ኒቆዲሞስ
ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ፡- ፫
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደመራን መፍቀሬ ሰብዕ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሥጢር ላይ ቆይታ እናደርጋለን፡፡
ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነበር፡፡ ስለጌታችን በሚያየውና በሚሰማው ነገር ልቡናው ስለተቀሰቀሰ በሌሊት ይመጣ ዘንድ መንፈሱ ግድ አለው፡፡ በቀን ያልመጣው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡
፩. በሌሊት ኅሊና በሚታዩና በሚሰሙ ነገሮች ስለማይታወክ ክት(ይሰሰባል) ይሆናል፡፡ ስለሆነም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በሚኖረው ቆይታ ኅሊናን በሚከፍሉ ነገሮች ላለመረበሽና በሚሠማው ለመጠቀም ሰዓተ ሌሊቱን መርጧል፡፡ አበው ለጸሎትም ቢሉ መጻሕፍት ለመመልከት የሌሊቱን ጊዜ መምረጣቸው ለዚሁ ነው፡፡ አንድም
፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነው፡፡ በዕድሜ ከሚያንሰውና ከማንኛው ረቢ(መምህር) የት እንደተማረ ከማይታወቀው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ቃልን ሊጠይቅ ሲሔድ የሚያዩት ሁሉ፤ይህ ሰው ትምህርት ሳይጠነቅቅ ቀርቶ ኑሯልን ብለው እንዳይተቹት ስሙን(ደረጃውን) ለመጠበቅ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይመስላል፡፡ ለባለስልጣኑም ሆነ ለተራው፤ለባለጠጋውም ሆነ ለድሀው፤ ለትንሹም ለትልቁም መለኮታዊው ጥሪ(ግብዣ) በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቀርቧል መልስ መስጠት የየራሳችን ድርሻ ነው፡፡ ማቴ 22፥1-8
ስንቶችን የሥልጣን ደረጃቸው ወይም አዋቂዎች ተብለው የተሠጣቸው ወንበር ወደ ሕይወት ለመቅረብ ግድግዳ እንደሆነባቸው እናውቃለን፡፡ የተማረ ወይም ባለስልጣን ወይም ታዋቂ ከሆነ በእግዚአብሔር ቤት መገኘት በካህናት እግር ሥር ተቀምጦ መማርን ራስን ከማዋረድ እንደሚቆጥር ግልጽ ነው፡፡
የምድራችን መሪዎችና ታላላቆች በምክረ ካህን ሲኖሩ በአደባባይ በፀሐይ ፊት ለጌታ እግዚአብሔር ሲሰግዱ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይሾምና፣ ይሽር፣ያከብርና ያዋርድ ባለጠጋም ሆነ ነዳይ ያደርግ ዘንድ ሁሉን ቻይ ነውና፡፡ በእግዚአብሔር መታመናችን ከክብር ውርደት ወይም የፖለቲካ ክሰረት የሚያመጣብን አይደለም፡፡
ባለመድኃኒት ራስህን ፈውስ ነውና በቤተክህነቱም ላሉ የሕዝብ አለቆች የሚበጅ የኒቆዲሞስ መንፈስ ነው፡፡ ትምህርት የማያስፈልገው ምክር የማያሻው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ ወንበሩ ታላቅ ቢሆንም ተቀማጩ ሰው መሆኑን ያስብ፡፡
፫. አይሁድ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር(የሚያምን) ቢገኝ ከምኩራባቸው ሊያወጡት ተስማምተው ስለነበር፤ ኒቆዲሞስ በግልጥ ለመምጣት ያልደፈረው አንድም በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ዮሐ 9፡ 22
ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ በሕይወቱ ላይ የታየው ለውጥ በወንጌላቱ ተመስክሯል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳዊያን የዳስ በዓል በሚከበርበት ዕለት ጌታችንን እንዲይዙት የላኳቸው ሎሌዎች በትምህርቱ ከመደነቃቸው የተነሣ የተላኩበትን መፈፀም ተስኗቸው በተመለሱ ወቅት ሲበሳጩ ኒቆዲሞስ “… ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ተከራክሯል፡፡ ዮሐ7፥50-52
ይህም በአይሁድ ሸንጎ ስለጌታችን የተከራከረ የመጀመሪያው ሰው ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ ጌታ በተሰቀለባት ዕለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ሥጋውን ከመስቀል አውርዶ የገነዘ ይህ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚያች ደቀመዛሙርቱ እንኳ አይሁድን ፈርተው በተበተኑባት ዕለት በድፍረት የጌታን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር መምጣቱ እርሱ መሢህ መሆኑን በፍፁም ልቡ አምኖ ለመቀበሉ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዮሐ 19፥38-42
ከአይሁድ ሊቃናት መካከል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመንና በድፍረት ለመጋፈጥ የመጀመሪያ የሆነው ኒቆዲሞስ ከጌታችን ጋር በተነጋገረባት በዚያች ሌሊት “የእስራኤል መምህር ተብሎ መጠራቱ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡
ኒቆዲሞስ የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር በግልፅ ከተነገራቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ደረጃውን ከደቀመዛሙርት መካከል እንደ አንዱ ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔርን በንፁህ ልብ መከተል ምንኛ መልካም እንደሆነ በዚህ እናያለን፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲነጋገር እንደሳምራዊቷ ሴት ወይም እንደ ስምዖን ፈሪሳዊ ወዘተ… በተለመደ ቃላትና ቀለል በሚል ሀሳብ አልጀመረም ታላቅ በሆነ ምሥጢርና ተሰምቶ በማያውቅ ቃል እንጂ፡፡ ይህም ከእኛ ወዲያ ላሳር ለሚሉ ፈሪሳውያን አላዋቂነታቸውን የገለጠ ነው፡፡
አንድም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፡፡ ነገር ግን የዚህችን ዓለም ጥበብ አይደለም፤የሚሻሩትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን፡፡” እንዲል ከእውቀቱ ብስለት የተነሣ የአይሁድ ሸንጎ አባል የእስራኤል መምህር ለሆነ ለእርሱ ምስጢር መናገርን የተገባ ሆኖ ስላገኘው ነው፡፡ 1ቆሮ 2፡ 6