Login
Main menu

Items filtered by date: Wednesday, 18 March 2015

ሆሣዕና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሆሣዕና፡- በዚህ ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ቀን እናስባለን፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከጌታችን ፱ቱ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ከሌሊት ጀምሮ በታላቅ መንፈሣዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በሌሊቱና በዑደቱ ሥርዓት ላይ ብቻ ከዘጠኝ ያላነሱ ምስባኮች ስለሚደርሱ ሁሉን መተርጐምን ለጊዜው ታግሠን የትኞቹ እንደሆኑ እንድናውቅ ብቻ ማመላከቻ እንሰጣለን፡፡

ምስባክ፡-መዝ፹፥፫፤መዝ፻፲፯፥፳፮፤መዝ፻፳፩፥፩፤መዝ፻፵፯፥፩፤መዝ፻፲፯፥፳፯፤መዝ፱፥፲፩፤መዝ ፰፥፪፤መዝ፵፱፥፩፤መዝ፷፯፥፴፬

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ አራቱም ወንጌላውያን ተባብረው ጽፈውታል፡፡ በማቴ 21፥1-17፤በማር11፥1-10፤ሉቃ19፥29-38፤በዮሐ12፥12-19 በመሆኑም አንዱ ወንጌላዊ የመዘገበውን ብቻ የጽሑፋችን መነሻ ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ወንጌላት መዳሰስን መርጠናል፡፡

ጌታችን ራሱን ለዓለም ገልጦ ማስተማር ከጀመረ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይኽ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚሁም ጊዜ ቤዛነትን ፈጽሟል፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በአህያናበውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈፀም ነው፡፡

ትንቢቱ “ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ትን.ዘካ 9፥9

ምሳሌውም፡- በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመነ ጸብዕ(ጦርነት) መምጣቱን ለማመልከት በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታዩ፤ ዘመነ ሰላም መምጣቱን ለማመልከት ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ለአራተኛ ጊዜ የመጣው በደሙ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በመካከላችን ፍፁም ሰላምን(ዕርቅን) ለማድረግ ነውና ይህንኑ ሲያመለክት ነው፡፡ በመከራዬ፣ደሜን በማፍሰሴ፣በስቅለቴ፣በሞቴ ሰላም የሚሆንላችሁ ጊዜ ቀርቧል ሲለን ነው፡፡

“ፈትታችሁ አምጡልኝ ለጌታ ያስፈልጉታል”

ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ወደምትባል መንደር ሲደርስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ሲልክ የሰጣቸው ትዕዛዝ ነው፡፡ የታሠሩ አህያና የአህያይቱን ግልገል ሲያገኙ የሚያደርጉትንና ለሚጠይቋቸው የሚሠጡት መልስ፡፡

ነባቢት ነፍስ ያለችው ሰውም ሆነ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታት መታሠርን አይወዱም፡፡ምክንያቱም በተፈጥሮ ያገኙትን የመንቀሳቀስ መብት ይፃረራልና ነው፡፡መታሠር ነፃነትን፣ መታሠር ፈቃድን ይጋፋል፡፡ እኒያ እንስሳት የታሠሩበት የራሱ ምክንያት ይኖራል፡፡ እንስሳት እንዳይጠፉ፣ሌባ እንዳይሠርቃቸው ወይም የሚያጠፉት ነገር ሲኖር እንዳይደርሱበት ለማድረግ ይታሠራሉ ወይም በሌላ አነጋገር ነፃነታቸው ይገደባል፡፡

ሰውንም እንደአስፈላጊነቱ ከጥፋት ለመጠበቅ በሕግና በደንቦች ይታሠራል፡፡ አስተዋይ የሆነ በኅሊና ህግ ይጠበቃል፡፡ እኒህን ሁሉ ያልተጠቀመባቸው በቦታ እንዲገደብ ያደረጋል፡፡በሰው ላይ በጫና ሳይሆን በስምምነት የሚወጡ አብዛኛዎቹ ሕጎች ነፃነቱን አይነጥቁትም፡፡ በኅሊናው ሕግ የሚመራ ግን በአፍአ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ከሚኖርበት ሙግት ነፃ ስለሚሆን ፍፁም ሰላም ይኖረዋል፡፡ ከራሱ ከመሰሎቹ፣ከተፈጥሮና ከኒህ ሁሉ ገዢ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ህብረት፣ስምምነት፣ፍቅር፣አንድነት ይኖረዋል፡፡

ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ሲልክ “ ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱን መተርጉማን ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት(ከኃጢአት ማሠርያ) የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሠ ለማጠየቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ተመልከት)

ከእስራታቸው ተፈትተው ለጌታ ያስፈልጉታል እንደተባለ ጌታ ተቀመጠባቸው፡፡

- አዳምና ዘሩ ከሞት እስራት ነፃ ወጥተው የትንሣኤ ጌታ የሆነው የእርሱ ማደርያ ሆኑ፡፡

-አዳምና ዘሩ ሞትን ከሚያስከትል የሕግ እስራት ተለቀው፤ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ላወረደው አምላክ ዙፋን ሆኑ፡፡ በኦሪት የተሠጡን ትዕዛዛት ደገኛ ነበሩ፡፡ በማናቸውም ምክንያት እነዚያን ትዕዛዛት የሚተላለፍ ቢኖር ቅጣቱ በሞት ይፈፀማል፡፡ ይህም ሰውን ከሕጉ መልካምነት ይልቅ የቅጣቱን ክፋት እያሰበ በባርነት መንፈስ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

ሰውም የእግዚአብሔርን አሳብ መረዳት ስላልቻለ ግንኙነታቸውን በፍርሃትና በሕግ ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሰብረው መውጣት የቻሉ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ሕጉን መተላለፍ በድንጋይ መወገርና በእሳት መቃጠልን ሳይሆን ከፍቅሩ መለየትን እንደሚያስከትል አስተማረ፡፡ አሁን ሕጉን የምንጠብቀው የሞት ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን የአባታችንን ፍቅር ላለማጣት ነው፡፡ ሕጎቹ አልተሻሩም ቀድሞም ደገኛ ሕግ ነበሩና፡፡ ጌታችን ያሻሻለው እኛ ለሕግጋቱ ያለንን ግንዛቤ ነው፡፡ ሕጉን የምንፈፅምበትን መንፈስ ነው በውስጣችን ያደሰው፡፡ሕጉ በፍቅር ይጠብቀናል እኛም ሕጉን በፍቅር እንፈፅማለን፡፡ የአዲስ ኪዳን መንፈስ የወንጌል የምስራች ይኸው ነው፡፡ ዮሐ 14፥15፣ዮሐ15፥9-11 ሮሜ 7፥1-20

ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “እግዚአብሔርን ስንወድ ትዕዛዛቱን ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድበዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፡፡ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” 1ዮሐ 5፥2-4

ፈታችሁ አምጡልኝ በማለቱ የእስር ሠንሰለታችን ተቆረጠ፡፡ ሞት በሰው ላይ የሠለጠነው ኃጢአትን ምክንያት አድርጎ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ዓለምን የገዛው ኃጢአትንና ሞትን መውጊያው በማድረግ ነበር፡፡ ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋህዶ ኃጢአትን ባለመስራት ኃጢአትን፤ በሥጋ ሞቶ በመነሣት ሞትን፤በደመሰሰ ጊዜ የዲያብሎስ ግዛት ፈረሰ፡፡ ምክንያት የሚያደርግ ኃጢአትን ነበርና ጌታችን ግን “የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች የለውም” በማለቱ የሰው ልጅ ለባርነት ምክንያት የሆነው የኃጢአት መርዝ እንደተወገዱለት አረጋገጠልን፡፡ ይህን የተናገረ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የሚጠራ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ዮሐ14፥30፤1ቆሮ 15፥54-57

ይህ ብቻ ያይደለ በጸሎት በተመስጦ ከዚህ ዓለም ጭንቅና ፈተና፤በፆምና በተጋድሎ ከፍትወታትና ከእኩያት፤እውነትን በማወቅ ከወግና ከልማድ ትብታብ መፈታትን አደለን፡፡ ጥንትም ሰው የተፈጠረ በገዢነት መንፈስ እንጂ በተገዢነት ሁኔታ አልነበረም፡፡ሰው ሁሉን ይገዛል እርሱ የሚገዛው ግን ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛትም ነፃነት ነው፡፡  ለጌታ እግዚአብሔር ከመገዛት በራቅን ቁጥር ራሳችንን መግዛት አቃተንና ከእንስሳት እንኳ በግብር አንሰን እስክንታይ ተዋረድን፡፡ ሕግጋት ይመሩን ይደግፉን ዘንድ ቢሰጡንም ለመፈፀም አቅም አጣን፡፡ በመሆኑም ሕግጋቱ ኃጢአታችንን እየገለጡ እንደገና ዕዳ ሆኑብን፡፡ ቅ.ጳውሎስ “ነገር ግን በህግ ባይሆን ኃጢአትን ባለወቅሁም ነበር” እንዳለ ሮሜ 7፥9-10

ጌታችን ሰውነታችንን በወደዳትና በተዋሀዳት ጊዜ ከጸጋው ብዛት የተነሣ ከሕግ በላይ አደረግን፡፡ ከጌታችን ጋር ፍፁም ህብረት ያደረጉ ሁሉ ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋው በታች ይሆኑ ዘንድ ተባለላቸው፡፡ በሕግ ቢኖሩም ሕግ እንዳለባቸው አያስቡም በጸጋው ይደነቃሉ እንጂ፡፡

ይህ ሁሉ ነፃ የመሆን የመፈታት ማሳያ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ ነው “በነፃነት እንድንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን” ያለው፡፡ ሮሜ 3፥21-31፤ሮሜ 6፥12-19፤ገላ 5-1

አስተውሉ “ፈትታችሁ ልቀቋቸው” አላለም “ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁም ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ”አለ እንጂ፡፡ ከኃጢአት፣ከዓለም፣ከምኞት፣ከወግና ከልማድ ወዘተ…መፈታትን ወደርሱ ቀርበን ማደርያው ለመሆን ከእርሱ ጋር ለመሆን እንጂ ልንባዝን አይደለም፡፡

ወደ ሕይወታችን የተላኩ ካህናት ከእስራት የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡የሚፈቱን ወደ ጌታችን ለማቅረብ ነው፡፡ ከጌታችን ጋር የምንዋሃደውም ቅዱስ ሥጋውንና ክብሩ ደሙን በመቀበል ነው፡፡ ማንም በራሱ ሥልጣን ከኃጢአት እስራት መፈታት አይችልም፡፡ በራሴ ወደ ጌታ እቀርባለሁ በማለት የድፍረት ቃል መናገርም የተገባ አይደለም፡፡ እነሆ ሂዱ በማለት የሚፈቱንን የመንግስቱን ካህናት ልኳል፡፡ እነርሱም ከኃጢአት የምንፈታበትን ትምህርት ሥርዓት ጸሎትና ሥልጣን ይዘው እንፈታ ዘንድ ይጋብዙናል፡፡ ለምን? ለሚል መልሳቸው ለጌታ ታስፈልጉታላችሁ! ነው፡፡ ማቴ 18፥18፤ዮሐ 20፥23

ሰው ሆይ የተሰጠህን ክብር ተመልከት፡፡ ፍጡር ሳይኖር በፈጣሪነቱ፤ተገዢ ሳይኖር በአምላክነቱ፣ አመስጋኝ ሳይኖር በአኰቴቱቅድመ ዓለም ነግሦ ለሚኖር፤እልፍ አእላፋት ወትልፊት አእላፋት መላእክት፤የሚታየውና  የማይታየው ሁሉ ለሚገዛለት ለእርሱ ታስፈልጉታላችሁ መባላችን እንዴት ያለ ክብር ነው?፡፡ ፈጣሪነቱ በእኛ ታወቀ አንል ከእኛ ይልቅ ብዙ ፍጥረት ተዘርግቷል፤ያለእኛ ተገዢነት ጌትነቱ አይሟላም እንዳንል ሳንፈጠርም በጌትነቱ ኑሯል፤ ታዲያ “ለጌታ ያስፈልጉታል”መባላችን ስለ ምንድር ነው?/ቅዳሴ ዲዮስቆርስ/


 

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ልዑሉ ሲናገር “የእኛ ሕዝብህ መሆን ላንተ አያስፈልግህም ያንተ ጌትነት ለእኛ ያስፈልገናል እንጂ፤የእኛ ልጅነት ላንተ አይጠቅምህም ያንተ አባትነት ለእኛ ይጠቅመናል እንጂ” በማለት ገልፆታል፡፡ አባትነቱ በእኛ ልጅነት አይደነቅም፤ጌትነቱም በእኛ ተገዢነት አይከብርም፡፡ ዛዲያ “ታስፈልጉኛላችሁ” መባሉ ስለምንድር ነው?

እንመርምረው ዘንድ አይቻለንም! መልስ እናገኝለት ዘንድም ቅጥነተ አእምሯችን አይወስነውም! እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለ ርኅራኄስ እንደምን ያለ ርኅራኄ ነው ብለን ከማድነቅ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?/ ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ/

ጌታ ሆይ ልትፈልገን መጥተሃልና፤ታስፈልጉኛለችሁ ብለህም በክብር ጠርተኸናልና፤በአፈ አበው ቀደምት፣በልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት፣ጻድቃን ወሰማዕታት፣አእሩግ ወሕፃናት፤በአኰቴተ መላእክት ወሊቃናት እናመሰግንሃለን፡፡ ምስጋናና ክብር ኃይልና ባለጠግነት ጌትነትም በመታረዱ ለፈለገን ለበጉና ለአባቱ ለመንፈስ ቅዱስም ይገባል መቼም መች ለዘላለሙ አሜን! ራዕይ 4፥6-14

ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ ይመጣል

ለጽዮን ንጉሷ እንዲሚመጣ በአፈ ነቢያት ተነግሯታል፡፡ የሚመጣው ግን እንደነ ሰሎሞን በዝሆን ጥርስ በብርና በወርቅ ባጌጠ፤በሀምራዊ ግምጃ በተሸፈነ ሠረገላ ሳይሆን በአህያና በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ የዋህ ሆኖ ነው፡፡

የዋህ የሚለው ኀዳጌ በቀል መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጌታችን የመጣው አንገተ ደንዳና ወደ ሆነ የነቢያቱንና የካህናቱን ደም ወዳፈሰሰ ሕጉንም በወግና በልማድ  ወደ አፈረሰ ሕዝብ ነው፡፡ መጻሕፍቱን የነቢያቱንም ቃል ያነባሉ ለመቀበል ግን አይፈልጉም፡፡ ምንም እንኳ ሰይፈ በቀል በእጁ ቢሆንና ፍርድ ቢገባቸውም ሰው የመሆኑ ዓላማ ሁሉን ለማዳን እንጂ በአንድ ስንኳ ለመፍረድ ስላልሆነ በየዋህነት ተገለጠ፡፡ የነቢያትን ደም ባፈሰሰ እጃቸው የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ በመስቀል ሰቅለው ጽዋቸውን ቢሞሉም “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለቱ የምህረት እንጂ የበቀል ጊዜ አለመሆኑን አሳያቸው፡፡ የምህረት የይቅርታ ጊዜ አለ፤ከወዳጆቹ ከነቢያት ጀምሮ ላፈሰሱት ደም የበቀል ጊዜ ደግሞ ይኖራል፡፡ ዮሐ 3፥16፤ማቴ21፥33-46፤ማቴ 23፥29-36

“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው”

ሆሣዕና በዕብራውያን ቋንቋ “አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” የሚል ትርጉም አንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ሆሣዕና የሚለው ቃል ሰው ሲደነቅ ወይም ሲደሰት ከሚያወጣው ድምፅ ጋር በማመሳሰል በሌላ ቋንቋ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው እንደማይቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱም ትርጓሜ አይጣላም፡፡

አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው ቢሉ ጉዞው ወደ መስቀል ነበርና እውነተኛ መድኃኒትም እርሱ ነውና የተገባ ምስጋና ነው፡፡

ቃለ አንክሮ ቃለ ትፍስሕት ነው ቢሉም በዚያ የተሰበሰቡ አብዛኞቹ ያደረገውን ተዐምራቶች እያወሱ ይመሰክሩም ስለነበር፡፡ አንድም ከነበረው የአቀባበል ሁኔታ አንድም እንደ ኢትዮጵያ ሊቃውንት ትርጓሜ የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት ይታይ ነበርና አድናቆቱ የተገባ ነው፡፡

ሆሣዕና እያሉ የሚያመስግኑት ሁሉ“የዳዊት ልጅ” እና “ጌታ” ብለው ጠርተውታል፡፡ በዚህም የዳዊት ልጅ በማለታቸው ፍፁም ሰው መሆኑን አንድም“እግዚአብሔር ማለ አይፀፀትም ከወገብህ ከሚወጣ ከዘርህ በዙፋንህ አኖራለሁ” የተባለው ትንቢት መፈፀሙን ያጠይቃል፡፡አይሁድም በገዛ አፋቸው ክርስቶስ ማነው? ብሎ ሲጠይቃቸው የዳዊት ልጅ ነው ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ አሁን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ላለማመን ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ 2ሳሙ7፥12-14፤ማቴ22፥41-46

በ“ጌታ” ስም የሚመጣ ማለት እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሎ የሚመጣ የተባረከ ነው ብለዋል፡፡ አይሁድ “YHWH” የሚለውን በአብዛኛው የሥነ-መለኮት ሊቃውንት “ያህዌ” የሚል ግምት የሚሠጠውን በኮሬብ ለሙሴ የተገለጠ ስመ አምላክ ለመጥራት ሰለማይደፍሩ “Adonai” ወይም “ጌታ” በሚል ቀይረውታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጌታ የሚለው ቅፅል በቀጥታ ለእስራኤል አምላክ የሚነገር በመሆኑ “በጌታ ስም” “የሚመጣ” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ገልፀዋል፡፡ ማቴ 22፥41-46

ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በዕለተ ሆሣዕና ይመሰክሩ የነበሩ መጻሕፍት አንብበው ከሊቃውንት አፍ ተምረው ትንቢት የተረጎሙ ሱባዔ የቆጠሩ አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጭምር ነበሩ፡፡ አይሁድንም ይበልጥ ያስቆጣው ህፃናቱ ያመሰገኑበት መንፈስ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ተዐምር ነውና፡፡

ምንጊዜም ንፁህ ምስጋና ፣ ንፁህ ጸሎት፣ንፁህ መሥዋዕት፣ንፁህ ልቡና፣ ንፁህ አገልግሎት ይበልጡንንፁህ ሕይወት አጋንንትን፣ ክፍዎችን፣ ተንሎለኞችን፣ ተረፈ አይሁድን፣መናፍቃንን፣ አረማውያንን ያስቆጣል፡፡ ይህ እንዲቋረጥ የማያኖሩት እንቅፋት የማይፈፅሙት ድርጊት አይኖርም፡፡ ንጹሐ ባህርይ ከሆነው ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ በንፁህ ህይወት የኖሩ በንፁህ አገልግሎት የፀኑ ሁሉ ተገፍተዋል ተዋርደዋል፤ለሞትም ወደ መታረጃቸው ተነድተዋል፡፡ ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ንፁህ ሁን በዓለም ወደ ኋላ ትቀራለህ ትዋረድማለህ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ግን ትቀድማለህ ትከብርማለህ፡፡ ማቴ 14፥1-4 ዮሐ15፥18-21

ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁሉ ይዘው የተቀበሉት የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ወደ መስቀል የሚወጣ ለድል ነውና፡፡ ይህ ሁሉ የሰው አቀባበልና ምስጋና ጌታችንን ለአመል ከዓላማው አላዘናጋውም፤ ለመጣባት ለዚያች ሰዓት አዘጋጀው እንጂ፡፡ አድናቆት ሊያጅበን ምስጋና ሊነጠፍልን ይችላል፤ዓላማችን ምን መሆኑን ግን ልንረሳ አይገባንም፡፡ ከሰዎች ክብርን ብንቀበል ከእግዚአብሔር ከሆነው ክብር ከተጣልን ምን ይጠቅመናል፡፡ ሊጠቀምብህ የሚፈልግ ያወድስሃል ሊጠቅምህ የቆረጠ ግን ይገሥፅሃል፡፡ ወዳጀህን መምረጥ ያንተ ድርሻ ነው፡፡

የአይሁድ ሊቃናት እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻለችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል“ ይባባሉ ነበር፡፡ ቅንዐት ጥላቻን ይወልዳል ጥላቻ ደግሞ ሞትን፡፡ ጌታችን እንደቃሉ ወደ ትክክለኛዋ ሰዓት ቢመጣም በቁሙ ሲታይ ግን የሆሣዕና ትዕይንት በአይሁድ ሊቃናት ላይ ያሳደረው ቅንዐትና ቁጣ በሞቱ ላይ እንዲቆርጡ በከፍተኛ ሁኔታ አነሣስቷቸዋል፡፡እርሱ ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንደ ሰዓቱ ደርሶአል፡፡እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ብትሞትም ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች”በማለት በሞቱ ይበልጡ ብዙዎችን እንደሚያድንና ወደ ራሱ እንደሚስብ ነግሯቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር መንግስት ከጥንት ጀምሮ የሚጋፏት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን ከመጨመር ልዑለ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከመከተል አላስቆሙትም፡፡ ገና በሃይማኖቱ ጠንክሮ እየቆመ በኅሊና ትንሣኤ ኃጢአትን ድል አድርጎ እየዘመረ ይከተለዋል፡፡ የታመነ መሪ ነውና፡፡“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ መከተል ማለት በግብር መምሰል በአርአያነቱ መጽናት ነው፡፡ በህይወታችን በኑሮአችን ከመሰልነው በሞቱ እንመስለዋለን በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን፡፡ ክርስትና ማለት ቅሉ ይኸው ነውና፡፡ የበዓሉ ጌታ ቸርነቱ ይደረግልን! ማቴ11፥12፤ዮሐ10፥1-18፤ሮሜ 6፥5

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት

ሚያዚያ፣2008 ዓ.ም

 

 

Read more...

ስቅለት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በአብ ስም አምኜ አብን ወላዲ ብዬ በወልድ ስም  አምኜ ወልድን ተወላዲ ብዬ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኜ መንፈስ ቅዱስን ሠራፂ ብዬ ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብል በባህርይ በህልውና በፈቃድ በሥልጣን አንድ አምላክ ብዬ በማመን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ሳያደርጉ እማር አስተምር እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና፡፡

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለት አደረሳችሁ!

አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!

      ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ታላቅ ቃል የተናገረው በመስቀል ላይ በነበረበት ሰዓት ነው፡፡ ምንም እንኳ በነቢዩ በኢሳይያስ እለተ ዓርብን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት " በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም" ያለው፤ የጌታን ትዕግስቱን ሲያጠይቅ፤ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ያለውን ፈቃደኝነት ሲያሳይ እንጂ ለምዕመናን ጥቅም የሚሆን ቃላቶችን አልተናገረም ለማለት አይደለም፡፡

     ጌታ በመስቀል ሆኖ የተናገራቸውን ቃላት በቤተክርስቲያን "ሰባቱ አጽራሐ መስቀል" ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእኒህ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል ደግሞ ቀዳሚው(የመጀመርያው) " አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዚኢየአምሩ ይገብሩ" የሚለው ነው፡፡

ስለምን ጌታ ከሰባቱ አጽራሐ መስቀል በቀዳሚነት ይህን ተናገረ ቢሉ፡-

ሀ. ወደዚህ ዓለም የመጣው ለዚሁ ነውና ነው፡፡ ይኸውም ትዕዛዝን በማፍረስ ከእግዚአብሔር የተጣላውን(የራቀውን) አዳምን ካሣ ከፍሎና ቤዛ ሆኖ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ነውና ይኽንኑ መፈፀምን ከሁሉ አስቀድሞ ጌታችን ስለዚሁ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ ሐዋርያት ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ የሚበላ ሲያቀርቡለት " እናንተ የማታውቁት የምበላው አለኝ" በማለት ሲመልስ፤ ሌላ ሰው የሚበላ ያመጣለት ሲመስላቸው ድግሞ "የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው" በማለት አስረድቷቸዋል " ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል" በሚል አስተምህሮውም ምን ያህል ለዚህች ሰዓት ዝግጁ እንደነበር አስረግጧል፡፡ ዮሐ 4፥ ፣ዮሐ 9፥

      ጌታችን የሰውን ድኅነት የመጣበትን ዕርቅ የመፈፀም ሥራ ከመደብደቡ፣ከመገረፉ፣ከመንቸንከሩ በአጠቃላይ ከተቀበለው ጸዋትወ መከራም ይበልጥ ቅድሚያ ትኩረት ይሠጠው እንደነበር በዚህ እናውቃለን፡፡ ከህማሙ ይልቅ ቅድሚያ የሰጠው የሰውን ድኅነት መሆኑ በዚህ ቃል ተረጋግጧል፡፡ የመቁሰሉ የሞቱ ዓላማ ይኸው ነውና፡፡

ለ. ጠላትን መውደድን በተግባር ለማስተማር ነው፡፡ ጌታ ሲያስተምር " ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ ፣ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ" እንዳለ፤ ጠላቶቹ ሳለን ለወደደን ለእኛ ቅድሚያ ሰጥቶ፤ ለሰቃልያኑም ራርቶ ይቅርታን ለመነልን፡፡ ይህን የሚፈፅሙ ማን መሆኔን ባያውቁ ነው ሲል ይቅርታውን አበዛልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም "አውቀውትስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር" እንዳለ በዚህም ሰው በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ቢተላለፍ ንስሐ ከገባ ስርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኝ አስታወቀን፡፡ ለእኛም ስለይቅርታ በቃል ያስተማረንን በተግባር ፈጽሞ አብነት ሆነን እኛም እርሱን አብነት አድርገን ምን ቢበድሉን ፈጽመን ይቅር እንድንል በተግባር አሳየን ሰማዕታትም አርአያውን ተከተሉ፡፡የሐዋ.ሥራ 7፥60

. ጌታ ሌሎቹን ስድስቱን ተናግሮ ይህን ትቶ ቢሆን ኖሮ በኋላ ዘመን የተነሱ መናፍቃን ወልደ ማርያም ሲሰቀል ወልደ እግዚአብሔር ተለይቶት ነበር ለሚል የስህተት ትምህርታቸው ይመቻቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በመስቀል የተሰቀለው፣ መከራን በነሣው ሥጋ የተቀበለው እርሱ በመስቀሉ ላይ ሳለ በመከራው ሰዓት "አባት ሆይ" ብሎ በመጣራቱ መለኮት በለበሰው ሥጋ መከራን ተቀበለ ሞተ…ወዘተ የሚለውን እውነተኛ ትምህርት አጸና፡፡ ይህን ትቶ "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ" "ተጠማሁ" ወዘተ…የሚለውን ብቻ ተናግሮ ቢሆን ለስህተት ትምህርታቸው ማስረጃ ባደረጉት ነበር፡፡ ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ከሥጋ ለቅፅበተ ዓይን እንኳ እንዳልተለየ በዚህ አውቀን ተረዳን፡፡ዕሩቅ ብእሲ(ፍጡር) እግዚአብሔርን " አባት ሆይ" ብሎ ይጠራ ዘንድ አይቻልምና፡፡ እርሱም ተከሶ የተሰቀለበት ምክንያት ይኸው ነውና፡፡ በዮሐንስ ወንጌል" እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሐር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር፡፡" ዮሐ 5፥18

በተጨማሪም ያቺ ሰዓት የይቅርታ የምህረት እንጂ የክስና የፍርድ ሰዓት አልነበረችምና ለሰቃልያኑ እንኳ ምህረትን አደላቸው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ" እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፤ከቁጣም የራቀ ምህረቱም የበዛ ነው ሁልጊዜም አይቀስፍም ለዘላለምም አይቆጣም እንደ ኃጢአታችንም አላደረገብንም፤ እንደበደላችንም አልከፈለንም " እንዳለ፤ በዮሐንስ ወንጌልም " በእርሱ የሚያምን ሁለ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና፡፡" ጌታም " ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ልፈርድ አልመጣሁም" በማለት ያቺ የይቅርታ ሰዓት በእርሱም ሆነ ከርሱ ርቀው በኖሩ ፍጥረቶቹ በጽኑ ናፍቆት ትጠበቅ ስለነበር ነው ይቅርታውን የገለፀባት፡፡ ዮሐ 3፡16

     ለሰቃልያኑም ዕድሜ ለንስሐ ሰጣቸው፡፡ ምናልባት በጊዜ ስቅለቱ የተፈፀመውን ዓይተው ሊድኑ ለሚችሉ የመዳን ዕድልን ለመስጠት ነው፡፡ በዚህም የሆነውን ዓይተው ፍፁም አምላክነቱን የተረዱ ፈያታዊ ዘየማንና የጭፍሮች አለቃ የነበረው አምነው መስክረዋል፡ "ጌታ ሆይ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ" እና "ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር" በማለት፡፡ ሉቃ 23፥39-43፤ ማር 15፥39

    ለሌሎቹም በስቅለቱና በሞቱ ባያምኑ ዜና ትንሣኤውን ሲሰሙ ምናልባት አምነው ፊታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ 40 ዘመን ታገሣቸው፡፡ ይህም የይቅርታውን ስፋት የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙዎችም ተጠቅመውበታል፡፡ ያልተጠቀሙበት ግን በ70 ዘመን ጥጦስን አስነስቶ ቀጥቷቸዋል፡፡


 

        ጌታ " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" በሚለው ቃሉ በመስቀሉ ላይ" ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ ጌታ በልደቱ ተፈጥሯችንን፣ በጥምቀቱ ጥምቀትን፣ በፆሙ ፆምን፣ጸልዮ ጸሎትን አንዳች ሳይኖረው ኑሮ መንኖ ጥሪትን፣የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ ትህትናን፣ታግሦ ትዕግስትን፣ መከራ መስቀልን ተቀብሎ ሰማዕትነትን ወዘተ…ፍፁም እንዳደረጋቸው ይቅር ብሎም ይቅርታን ፍፁም አደረጋት፡፡ እርሱ በዚያ ሰዓት የፈፀመው የይቅርታ ሥራ ተከታይ ተቀፅላ የማያስፈልገው የማይደገም ዘላለማዊ ይቅርታ ነው፡፡

      የአዳም በደል(ኃጢአት) ፍፁም አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትን የሠራው ከባህርዩ አንቅቶ ሳይሆን በዲያብሎስ ተታሎ ነውና፡፡ የዲያብሎስና የአዳም በደል ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ የኃጢአት የስህተት የሐሰት ሁሉ ነቅዑ ዲያቢሎስ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ዲያብሎስን "…እርሱ ከመጀመርያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም፡፡ ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል ሐሰተኛ  የሐሰትም አባት ነውና" በማለት የክፋት ሁሉ ምንጩ መነሻው ዲያብሎስ እንደሆነ መስክሮበታል፡፡ ሰው ከዲያብሎስ ያልተማረው ከራሱ አንቅቶ የሠራው ወደፊትም የሚሠራው ኃጢአት የለም አይኖርምም፡፡ ዮሐ 8፡፡  ጌታ የተንኮል ምክሩን እስኪያፈርስበት ድረስ የዲያብሎስ ጥረትም ይኸው ነበር፡፡ ሰውን አዘቅት ውስጥና፤ አምላኩንና የቀደመን መልኩን(ክብሩን) በመርሳት በድንቁርና ጨለማ ተውጦ በመዳኑም ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር ቅዱስ እግዚአብሔርም አዳምን እንደ ዲያብሎስ ይህስ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ከሚጨምር በቀር የቀደመ ሕይወቱ ናፍቆት አይደለም የመዳን ምኞት የሌለው ነው በማለት ከማዳኑ ቸል እንዲለው ተመኝቶ ነበር፡፡

      ምንም እንኳ በመጽሐፍ "በሥራቸው ረከሱ ጎሰቆሉ፣ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፣ የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ፡፡ ሁሉ ዓመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም አንድም ስንኳ የለም " ቢባልም በየዘመናቱ የአዳምን ዘር ወክለው የድኅነትን ምኞትና ተስፋ አንግበው በቅዱስ እግዚአብሔር ፊት የሚታዩ ቅዱሳን አልጠፉም፡፡ መዝ 13፡ 1-3

     ይልቁንም ዲያብሎስ በአዳም ዘር ውስጥ ከርሱ ባህርይ ከምትገኝ ንጽህት ዘር ተወልዶ እንደሚያድነው የሰጠው ተስፋ፤ያቺ ንጽህት ዘርም እንደ ሚያበራ ንፁህ ዕንቁ በአበው አካልና ባህርይ ውስጥ ስትፋለስ መምጣቷ ኃጢአት በአዳም ላይ ባህርያዊ እንዳይሆንና ዲያብሎስም የተመኘው እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል ፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ" ተፈፀመ ተስፋ አበው በማርያም ድንግል፤ ወበቀራንዮ ተተክለ መድኃኒት መስቀል"(የአበው ተስፋ በድንግል ማርያም ተፈጸመ፤ መድኃኒት መስቀልም በቀራንዮ ተተከለ) ያለው እኛም "ምክሀ ዘመድነ" ምክንያተ ድኂን (የባህርያችን መመኪያ የድኅነታችን ምክንያት) የምንላት፡፡

    በመሆኑም ፈፅሞ በበደል ከእግዚአብሔር የይቅርታ ድንበር ውጪ ያልሆነውን አዳምን የበደለው በምክረ ከይሲ ተታሎ እንጂ ከባህርይ አንቅቶ እንዳልሆነ ጌታ ሲመሰክርለት " የሚሠሩትን አያውቁምና" አለ፡፡ አውቆ አጥፊ እና በስህተት የሚበድል እኩል አይሆንምና በዲያብሎስ ቅጣት ለአዳም ድኅነት ተፈረደ፡፡ አንድም

      አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ማለቱ ፍፃሜውን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ "ሶበ ትረክቦ ኃጢአቱ ይጸልዓ" እንዳለ፣ ዲያብሎስ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን እንዳያስተውሉ ቢጋርድባቸው ነው እንጂ፤ ኃጢአት ምን ፍዳ እንደሚያመጣባቸው ፈፅመው ጠንቅቀው ቢረዱ አሁን የሚሠሩትን አይሠሩትም ነበር ሲል ነው:: ዛሬም ጊዜ እንኳ ሰው ይህን ቢያውቅ ዘላለማዊው ቅጣትም ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ ቢረዳ ዛሬ የሚሠራውን ባልሠራው ነበር፡፡ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑ በራሱ እጅግ አስጨናቂ ነውና፡፡ ቅዱሳን ኃጢአትን ብቻ ያይደለ በዓለም ያለ ግብርን ሁሉ እንደ ምናምን ቆጥረው እርግፍ አድርገው ትተው በፍፁም ኃይላቸው፣ በፍፁም ነፍሳቸውና በፍፁም ልባቸው ጌታን የሚከተሉ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትንና ምረረ ገሃነምን በመረዳታቸው ነው፡፡

      ጌታ በመስቀል በነበረባት በዚያች ሰዓት ራሱን ፍፁም የአዲስ ኪዳን መስዋዕት፤ ዘላለማዊ ካህን (አስታራቂ) እና ይቅር ባይ(ታራቂ) በመሆን አቀረበ፡፡

      አዳም ከፈጣሪ ትዕዛዝ ከወጣ በኋላ ጸጋው በመገፈፉ ጠባዩ በማደፉና ባህርይው በመጎስቆሉ የተነሳ ይኸው በዘሩ ተጋብቶ የጠብን ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ሊገኝ አልተቻለም ነበር፡፡ ሁሉ በኃጢአት ስለተያዘና የእግዚአብሔር ክብር ስለጎደለው እርቅን ማምጣት አልቻለም፡፡ከአዳም ጀምሮ የነበሩ  ታላላቅ አበው፣ከሙሴ ጀምሮ የተነሱ ነቢያት ከአሮን አንስቶ የነበሩ ካህናትና ከእያሱ ኋላ የተነሱ መሣፍንት ዳዊትንም የተከተሉ ነገሥት በጸለዩት ጸሎት ባቀረቡት መሥዋዕት ኃጢአትን በደልን ማራቅ ህዝቡንም ከህዝቡ ማስታረቅ አልቻሉም ነበር፡፡

     በብሉይ ኪዳን የነበሩ ካህናት ስለህዝቡ ኃጢአት መስዋዕትና ምልጃ ከማቅረባቸው በፊት ስለራሳቸው ኃጢአት መስዋዕት ማቅረብ ነበረባቸው ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊ ድኅነት ጊዜያዊ እርቅ ከማምጣት ያለፈ የፈየደው ነገር አልነበረም፡፡ እነርሱም ህዝቡን እንደጥላ(ምሳሌ) በነበረችው ድንኳንና የኦሪት ሥርዓት ሲያገለግሉ ከኖሩ በኋላ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተከትሏቸው ይወርዱ ነበር፡፡ እነርሱም የበለጠ ሊያድናቸው ወደሚችል በብርቱ ጸሎትና ምልጃ ይቃትቱ ነበር፡፡ " አንሥዕ ኃይለከ ወነአ አድኀነነ"(ኃይልህን ግለጥና መጥተህ አድነን) እያሉ በዘመናቸው ሁሉ ይጮኹ ነበር፡፡

    ከዚያም በላይ ከጻድቁ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዘካርያስ ድረስ በኩላብ ተቸንክረው በመጋዝ ተተርትረው ደማቸው ቢፈስም ለዓለም አይደለም ለራሳቸውም ቤዛ መሆን አልቻለም የኒህ ሁሉ ደም ይካሰስ ይፈራረድ እንደሆን እንጂ ይቅርታን ሰላምን ሕይወትን አንድነትን አላመጣም፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ "እግዚአብሔርም አየ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ ሰውም እንደሌለ አየ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው፡፡ጽድቁንም እንደ ጥሩር ለበሰ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቁር አደረገ…" እንዳለ የተፈረደውን ፍርድ ሊያስቀር የሚችል እንደሌለ ባወቀ ራሱ ወደዚህ ዓለም መጣ ሥጋንም ለብሶ ተገለጠ፡፡    ኢሳ 59፡ 15-17

     ጌታ ዓለሙን ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱም ጋር ለማስታረቅ ሲገለጥ ክህነቱ(የማስታረቅ አገልግሎቱ) ከብሉይ ኪዳን ካህናት በእጅጉ የራቀና የመጠቀ ነበር፡፡

፩. የብሉይ ካህናት መሥዋዕት ሲያቀርቡ መጀመርያ ለራሳቸው ቀጥሎ ለህዝቡ ነበር፡፡ እርሱ ግን ያለ ኃጢአት ያለ ነውር ስለተገለጠ  ለራሱ መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ሲናገር " ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መሥዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል፡፡ዕብ 5፥5-4

፪. የብሉይ ካህን በዘር ጨምሮም በቅዱስ ቅባት ተቀብቶ የክህነትን ሥራ ይሠራል፡፡ ሰያሜ ካህናት የሆነው ጌታ ግን ከማንም አልተቀበለውም፡፡ ስለ እርሱ እንደተባለ" አንተ እንደ መልከፄዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ" ሿሚ የለበትም፡፡ዕብ 5፥5-6

፫. የብሉይ ካህን ጊዜአዊ እርቅን የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሊያሰጥ የሚችል የፍየልና የኮርማዎች ደም ያቀርብ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሥጋን ነፍስን ደመ ነፍስን የሚቀድስ ክቡር ደሙን አፍስሶና ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ አስታረቀን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ" የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ፤ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን?" በማለት ገልፆታል፡፡ ዕብ9፥13-14 

     ጨምሮም "…የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ "መስዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ኃጢአት በሚሠዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ፡፡በዚያን ጊዜ እነሆ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደተፃፈ አምላኬ ሆይ ፍቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ" ይላል፡፡ በዚህ ላይ መሥዋዕትና ስለ ኃጢአትም የሚሠዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደህግ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ቀጥሎ እነሆ አምላኬ ሆይ ፈቃድህ ላደርግ መጥቻለሁ ብሎአል፡፡ ሁለተኛውን ሊያቆም ፊተኛውን ይሽራል በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል፡፡" በዚህም ቃል በግልፅ ቃል መሥዋዕተ ኦሪት ተሽሮ መስዋዕተ ሐዲስ እንደተተካ ይህ የሆነበት ምክንያትም የኃጢአት ሥርየት ማምጣት አለመቻሉና መለኮታዊውንም ፍርድ አለማርካቱ መሆኑን አትቷል፡፡ዕብ 10፥4-10

     የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት የእውነተኛይቱ ምሳሌ በምትሆን ቅድስተ ቅዱሳን በዕለትና በዓመት ኃጢአትን ሊያስወግዱ የማይችሉበትን መስዋዕቶች ብዙ ጊዜ ያቀርብ ነበር፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ወደ ምሳሌይቱ ሳይሆን አማናዊ ወደሆነችው ቅድስት አንድን መስዋዕት አንድ ጊዜ አቅርቦ ኃጢአትን በማስወገድ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "… ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሠራች የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደምትሆን ቅድስት አልገባምና፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርሰዋ ወደ ሰማይ ገባ፡፡ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፡፡ እንዲህ ቢሆንስ ዓለም ከተፈጠረ  ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፡፡ አሁን ግን በዓለም ፍፃሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሺር አንድ ጊዜ ተገልጦአል…" ጨምሮም  " ሊቀ ካህናት ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፡፡ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፡፡" በማለት ጽፏል፡፡ዕብ 9፥24-28፤ ዕብ 10፥11-12

      ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የማስታረቅ አገልግሎቱን በራሱ ብቻ አላስቀረውም ይልቁንም የአዲስ ኪዳን ካህናት እንደራሴው በመሆን በእርሱ ተገብተው በሚሠውት የእርሱ ሥጋና ደም በእምነት ለሚቀርቡ ሁሉ ጊዜአዊ ያይደለ ዘላለማዊ ድኅነትን ፍፁም ይቅርታን ለምዕመናን ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ"…ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፤ በደላቸውም አይቆጥርባቸውም ነበር፡፡ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ " በማለት የአዲስ ኪዳን ካህናት ከብሉይ ካህናት ምን ያህል የሚበልጥ የክህነትን ክብር እንደተቀዳጁ ጽፏል፡፡ 2ቆሮ 5፥18-21

     ከላይ በተብራራው ላይ መሥዋዕቱ እርሱ መሥዋዕቱን አቅራቢውም እራሱ መሆኑን በተረዳ ነገር አይተናል፡፡ ሌላው በዚሁ የምናየው ነጥብ ተወካፌ መሥዋዕቱ እርሱ ራሱ መሆኑንም ነው፡፡ በአዳም የሞትን ፍርድ የፈረደበት እርሱ፤የይቀርታን የድኅነትን ቃል " አባት ሆይ የሚሠሩትን አያውቁምና ይቀር በላቸው" በማለት አወጀልን፡፡ በዚህ ቃል የጠብ ግድግዳ ፈረሰ የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ለሰው ዘር ፍፁም ካሣ ተክሶ አዳምም ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመለሰ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም" እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፡፡ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትዕዛዝ የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው" ብሏል፡፡ አክሎም " እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡ እርሱ ሰላማችን ነውና፡፡ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግደግዳን በሥጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፤ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡" በማለት ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ እንዴት እንደታረቀን አስተምሯል፡፡ኤፌ 2፥13-16፤ቆላ 2፥13-15

     በአዲስ ሥርዓት በሆነ ደሙ ላጠበን ከበደላችንም ሁሉ ላነፃን ይቀርታውንና ምህረቱን ላበዛልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ከሆነ ከሰማያዊ አባቱ ጋር ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ዛሬም ዘወትርም መቼም መች ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!

ይቆየን!

ጥር 2005 ዓ.ም

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 

Read more...
Subscribe to this RSS feed

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ