Login
Main menu

በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

ሐምሌ ፭

‹‹ በዓለ ዕረፍቶሙ ለብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሐዋርያቲሁ ለክርስቶስ ወአእማዲሃ ለቤተክርስቲያን ››

ሐዋርያ ነጠላ ሲሆን ሐዋርያት ብዙ ቁጥርን ያመለክታል፡፡ ቃሉ ሖረ ከሚለው የግዕዝ ግስ የሚወጣ ሲሆን‹‹ተጓዥ›› ‹‹ሂያጅ›› የሚል ትርጉም ይሠጣል፡፡ የጌታ ሐዋርያት ይህ ስም የተሠጣቸው መልካሙን ዜና ይዘው ወደ ዓለም ሁሉ በመሄዳቸው ነው፡፡‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው….››እንዲል ማቴ 28÷19

ሐዋርያት እንደቃሉ ተጉዞው የዓለሙን መልክ ሁሉ ለወጡት፤ ጨለማውን ገፈፉት አልጫውን አጣፈጡት፡፡በምድር በአፀደ ሥጋ ከመኖራቸው ጀምሮ በስሙ ሞትን ተቀብለው ከዚህ ዓለም እስከመለየታቸው ባለው ጉዞ ብርሃንነታቸውን ገልጠው አሳዩ፡፡ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ብሔራዊት የሆነችዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ (በሌሎችም ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ይሔው ትውፊት እንደተጠበቀ ነው) ከራሱ ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከቃሉ የተማሩ የእጁን ተዐምራት ቆመው የተመለከቱ፤በዋለበት እየዋሉ ባደረበት እያደሩ ብዙ ምሥጢራትን የገለጠላቸው፤ በእጆቻቸው የዳሰሱት አብረውትም የበሉና የጠጡ፤ የመከራው የስቅለቱ፣የሞቱ፣የትንሳኤውና የዕርገቱ ቀዳሚ ምስክሮች፤ከራሱ ከባለቤቱም ሥልጣነ ክህነትንና የቤ/ክ አደራ የተቀበሉ በመሆናቸው ‹‹ሐዋርያ›› የሚለው መጠሪያ ከእነርሱ በቀር ለማንም ለማን ቀፅላ አታውቅም፡፡ ከእነርሱ በኋላ የተነሱትን ሁሉ የጠራቻቸውና የምትጠራቸው ሐዋርያነ አበው(Apostolic Fathers) የቤ/ክ ጠበቆች(Apologetics)፣ሊቃውንት፣አበውጳጳሳት፣መምህራን፣ካህናት ወዘተ… በማለት ነው፡፡ እኒህ ሁሉ የሐዋርያትን ሥልጣንና ተግባር ይዘው ቢገኙም ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለነበሩት የተለየ አክብሮት በመስጠት‹‹ሐዋርያ›› የሚለውን ስያሜ በእነሱ ላይ ብቻ ጠብቃው ኖራለች እንጂ ዛሬ ብዙ ደፋሮች እንደሚጠቀሙበት አይደለም፡፡ በነቢያትም እንዲሁ ነው፡፡

ስለ ሁሉ ሐዋርያት የሕይወት ገድል ለመተረክ ጊዜም አይበቃም አቅሜም አይፈቅድም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ሁሉ ስለተወከሉባቸው ሁለቱ ታላላቅ ሐዋርያት ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ በመጠኑ ማለት እወዳለሁ፡፡አንዱ የሕዝብ ሌላኛው የአሕዛብ ሐዋርያ ናቸውና፡፡ ከዚህ የወጣ የለም፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ከዓሣ አጥማጅነት ቅዱስ ጳውሎስ ከደማስቆ መንገድ እንዴት እንደተመረጡ፤የቅዱስ ጴጥሮስን የተለምዶ ሕይወትና ቅዱስ ጳውሎስ ምሁረ ኦሪትነት ለመተረክም አልሻም፡፡ ብዙዎቻችን የምናውቀው ነውና፡፡ ሁለቱም የተሠጣቸውን አደራ በትጋት ፈጽመው ናፍቆታቸው ተፈፅሞላቸዋል፡፡

ማንሳት የምፈልገው ከእነርሱ ሕይወት እኛ የምንማረው ምንድር ነው?የሚለውን ነው፡፡

 ሊቀ ሐዋርያትበዕድሜውም አዛውንት እንደመሆኑ ከጌታም ጋር ብዙ ጊዜ እንደማሳለፉም ቅድሚያ የቅዱስ ጴጥሮስን ሕይወት በጨረፍታ እንዳስሳለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዓሣ ፋንታ ሰውን የምታጠምድ አደርግሃለው›› ተብሎ ከተጠራበት ሰዓት አንስቶ ከጌታችን ጋር ማስመሰል በሌለበት ሕይወት ኖሯል፡፡ ከጌታችን የተሠወረ ምንም ነገር እንደሌለ የታወቀ ነገር ቢሆንም ቅሉ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን ከራሱ በሚወጣ የዋህነትና ቅንነት በጎም ሆነ የሚነቀፍ ጠባዩ በጌታ ፊት የተገለጠ ነበር፡፡ በወንጌል የተፃፈው የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት፤ ጥንካሬው ብቻ ሳይሆን ድክመቱ፣ስህተቱም ሆነ እውቀቱ፣ማስተዋሉም ሆነ ችኩልነቱ ብዙ ትምሀርት ትቶልን አልፏል፡፡ከጌታችን ጋር የነበረ ሕይወቱ በመውደቅና በመነሳት  የተሞረደየተቃናና የዳበረ ሐዋርያ ነው፡፡

ታላቁ ውድቀቱ ለታላቁ ትንሣኤው ምክንያት መሆኑን ማስተዋል ምን ያህል ያፅናናል፡፡ ምን ያህል ተስፋ መቁረጥን  ይሠብራል፡፡የቅዱስ ጴጥሮስ አዲስ ሕይወት ጅማሬ በጥብርያደስ ባህር ከጌታ ጋር ከነበረው ቆይታ ይነሳል፡፡ ‹‹የዮና ልጅ ስምኦን ትወደኛለህን?›› የምትለዋ ጥያቄ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት ወሳኝ ነበረች፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን ለታላቅ አገልግሎት ኃላፊነት ሊሠጠው ፈቃዱ ሆኗል፡፡ግን በእርሱ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋል፡፡ እርሱም በሰጠው ምላሽ ፈተናውን አልፏል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ሦስት ጊዜ መካድና መፀፀት፤ የመድኃኒታችንም የይቅር ባይነቱ ስፋት ቅዱስ ጴጥሮስን ደግሞ ለተሻለ ሕይወት ወለደው፡፡ከውድቀቱ የተነሳ የተሻለ ጠንክሮ የተሻለ አስተውሎ የተሻለ ተቀርጾ ነበር የተነሳው፡፡ ዮሐ 21

የቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት በዚያች ቃል ታሠረች፡፡ ‹‹አንተ ሁሉን ታውቃለህ እንድወድህም አንተ ታውቃለህ›› በምትለዋ ቃል፡፡ ከዚያ ለጥቆ በነበረ ሕይወቱ መልሱ ይኸው ነበር፡፡ ስለምን ትሰብካለህ?ስለምን ትፀልያለህ?ስለምን ታመሠግናለህ? ስለምን ትታሠራለህ?ስለምን ትገረፋለህ?ስለምን ትሞታለህ? ስለምንስ ትኖራለህ?ወዘተ… ብለን ብንጠይቀው መልሱ ምክንያቱም ‹‹ስለምወደው››  የሚል ነው፡፡ በአንተስ ላይ ስለምን ይህ ሁሉ ይደርስብሃል ብንለው ‹‹ለእርሱ ባለኝ ፍቅር ላይ እርግጠኛ ስለሆነ›› የሚል መልስ ይሰጠናል፡፡

ጌታችን ሐዋርያቱን በቃሉ ላይ የሾማቸውና ትምህርታቸውን በብዙ ድንቅ ተዓምራት ያፀና የነበረ እንዲሁ አይደለም፡፡ወደ እስራት፣ወደ ግርፋት፣ ወደ መከራ፣ ወደ ሞት፣ የወሰዳቸውም ለእርሱ ባላቸው ፍቅር እርግጠኛ ስለሆነ ነው፡፡ እኛስ ጋር ያለው እንዴት ነው?

ጸሎታችን፣ምስጋናችን፣ጾማችን፣ምጽዋታችን … ወዘተ አጠቃላይ ክርስቲያናዊ ሕይወት የምንኖረው ለምንድነው? አገልጋዮችስ የምንቀድሰው፣ ሕፃናትን የምናጠምቀው፣ በሰዓታት በማኅሌት የምናድረው፣ የምንሰብከው ወዘተ… ለምንድር ነው? በዚህ ሁሉ እኛ ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር እገልጣለን ወይስ የልማድ እስረኞች ነን፡፡


 

የአንድ ሰነድ ማረጋገጫው ማኅተም እንደሆነ ሁሉ እኛም ከክርስቶስ ጋር ላለን ሕብረት አብረነውም የምንሠራ ለመሆናችን ማኅተሙ ‹‹ትወደኛለህን?›› ብሎ ለሚጠይቀን ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ነው፡፡ ይህን ማሰብ ልብን ያሳምማል፡፡ሁሉን በሚያውቀው በእርሱ ፊት መተወን ሲያስተውሉት ያሳቅቃል፡፡ ተውኔታችንን ሕይወት አልባ ትወናችንንም ለዛ ቢስ ያደርገዋል፡፡ እንዴት ያለ አለመታደል ነው የሕይወት ዘመን ክስረት?!

ዛሬ ያለን የክርስቶስ ተከታዮች ሕይወታችን ለሌላው ትምህርት መሆንም አልቻለም፡፡ምክንያቱም ሁል ጊዜ የሚገለጠው ጥንካሬያችን ንፅሕናችን ቅድስናችን እንጂ ድክመታችን ጥፋታችን ነውራችን አይደለምና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ  ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ እምነቱ እንደተገለጠ ‹‹የምትሉትን አላውቀውም››ብሎ የተናገረው ክህደቱም ተገልጾ በመታየቱ ከሕይወቱ ተማርን፡፡ ሁሌ ጥንካሬን ሁሌ ቅድስናን የምንሰማበትን ሕይወት ግን ከምንማርበት ይልቅ ተጠራጠርነው፡፡

በቤተ/ክ ታሪክ ለታላቅ ቅድስና ሕይወት የበቁ ቅዱሳን በቀደመ ሕይወታቸው ታላላቅ ስህተት የሠሩ ናቸው፡፡በእነርሱ ላይ የተገለጠች ታላቅ የእግዚአብሔርን ይቅርታ በማድነቅ ለንስሐና ለቅድስና ሕይወት እንድንበረታታ ነው ታሪካቸው የሚተረከው፡፡

ለእግዚአብሔር ባለን ፍቅር እርግጠኞች ከሆንን በስሕተት ወይም በፍርሃት ለሚገጥመን ውድቀት ይቅርታው ቅርብ ናት፡፡ ከወደቅንም በኋላ ማረጋገጥ የሚፈልገው ለእርሱ ያለንን ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፍቅር የሌለው ሰው ለንስሐ አይቀርብም፡፡ ፍቅር የሌለው ንስሐም ሥርየትን አያስገኝም፡፡ከፍፁም ፍቅር የተነሳ ንስሐ ስንገባ ግን የጌታ እግዚአብሔር ይቅርታው በእኛ ላይ ትደንቃለች፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ንስሐ የጌታ እግዚአብሔር ይቅርታ ወደ ቀደመ ክብራችን መመለስ ብቻ አይደለም ከዚያ ወደሚበልጥ ከፍታ በማውጣት ትገለጣለች፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ጌታ እግዚአብሔርን በስንቱ ነገር ይቅርታ እንደምንጠይቅ ግራ እስኪገባን ድረስ በደላችን ይከድነናል አለማስተዋላችንም ይሸፍነናል፡፡የሚታገሉንን ለመጣል፣የሚቃወሙንን ለማጥፋት፣የሚያጠቁንን ለማጥቃት ስንት ጊዜ ተጠበብን፡፡ስንቱን ሸፍጥ በስሙ ስንቱን በደል በኃይሉ የተገኘ ፍትሕ አስመሰልነው፡፡በፍቅር ሳንታገል ተሸንፈን ሳናሸንፍ የትግላችን መሪ የውጊያችን ፊታውራሪ ልዑሉ መሆኑን ለፈፍን፡፡ የጥላቻችንን ድል የቅዱስ ስሙ መመስገኛ አደረግን፡፡ ታዲያ ለዚህ ላልተገለጠው በደላችን የሸፍጥ ጽድቃችን እንደ ነቀርሳ ውስጥ ውስጡን ርኩሰት ለበላው ቅድስናችን ቀርቶ ለተገለጠው ኃጢአታችን ምን ንስሐ ይበቃዋል? አሁን የኖርነውን ዕድሜ ደግሞ ቢጨመርልን ለመፀፀት አይደለም ለማስታወስ እንኳ ይበቃን ይሆን?

በሁሉ የምመስልህ ወንድሜ ሆይ! በሕይወት ለመቆየታችን በፊቱም ለመታየታችን የኃጢአትን ይቅርታ ለማግኘታችን ምክንያቱ የልዑሉ የይቅርታ ስፋት እንጂ የእኛ የንስሐ ጥልቀት አይደለም፡፡ ይህን ባመንበት ቅፅበት ወደ ምህረት ደጃፍ መቅረብ እንጀምራለን፡፡

ግን ደግሞ እንደ እውነቱ የሁላችን ኃጢአት ተገልጦ አለመታወቁ የይቅርታ ልብ በጠፋበት በዚህ ዘመን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰውን ፀፀቱን ንስሐውን አይቶ ይቅር (ከልቡ) ብሎ የተሻለ ክብር ከሚሠጠው ይልቅ የሚረግም የሚፈርድና መጠቀሚያ ለማድረግ የሚያደባ በበዛበት ጊዜ ተጋላጭ ሆኖ መገኘት አለመፈለጉ በዘመኑ ክርስቲያኖች ላይ ያለንን የእምነት ጥርጣሬ የሚያሳይ ነው፡፡ ማስተዋል አቃተን እንጂ የክርስትና መሠረቷ ይቅርታ ነበር፡፡ ጌታችን በመስቀሉ ደሙን አፍስሶ እኛ በበደልን እርሱ ክሶ ይቅር ባይለን ኖሮ ወዴት እንታይ ዘንድ አለን ነበር? እርሱም ያስተማረን የሰማዩ አባታችሁ ይቅር እንዲላችሁ እናንተም የበደሏችሁን እንዲሁ ይቅር በሉ በማለት ነበር፡፡ሰው ራሱን የሚገልጠው ውጤቱን ገምቶ ነው፡፡ የይቅርታ ጉልበት በመካከላችን ተገልጦ ቢሆን ኖሮ የማስመሰል ሕይወት ምንኛ በሞተ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ይቅርታ ስትደክም ኃጢአት በሥውርነገሠች፡፡

ከቅዱስ ጴጥሮስ ሕይወት በጨረፍታ ቢሆንም እንኳ ከቀመስን የአሕዛብ ሐዋርያ ወደ ተባለ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ እናልፋለን፡፡

አስቀድሜ ይህን ለመጻፍ በመድፈሬ በራሱ ታላቅ ይቅርታን ሕይወታቸውን ኖረውለት ሞቱን በሚመስል ሞት ከመሰሉት ከሐዋርያት ጌታ እለምናለሁ፡፡የዚህ የተወደደ ሐዋርያ ሕይወትስ ይጽፍ ዘንድ ማን ይደፍራል? ይህ ከመታሰብ በላይ ነውና፡፡ እንዲያው ለቅምሻ ያህል እንሞክራለን፡፡በዚህ ጽሑፍ ተነሣስታችሁ ይበልጥ ቅዱስ ጳውሎስን ማወቅ ለምትፈልጉ ግንየሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሰባት ቁጥር ስድሳን መነሻ አድርጋችሁ የሐዋርያት ሥራን ሙሉውንና መልእክታቱን አንብቡ፡፡ስታነቡ ግን በጸሎትና በታላቅ ተመስጦ ይሁን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ቃልና ዓረፍተ ነገር የውቅያኖስ ያህል ጥልቀት ያለው ነውና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስን በመጽሐፍ ቅዱስ የምንተዋወቀው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲገደል የገዳዮቹን ልብስ ሲጠብቅ ነው፡፡ ምንም እንኳ የታላቁን ሰማዕት ደም ለማፍሰስ እጆቹ ድንጋይ እንዳያነሱ መንፈስ ቅዱስ ቢጠብቀውም በመገደሉ ግን ተስማምቶ ነበር፡፡የወደፊቱን የአሕዛብ ቤ/ክ ካህንና ሐዋርያ መንፈስ ቅዱስ ከደም ጠብቆታል፡፡ የሰማዕታት ደም ሥራ ሳይሠራ በከንቱ አይቀርምና የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ጳውሎስን ለቤ/ክ አስገኝቷል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ለኦሪት በነበረው ቅንዓት ክርስቲያኖችን ለማሰር ከሊቀ ካህናቱ ደብዳቤ ተቀብሎ ወደ ደማስቆ ሲሔድ ነው ከክርስቶስ ጋር የተገናኘው፡፡ ከኦሪት ሊቀ ካህናት ሰዎችን ለማሠርና ለማሠቃየት ነፃነታቸውን ለመግፈፍና እምነታቸውን ለማስካድ ሥልጣን ተቀበለ፤ ከአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ከጣዖት፣ከኃጢአት፣ ከድንቁርና ጨለማና ከዲያብሎስ እስራት ነፃ እንዲያወጣ፤በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለሚገኝ አዲስ ሕይወት በእምነት እንዲፀኑ ለማስተማር ሥልጣን ተቀበለ፡፡የኦሪቱ ሊቀ ካህናት በቁጣና በጭካኔ ላከው የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት ግን በፍቅርና በርኅራኄ አሠማራው፡፡

ጌታ እግዚኣብሔር ያለ ዓላማሰውንም ሆነ ሌላውን ፍጥረት አልፈጠረምና ዓላማ ያለው ሰው ይወዳል፡፡በእርግጥ ሰዎች አጥፊ መሆኑን አምነው የሚይዙት ዓላማ ያለውን ያህል እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ካለ ማስተዋል የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚዋጉ እየመሰላቸው እራሱን እግዚአብሔርን የሚያሳድዱ አይጠፉም፡፡ጌታም በቃሉ‹‹…የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል›› ያለ ይህን ሲያመለክት ነው፡፡ ዮሐ16÷2

ነገር ግን ሁልጊዜ ክፉ ነገሮችን ለበጎ የሚለውጥ ጌታ እግዚአብሔር የቅዱስ ጳውሎስንም ቅንዓት ለወንጌል አገልግሎት ለቤ/ክ መስፋት እንዲልውል ፈቃዱ ሆነ፡፡ የዮሴፍ ወንድሞች ቅንዓት በኋላ ለእስራኤል ከረሃብ መዳን ምክንያት እንደሆነ የቅዱስ ጳውሎስም ቅንዓት አሕዛብን ከቃለ እግዚአብሔር ረሃብ ለመዳን ምክንያት ሆኗል፡፡


 

በደማስቆ መንገድ ቅዱስ ጳውሎስ የጠየቀው ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ነው፡፡ የመጀመሪያው ጌታ‹‹ስለምን ታሳድደኛለህ?››ሲለው፤‹‹ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?›› በማለት የጠየቀውና ማንነቱን ካወቀ በኋላ ደግሞ ‹‹ጌታ ሆይ ምድ አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?›› የሚለው ፍፁም ራስን የመስጠት(የመገዛት)ጥያቄ ናቸው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የሚያናግረው የሚወቅሰው ማን መሆኑን ካወቀና ምን ማድረግ እንዳለበት ከተናገረው በኋላ ወደ ኋላ አልተመለሰም፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባው እንድትነግረው የተላከውም ወደ ቤተክርስቲያን ነው፡፡

ፊት ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ምዕመናንንም ለመሳደድ ተሰልፎ እንዳልነበር ኋላ ግን ጣዖትንና ክህደትና የሚያፈርስ የመንፈስ ቅዱስ መዶሻ፤የጠንቋና የአስማተኞች ሥራይ ማርከሻ፣የሕሙማንና ተስፋ የቆረጡ ሁሉ መፈወሻ ሆነ፡፡ ይህ ነው ለውጥ፤ ይህ ነው ክርስትና፤ ይህ ነው ሐዋርያነት፡፡ 

ዛሬስ ክርስቶስ ከመሳደድ አርፏልን? የሚሳደደውስኢ-ክርስቱን በሆኑት ብቻ ነውን? በሚሉት መጠይቆች እስኪ ራሳችንን እንመርምር፡፡

ኢ-ክርስቱን በሆኑት ክርስቶስ እንደሚሳደድና እንደሚታረድ በሶርያ በኢራቅና በሊብያ ያየናቸው የዘመናችን ዘግናኝ ጭካኔዎችና ቁርጥ የሰማዕትነት መንፈስ በቂ ማስረጃ ስለሆነ ብዙ ማለት አያስፈልግም፡፡(በረከታቸው ይደርብን)

በእኛ በክርስቲያኖችስ ክርስቶስ አይሳደድም? ባል ሚስቱን፤ሚስት ባሏን፤ወላጆች ልጆቻቸውን፤ልጆች ወላጆቻቸውን፤  ወንድም ወንድሙን፤እህት እህቷን ፤ ጓደኛ ጓደኛውን፤ ጎረቤትም አብሮት የሚኖረውን፣የትምህርት የሥራ አጋሩን ወዘተ… ቀን ስጠኝ ጊዜ ፈቀደልኝ ብሎ የሚበድል የሚያሰቃይ ላቡን ድካሙን የሚቀማ ከሥራ የሚያፈናቅል ይህ ሁሉ ክርስቶስን አሳዳጅ አይደለምን?

በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ (በቤተመንግስትም ሆነ በቤተክህነት) የሥልጣን ዙፋን ላይየተቀመጥን ጊዜ ሰጠን የብዕርናየአፈሙዝ ኃይል አጋደለልን ብለን ድሀውን የምንረግጥ፤ ያለመማለጃ ጆሯችን የማይሰማ ዓይናችን የማይገለጥ፤ ስህተታችንን የሚያርም ግፋችንን የሚቃወም ሲገኝ የምናስር የምናግዝ የምናሠቃይ የምንገድል ክርስቶስን ማሳደድ አይደለምን?

ዛሬ በእኛ ክፋት ክርስቶስ በረሃብ ጠውልጓል፤ የጎዳና አዳሪ ሆኗል፡፡ በመድኃኒት ከሰው ተራ ወጥቶ ይባዝናል፤ በጠበል በሆስፒታል ጓሮ ወድቋል፡፡ እኛ ግንከረሃቡ ነጥቀን ታላላቅ ቤተ መቅደሶች እናንጻለን፤ ጥም ካደረቀው ሰውነቱ ለተቀዳ ደሙ የወርቅ ጽዋ እንገዛለን፤እርሱ ጎዳና ወድቆ እኛ በምንጣፍ እናስቀድሳለን፤ የእርሱ እርቃን ተጋልጦ እኛ መጋረጃ እንመርጣለን ፡፡

የጥፋት ሀብት የሰበሰብን ረሃብ ክብሯን ያስጣላት ማጣት በሴትነቷ የፈተናት እህታችንን ርኩሰታችን ልንተፋባት ብልግናችንን ልናስታግስባት በገንዘብ ስናማልላት ከሰውነት ክብር አዋርደን ለመናገር የሚቀፉ ነውር ስንፈፅምባት ክርስቶስን ማሳደድ መሆኑን ረሳነውን?ለመዘርዘር የማይበቃን በታናናሾች ላይ የሚደረግ ሁሉ በእርሱ ላይ እንደሚደረግ ለነገረን ለእርሱ ይህ ሁሉ ስደቱ ሕመሙ አይደለምን?

የሰውን አእምሮ አፍዝዞ ሕዋሳቱን አደንዝዞ ለሀገር ለወገን በሚጠቅምበት የወጣትነት ዕድሜው የእፅ ምርኮኛ የሱስ እስረኛ በማድረግ ከዚያ በሚገኝ ገቢ ኑሮአቸውን ያጸደቁ ‹‹ቢዝነስ›› ነው እያሉ የሚመጻደቁ እኒህ ሁሉ ክርሰቶስን አሳዳጆች አይደሉምን?

ዛሬ የዓለምሕዝብ ምን ያህሉ ይሆን በዚህ ሥራ የተጠመደ? ብዙዎቻችን አገር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ፣የኬሚካልና ባዮሎጂካል መሣሪያዎችን ጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች እያልን ስንቃወም እንኖራለን፡፡ ነገር ግን ትውልድ ገዳይ የትምህርት ፖሊሲዎችን፣ ልቅ የተለቀቁ ጎጂ መጤ ባህሎችን፣ ሰው ፈሪሃ እግዘአብሔር እንዳይኖረውና በራሱ ላይ ብቻ ተጣብቆ እንዲኖር የሚያስተምሩ ሙት የፍልስፍና መጻሕፍትን፤በፊልም፣በሬድዮ፣በኢንተርኔት የሚለቀቁ ልቅ የወሲብና የወንጀል ፊልሞችና ፕሮግራሞችን ወዘተ… እኒህ ሁሉትውልድ ጨራሽ መሣሪያዎች  የሚያሳስቡት ግን እጅግ ጥቂቶችን ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታ ሆይ አንተ ማነህ?›› ብሎ በጠየቀው ጥያቄ ታላቅ መልስ አግኝቷል፡፡

የጌታችን መልስ‹‹አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ›› የሚል ነበር፡፡ በዚህ መልስ ጌታችን ለቅዱስ ጳውሎስ የምዕመናን ስደት የእርሱ ስደት፤የክርስቲያኖች መከራና ስቃይ የእርሱ መከራና ስቃይ መሆኑን አስረድቶታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለተበደሉ የሚፈርድላቸው ለተገፉ የሚበቀልላቸው፤ ትዕቢተኞችን የሚያዋርድ የተዋረዱትን ደግሞ ክብር የሚሠጥ፤ የአቤልም ሆነ የቃየል አምላክ ሥራቸውንም የሚመዝንና ዋጋቸውን የሚከፍል በባህርዩ የማይሞት ሥልጣኑ የማይሻር ለግዛቱም ወሰን የሌለው የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ መሆኑን ከመልሱ ተረድቷል፡፡‹‹የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሃል›› የሚለው ማስጠንቀቂያ አጥንቱ ደርሶ ዘልቆ ሳውልን አርዶታል፡፡ዛሬም በመውጊያው ብረት ላይ የሚዘብት ብዙ አለ እስኪያዝ ድረስ፡፡

ወዳጄ! በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ብትቀመጥ፣ የሀብት ጫፍ ብትቆናጠጥ የዕውቀትን ማማ ብትረግጥ የሁሉ መጨረሻ አንድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለሥጋ እርካታ ይሆን እንደሁ እንጂ ነፍስህን ከተጠያቂነት አያስጥላትም፡፡


 

የዛሬን አያድርገውና ታላቅ የክርስቲያኖች መናገሻ የነበረችው አግያ ሶፍያን የመሰለ ታላቅ ቤተክርስቲያን የነበረባት ቁስጥንጥንያ የዛሬዋ ኢስታንቡል የሮማ ግዛት ሁለተኛዋ መናገሻ ነበረች፡፡ በአንድ ወቅት በግርማው የተፈራ በዝናው የከበረ በኋይሉ የታፈረ ታላቅ ቄሣር ዘውድ ጫነ፡፡ በዚህ በዓለ ንግስ ላይ መኳንንቱና መሳፍንቱ እንደየማዕረጋቸው ንግግር እያደረጉ ታማኝነታቸውን ይገልጡ ነበር፡፡ቤተክርስቲያንን በመወከል በጊዜው የነበረው ፓትሪያርክ ንግግር እንዲያደርግ ሲጋበዝ በዙፋኑ ላይ በታላቅ ግርማ ተቀምጦ ለነበረው ቄሣር እንዲህ አለ‹‹የዓለምን የሥልጣን ጫፍ ጨብጠሃል፤ መግደልም ሆነ ማዳን የሚችል ሰይፍ ታጥቀሃል፤ ካንተ በታች እንጂ ካንተ በላይ የሚታይ የለም፤ሁሉን ማድረግ እንደምትችል አንተ ታምናለህ እኛም ይመስለናል፤ግን ይህ ሁሉ እውነት ያይደለ ቅዠት ነው፡፡ምክንያቱም ያመንካቸው የሚክዱበት ወዳጆችህ የሚሸምቁበት ሰይፍ የጨበጠ ክንድህ የሚዝልበት ከሁሉ በላይ በሆንክባት ምድር ከሥሯ ተኝተህ ሁሉ ከበላይህ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል፡፡ አፈር ነህና ወደ አፈርም ትመለሳለህ!››

ማመናችን ወይም አለማመናችን የማይለውጠው የዘላለም እውነት ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ ከዚያ እውነት ጋር የምንገናኝበት ቅጽበት ለእያንዳንዳቸን ከጥላችን ይልቅ ቅርብ ነው፡፡በየትኛውም ቀንና ሰዓት ደቂቃና ሰኮንድ ያን እውነት በድንገት እንጋፈጠዋለን፤እጃችንን እንዘረጋለን ወደ ሚወደውም ይወስደናል፡፡ይኸውም‹‹ሞት››ነው፡፡ ልክ በዚያች ቅፅበት እንኳን በሌላው ላይ በራሳችን ላይ ያለን ሥልጣን ያበቃል፡፡በምድር ሳለን የተሠጠን ዕድል ለሞት መዘጋጀት እንጂ ሞትን ማስቀረት የሚችል አይደለም፡፡ከሞት ማዶ ከመቃብርም ወዲያ በዳይና ተበዳይን ገፊና ተገፊን ለመዳኘት ሥልጣን ያለው እውነትና ፍትህ የዙፋኑ ጌጥ የሆኑ‹‹የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ›› ያለው እርሱ ሁሉን ይጠብቃል፡፡ በዘላለማዊው ዳኛ ፊት በኃፍረት ወይም በሀሴት ለመቆም ውሳኔው ያለው በእጃችንየተሠጠንም ጊዜ አሁን ነው፡፡መለወጥ ከፈለግን መለወጥ ትችላለንና ይህተጽፎልናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ከሰማና የሆነበትን ካየ በኋላ ለመወሰን ያለው ጊዜ አሁንመሆኑን አውቋል ፡፡ኅሊናውን ማንበብ ቢከብድም ደግሞ ከጠየቀው ጥያቄ ቀድሞ የኖረበት እውነት መናዱንና አዲስ ለተገለጠበት እውነት ራሱን ምርኮ ለማድረግ መዘጋጀቱን ያሳያል፡፡ ማንም ሰው ቢሆን የለመደውን፤ረጅም ዕድሜ የኖረበትን፤ እውነት ነው ብሎ የተቀበለውን በቀላሉ መላቀቅ ይከብደዋል፡፡መክበድ ብቻ ሳይሆን ያስፈራዋል፡፡እንደ ታላቅ ሽንፈት ስለሚያየው እልህ ይጋባል፡፡ወደ ሕይወት መንገድ ለመምጣት የብዙዎች ችግር ይኸው ነው፡፡

ይልቁንም አንድ ቀን ከጌታ እግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት (የተለየመገለጥ) በራዕይ፣ በሕልም፣ በተዐምራት፣ በመከራ፣ በፈተና፣ በሞት… ወዘተ ሊሆን ይችላል ይዘነው የነበርነውን እውነት ይበልጥ ያጎላልናል ወይም የተከበርክበት እውቀት የደሰኮርከው ፍልሰፍና የሰበከው ስብከት የሞትክለት ሕይወት ባዶ መሆኑን ያሳይሃል፡፡

እውነት በባሕርይዋ እንደ እሳተ ገሞራ ያንቀላፋች ፍም ናት፡፡ጭምትነት፣ ገርነት፣ ራስን መሰወር፣በሒደት በመድመቅና ኃይሏን በመግለጥ፣ በዘመናት ውስጥ ሳትፋለስ ፀንታ በመቆየትም ትታወቃለች፡፡ ጊዜን መስላ አትገለጥም፡፡ጊዜያት ሁሉ የእርሷን መገለጥ አብሳሪ ታሪኳንም ዘካሪ ይሆናሉ እንጂ፡፡ አዝማናትን በመለወጥ እንጂ በመመሳሰል አትታወቅም፡፡ሁሉን ትማርካለች ሁሉን ትስባለች ለሁሉ ራሷን ትሰጣለች፡፡

ያወቋት በድካም ውስጥ ኃይልን፣በድንቁርና ውስጥ ጥበብን፣ በንድየት ውስጥ ብልጥግናን፣ በሞት ውስጥ ሕይወትን ያመልካሉ፡፡ ጠቢባንና አስተዋይ ነን ከሚሉ ተሰውራ ለሕጻናትና ለዚህ ዓለም ሞኞች የመገለጧ ምሥጢርም ይኸው ነው፡፡ ምርጫ እንጂ ሽርክና የእርሷ ፈሊጥ አይደለም፡፡ እርሷን የሚሹ ሁሉን ያጣሉ ከእርሷ የሚሸሹም የሚበልጠውን ያጣሉ፡፡ ያቺ ቀን ከባድ ናት የኖርክበት ሲናድ ሕይወትህን የሰጠህለት መና ሲሆን የምታይባት ቀን፡፡ያቺ ዓለም የዚህን ዓለም ሸቀጥ ሊያሳርፍ የሚችል ወደብ የላትም፤ቀድሞ ከዚያው የተሠጠህንና አክብረህ የያዝከውን ይዞ ከመሔድ በቀር፡፡

ጳውሎስ ተማረከ! ኃይሉ፣እውቀቱ፣ስሜቱ፣ ፍላጎቱ፣ የመኖር ዓላማው ወዘተ… ተማረከ፡፡‹‹ጌታ ሆይ ምን አደረግ ዘንድ ትወዳለህ?›› በሚል የእውነት መንፈስ ራሱን እስከወዲያኛው ሰጠ፡፡ የእርሱን ምኞት ቀብሮ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ኖረ፡፡ የዳግም                  ልደቱየሕይወት ፍልስፍና ‹‹ብንኖር ለክርስቶስ እንኖራን ብንሞትም ለክርስቶስ እንሞታለን›› የሚል ነበር፡፡

ጌታ እግዚአብሔር ሰውን በሁለት መንገድ ይማርካል፡፡ የመጀመሪያው በፍቅሩ ይማርካል፤በቃሉ ይጠራል በቸርነቱ በርኅራኄው ይጎበኛል፡፡ ሰምተው የመለሱለት ሕይወትን ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛው በኃይሉ በሥልጣኑ ይማርካል፡፡ ይህ ለሕይወት የሚሆንላቸው እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን ፍርድ የሚያገኛቸው ናቸው፡፡

ካለፈው የሕይወት ውጣ ውረድ ልምዳችን በመነሣት የጌታ እግዚአብሔርን ከኅሊና በላይ የሆነ ገናንነት በመረዳት ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ምርኮ አድርገን ብንሰጥ ሰማይና ምድር የሚዘክሩትን ሥራ በእኛ ይሠራል፡፡ስማችንም በሰማያዊው መቅደስ በሕይወት መጽሐፍ ይፃፋል፡፡በሕያዋን ምድር በበጉ ከተማ እንግዶችና መጻተኞች አንሆንም፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ነንና፡፡


 

ከሁለቱ የቤተክርስቲያን አዕናቁ ሕይወት በላዕላይ ዳሰሳ ይህን ከተማርን ከዘመኑ አንጻር አገልጋዩች ምን ሆነው (ታጥቀው) መገኘት ይኖርባቸዋል የሚለውን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

1.  በመንፈሳዊውም ሆነ በዘመናዊው እወቀት ሙሉ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡በመንፈሳዊው የቤተክርስቲያንን እውነተኛ አስተምህሮ በተጨማሪም የተቃዋሚዎችን አካሔድና አስተምህሮ ጠንቅቀው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በየዘመናቱ የተነሱ የሰው ልጅን አስተሳሰብ ያጣመሙ ወይም ያቃኑ ፍልስፍናዎችን መረዳትና በቂ መልስ(ሙግት) ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡በሳይንሱም በይበልጥ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለቸው በሕክምና፣በሥነ-ልቦና፣በማኅበራዊ ሳይንስ፣ ኪነጥበብ፣ ቴክኖሎጂ ወዘተ… ጋር ትውውቅ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ዛሬ የሰውን ጥያቄ ጹም ጸልይ በሚል ብቻ የምንመልስበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡ በክርስቲያኑ በእምነት የሚገለጡና በአመክንዮ የሚመለሱትን ለይተን ማሳወቅ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ምዕመናንም መንቃት ከልማድ መውጣት ይጠበቅብናል፡፡ ብዙዎቻችን ለቤተክርስቲያን ከጧፍ፣ከዕጣን ፣ከመጋረጃና ከምንጣፍ የዘለለ መባመስጠት አለመደብንም፡፡ ስንቶቻችን ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች በይበልጥ መንጋውን ለመጠበቅ ለሚደክሙ መጻሕፍትን፣ የትምህርት ዕድሎችን፣ የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣በጽሙና ሊያነቡ የሚችሉበትን ሥፍራ፣ እነርሱ ያለ ሀሳብ የቤተክርስቲያንን ሥራ እንዲሠሩ ለኑሮ የሚስፈልጋቸውን ወጪ፣ የመጻሐፍት የመጽሔትና የጋዜጣ ማዘጋጃ ወጪን የመሳሰሉት ስናመቻችና ስንደግፍ እንታያለን፡፡እኛ ብል ለሚበላው ምንጣፍ ስንጨነቅ ስንቶችን የኃጢአትና የክህደት ብል እንዳይበላቸውየሚጠብቅ እውቀት በከንቱ እየቀረ ነው፡፡በተጠናና  በተቀናጀ ስልት በሚዘረጋ የትምህርተ ወንጌል አደረጃጀት እንጂ በሠርክ ጉባዔ ስብከትና በበዓላት ድምቀት ብቻ ትውልዱን ይዘን እንቀጥላልን ማለት ከሞኝነት ያለፈ ዕብደት ነው፡፡ በተናጠልም ሆነ በኅበረት በመሆን አሥራት በማውጣት ወይም የተለየ በጀት በመመደብ አገልጋዮችን መደገፍ ከሚበልጠውየወንጌል ትሩፋት መሳተፍ ነው፡፡ የጥንቷ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ምዕመናን መለያ የአብነት ተማሪዎችንና መምህራንን መደገፍ መጻሕፍትን አጽፈው አስደጉሰው ለየአድባራቱና ገዳማቱ መስጠት ነበር፡፡

2.  የለውጥ አላማጆች(Activist) መሆን፡- በዓለም ታሪክ በተደረጉ የለውጥ ጉዞዎች፣የነጻነት ትግሎችና፣የሰው ልጆች ድኅንነት መጠበቅ የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎች ድርሻ ጉልህ ነበር፡፡ማሀተማ ጋንዲ፣ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ አቡነ ዴዝሞን ቱቱ፣ በሀገራችን ታሪክ ስንመጣ መንግሥታትን በማደራርና ደም መፋሰስን በማስቀረት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ተክለሃይማኖት፣የሃገርን ነጻነት በማስጠበቅ ጻድቁ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና የጎሬው አቡነ ሚካኤል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ዛሬም ካለን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሰው ልጆች ተፈጥሯዊም ሆነ ሕጋዊ መብቶች መከበር፣በተፈጥሮ ደኅንነት ጥበቃ፤በሀገራዊና ማኅበረሰባዊ  ጉዳዮች ቀዳሚ ወኪሎችና ተሟጋቾች መሆን ይጠበቅብናል፡፡በዘመናዊው አስተሳሰብ የፈላስፎች የፖለቲከኞችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ትልቁ ግብ ሕብረተሰቡን ከሃይማኖትና ከሃይማኖት አባቶች ምሪት ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖቱን የሚያጠብቅና የሃይማኖት አባቶቹን የሚያከብርና የሚከተልን ሕዝብ እንደፈለጉ መንዳት አይቻልምና፡፡ ሃይማኖትና የሃይማኖት አባቶች ለብዙ ሺህ ዓመታት ይዘውት የነበረውን ቦታ ፈላስፎች ፖለቲከኞችና የኪነ-ጥበብ ሰዎች መቆናጠጥ ይፈልጋሉ፡፡በምዕራቡ ዓለም የሆነውና በስኬት የተፈፀመው ይኸው ነው ፡፡ ሕብረተሰቡ በስልጣኔ ስም ላመነበት ሳይሆን ለተቀረፁለት ሥርዓት(system)ባርያ ሆኖ እየኖረ ያለው ለዚህ ነው፡፡በንግግር የሚጠቅሳቸው በኑሮ ዘይቤውም አብነት የሚያደርጋቸው እነዚህኑ ስለሆነ ከፍተኛ ለሆነ የሥነ-ምግባር ዝቅጠትና የሞራል ውድቀት ተደርጓል፡፡ሌላው ቀርቶ ከሰብአዊ ባህርይ እስከማፈንገጥ ደርሷል፡፡ምክንያቱ አርአያ(Icon) ከሚላቸው የሚያየውና የሚሠማው ቅንጦትን፣ ስግብግብነትን፣ዝሙትን፣ሰዶማዊነትን ወዘተ…ነው፡፡ይህ በእኛ እንዳይደገም ተጨባጭና ቀጥተኛ(Rational)በሆነ መንገድ የሚመክሩ የሚሞግቱና ተፅዕኖ የሚያሳድሩ በሕዝቡ የታመኑ የሃይማኖት አባቶች መሆን ይጠበቅብናል፡፡

ወደድንም ጠላንም በሕዝቡ ውስጥ ያለንን ቦታለመንጠቅ ያሰፈሰፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ እየተሳካላቸውም ነው፡፡ ለመመለስ ግን አሁንም አቅሙ አለን፡፡ሕዝቡ የሚፈልገው በእኛ እርግጠኛ መሆንን ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ልንሠጠው ያልቻልነው ያን ነው፡፡በየትኛውም ዘርፍ ሕዝቡ ከኋላ ሆኖ የሚገፋው ሳይሆን ከፊት ሆኖ የሚመራው፣ለዓላማው እንዲሞት የሚሰብከው ሳይሆን ሞትን ተጋፍጦ የሚያሳየው መሪ ይፈልጋል፡፡ለዚህ ደግሞ ከመንፈሳዊ መሪዎች የቀረበ የለም፡፡

በበጎ አድራጎት ሥራ ቤተክርስቲያንና የሃይማኖት አባቶች ፊትአውራሪ መሆን ሲጠበቅብን ከእኛ ይልቅ እየተሠራ ያለው በጎ ኅሊና በቀሰቀሰላቸው ሰው መሆን ግድ ባላቸው ምዕመናን ነው፡፡መቅደም ሲገባን ተቀድመናል፣ እንኳ ለመምራት ለመመራትም በምናስቸግርበት ሁኔታ ላይ መገኘታችን ምንኛ አሳዛኝ ነው፡፡

ሕዝቡ ግን አሁንም ከሃይማኖት አባቶች ጉያ ላለመውጣት ያለው ምኞት ትንሽ በሚንቀሳቀሱ አባቶች(እውነተኞች ወይም አስመሳዮች)ሥር ከሚያሳየው ተስፋን ያዘለ መሰባሰብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ልንሠራ ነገሮችን ልንለውጥ የምንችልበት ቀን ሳይጨልም መንቃት የእኛ ፋንታ ነው፡፡


 

3.  ጽናት፡- ኅብረተሰቡ በተለያየ ችግር ምክንያት ቅስሙ ተሰብሯል፡፡የኢኮኖሚ ቀውስ፣ሥራ አጥነት፣ጦርነት፣ ያልተገለጠ የየማጀቱ ረሃብ ወዘተ… አድቅቆታል፡፡ከዚህ ሁሉ መጽናኛው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡እግዚአብሔርን እንዳገኘ የሚሰማው ደግሞ የሃይማኖት አባቶቹን ሲያገኝ ነው፡፡

በመሆኑም አገልጋዮች ከችግር ይልቅ መፍትሔ ላይ የሚያተኩሩ ለየትኛውም አስጨናቂ ሁኔታ የማይበገሩ መንፈስ ጽኑ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምድር የሥነ-ልቦና አማካሪዎች አይታወቁም፡፡ አሁን እንኳ በተለያዩ ቦታዎች የተከፈቱ የምክር አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ቢኖሩም፤በሚዲያም በነጻ ምክር የሚሠጡ ፕሮግራሞች ቢተላለፉም የሕዝቡ ቀዳሚ ምርጫ ግን አሁንም የሃይማኖት አባቶቹ ካህናት ናቸው፡፡ምክንያቱም፡-

ሀ. የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብና በችግር ወቅት ጠባዩን እንዳይቀይር እያበረታቱ፤በጦርነት በመከራ ጊዜ ወኔው እንዳይከዳው  እያጠነከሩ ይዘውት ከኖሩ ካህናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው፡፡ በሥጋ ከወለዱት ወላጆቹ ይልቅ ያከብራቸዋል፡፡ ስለዚህ እነርሱ አጠገብ በመገኘቱ ብቻ የሚሰማው ደኅንነት ሌሎች ባለሞያዎች ጋር አይሰማውም፡፡

      ለ. በኢትዮጵያ ምድር አሁንም ቢሆን ሳይንስ በሃይማኖት ላይ የበላይ ለመሆን ስላልቻለና ሕዝቡ እምነቱን ስላልጣለበት ፡፡

      ሐ. ለምሥጢር ትልቅ ግምት የሚሠጠው ሕዝባችን ካህናቱ ዘንድ ምሥጢሩ እንደሚጠበቅለት እርግጠኛ በመሆኑና፤ ይህንንም ከእግዚአብሔር እንደተሠጠው ዋስትና ስለሚቆጥር፤ ከባለሞያዎቹ ጋር ግን ይህ ልምድ ስለሌለውና በመካከላቸውም የምሥጢሩን ድኅንነት የሚያስጠብቅ ዋስትና አለ ብሎ ስለማያምን

መ.ትልቁና ዋነኛው ሕዝቡችግሩን ለካህናቱ ሲነግር ለእግዚአብሔር እንደነገረ ፍፁም ስለሚያምን፤ለሥነ-ልቦና ባለሞያዎች መንገርን ግን ለአንድ ተራ ሰው ችግራችንን ነግረን ከምንጠብቀው ምላሽ የተለየ ስለማይጠብቅ(ካህናቱ ዘንድ ጸሎት፣ ሱባዔ፣ሥልጣን፣ተዐምራት፣መለኮታዊ ኃይል ወዘተ… አለ ብሎ ማመኑ፤ ሌሎቹ ጋር ግን የተለየ ነገር ስለማይጠብቅ)

ሠ.በሕይወት ልምዱ ብዙዎች ለካህናት ነግረው ችግራቸው እንደተፈታ ምስክርነት ስለሚሰማና በአንፃሩ በሥነ-ልቦና አማካሪዎች ዘንድ ስላለው መረጃ ስለሌለው፡፡

ረ.ሕዝቡ(ምዕመኑ) ካህናት ጋር ለምድራዊ ሕይወት መረጋጋትን ለነፍሱ ደግም ሥርየትን ሽቶ እንደመምጣቱ፤ የሥነ-ልቦና ባሞያዎች ጋር የዚህ ዓይነት አገልግሎት እንደማይገኝ ማወቁ ወዘተ…

ስለዚህ ካህናት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሀዘኑ አፅናኝ፣ የደስታው ባራኪ፣የችግሩ አጋር፣የጭንቀቱ መተንፈሻ፣የነፍሱ ምሥጢረኛ እንደመሆናችን ችግርን የሚረግጥ ጽናት ተስፋ መቁረጥን የሚሰብር ጥርካሬ ከእኛ ይጠበቃል፡፡ድቡሽት ላይ ቆሞ ረግረግ ውስጥ ያለን ማውጣት እንደማይቻል፤ ለችግር በቀላሉ እጅ የምንሠጥ ሆነን ሌሎችን መርዳት አይቻለንም፡፡

4.  መንፈሳዊነት፡- መንፈሳዊነት ስል የተገለጠ የሚሠራ የማስመሰል ያልሆነ ማለት ነው፡፡ ይልቁንም ዛሬ ብዙዎቻችን ለመንፈሳዊነት የምንሠጠው ግምት አናሳ ሆኗል፡፡ከመንፈሳዊነት ይልቅ ዘመናዊነት(በተንሸዋረረ ትርጉም) ማርኮናል፡፡ሕዝቡም የኸው ደዌ ተጋብቶበት የእኔ አባት እኮ ዘመናዊ ናቸው ሲል ይደመጣል፡፡የሚጠቅመን ግን ዘመናዊ ሳይሆን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡

ላያችን ቢመስለውም ውስጣችን የሚፈልገው ግን ሌላ ነው፡፡ የድሮው የአበው የአነጋገር ለዛ፣ በጨዋታቸው ያለ ቅኔ፣ በነገራቸው ውስጥ ያለ ምሥጢር፣ ከእርጋታቸው የሚፈስ ግርማ ሞገስ ይናፍቀናል፡፡አብሯቸው የኖረ መስቀላቸው፣ ወዝ የጠገበ ዳዊታቸው፣ ዕጣን ያወደው ቀሚስና ካባቸው፣ ንባብና እንቅልፍ ማጣት ያፈዘዘው ዓይናቸው ብዙ ይነግረን ነበር፡፡

ቀደምት አበው ከሕዝቡ ሳይለዩ ሕዝቡንም ሳይመስሉ ይዘውት ኖሩ፤ዛሬ ሕዝቡን መስለን ከሕዝቡ ተለይተን ይዘነው ጠፋን፡፡ትዝታ ምንኛ ደግ ነው፡፡ቢያንስ ዛሬን በትናንት እንታዘበዋለን፡፡ዛሬ እንመገበው ስናጣ የኋሊት ተመልሰን በትናንት እንጠግባለን፡፡

ይብላኝ ትናንትን ለማያውቅ ትዝታ ለሌለው፤

ድሮ እኮ እንዲህ ነበር ብሎ ማውራት ለማይችለው፡፡

ሐዋርያነት ትናንትን ከዛሬ ዛሬን ከዘላለም ጋር ማገናኘት ማዋሐድነው፤ እንደ ሁለቱ የዓለም ብርሃናት፡፡ ለተረዳው ላወቀበት ለኖረበት ለሞተለት!!!

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስ ጸጋና በረከታቸው ድል የማይነሣ ጽኑ እምነታቸው በሁላችን ላይ ይደርብን!አሜን!

ቀሲስ ታምራት ውቤ

ሐምሌ 2005 ዓ.ም

                      መታሰቢያነቱ ፡- በፈቱት ምላስ ለሚሰደቡ ባስተማሯቸው ለሚናቁ ለነ የኔታ፤ ለነበሩ ላሉ ለሚኖሩ ትሁን፡፡

Read more...
Subscribe to this RSS feed

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ