Login
Main menu

ጰራቅሊጦስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

ጰራቅሊጦስ የሚለው ቃል የጽርዕ ሲሆን ‹‹የቅርብ ረዳት፤በአጠገብ ሆኖ የሚያፅናና የሚያረጋጋ›› የሚለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ይህ መጠሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ከተጠራባቸው ስሞች አንዱ ነው፡፡

     ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለዓለም ከገለጠና ምሥጢረ መንግሥትን ሦስት ዓመት ለሐዋርያት ሲያስተምር ከቆየ በኋላ ጊዜው እንደደረሰ አውቆ ለሐዋርያት ከእነርሱ ተለይቶ እንደሚሔድ ነግሯቸው ነበር፡፡ በእርግጥ ሐዋርያት ተላልፎ የመሠጠቱንና የሞቱን ነገር ደጋግመው ሲሰሙት የነበረ ቢሆንም የተቆረጠው ቀን መድረሱን ሲረዱ ግን ከፍተኛ ድንጋጤ ወደቀባቸው፡፡

     በዚህ ጊዜ ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ እሔዳለሁ ስላችሁ ደስ ሊላችሁ ይገባል፤እኔ ካልሔድኩ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና ያላቸው፡፡ ጌታችን የሐዋርያትን መደንገጥ ማዘንና መሸበር ሲያይ መንፈስ ቅዱስ ወደ እነርሱ የሚመጣው ሊያረጋጋቸውና ሊጽናናቸው መሆኑን አብስሯቸዋል፡፡ ያድርባችኋል በውስጣችሁም ይኖራል እርሱም ዓለም ሊቀበለውና ሊያውቀው የማይችል የእውነት መንፈስ ነው በማለትም አስረድቷቸዋል፡፡

     የክብር ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነሥቶ ከተነሳ በኋላ

በ$ኛው ቀን ሲያርግ ‹‹አብ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› በማለት ተስፋን ሰጥቷቸው ሄዷል፡፡ ከአሥር ቀን በኋላም እንደ ቃሉ ተፈጽሟል፡፡ ሉቃ 24፥49

     መጀመሪያ በሐዋርያት ለጥቆም በምዕመናን ላይ መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው ስንል ሀብቱ ጸጋው ኃይሉ ማለታችን እንጂ በአካል በእነርሱ አደረ ለማለት አይደለም፡፡ያደረባቸው ሰዎች በሚያሠራቸው ሥራ ተገልጠው ይታወቃሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስየሚሠራው ሥራ የሚሰጠውም ኋይልና ጸጋ በዓለም ባለ የትኛውም ጥበብ፣ ሀብትና ሥልጣን ሊገኝ(ሊሠራ) ፈጽሞ የማይችል ነው፡፡

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ባደረባቸው ጊዜ ከብልየት ታደሱ በአዕምሮ ጎለመሱ፤ ፍሩሃን የነበሩ ጥቡዓን ሆኑ፡፡አንዲት ቋንቋ ብቻ ይናገሩ የነበሩ  ፸፩ቋንቋ ገለጠላቸው፡፡ መተርጉማን ስለምን ቋንቋው ፸፪ሆነቢሉ በጊዜው በዓለም ይነገር የነበረ ቋንቋ(ልሳን) ይኸው ነበርና ለዓለም ሁሉ ወንጌል መንግሥትን ይገልጡ ዘንድ ፈቃዱ መሆኑን ሊያጠይቅ ነው ይላሉ፡፡ የሐዋ.ሥራ 2፥1-ፍጻሜ

     ከዚህም በተጨማሪ መጻሕፍትን ከገበታ እስከ ገበታ አወቁ ምሥጢር ተገለጠላቸው፤ ትንቢተ ነቢያትን እነርሳቸውን መስለውና ተካክለው ተረዷቸው ተረጎሟቸው አመሰጠሯቸው፡፡ጌታችን የትምህርታቸውን(የቃላቸውን)ደገኛነትም በሚከተሏቸው የተለያዩ ምልክቶች አጸናላቸው፡፡ ያመኑትን ድውያንን ፈወሱ ሙታንን አነሱ፡፡ለወንጌል እንቅፋት የሆኑባቸውን በተግሳጽ በመቅሰፍት ከመንገድ አስወገዱ፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ሀብት ጸጋና ኃይል በየትኛውም ምድራዊ ኃይል፣ ሥልጣን፣ጥበብና ብልጥግና ሊገኝ የማይችል ከላይ(ከአርያም)ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ ማር 16፥17፤የሐዋ.ሥራ 3-6፤የሐዋ.ሥራ 13፥7-12

     ለመግቢያ ያህል ይህን ካልን ጰራቅሊጦስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡ ጰራቅሊጦስ ማለት፡-

1. መጽንዒ ወይም የሚያጸና ማለት ነው፡፡ሐዋርያት ወንጌል መንግሥትን ለመስበክ የወጡት መልእክታቸውን አሜን ወአሜን ብሎ ለመቀበል በናፍቆት ወደ ሚጠብቅ ሕዝብ አይደለም፡፡ ይልቁንም በጥላቻ በተመረዙ አይሁድና በጣዖት አምልኮ በደነዘዙ አሕዛብ መካከል ነው፡፡

     የክርስትና አስተምህሮ በወቅቱ ከነበረው የዓለም ኅብረተሰብ ባህልና አኗኗር ጋር የብርሃንና የጨለማ ያህል መራራቅ ነበረው፡፡በመሆኑም አይሁድን ሥርዓተ ኦሪትን አሕዛብን ልማደ ጣዖትን ለማስጣል ሲወጡ ብዙ ግፍንና መከራን ተቀብለዋል፡፡ጌታችን እንዳላቸው ኃይልን ሳይቀበሉ ለስብከት ወጥተው ቢሆን ኖሮ መንፈስ ቅዱስ ባላደረበት ሰውነታቸው መከራ ቢያጸኑባቸው ፈጥነው ይክዱ ነበር፡፡ስለዚህ የሚመጣውን ለመቀበል መጨከን እንዲችሉ የሚያጸና መንፈስ ቅዱስ አድሮባቸዋል፡፡

     አበው መንፈስ ቅዱስ ስለምን በእሳት አምሳል ታያቸው የሚለውን ሲተረጉሙ፤በእሳት የተቃጠለ(እሳት የነካው)መሬት ለአዝርዕት ለአትክልት እንዲመች መንፈስ ቅዱስ ያደረበትም ሰውነት ለገድል ለትሩፋት የተመቸ ነው፡፡አንድም ሸክላ ሠሪ ሸክላ ሠርታ በእሳት ተኩሳ እንደምታጸናው መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ጽኑ ነውና ይላሉ፡፡

     መንፈስ ቅዱስ ባያድርባቸው ኖሮ ነቢያት በትንቢት ሐዋርያት በስብከት፣ሰማዕታት በደም ጻድቃን በገዳም ፀንተው ለመገኘት ባልተቻላቸውም ነበር፡፡

2. መንጽሒ፡-የሚያነጻ ማለት ነው፡፡ሰው ኃጢአት ሢሠራ የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስለው መልኩ ይበላሻል ባህርዩ የጎሰቁላል ጠባዩም ያድፋል፡፡በሠራነው ተጸጽተን ንስሐ ገብተንና በካህኑ የተሰጠንን ቅኖና ፈጽመን ካህኑ ከሚያደርሰው ጸሎት ጀምሮ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እስከ መቀበል ድረስ የኃጢአት ሥርየታችን የሚከናወነው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

እሳት ብረት ቢሉ ዝገቱን ወርቅ ቢሉ ዕድፉን አስወግዶ የቀደመ የተፈጥሮ ባህርያቸውን እንደሚያሲዛቸው እኛም በኃጢአት ምክንያት የጠፋ መልካችን ያደፈ ጠባያችን የጎሰቆለ ባህርያችን ነጽቶና ታድሶ ወደ ክቡር(ማንነቱ)የሚመለስ በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

     እመቤታችን በተለየ አካሉ አግዚአብሔር ወልድን ጸንሳ ለመውለድ እንድትችል ጥንት በአበው ባሕሪይ በማዕከል በማኅፀነ ሐና ኋላም በሕልውና ሳለች ንፅህት አድርጎ የጠበቃት ያዘጋጃት ያበቃት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ያነጻ የከፈለ ያዋሀደ መንፈስ ቅዱስ ነው እንዲሉ ሊቃውንት፡፡

3. ናዛዚ፡- የሚያፅናና ማለት ነው፡፡ በዚህ መከራ በበዛበት ዓለም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በመልካም ሥራ በመትጋት በአብ ኅሊና ታስበው ያሉት በዚህ ዓለም በሚደርስባቸው መከራሲያዝኑና ሲተክዙ የሚያፅናናቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡

     በመግቢያው እንዳየነው የሚያጽናና ስንል የቅርብ ረዳት የመንገዳችን ደጋፊ የነፍሳችንን ሲቃ አዳማጭ የማይለይ ታዳጊ ማለታችን እንጂ ተራ ደርሶ ሒያጅ አጽናኝ ማለት አይደለም፡፡በዓለም የሚወድቅብንን ሀዘንና ሰቆቃ ሁሉ ድል አንድንነሳው የሚያደርገን እርሱ የቅርብ አረጋጊ አጽናኛችን በመሆኑ ነው፡፡

     የቅዱሳን ሀዘን ራበኝ ጠማኝ ሀብት ንብረት ጠፋብኝ ወረት አነሰኝ ዘመድ ወገን ሞተብኝ ብለው አይደለም፡፡ ፍትሕ ሲጓደል ድሃ ሲበደል፤ እውነት ስትኮስስ ሀሰት ሲነግስ፤ የአዳም ዘር ፍርድ እንዳለ ዘንግቶ በኃጢአት በበደል ሲረክስ፤ ጻድቃንሲበደሉ ኃጥአን በምቾት በቅንጦት ሲደላደሉ ሲያዩ አምርረው ያዝናሉ፡፡ይልቁንም በቤተ እግዚአብሔር እውነተኞች መምህራን በግፍ ሲባረሩ መናፍቃንና ለመንጋው የማይራሩ ምንደኞች ሲከበሩ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲጣስ ሥርዓት ሲፈርስ፤ ከጽድቅ ይልቅ የግብዝነት ካባ ሲደረብ ሲመለከቱ ልባቸው በሀዘን ነፍሳቸው በምሬት ይቆስላል፡፡

     በዚህ ጊዜ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በማይመረመር ፍርዱ የደሀን ደም ሲበቀል ፍትሕን ሲተክል፤እውነትን ሲያነግስና ሀሰትን ሲደመስስ፤ በኃጢአት የከበሩ ሲዋረዱ ስለጽድቅ የተዋረዱት ሲከብሩ ፤ በኃጢአት በክህደት የተያዘውንም ሕዝብ በመጽሐፍት በመምህራን አንደበት መክሮና አስተምሮ ሲመልስ፤ በቤቱም እውነተኞቹን መምህራን አስነስቶ መናፍቃንና ምንደኞን ለይቶ አውጥቶ ሥርዓትንሲመልስ አምልኮተ እግዚአብሔር በግብዝነት ሳይሆን በእውነትና በመንፈስ ሲሆን ሲመለከቱ የቅዱሳን ልባቸው ይታደሳል ነፍሳቸው ይጽናናል፡፡ ይህም በዘመናት ሁሉ የታየ በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በታሪክ መጻሕፍት የተዘገበ ነው፡፡በፍርዱ ቅዱሳንን ያጽናናል ግፈኞችን ደግሞ እንደሥራቸው ጽዋቸውን ይግታቸዋል፡፡ የእመቤታችንንና የሐና እመ ሳሙኤልን ጸሎት ልብ ይሏል፡፡ ሉቃ 1፥46-ፍጻሜ፤ 1ኛ ሳሙ 2፥1-10

 


 

4. አራኃዊየሚከፍትማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ኢየሱስን ጌታ(የሕያው እግዚብሔር ልጅ፤አምላክ ወልደ አምላክ ሊል የሚችል የለም፤ እንዳለ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተገለጠ እርሱን ዓለማትን ካለመኖር ወደ መኖር የመጣ መጀመሪያውና መጨረሻው የሆነ አምላክ ብሎ ማመን በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ ከባድ ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 12፥3

     የተመሰገነው ሐዋርያ‹‹በወንጌል አላፍርም››ማለት ወረደ ተወለደ እንደ ሰው ተመላለሰ፤ ተገረፈ ተሰቀለ ሞተ ተነሳ ዐረገ ብዬ በማመንና በማስተማር አላፍርም ያለ ለዚህ ነው፡፡ሰዎች አምላክ ብለው በኅሊናቸው የሳሉትና የጌታችን ትሑት ሆኖ በመካከላችን መገለጥ በቀላሉ ለመቀበል የሚቸግር ነውና፡፡ ሮሜ 1፥16

     በሐዋርያት ሥራ ሐር ሻጭዋ ልድያ ሰለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጳውሎስ የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት ተብሎ የተጻፈ ለዚህ ነው፡፡ የሐዋ.  ሥራ 16÷14-15 የእግዚአብሄርን ቃል  ሰምተን መንፈሳዊ ፍሬ የማይታይብን ከሆነ ምክንያቱ የልብ አለመከፈት ነው፡፡ ቃሉን ሲሰማ ልቡ የተከፈተ ሰው ወዲያው ምን ላድርግ ብሎ ይጠይቃል ለንስሐም ቀጠሮ አይሰጥም ወደ ጥንት ኑሮውም አይመለስም፡፡

     መንፈሳዊ ሥራን ለመሥራት ወንጌልንም ለመስበክ ጽኑ መሻታችንን ዓይቶ ሁሉን የሚያመቻች ማሕየዊ(ሕይወትን የሚሰጥ) መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡በራዕይ ‹‹ሥራህን አውቃለሁ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም›› በማለት በፍልድልፍያ ላለች ቤተክርስቲያን አለቃ ታላቃ የወንጌል ሥራ ከፊቱ እንዳኖረለት የነገረው የልብ መሻትን አይቶ ሁሉን የሚያመቻች እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ ራዕ 3፥7-8

5. መስተፍሥሒ ማለት ደስ የሚያሰኝ ደስታን የሚመላ ማለት ነው፡፡ደስታ ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ይህ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ በመብልና በመጠጥ በመሾምና በመሸለም እንደሚገኘው ዓይነት ጊዜያዊ ደስታ ወይም በኃጢአት የሚሆን ፍርድና ሀዘን የሚከተለው ደስታ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ደስታ ማለት እግዚአብሔርን በመፈለግና በመከተል፤በቅድስናው ሥፍራ ተገኝቶ በእምነት በእውነት ሆኖ በማምለክ በመድኀኒታችን የማዳን ሥራ፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ትርጉም ያለው ግንኙነት፤ ወንጌል ሲሰበክና ሰዎች ወደ ድኅነት ሲቀርቡ ወዘተ. . .እኒህንና እኒህን በመሳሰሉት ነው፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ መንግስተ ሰማያት አዋቂዎች ነን በሚሉ ጻፎችና ፈሪሳዊያን ሳይታወቅ በመንፈሳቸው እንደሕጻናት የዋህ ለሆኑ ሐዋርያት ስለተገለጸላቸው. . . በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አደረገ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ሉቃ 10፥21

     ሌላው መሐሪና ይቅር ባይ፤ ስመ ድኅነትና ስመ ሥርዓት ስለሆነው ስሙ መከራን ለመቀበል የተገቡ ሆነው ስለተገኙ ሐዋርያት ሐሴት ያደርጉ ነበር፤ደስታ ይሉሀል በሰማዕትነት ሥቃይ ውስጥ ሆነን ራሳችንን ለክርስቶስ አሳልፈን በመስጠታችንና ከእርሱ ጋር ለመሞት ስለተመረጥን የሚሰማን ደስታ ነው፡፡ በዚህ ዓለም በመንፈስ ቅዱስ ሀሴት ስለማድረግ ካሰብን ከዚህ የሚበልጥ ደስታ የለም፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚያዘጋጅ የሚያበቃ በዓለም ከሚሆን ደስታም የሚለይ ስለሆነ ነው ጌታ መንፈስ ቅዱስ መስተፍሥሂ የተባለው፡፡ ማቴ 5፥11-12፤የሐዋ.ሥራ 5፥40-42

አንድም በዚህ ዓለም ያለን መከራ አልፈን በሃይማኖት ጸንተን በትሩፋት ሥራ ከብረን ከሥጋ ርስት ስንለይ በዘላለም ቤት የዚህን ዓለም መከራ እስክንረሳ በሚያደርስ ደስታ ያኖረናል መስተፈስሂ ይባላል፡፡ ራዕ 14፥13፤ሮሜ 8፥18

6. ከሣቲ፡-ሕይወትን የሚሰጥ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ደስ ለሚያሰኙት ወዳጆቹ ብዙ ነገር የተለያየ ምሥጢርን እንደየዐቅማቸው ይገልጥላቸዋል፡፡ ከቀድሞ ጀምሮ አካላዊ ቃል ዓለምን ለማዳን ከድንግል እንደሚወለድ ለነቢያት የገለጠ በእነርሱም አድሮ ለዓለም ያስተማረ እርሱ ነው፡፡ ‹‹ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማሕየዊ ዘሠረፀ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት…›› እንዲል ጸሎተ ሃይማኖት፡፡

     የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትም መንፈስ ቅዱስ ያላደረበት አእምሮ ሊረዳው አይችልም፡፡ዓለም ይህንኑ(ነገረ ሥጋዌን) በተለያየ ፍልስፍናና አስተሳሰብ ለመተንተን እየሞከረ በስህተት ገደል የሚወድቅ ለዚህ ነው፡፡ስምዖን ጴጥሮስ በፊሊጶስ ቂሣርያ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ ሲመሰክር ጌታ መልሶ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጠልህም የሰማዩ አባቴ እንጂ(አሐቲ ሥምረት መሆኑን ልብ ይሏል) በማለት የነገረው፤ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጦ የታየ ጌታችንን አምላክ ወልደ አምላክ ብሎ ማመን ለሥጋዊአእምሮ ጠጣር በመሆኑ ነው፡፡

     ሐዋርያት ምሥጢረ መንግስትን እንዲያውቁ የሙሴና የነቢያት መጻሕፍትን ሁሉ እንዲያስተውሉና እንዲተረጉሙ በአጠቃላይ ሰማያዊ የሆነውን እውቀት ሁሉ የገለጠላቸው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ቅ.ጳውሎስ ‹‹…እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም፡፡እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዘብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም፡፡›› ብሏል ጨምሮም ‹‹ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታወቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ››በማለት ምስጢር ገላጭ የሆነ እርሱ ብቻ መሆኑን አሳውቋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ትንቢት መናገርም ሆነ ትንቢትን መተርጎም ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ሲያስረዳ‹‹ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤በመጽሐፍ ያለው ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፡፡ 2ጴጥ1÷20-21፤1ቆሮ2÷11-12፤ ኤፌ6÷19

ሰዎች በትዕቢት ሲያዙ ደግሞ የሚያነቡትን እንዳያስተውሉ ምሥጢርን ይሰውራል፡፡ ሐዋርያት ጌታችንን ለምን በምሳሌ እንደሚያስተምር ሲጠይቁት ‹‹ለእናንተ የመንግስተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም››ያለ ይህን ለማመልከት ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎስም‹‹ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው፡፡››ብሏል፡፡በቆሮንቶስ መልእክቱም ዓለም በጥበቧና በምርምሯ እግዚአብሔርን ለማወቅ እንዳልቻለች በተብራራ ሁኔታ ተገልጿል:: ማቴ13፥10-11፤ 1ቆሮ1÷18-27፤2ቆሮ4÷3 ስለዚህ ከትዕቢተኞች ምሥጢር የሚሰውር መንፈስ ቅዱስ ለትኁታን ደግሞ ስለሚገልጥ ከሣቲ ተብሏል፡፡

7. አለባዊ ማለት ማስተዋልን የሚሰጥ ማለት ነው፡፡ሰዎች ጌታ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ሳያከብሩት ሲቀሩና ኃጢአት መሥራት ሲደፋፈሩ ለማይረባ ከንቱ አእምሮ ተላልፈው ይሰጣሉ፡፡ከንቱ አእምሮ ማለት ማስተዋል የተሳነው ለመምረጥ ለመወሰን በሚሰራውም ነገር የሚጠብቀውን ውጤት(ፍርድ) ለመረዳት የተዘጋበት፤ ምክር የማይሰማና ተግሳጽ የማይቀበል ማለት ነው፡፡

     ማስተዋል የተነሳቸው ለከንቱ አእምሮ ተላልፈው የተሰጡ ሰዎች የጌታ እግዚአብሔርን መኖር ይክዳሉ በግብራቸውም ከእንስሳት አንሰው ይታያሉ፡፡‹‹ልብ እንደሌላቸው እንስሳት ሆኑ››ያለው መጽሐፉ እንደነዚህ ያሉትን ነው፡፡በነቢዩ በኢሳይያስ‹‹ሂድ ይህን ሕዝብ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው›› በሚል ጠባያቸው ተገልጿል፡፡ ኢሳ 6፥9፤ሮሜ 1፥20-28

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ እውቀት በማጣት ጨለማ ላለ ሕዝብ እግዚአብሄርን የማወቅ ብርሃንን እንዲያይ ማስተዋልን ይሰጣል፡፡ዮሐንስ መጥምቅ ጌታችንን አያውቀው እንደነበርና ለእርሱም የገለጠለት መንፈስ ቅዱስ እንሆነ መስክሯል፡፡ዮሐ1÷3

ጌታችን ሐዋርያትን ብዙ ነገር ከነገራቸው በኋላ ከዚያም በላይ ሊነግራቸው ይችል እንደነበር እነርሱ ግን በነበሩበት ደረጃ ቢነግራቸው ለማስተዋል እንደማይችሉ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ግን እንደሚመራቸው (ማስተዋልን እንደሚሰጣቸው) እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፤‹‹የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡ ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል…ዩሐ16÷12-13 ቤተክርስቲያን በቸርነቱ እየጠበቀ በምግብናው የሚመራት ጌታ መንፈስ ቅዱስን‹‹ሀበነ እግዚኦ አዕይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ ወአዕዛንነሂ ቃለ ዘባህቲትከ ይስምዓ››ስትል በጸሎቷ ትማልላለች፡፡ዓይነ ሥጋችን ግዙፉን ዓይነ ልቡናችን ረቂቁን፤አንድም ዓይነ ሥጋችን ሥነ ፍጥረትህን በማየት ዓይነ ልቡናችን ቸርነትህን ምህረትህን መግቦትህን በማስተዋል አንተን ብቻ ማየት(ማምለክ) እንድችል፤ዕዝነ ሥጋችንና ዕዝነ ልቦናችንምሕይወት የሆነ ያንተን ቃል ብቻ መስማት ይችል ዘንድ አቤቱ ስጠን ስትል ነው፡፡

     ካለ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ጥበብን ይልቁንም መንፈሳዊ ጥበብን(ምሥጢርን) ገንዘብ አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ነው፡፡የጠቢባንን ምክር የአዋቂዎችንም ማስተዋል የሚያስረሳቸው እርሱ በትኅትና በየዋህነት ደጅ ለሚጠኑ ሁሉ ግን ማስተዋልን ይሰጣል፤ፈቃዱ እንዱሁ ነውና፡፡


 

8. መስተናግር ማለት ሃይማኖትን፣ የጥበብን ቃል፣ ምሥጢርን የሚያናግር የሚያስተረጉም ማለት ነው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሀምሳ በአይሁድ መካከል ቆሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ቢናገር በአንድ ጊዜ ስብከት ሦስት ሺ ሰዎች ማሳመን ችሏል፡፡ ይህ የሆነው ከቅዱስ ጴጥሮስ ዝግጅት ሳይሆን ‹‹ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል›› ብለው ሲያሙ ለነበሩ አይሁድ የተሰጠ የመንፈስ ቅዱስ መልስ ነበር፡፡ቅዱስ ጳውሎስ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል፡፡ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል…ለአንዱም ትንቢትን መናገር…ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር…ይሰጠዋል››ሲል የመንፈስ ቅዱስን የማናገር ኃይል አብራርቷል፡፡እንግዲህ በዋናነት መንፈስ ቅዱስን መስተናግር(የሚያናግር)ስንል፡-

ሀ. ሀብተ ትንቢትን ሰጥቶ ኃላፍያትን መጻእያትን የሚያናግር

ለ.የጠፋውን ለመመለስ የጠመመውን ለማቅናት የጥበብን ቃል የሚሰጥ(የሚያናግር)

ሐ.የሃይማኖትን ቃል ለማቅናት እውቀትን(ምሥጢር በመተርጎም) የሚናገር

መ.ለእያንዳንዱ ነገድና ሕዝብ ቋንቋውን ተናጋሪ ኅብረተሰብን መስሎና ተካክሎ መናገር ማለት ነው፡፡ 1ኛ ቆሮ 12፥4-11

ከዚህ የሚልቀው ደግሞ እነሆ፡-

‹‹ለእርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወስዳላችሁ፤አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁም››ማቴ 10፥18-20

ጌታችን በሰማዕትነት ሰዓት ከነገሥታቱና ከጠቢባኑ በእኛ ያለውን እውነትና ተስፋ ለማስተሐቀር እንዲሁም በሀይማኖታችን ለመዘበት ለሚያነሱት ጥያቄና ክርክር እንዳንጨነቅ በዚያኑ ሰዓት በእኛ ውስጥ ያለ ጌታ መንፈስ ቅዱስ የምንናገረውንና ተከራካሪዎቻችንን የምናሳፍርበትን ቃል እንደሚሰጠን የተናገረው ማረጋገጫ ነው፡፡

9. መስተሥርዪ፡-መንፈስ ቅዱስ መስተሥርዪ ይባላል፡፡ኃጢአትን የሚያርቅ የሚያስወግድ የሚደመስስ ማለት ነው፡፡መንፈስ ቅዱ በአርባ በሰማንያ ከተጠመቅንበትና ከሥላሴ ልጅነትን ካገኘንበት ቀን ጀምሮ በእኛ ያድራል፡፡ሃይማኖትን ካልካድን በስተቀር አይለየንም፡፡ይህን ሲያይ ነው ቅዱስጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?›› ያለው፡፡ 1ኛ ቆሮ 3፥16

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአታችንን ሊሽር በደላችንንም ሊደመስስ የመጣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አሐቲ ሥምረት ነው፡፡ኤፍሬም ሶርያዊ‹‹እስመ በፈቃዱ ወለሥምረተ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ መጽአ ወአድኃነነ›› እንዳለ፡፡ ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ፡፡ በአባቱ በራሱና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መጥቶ አዳነን ማለት ነው፡፡ይህቺ ሥምረት(ፈቃድ) አንዱ ቀድሞ አስቦ ለሌላው የሚገልጻት መቀዳደም መለያየት ያለባት አይደለችም አንዲት ናት አንጂ፡፡ሰው በልቡ የሚያስበው ከመንፈሱና ከቃሉ መወቀዳደም እንደሌለበት ማለት ነው፡፡በመሆኑም በሰው ልጅ መዳን ውስጥ የፈቃድ መለያየት የለምና መንፈስ ቅዱስመስተስርዪ ይባላል፡፡አንድም

     በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ምሥጢራት ሁሉ የሚፈፀሙ(የሚከብሩ)በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡በጥምቀት ለሚገኝ ሥርየተ ኃጢአት ፈጸሚው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባ ወቅት በካህኑ ላይ አድሮ የሚናዝዝ የኃጢአትንም ሥርየት የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ጌታችን ከትንሳኤው በኋላ ‹‹እፍ ብሎ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል›› በማለት ለሐዋርያትሥልጣነ ክህነትን ሰጥቷቿል፡፡ በዚህ ዓለም የካህናት ተግባር ሰዎች ሁሉ ስለኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታንና ሥርየትን እንዲያገኙ ማገልገል ነው፡፡በጥምቀት፣በማስተማር፣በመምከርና በመገሰፅ፣በመናዘዝ፣እንዲሁም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በማቀበል በስሙ የሆነ የኃጢአት ሥርየትን መስበክ የምሥጢረ ክህነት ዋና ተግባር ነው፡፡በመሆኑም ክህነትን ከመስጠት ጀምሮ ምሥጢራት ሁሉ የሚፈጸሙ በመንፈስ ቅዱስ በመሆኑ መስተሥርዪ ተብሏል፡፡ ዮሐ 20፥22-23

     መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ በሚመጣ ጊዜ ስለ ሶስት ነገር ዓለምን እንደሚወቅስ ተናግሯል፡፡ ‹‹…እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፡፡ ስለ ኃጢአት በእኔ ስለማያምኑ፤ ስለ ጽድቅም ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው›› ዮሐ16÷8-11

     በዘመነ ሐዲስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ዓለምን ማዳኑን ከመካድ በላይ ኃጢአት የለም፡፡መንገድ ሕይወትና እውነት የተባለች በእርሱ ያለን ይህቺ ሃይማኖት ናት፡፡ሃይማኖትን መካድ ከመንፈስ ቅድስ ልጅነት የመለየት መጨረሻው ምልክት ነው፡፡

     በአንጻሩ ወረደ፣ተወለደ፣ተሰቀለ፣ሞተ፣ ተነሣ፣ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ዐረገ፣ ፣ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ብሎ ከመመስከር የበለጠ ጽድቅም የለም፡፡ ቅ.ጳውሎስ‹‹እግዚአብሔርን የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ለመላእክት የታየ፣በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣በክብር ያረገ››1ጢሞ3÷16 ብሎ ክርስተናን በጥቅል ያስቀመጠ ለዚህ ነው፡፡ሐዋርያት በአጽናፈ ዓለም ጻድቃን በገዳም ሰማዕታት በደም የፈጸሙት ጽድቅም ይኸው ነው፡፡ ሁሉም አምላክ ሰው ሰውም አምላክ የመሆኑ ሕያው የሕይወት ምስክሮች ናቸው፡፡

     መንፈስ ቅዱስ የዚህ ዓለም ገዢ የተባለ ዲያቢሎስ እንደተፈረደበትም አብስሯል፡፡ፍርዱ ግን በዲያብሎስ ብቻ አይደለም በክህደት በኃጢአት እርሱን በሚመስሉት ላይ ሁሉ እንጂ፡፡ዮሐንስ በወንጌሉ‹‹በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና፡፡…በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤በማያምን ግን በአንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈረዶበታል››ዮሐ3÷16-19 ብሎ የዲያብሎስን የክህደት መንገድ የመረጡ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከመንግስተ እግዚአብሔር በአፍአ የሚጣሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ዲያብሎስን በግብር በክህደት የሚመስሉት ሁሉ ፍጻሜያቸው እርሱ በሚኖርበት መኖር በእርሱ ላይ የተፈረደውንም መቀበል ነው፡፡

     ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይህን ሁሉ የሚሠራ እኛ ለዘላለም በሕይወት እንኖር ዘንድ ነው፡፡ ራሳችንን ለፈቃዱ ካስገዛን፤የእርሱ ማደሪያ መቅደሶች መሆናችንን አውቀን ህዋሳቶቻችንን ሁሉ በቅድስና ከጠበቅን በቅዱሳን ላይ አድሮ የሥራውን ሥራ በእኛም አድሮ ይሠራል፡፡ ሕይወትን ከሚሠጥ ከእርሱ ጋርም ለዘላለም በሕይወት እንኖራለን፡፡ሃይማኖትን ከመልካም ሥራ አስተባብረን እንድንይዝ በጌታችን በደሙ መገዛታችንንም ከንቱ እንዳናደርግ በማስተዋልም እንድንኖር ነው ቅዱስ ጳውሎስ‹‹ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ››ያለን፡፡ኤፌ3÷30 የእግዚአብሔር ልጆች የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች የመሆናችን ማረጋገጫ ማኅተማችን እርሱ ነውና፡፡

ዓለማትን የፈጠረ በነቢያት አድሮ የተናገረ በሐዋርያትም እውነትን ያስተማረ ጻድቃን ሰማእታትን ለገድል ያዘጋጀ እግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ተረክቦ ይመራልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን! ጌታ ቢፈቅድ ብንኖር በሌላ የሕይወት ቃል እስክንገናኝ የአብ ቸርነት የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ሕብረት ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን!

ግንቦት2007

 

ቀሲስ ታምራት ውቤ

Read more...
Subscribe to this RSS feed

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ