅህ ጥሎልሃል ከሚሉ ጋር ተባብሬ አልተገኘሁም ሲል ነው፡፡
ዳዊት ምን ያህል የዋህና ኃዳጌ በቀል መሆኑን መጽሐፍ “ዳዊት ከሳዖል ልብስ ዘርፉን በመቁረጡ አዘነ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ የስንት ወንድሙን አንገት በሰይፍ፣ የስንት ወገኑን አንጀት በረሃብ፣ የስንት ባልንጀራውን ተስፋ የተሞላ ሕይወት በመድኃኒት፣ስንቱን ትዳር በነገር ቆርጦ ሲጥል ቅንጣት የማይሠማው ጨካኝ በሞላበት ዓለም እንዲህ ዓይነት ልብ እንደምን ያለ ነው?
ሊገድለው ሠራዊት አስከትሎ የወጣ በተደጋጋሚ ጦር ወርውሮ የሳተ ለመግደል ቁርጥ ህሊና ያለው ጠላት ላይ የማይጨክን ክንድ እንዴት የተባረከ ነው? በዚህ ዓለም ስንቱ በጠላቱ ያይደለ በወዳጁ፣ በባዕድ ያይደለ በዘመዱ፣በመጻተኛ ያይደለ በወገኑ ላይ ግፍ ሠራ፡፡ ዳቦ ሲጠብቅ ድንጋይ፣ ዓሣ ሲለምን እባብ አቀረበለት፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ማዕምረ ኅቡዓት ልብ የሠወረውን ኩላሊት የሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ከኅሊና አስቀድሞ የሚመረምር ከሀሳብ አስቀድሞ የሚፈትን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሰው ከሰው ተሠውሮ እንዲሠራ አይደለም፡፡ጽድቃችን ይሁን ኃጢአታችን፣ነውራችን ይሁን ክብራችን በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ የቦታ ርቀት የጨለማ ጽናት ልዑሉን አይጋርደውም፡፡ ሁሉን ያያል ሁሉን ያውቃል ሁሉን ይመረምራል፡፡ ኪዳን ዘነግህ
የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ” ያለ በግብፅም ምድር ሆነ በከነዓን የእግዚአብሔር ዓይኖች የተገለጡ መሆናቸውን በማወቁ ነው፡፡ በፍትወት ተቃጥላ በኃጢአት ሠክራ የነበረች የጲጥፋራ ሚስት ግን ይህን ማስተዋል የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ዘፍ 39፥7-11
ሰው ኅሊናው በፍትወት ሲሸነፍ በኃጢአት ፍቅር ሲማረክ ጌታ እግዚአብሔር በሁሉ የሚገኝ መሆኑን ለማየት አዕምሮው ይጨልማል፡፡ ቅዱስ አምላኩን በሥራ ለመካድ ደግሞ የሚመርጠው ጨለማን ነው፡፡ ይህም ኅሊናው ከእግዚአብሔር በመለየቱ የወደቀበትን ጨለማ ያሳያል፡፡ ጌታም “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም” በማለት ኃጢአትንና ክፉ ሥራን የሚወዱ ከጨለማ ጋር ያላቸውን ዝምድና አስታውቋል፡፡ ዮሐ3፥20
ህፃናት ጥፋት ሠርተው የሚቀጡ መሆናቸውን ሲያውቁ ከቤተሰብ ይደበቃሉ፡፡ሲደበቁ በዋናነት የሚሠውሩት ከሌላው ሰውነታቸው ይልቅ ፊታቸውን ነው፡፡ በእነርሱ የአስተሳሰብ ደረጃ እነርሱ የማያዩት ሁሉ ሊያያቸው አይችልም፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡
ነቢዩ ዳዊት ግን “ዓይንን የፈጠረ አያይምን ጆሮንስ የፈጠረ አይሰማምን…” በማለት ልዑሉን ይገልፀዋል፡፡ በእኛ አነጋገር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ፡፡ መዝ 93፥7-10 በቅዳሴም “እግዚአብሔር ያያል ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” በማለት ማወጁ ወደ ኅሊናችን እንድንመለስ አይደለምን? ቅዳሴ እግዚእ ቁ.፲፫
ስለ ኒቆዲሞስም “በሌሊት ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም” ማለቱ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ በሌሊት ሲመጣ ሁሉን በሚያውቅ በእርሱ ፊት በተንኮል እንዳልቀረበ ያጠይቃል፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደጌታ የሄደ በተንኰል ሊያጠምደው ወይም እንደ ሌሎቹ ረበናተ አይሁድ በጥያቄ ሊፈትነው አልነበረም፡፡ የእስራኤል መጽናናት በእርግጥ ጊዜው እንደደረሰ ለማወቅ እንጂ፡፡
እንደሌሎችም “ይህ የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? የሚል ቃል በአንደበቴ እናገር ዘንድ አልወደድሁም፡፡ ይልቁን “… እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን በማለት ከመመስከር በቀር፡፡ አመጣጡ መልካም ስለነበር ጌታችን ታላቅ የሆነ ከእግዚአብሔር ልጅነት የሚገኝበትን ምሥጢር ገልፆለታል፡፡ ዮሐ 3
ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ፡- ፫
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደመራን መፍቀሬ ሰብዕ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሥጢር ላይ ቆይታ እናደርጋለን፡፡
ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነበር፡፡ ስለጌታችን በሚያየውና በሚሰማው ነገር ልቡናው ስለተቀሰቀሰ በሌሊት ይመጣ ዘንድ መንፈሱ ግድ አለው፡፡ በቀን ያልመጣው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡
፩. በሌሊት ኅሊና በሚታዩና በሚሰሙ ነገሮች ስለማይታወክ ክት(ይሰሰባል) ይሆናል፡፡ ስለሆነም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በሚኖረው ቆይታ ኅሊናን በሚከፍሉ ነገሮች ላለመረበሽና በሚሠማው ለመጠቀም ሰዓተ ሌሊቱን መርጧል፡፡ አበው ለጸሎትም ቢሉ መጻሕፍት ለመመልከት የሌሊቱን ጊዜ መምረጣቸው ለዚሁ ነው፡፡ አንድም
፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነው፡፡ በዕድሜ ከሚያንሰውና ከማንኛው ረቢ(መምህር) የት እንደተማረ ከማይታወቀው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ቃልን ሊጠይቅ ሲሔድ የሚያዩት ሁሉ፤ይህ ሰው ትምህርት ሳይጠነቅቅ ቀርቶ ኑሯልን ብለው እንዳይተቹት ስሙን(ደረጃውን) ለመጠበቅ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይመስላል፡፡ ለባለስልጣኑም ሆነ ለተራው፤ለባለጠጋውም ሆነ ለድሀው፤ ለትንሹም ለትልቁም መለኮታዊው ጥሪ(ግብዣ) በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቀርቧል መልስ መስጠት የየራሳችን ድርሻ ነው፡፡ ማቴ 22፥1-8
ስንቶችን የሥልጣን ደረጃቸው ወይም አዋቂዎች ተብለው የተሠጣቸው ወንበር ወደ ሕይወት ለመቅረብ ግድግዳ እንደሆነባቸው እናውቃለን፡፡ የተማረ ወይም ባለስልጣን ወይም ታዋቂ ከሆነ በእግዚአብሔር ቤት መገኘት በካህናት እግር ሥር ተቀምጦ መማርን ራስን ከማዋረድ እንደሚቆጥር ግልጽ ነው፡፡
የምድራችን መሪዎችና ታላላቆች በምክረ ካህን ሲኖሩ በአደባባይ በፀሐይ ፊት ለጌታ እግዚአብሔር ሲሰግዱ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይሾምና፣ ይሽር፣ያከብርና ያዋርድ ባለጠጋም ሆነ ነዳይ ያደርግ ዘንድ ሁሉን ቻይ ነውና፡፡ በእግዚአብሔር መታመናችን ከክብር ውርደት ወይም የፖለቲካ ክሰረት የሚያመጣብን አይደለም፡፡
ባለመድኃኒት ራስህን ፈውስ ነውና በቤተክህነቱም ላሉ የሕዝብ አለቆች የሚበጅ የኒቆዲሞስ መንፈስ ነው፡፡ ትምህርት የማያስፈልገው ምክር የማያሻው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ ወንበሩ ታላቅ ቢሆንም ተቀማጩ ሰው መሆኑን ያስብ፡፡
፫. አይሁድ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር(የሚያምን) ቢገኝ ከምኩራባቸው ሊያወጡት ተስማምተው ስለነበር፤ ኒቆዲሞስ በግልጥ ለመምጣት ያልደፈረው አንድም በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ዮሐ 9፡ 22
ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ በሕይወቱ ላይ የታየው ለውጥ በወንጌላቱ ተመስክሯል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳዊያን የዳስ በዓል በሚከበርበት ዕለት ጌታችንን እንዲይዙት የላኳቸው ሎሌዎች በትምህርቱ ከመደነቃቸው የተነሣ የተላኩበትን መፈፀም ተስኗቸው በተመለሱ ወቅት ሲበሳጩ ኒቆዲሞስ “… ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ተከራክሯል፡፡ ዮሐ7፥50-52
ይህም በአይሁድ ሸንጎ ስለጌታችን የተከራከረ የመጀመሪያው ሰው ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ ጌታ በተሰቀለባት ዕለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ሥጋውን ከመስቀል አውርዶ የገነዘ ይህ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚያች ደቀመዛሙርቱ እንኳ አይሁድን ፈርተው በተበተኑባት ዕለት በድፍረት የጌታን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር መምጣቱ እርሱ መሢህ መሆኑን በፍፁም ልቡ አምኖ ለመቀበሉ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዮሐ 19፥38-42
ከአይሁድ ሊቃናት መካከል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመንና በድፍረት ለመጋፈጥ የመጀመሪያ የሆነው ኒቆዲሞስ ከጌታችን ጋር በተነጋገረባት በዚያች ሌሊት “የእስራኤል መምህር ተብሎ መጠራቱ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡
ኒቆዲሞስ የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር በግልፅ ከተነገራቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ደረጃውን ከደቀመዛሙርት መካከል እንደ አንዱ ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔርን በንፁህ ልብ መከተል ምንኛ መልካም እንደሆነ በዚህ እናያለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲነጋገር እንደሳምራዊቷ ሴት ወይም እንደ ስምዖን ፈሪሳዊ ወዘተ… በተለመደ ቃላትና ቀለል በሚል ሀሳብ አልጀመረም ታላቅ በሆነ ምሥጢርና ተሰምቶ በማያውቅ ቃል እንጂ፡፡ ይህም ከእኛ ወዲያ ላሳር ለሚሉ ፈሪሳውያን አላዋቂነታቸውን የገለጠ ነው፡፡
አንድም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፡፡ ነገር ግን የዚህችን ዓለም ጥበብ አይደለም፤የሚሻሩትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን፡፡” እንዲል ከእውቀቱ ብስለት የተነሣ የአይሁድ ሸንጎ አባል የእስራኤል መምህር ለሆነ ለእርሱ ምስጢር መናገርን የተገባ ሆኖ ስላገኘው ነው፡፡ 1ቆሮ 2፡ 6
መድኃኒታችን “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ” በማለት በእግዚአብሔርና በምዕመናን ዘንድ የሚደረገውን የአዲስ ኪዳን ማሠሪያ ውል ነግሮታል፡፡ምሥጢሩም ከአእምሮው በላይ መሆኑ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በሚል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ ምሥጢራት ምስጢር መባለቸው ቅሉ ከሰው አእምሮ በላይ በመሆናቸው እንጂ የተሸሸገ ነገር ኖሯቸው አይደለም፡፡
በምሥጢረ ጥምቀት ሰው በካህኑ እጅ ጸሎት ተደርጎ ሲጠመቅ የሚታይ አገልግሎት ይፈፀማል በቅዱስ ቅባትም(ሜሮን) ይታተማል፡፡ በዚህ ወቅት በሚታይ አገልግሎት(ሥርዓት) የማይታይ ጸጋን እናገኛለን ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅነት ነው፡፡
ከእግዚአብሔር መወለዳችንን በምን እናውቃለን ቢሉ በእምነት ነው፡፡ በሥጋ የወለዱንን በእምነት እንደተቀበልን መንፈሳዊውም ይኸው ነው፡፡ ወላጅ መውለዱን ያውቃል ልጅ መወለዱን ያምናል፡፡
በእናቱ ማኅፀን ያለ ተወልዶ ካልሆነ በቀር የዚህን ዓለም ብርሃን ማየት አይችልም፡፡ወላጆቹን ዘመዶቹን ሁሉ ማወቅ መገናኘት አይሆንለትም፡፡ እኛም በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለድን የእግዚአብሔርን መንግስት ብርሃን ማየት አይቻለንም፡፡እንደ ወላጅ ሥሉስ ቅዱስን እንደ ዘመድ የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑ ቅዱሳንን መገናኘት አይሆንልንም፡፡ መወለድ ወደዚህ ዓለም መግቢያ በር እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ለመንፈሳዊው ዓለም(ለእግዚአብሔር መንግሥት) መግቢያ በር ነው፡፡
ጌታችን ይኽን ምሥጢር በነፋስም ምሳሌ ቢነግረው ሊረዳው ስላልቻለ “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታቸንን አትቀበሉትም፡፡ ስለ ምድራዊው ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” የሚል ተግሣፅ ተነግሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ በአእምሮው ሊገነዘበው ያልቻለን ነገር ለማመን አለመፈለጉን ጌታ አውቆበታል ሃይማኖት ግን ከሥጋዊ ደማዊ አእምሮ እጅግ የራቀና የረቀቀ ምሥጢር ስለሆነ ከእውቀቱ ማነስ የተነሣ ከማመን እንዳይዘገይ የተሠነዘረ ተግሣፅ ነው፡፡
በልዑል እግዚአብሔር ባህርይና በሀልዎቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም በሃይማኖት የሚፈፀሙ ምሥጢራትና ተዐምራቶች ሁሉ ከአእምሮ በላይ ናቸው፡፡ በእኔ የእውቀት ልክ ስላልሆኑ አልቀበልም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ይህን የሚል የራሱን ሁኔታ ጭምር መካድ ውስጥ ይገባልና፡፡ ምክንያቱ የሰው ተፈጥሮና ማንነት በራሱ ከሰው አእምሮ በላይ ነውና፡፡
- ለኒቆዲሞስ የነፋስን ምድራዊ ምሳሌ አቅርቦ ሲያስረዳው ስላልገባው ከነፋስ ይልቅ ረቂቅ የሆነ የመንፈስን ነገር ቢነግረው እንደማያምን አስረግጦለታል፡፡ አንድም
በምድር የሚፈፀመውን የጥምቀት ሥርዓት አምነህ መቀበል ካልቻልክ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊና መንፈሣዊ ልደት አምነህ መቀበል እንዴት ይቻልሃል? ሲለው ነው፡፡ አንድም በአፈ ነቢያት በቃለ መፅሐፍት የተነገረውን በኅቱም ድንግልና የሆነ ምድራዊ ልደቴን ብነግራችሁ ካላመናችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያለመቀዳደም ያለመበላለጥ የሆነ ሰማያዊ ልደቴን ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ሲል ነው፡፡
ለጥቆም “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ ማንም የለም፤እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት የሚነግረው ሁሉ እንደነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በሚል ከባህርይ እውቀት ባልመነጨ ሁኔታ ሳይሆን በባህርዩ የሚያውቀውን በጌትነቱ ያዘጋጀውን መሆኑን ነግሮታል፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ንግግር ሲጀምር “…እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለት ወደ እስራኤል በተለያየ ጊዜ እንደሚላኩ ነቢያት ወይም መምህራን ቆጥሮት ነበርና ለዚያ የተሠጠ መልስ ነው፡፡ እኔ ነቢይ ወይም መምህር ብቻ ያይደለሁ የነቢያት ጌታ የመምህራን እውቀት ነኝ፡፡ እነርሱ በሰሙት ቃል በተገለጠላቸው ራዕይ ይናገራሉ እኔ ግን የሰማያት ምሥጢር ባለቤት እንደመሆኔ በባህርይ እውቀት እነግርሃለው፡፡ አንድም
ከሰማያት(ከልዕልና) በፈቃዱ ሰውን ለማዳን የወረደ፤ኋላም ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞ በሥልጣኑ በክብር ወደ ሰማይ የሚወጣ ከእኔ በቀር የለም ሲለው ነው፡፡ በውሱን አካል ቢገለጥም ምሉዕነቱ እንዳልተለወጠ ያጠይቃል፡፡ ውሱን የሰው አካል ምሉዕ ሆነ፤ምሉዕ(የማይወስነው) መለኮት በሥጋ ተወሰነ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ቦታውን ሳይለቅ ምድር ደርሶ ጨለማን እንደሚገልጥ፤በልቡና ያለም ሀሳብ ከልብ ሳይለይ በቃል በጹሑፍ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥም እንዲሁ ነው፡፡
አያይዞ “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” በማለት ተናገረ፡፡ ኒቆዲሞስ በአጭር ቆይታ የአዲስ ኪዳን መልክ ምን እንደሚመስል ተስሎለታል ሁለቱ ቁልፍ ነገሮች በጥምቀት የእግዚአብሔር መንግስት ዜግነት የሚገኝበትንና፤በጌታችን ሞት የዓለም ድኅነት የሚፈፀም መሆኑን ገለጠለት፡፡
ጌታችን እንደሚሞትና ሞቱም በምን ዓይነት መንገድ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጥ የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡ የሞቱም ዓላማ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መሆኑን ጭምር አስረዳው፡፡
ወገኖቼ እነሆ የክርስትና መልክ፡- በክርስትና ምንጊዜም ማመንን መከራ፣ጥምቀትን ሞት፣ሞትን ትንሣኤ ይከተለዋል፡፡ ይህ ከሌለ መንገዱ ላይ አይደለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀትን ምንነት ሲገልጥ “…ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?... ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡” ብሎታል፡፡ በግልጥ በስሙ የተጠመቅን በሞቱ ልንመስለው ቃልኪዳን ገብተናል፡፡ በሞቱ ያልመሰሉት በትንሣኤው አይመስሉትምና፡፡ሮሜ 6፥1-23፤ቈላ 2፥8-15
በጥምቀት ለኃጢአት እንሞታለን፣አሮጌው ሰውነታችንን እንሰቅላለን፣በሕግ ከሚመጣ እርግማን ነፃ እንወጣለን፡፡ በአንፃሩ በሕይወት እንኖራለን፣አዲሱን ሰው እንለብሳለን፣ከጸጋው በታች እንሆናለን፡፡
ቤተክርስቲያን ለዚያ ነው ወዲያው እንደተጠመቅን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በማቀበል ሞቱን እንድናስብና በሞቱ መተባበራችንን እንድናትም የምታደርገን፡፡ ያልተጠመቀ የጌታን ሥጋውን ደሙን መቀበል እንደማይችል ሁሉ ተጠምቆም የጌታችን ሥጋና ደም ሳይቀበል የሚሄድ ክርስቲያን ሆኗል ልንል አንችልም፡፡ ሊነጣጠሉ አይችሉምና፡፡
ይህንኑ ለማመስጠር ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለጥምቀት ሲነግረው ከቆየ በኋላ አከታትሎም ስለ ስቅለቱ የነገረው፡፡ ለጥምቀታችን የሆነው ማየ ገቦና ለቁርባናችን የሆነ ደሙ የፈሰሰ በመስቀል ላይ በስቅለቱ ጊዜ ነውና፡፡ ከአዳም ጎን ሙሽራው ሔዋን እንደተገኘች ከዳግማዊው አዳም ከክርስቶስም ጎን ሙሽራው ቤተክርስቲያን ተገኘች፡፡ ዮሐ 19፥33-35
ክርስቲያኖች ሆይ በወላጆቻችን ክንድ በዮርዳኖስ ለመጠመቅ ስንቀርብ ተቀብሎን ልጅነትን ሰጥቶናል፡፡ ቀጥሎ የሚጠብቀን የቀራንዮ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ቀራንዮ የሚኬደው ግን በራስ ጽናትና በፍፁም እምነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተጠምቂያለሁ ብቻ ብለን የምንቆመው ለዚህ ነው፡፡ ክርስቶስን በፍፁም ኑሯችን ልንመስለው ግድ ነው፡፡ እኛን መስሎ የተገለጠ እርሱን በመምሰል እንከብር ዘንድ ነውና፡፡
ወገኖች ሆይ የአንድ ሰው በጨለማ ወደ ጌታችን መሔድ ለስንቶች በሕይወት ብርሃን የሚሆን መንገድ እንደገለጠ ተመልከቱ፡፡ የአንድ ሰውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያደርገው የልብ ግንኙነት ለዓለም ጥቅም እንደሚሆን አስተውሉ፡፡
በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት በክህደት፤ጽድቃችንን በኃጢአት፣ንፅሕናችንን በርኵሰት ሳናጎድፍ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሠጠች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይደግፈን! አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!