Login
Main menu

ፍና ቅዱሳን

መጽሐፉን ለማግኝት 

+251 923976850

+251 911249756

ከመጽሐፉ የተወሰደ 

 

‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው ፡፡ ዕብ. 13÷7

The paradise ወይም The Garden of the Fathers በሚለው ታላቅ መጽሐፍ፤ የእስክንድርያው ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ፤ የሄሊያ ፓሊስ ሊቀ ጳጳስ ጳላድዮስና ቅዱስ ጄሮም፤ ዘመናቸው ታላቅ የቅድስና ሕይወትን በመምራት ይታወቁ የነበሩ አበውን በአካል በማግኘትና፤ በአካል ለማግኘት ያልቻሉትንም ከደቀ መዛሙርቶቻቸው በመጠየቅ የተጋድሎ ሕይወታቸውንና ድንቅ የሆኑ ምክሮቻቸውን መዝግበው ትተውልናል፡፡ 

በአባቶች ዘንድ የቅድስናን ሕይወት ለመኖር የነበረን ቁርጠኝነት፤ ለወጣንያን የሥጋ ፈቃድን መቆጣጠርና የቅድስናን ሕይወት መለማመድን የሚያሳዩበት መንገድ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ለቃኘው ኅሊና እጅግ መሳጭ ነው፡፡ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ለሚመኝ ሁሉ የቅዱሳንን ሕይወት ከማንበብ የሚበልጥ ነገር አይገኝም፡፡

የንስሐቸው ጥልቀት ልብን ይሰብራል፤ የተጋድሏቸው ትዕግሥት ከዓለት ይልቅ ይጸናል፤ ምክርና ተግሣፃቸው የልብን ሸለፈት ለመግረዝ  ከባልጩት ይልቅ ይሰላል፤ ለጌታ እግዚአብሔርና ለሰው ልጅ ያላቸው ፍቅር ዕንባን በዓይን ይሞላል፤ ትኅትናቸው በትዕቢት ያበጠ ኅሊናን ያፈርሳል፤ ጸሎታቸው እንደ በረሃ የደረቀ ሰውነትን ያረሰርሳል፡፡ እምነታቸው ሕሙማነ ሥጋ ወነፍስን ለመፈወስ፤ የዲያብሎስንም ወጥመድ ለመበጣጠስ በልዑሉ ፊት ብርቱ ነው፡፡ ለእኛ የሕይወት መምህራን የክርስትናም አብነቶች ናቸው ቅዱሳን፡፡ 

ቤተክርስቲያን የቅዱሳንን ታሪክ የምትዘግበው ታሪክ የማስተማር ዓላማ ኖሯት አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ በቤተክርስቲያን ያልተመዘገቡ የስንቶች ታሪክ ታልፎ አይቀርም ነበር፡፡ ዋና ዓላማዋ ከቅዱሳን ሕይወት እንድንማርና የእነርሱን የተጋድሎ ጥበብ እንድንወርስ ነው፡፡

የዚህ መጽሐፍ ዓላማውም፡-

ሀ. በወንጌል በቃል (theory) ደረጃ ተቀምጦ የምናየውን ክርስትና እንዴት በተግባር መተርጎም (practical) እንደሚቻል ለማመላከት

ለ. የክርስትና ሕግ ከዚህ ዓለም ጠባይና ከሰው ድካም አንጻር ሊፈፀም የማይችል ሕግ ነው ብሎ ለሚያስብ፤ ጌታ እግዚአብሔር ሊፈፀም የማይችል ሕግ እንዳልሰጠንና፤ በሚደንቅ ጽናት የክርስትናን ሕይወት ኖረው ያለፉትን በማየት ከመንፈስ ዝለት ለመራቅ፤

ሐ. መጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ ሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ለምናነብ ሁሉ እንዲሁ በልማድ፤ ለእውቀት፣ የቋንቋ ክህሎትን ለማዳበር ወዘተ... ሳይሆን በእያንዳንዷ ነጥብ ራሳችንን በመመርመርና ከሕይወታችን ጋር በማገናኘት መሆን እንዳለበት ለማስገንዘብ ታስቦ የቀረበ ነው፡፡

ይህን መጽሐፍም ሆነ ሌሎችን ተመሳሳይ መጻሕፍትን የሚያነብ ሁሉ ዓላማውን መሳት የለበትም፡፡ ባወቅነው መጠን መጠየቅ አለና በተረዳነው ለመኖር መጋደል ይጠበቅብናል፡፡ በወንጌል የተገለጠው ክርስትና በተግባር ተፈጽሞ የምናየው በቅዱሳን ሕይወት ነው፡፡

ክርስትና የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስን መምሰል ነው፡፡ የቅዱሳን ምክር ደግሞ እኛ እርሱን እንደመሰልን እኛን ምሰሉ፤ በዕለት ተዕለት ኑሯችሁም እግዚአብሔርን ለመምሰል ራሳችሁን አስለምዱ የሚል ነው፡፡ ይህን ቋሚ የኑሮ መርሕ በማድረግ በየጊዜው የሚታይ ለውጥ ማሳየት ከክርስቲያን የሚጠበቅ ነው፡፡ ብዙዎቻችን መለወጥን አብዝተን እንፈልጋለን፡፡ የዘወትር ጥያቄያችንም እንዴት መለወጥ እችላለሁ? የሚል ነው፡፡ እውነታው ደግሞ የዚያኑ ያህል ለውጥን፤ ጠባዬ የምንለውን አሸንፈን በወንጌል አዲስ ሰው መሆንን አጥብቀን እንፈራለን፡፡ ለውጥ እንዲሁ አይመጣም፡፡ ለመለወጥ ማመን፣ መሻት፣ መወሰን ከዚያም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ በቅዱሳኑ ሕይወት የምናየውም ይኸው ነው፡፡ 1ጢሞ. 4÷ 8 ፤ 1ቆሮ 11÷1

የቅዱሳንን ታሪክና የኑሮ ፍሬ ከያዘው <<The Paradise>> ወይም <<The Garden of the Fathers>> መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ የተወሰኑ ታሪኮች በዚህ መጽሐፍ ተካተዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ታሪክ ለጥቆም ለሁሉም ሊመጥን በሚችል ደረጃ የተወሰኑ ማብራሪያዎች ቀርበውበታል፡፡ በታሪኮቹና በማብራሪያው ውስጥ፡- እውነተኛ ንስሐ ከተለምዶ የከንፈር ኑዛዜ ምን ያህል እንደሚለይ፤ የተሻለውን ስለ መምረጥ፣ ውሳኔ በክርስትና ውስጥ ምን ያህል ሥፍራ እንዳለው፣ በትንሹ ለምናማርርም በመከራ መታገስ ምን እንደሚመስል፣ ምክር መስማትና ተግሳፅን መቀበል ሕይወትን እንዴት እንደሚለውጥ፣ ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠትና በክርስቶስ የሆነ ፍቅር የማይቻለውን እንዴት እንደሚያስችል፤ የይቅርታን ታላቅ ኃይልና በትዕቢትም የሚገጥመንን ውድቀት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ በእያንዳንዱ ታሪክ ላይ የቀረበውን መንፈሳዊ ልምምድም በአቅማችን ግን በጽናትና በታማኝነት ለመለማመድ እንድንጥርም ተጋብዘናል፡፡

የእውነተኛ መንፈሳዊ መጻሕፍት ምንጭ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነውና፤ መጽሐፉን ያዘጋጀሁት ከሚያነቡት ከብዙዎች ራሴን እንደ አንዱ አድርጌ ነው፡፡ የሁላችን መምህር እርሱ ነው፤ ሁላችን ደግሞ ደቀ መዛሙርት!

መጽሐፉን ስናነብ ቢያንስ አንድ ለሕይወታችን የሚጠቅም ነገር እንድናገኝ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን!

መልካም ንባብ !

ቀሲስ ታምራት ውቤ

ነሐሴ 2008 ዓ.ም

 

3 comments

  • ዲጋ ሙገር
    ዲጋ ሙገር Monday, 06 February 2017 14:55 Comment Link

    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡ እግአብሔር ተዋህዶ እምነታችንን ያፅናልን፡፡

  • Metshet (ke Maheber MEDANIALEM)
    Metshet (ke Maheber MEDANIALEM) Friday, 02 September 2016 19:34 Comment Link

    It is such a wonderful spiritual book. I don't have a word. Thank you Kesis and I miss the next.

  • ገ/መድህን
    ገ/መድህን Monday, 22 August 2016 05:55 Comment Link

    ፍና ቅዱሳንን ሳነብ ከተገነዘብኩት ከብዙ በጥቂቱ ላካፍላችሁ፡-

    1. አለመታዘዝ የሁሉ ኃጥያት በር መክፈቻ መሆኑን፡ በታዘዝን ቁጥር የሌሎች ሀጥያቶችን በር እየዘጋን መሆኑን በመታዘዝ እንሞክረው፡፡ ውጤቱን ማረጋረጥ እንችላለን፡፡
    2. የጽድቅ ስራ የሚሰራው በትእግስት፣በጽናትና አቅምን ባገናዘበ መልኩ እንጂ በስሜታዊነት መሆን እንደሌለበት፡፡

    ቃለ ህይወት ያሰማልን!!

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.

back to top

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ