Login
Main menu

ሰቆቃወ አርድእት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

‹‹ሰቆቃወ አርድእት››

ዙሪያችን ለመስበር በሚያስፈራ ዝምታ ታጥሯል፡፡ ሁሉም ሲያየው ባደረውና በዋለው ትዕይንት ልቡናው ተቧጦ መንፈሱ ደቆ ሰው በመሆኑ ሳይቀር ተሳቆ በየጥጋጥጉ ተቆራምዷል፡፡ በዚያች ጠባብ ክፍል የተቀመጠ ሁሉ ብቸኛ ነው፡፡ማንም ማንንም ለማዋራት ለማፅናናትም ሆነ ሰቆቃውን ለመጋራት አቅም አልነበረውም ፡፡አልፎ አልፎ ከደረቀ ማንቁርት የሚወጣ ሳግ፤ በስቃይ ከተመታ ልብ የሚገነፍል ትንፋሽ ይሰማል፡፡

የሚያፅናና፣ የሚያበረታታ፣የሚመክር፣ አይዟችሁ የሚል የለም፡፡ ፍርሃት ከቦናል ጨለማ ወድቆብናል፡፡ነፍሳችንን ሀዘን እንደመቃብር ተስፋ መቁረጥም እንደ መርግ ተጭኗታል፡፡

ያ ቃል ነፍስን ከዓለም አሳብ ለይቶ እንደ ንስር የሚያመጥቃት፤ ያ ድምፅ ልብን በሀሴት አስክሮ ከሰማያት ደጃፍ የሚያደርሳት፤ ያ ርኅራኄ በኃጢአት የደቀቀችን ዝንቦች በጭካኔ እንደወረሩት ገጣባ ጀርባ አጋንንት የተቀራመቷትን ሰውነት የሚያሳርፋት፤ ዛሬ ካጠገባችን ርቋል፡፡

አይዟችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ፣ እወዳለሁ ንፃ. . .፣እምነትሽ አድኖሻል. . .፣እኔም አልፈርድብሽም. . .፣ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል በሰላም ሒጂ. . .፣ ዛሬ በዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል . . .የሚሉት ከአድማስ ደንጊያ የበረቱ ቃላት ትዝታቸው ብቻ ቀርቶልናል፡፡

በርጅና ምክንያት አጥንትና ጅማት ብቻ የቀራቸውን እግሮቼን ካጠፍኩበት ለመዘርጋት ስታገል አንድ ሰው ቀስ ብሎ ረዳኝ፡፡ የልብሱ ሽታ ነፍሴ የለመደችውን መዓዛ ስላስታወሰኝ እርጅና የተጫነው ሰውነቴ በሀዘን ተርገፈገፈ::ዕንባዬ ወደ ውስጤ ሰርጎ አንጀቴን ሲያቃጥለው ተሰማኝ፡፡ ዋ! ለካስ ለሚወዱት ለማዘንም(በዕንባ ዘለላዎች ፍቅርን ለመግለፅም) አቅም ያንሳል፡፡

ከነፍሴ ጥልቅ ጮኽኩ፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም ሊሰማው የማይችል ዋይታዬን፤ የሰው ጭካኔ ካስደነገጣት ነፍሴ የተጨመቀ ሰቆቃዬን ወደ አርያም ላክሁ፡፡

እረኛችን ሆይ! መንጋህ እኮ ተበተነ፡፡ በአንዲት ቀን ብትለየን ውስጣችን በሀዘን ከሰሎ ነፍሳችን በተስፋ መቁረጥ ቆስሎ እንግዳ በሆንባት ምድር እንደ ሽኮኮ በፈረሰ ግንብ ውስጥ ተቅበዝብዘን፡፡ ነፍሴ የወደደችህ ሆይ ንገረኝ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመስጋለህ? ከድንጋጤ የተነሳ ልቤ በውስጤ እንደ ሰም ቀለጠ ጉልበቶቼ ሁሉ ደከሙ፡፡ ነፍሴ እንደ ምድረ በዳ ተጠማችህ፡፡ አቤቱ እረኛዬ ሆይ! የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፡፡

ውጋት የሚያሰቃየው ደረቴ በአንድ እጄ ደግፌ ጉልበቶቼን ለመዘርጋት የረዳኝን ሰው ለማየት ከተደገፍኩበት ቀና አልኩ፡፡ አልባሌ ልብስ የለበሰ ሰው እንዳልሆነ ስዳስሰው ታውቆኛል፡፡ የክፍሉ ብርሃን ማነስና እርጅና የተጫነው ዓይኔ ማን መሆኑን ለመለየት ግን አላስቻሉኝ፡፡ማን መሆኑን ለማወቅ መጓጓቴን ስላወቀ ክፍሉ ጠርዝ ጋር የነበረውን መቅረዝ አምጥቶ አጠገባችን አኖረው፡፡አፌን ብከፍትም ቃል ማውጣት ግን አልተቻለኝም፡፡ ሁኔታዬን ስለተረዳ‹‹አባባ ናታን እኔ ነኝ የቀን ቀን ፈሪሳዊ የሌሊት ክርስቶሳዊ የሆንኩት እኔ ኒቆዲሞስ ነኝ›› አለኝ፡፡

የለበሰውን የፈሪሳውያንና የአይሁድ መምህራን ካባ ስመለከት በዚህች የታወቀች ዕለት ይህ የለበሱ ሁሉ ይፈፅሙት የነበረው ጭካኔ የእንባዬን ቀላይ ነደለው፡፡ አጥንታቸው ብቻ በቀረ ጉንጮቼ ላይ እየወረዱ ፂሜ ውስጥ ሰርገው ቀሩ በልቅሶ የሚርገፈገፍ ሰውነቴን ለማስከን ኒቆዲሞስ ትከሻዬን ጫን አድርጎ ያዘኝ በደከመ ድምፅ ‹‹ ግን ለምን. . .? ያ ሁሉ ጭካኔ ያ ሁሉ መጠን ያለፈ ጥላቻ፤ ግን ለምን. . .?በንፁሑ ላይ፡፡ ግፋቸው እየጨመረ ሲሄድ የገዛ ጭካኔያቸው ሲያስፈራቸው ጥላቻቸውን ለመሸከም ሲከብዳቸው አይቻለሁ፡፡ አባባ ናታን ‹‹ክፋት መንስዔን ጥላቻም ምክንያት አይሻም፡፡የዚህን ዓለም ጠባይዕ መመርመር አሰቻጋሪ ነው፡፡ ፍቅሩም ሆነ ጥላቻው ከእውነት ይልቅ ስሜትን የሚከተል ነው፡፡ ከሚስቀው ጋር ለመሳቅ፣ ከሚያለቅሰውም ጋር ለማንባት፣ከሚጮኸው ጋር ጮኸን ከሚፈርደው ጋር ለመፍረድ ርትዕ አያስፈልገንም፡፡ በቁጥር መብለጥ ጩኸት ማብዛት ብቻ በቂ ነው፡፡ይልቁንም የአድማውን መለከት የነፉት የአመፁን ችቦ የለኮሱት በሥልጣን ወንበር የተቀመጡ በብልጥግና የቀበጡ በሽበት የተጌጡ የሕዝብ አውራዎች ከሆኑ እውነትን ለመርገጥ ፍትህን ለመደፍጠጥ ቀላል ነው፡፡

በዚህ ሰዓት በፍርድ ወንበር የተቀመጠው ማስተዋሉን ፣ መርማሪም ጥበቡን ይደብቃል፡፡ የገዘፈውን ለማየት የጎላውን ለመስማት አቅም አይኖረውም፡፡በሁከት መካከል የዝምታን ምሥጢር መለየት፣ ከአድመኞች ወጥመድ እውነትን ማውጣት ከጨካኞች ጉያ ፍትህን ነፃ ማውጣት እስከ ዛሬ ወደ ምድር የወረደውን የዝናብ ነጠብጣብ የመቁጠር ያክል የማይሞከር ነው፡፡

የገዛ ወገኖቹ ይዞ የመጣውን ፍቅር ሊያክል ትንሽ የቀረው ጥላቻ ይዘው ተቀበሉት፡፡ ፈጥሮ የሠጣቸውን ውኃ እስኪ ነፍጉት ድረስ፡፡ አባባ ናታን‹‹ ምን እላላሁ? ነፍሴን በምክራቸው ያልጨመረ በፍርዳቸው ልቤን ያላኖረ ሰውነቴንም ከሸንጎዋቸው የለየ የእስራኤል አምላክ ይመስገን፡፡ በቅዱሱ ብላቴና ላይ ሲሸምቁ እንደ ተኩላም ሲያደቡ ዓይኖቼን እንዲያዩ የከፈተ እርሱ የተመሰገነ ይሁን››፡፡

አስፈሪውን ጸጥታ ለመስበር ድፍረታችንን ያዩ በክፍሏ ውስጥ የነበሩ ሌሎችም ቀስ እያሉ መጥተው አብረውን ተቀመጡ፡፡

የመቅረዟን መብራት በእንባዬ ግርዶሽ እያየሁ መንፈሴ ወደ ኃሙስ ሌሊት ተነጠቀ፡፡ መምህሩን ይዘውታል የሚል መርዶ ከሰሎሜ እንደሰማሁ ልቤ ጉሮሮዬ ውስጥ ተሰንቅራ ጉልበቶቼ እየተብረከረኩ ወሰዱት ወደተባለበት የቀያፋ ጊቢ ተፋጠንኩ፡፡ እዚያ ስደርስ ሐና ወደተባለው የሊቀ ካህናቱ አማት ወስደውት ኑሯል ጊቢው ጭር ብሏል፡፡

አረጋዊ መሆኔና እንደ በረሃ ዓለት ባገጠጡ የጉንጮቼ አጥንቶች ላይ የሚወርደውን ዕንባ ጨለማውና ሀጫ በረዶ የመሰለውን ፂሜ ተረዳድተው ስለሸፈኑልኝ በረኞቹ አንዳእ ሳይሉኝ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡

ከብርዱ የተነሳ እዚህም እዚያም ከሚነደው እሳት በቀር እረጭ ብሏል ምን ያህል እንደቆየሁ አላስታውስም፡፡ ብቻ ግራ ገብቶኝ ዙሪያውን ሳማትር የጩኸትና የሁካታ የስድብና የዛቻ ድምፅ እየቀረበኝ መጣ፡፡ወዲያው በገመድ የደኃሪት አስረው ወደፊትና ወደኋላ እያዳፉ ይዘወት መጡ፡፡የማየውን አምኖ መቀበል ቸገረኝ፡፡ ሀይ ባይ ከልካይ የለም ሊመታው የፈለገ ይመታዋል ሌላው ይገፈትረዋል፤ገሚሱ ምራቁን ይተፋበታል መቅረብ ያልቻለ ከሩቅ ሆኖ ይረግመዋል፡፡

የሊቀ ካህናቱ ዘቦች ከአሁኑ እርሱ በመደብደብ መድከማቸው ያስታውቃል፡፡ ወላጆቹ እንደጠፋበት ህጻን በማየው ነገር ግራ ተጋብቼ መካከል ላይ እንደቆምኩ ደርቄ ቀረሁ፡፡ ዘቦቹ ህዝቡን እኔ ካለሁበት ጥቂት ሲቀር ገታ አድርገው እርሱን ብቻ ለይተው መሀል ላይ ለበቅሎ ማሰሪያ የቆመ ግንድ ጋር ጠፍረው አሰሩት፡፡

ልብሱ ተቦጫጭቋል፡፡ መደረቢያው የለም፡፡እጆቹና እግሮቹ ተጋግጠዋል፡፡ፊቱ ለማየት በሚዘገንን ሁኔታ በደም በላብና በምራቅ ተሸፍኗል፡፡በታሰረበት ቦታ ከጉልበቱ ሸብረክ አንገቱን ዘለስ አድርጎ ከብርቱ ድካም ጋር ይታገላል፡፡ጥቂት ቆይቶ ቀና ብሎ ሲመለከተኝ አሁንም ዓይኖቹ ውስጥ የተለመደውን ርኅራኄና ፍቅር የጀመረውን ለመጨረስ የተዘጋጀ ቁርጠኝነት አየሁ፡፡ ፍርሃትም ሆነ ጭንቀት አይታይበትም፤ፍቅር ሀዘንና ርኅራኄ ግን ከዓይንኖቹ አሁንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይረጫሉ፡፡ በደምና በምራቅ ካደፈ በጡጫ ብዛትም ካባበጠ ፊቱ መካከል ዓይኖቹ በድቅድቅ ጨለማ እንዳሉ ከዋክብት ያበራሉ፡፡ሁሉን በፍቅርና በሀዘኔታ ያያል፡፡አባት ሕፃናት ልጆቹን በሚያይበት ሁኔታ ያስተውላቸዋል፡፡ሲመቱትም ሆነ ሲተፉበት ፊቱን አይሰውርም እይታውም አይቀየርም፡፡

ከሆዴ አንዳች ጥላቻ ሲገነፍል አፌንም ምሬት ሲሰማኝ ሁሉን በቁጣ ተመለከትኳቸው፡፡እርጅናዬን ድካሜን ሁሉ ረገምኩት፡፡ወይኔ በጉብዝናዬ ወራት ቢሆን የቻልኩትን ጥዬ እወድቅ ነበር፡፡እኒህን ጭራቆች እኒህን የሰው ልጅ የጭካኔው ጫፍ መገለጫዎች ከምድረ ገፅ ለማጥፋት አንዳች ኃይል ቢኖረኝ ስል ተመኘሁ፡፡በቁጣና በእልህ ጉሮሮዬ አብጦ ደም ሥሬ ተወጥሮ ዘወር ስል ዓይኖቼ ዓይኖቹ ላይ አረፉ፡፡

የማውቀው መዓዛ አወደኝ፡፡እናቱ ቀኝ እጇን ልቡ ላይ ጣለ ያደረገችበት ሕፃን በግርግም ሳለ ታየኝ የእናቱን ጡት ሽቶ ሲያለቅስ እርሷም በስስት እያየችው ለፈቃዱ ስትታዘዝ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፡፡ወዲያው ደግሞ በታላቅ ዙፋን ላይ እንደታደረ በግ ሆኖ አየሁት፡፡

ከዓይኖቹ የሚወጣው ብርሃን ዓይኖቼን ሲዳስሳቸው ጥላቻና በቀል ቁጣና እልህ ከውስጤ ሲጠፋ በምትካቸው ፍቅርና ርኅራኄ ሀዘኔታም ሲሰርፅ ተሰማኝ፡፡በእርሱ ዓይን ሳያቸው እነርሱን የመጥላት አቅም አነሰኝ ፡፡ ዕይታዬ ሲፈወስ በደም የራሰ ፊቱ ሲፈካ ከአይኑም የአልማዝ ፈርጥ የሚመስሉ ዕንባዎች ሲፈሱ ተመለከትኩ፡፡ እንባው እንደታላቅ ዥረት ሲፈስ ፍጥረት ሁሉ በሀሴት ሲታደስ ይታየኛል፡፡ዕፁብ ዕፁብ ኦ የዘላለም አምላክ የፍጥረት ሁሉ ጌታ የነፍሳችን ዕረፍት ይህን ፍቅር ይረዳ ዘንድ ማን ይችላል? ይህ የማይመረመር ትዕግስት ይገልጡት ዘንድ የማይደፈር ትኅትና ምን ይደንቅ?

ኅሊናዬ በሰዎች ክፋትና ጭካኔ እየታመመ በጌታ ቸርነትና ፍቅር እየተደመመ እያለ በትንሹ ረገብ ብሎ የነበረው ጩኸትና ርግማን ድጋሚ ሲፈነዳ በድንጋጤ ዞርኩ፡፡ እነሆ የመድኅን እናቱ ከዮሐንስ ጋር በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል መጣች፡፡ ግማሹ ይራገማል ግማሹ ይጮኻል እርሷ በመካከላቸው ስታልፍ ምንም ዓይነት መረበሽ አይታይባትም፡፡ ወደ ማንም አትመለከትም፡፡ዓይኗ አንድዬ ልጇን ብቻ በመፈለግ ያማትራል፡፡ የምትፈልገውን እንዳገኘት ለጥቂት ደቂቃ ባለችበት ቆማ ታስተውለው ጀመር፡፡ ቀና ብሎ ወደርሷ ሲመለከት ቀስ እያለች ወደርሱ ቀረበች፡፡ የጠራ የጨረቃ ፀዳል የሚመስለው ፊቷ ለዘላለም የሚቆም በማይመስል ዕንባ ይታረሳል፡፡ ዕንባዋ በአንገቷ ወርዶ ደረቷን አርሶታል፡፡ አትጮኽም አትወራጭም፡፡ ፊቷ ላይ ብቻ አንዴ ሀዘን አንዴ መደነቅ ሲያረብበት ግንባሯ ቅጭም ደግሞም በርኅራኄ ጥንዝል ይላል፡፡ ማንም ሊያስቆማት የሞከረ የለም፡፡ ደርሳ በዕቅፏ ልትይዘው የጎልማሳ ርምጃ ያህል ሲቀራት አንድ ዘብ አስቆማት አልተቆጣችም አልተቃወመችም ባለችበት ቆማ ዕንባ ባረገዙ ዓይኖቿ ውዷን እያየችው እጇን ዘረጋች፡፡ቁስሉን ልታጥብለት ስቃዩን ልታስታግስለት የእናትነት አንጀቷ ናፈቀ፡፡ ሀዘን አንጀቷን ሲያኝከው በልጇ የደረሰ መጎሳቆል መንፈሷን ሲያቆስለው ምጥ እንዳስጨነቃት ወላድ ሆዷን እቅፍ አድርጋ የሠራ አካላቱን በዓይኖቿ ትዳስሰዋለች፡፡

ጌታችን እናቱን ሲያያት ልቧን የሚወጋትን ሕዋሳቷን የሚቧጥጣትን የሀዘን ሰይፍ ለመቻል ትታገል ነበር፡፡የዘረጋች እጆቿን ለመያዝ እጁን ለመዘርጋት ቢሞክርም አልቻለም፡፡ብርቱ ንፋስ እንደመታው ዛፍ በሲቃ የሚናጥ ሰውነቷን እያየ አናገራት፡፡ቃል ግን አላወጣም፡፡ሁለቱ በሚተዋወቁበት በዝምታው አናገራት በጽሞና አደመጠችው ለፈቃዱም ታዘዘች ልምዷ ነውና፡፡

ዘወር ብላ የምትቆምበት ጥግ ስትፈልግ ጻዕረ ሞት መስዬ በቆምኩበት ተመለከተችኝ፡፡የብርሃን እናት ከፊቴ ስትቆም ዓይኖቿን እያየሁ ለመናገር ሞከርኩ፡፡ምላሴ ከትናጋዬ ተጣብቋል ሰውነቴ ውስጥ አንዳች ፈሳሽ የቀረ አልመሰለኝም፡፡መናገር አቅቶኝ አፌን ለመክፈት ስታገል ቀረብ ብላ እጆቼን ያዘቻቸው፡፡የሀዘን ማዕበል ሲንጠኝ ከልቅሶዬ ሳግ ጋር እየታገልኩ‹‹ለምን?ግን ለምን የብርሃን እናት ሆይ?ይህ ሁሉ በእርሱ ላይ ለምን?ምን በደል ተገኘበት?ምንስ ክፋት ታየበት?. . .መቀጠል አልቻልኩም፡፡

የብርሃን እናት‹‹እርሱ ሁሉን ያውቃል መንገዱን ይመረምር ዘንድ ማን ይችላል፡፡እንዳሰበ ይሠራል እንደፈቀደም ይፈፅማል፡፡ ነቢያት የተናገሩት የመጻህፍትም ቃል ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው፡፡ይህ ሁሉ እንደሚሆን አስቀድሞ እንደነገረን ልብ በል ናታን››አለችኝ፡፡ እርግማንን ሲሽር የበደልን ሥራ ሲቆርጥ ስለዚች ሰዓት መጥቷልና፡፡ የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ተግሳፃችንን ሊሸከም በደላችንንም ሊያስወግድ ተገልጧል፡፡የጀመረውን ይፈፅመዋልና በጽናት እንቁም አይዞህ ስትልኝ በረታሁ፡፡አጽናንተሸኛል የጌታዬ እናቱ ሆይ ብያት ሌሊቱን እንገፋ ዘንድ አንዱ ጥግ ሔደን ተቀመጥን፡፡

ለቅፅበት እንኳ ለዓኖቿ እንቅልፍን ለሽፋሽፍቶቿ ዕረፍት ሳትሰጥ ዕንባዋ እንደ ክረምት ዥረት እየፈሰሰ አደርን፡፡እርሱ ላይ ዱላ ባረፈ ቁጥር እያንዳንዷ ሕዋሷ ሲታመም ይታወቀኝ ነበር፡፡ ዕለተ ዓርብን መግለጽ የሚችል ምን አንደበት ነው? ልብ ይታመማል አእምሮም ይዝላል፡፡ከጠዋት አንስተው እያንገላቱ ገዥው ጊቢ ወሰዱት አንዲት ፅዋ ውኃ እንኳ እናቀብለው ዘንድ የሚፈቅድ ርኅሩኅ ልብ አላገኘንም፡፡

በዚህች ዕለት የአዳም ልጆች ጭካኔ የእርሱ ይቅር ባይነቱ ተገለጠ፡፡የገዛ ወገኖቹ ያልራሩለትን እርሱን የሮማ ወታደሮች የደም ጥማታቸው ተወጡበት፡፡

የማይሆን ሲሆንበት ሊደረግ ማይገባ ሲደረግበት ሁላችን እናቱን ከበን እናይ ነበር፡፡ በእያንዳንዱ መከራው የእርሷም አካል አብሮ እንደ ጽጌረዳ ይረግፍ ነበር፡፡

መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ መንገድ ሲጀምር እዚያው እንድቀር ሁሉም ግድ አሉኝ የብርሃን እናትን ግን ለመንኳት‹‹እባክሽን በተጓዘበት መንገድ ልጓዝ የደሙን ነጠብጣብ ተከትዬ ልሂድ፡፡ ከልቤ ናፍቆት ሰንፌ እንዳልቀር በጸጋሽ ደግፊኝ፡፡ እግሮቹ የቆሙበት ሥፍራ ልድረስ፤ ማዳንህን ዓይኖቼ አይተዋልና ባሪያህን አሰናብተኝ እለው ዘንድ በመስቀሉ ሥር ልዋል፡፡

የጌታዬ እናት‹‹እርሱ ከመከተል አትድከም የሁሉን ፍጻሜ ታይ ዘንድ ልብህን አበርታ›› አለችኝ በረታሁም፡፡

እነዚያ ጨካኞች እነርሱ ራሳቸውን ችለው መውጣት የከበዳቸውን መንገድ፤ውኃ እየጠጡና እያረፉ ሲጓዙ ከእርጥብ እንጨት የተሠራ መስቀል ተሸክሞ ለሚቃትተው ለእርሱ ግን ዕረፍትን ሊሰጡት አልወደዱም፡፡ ስለ እርሱ የእኔ ልብ በውስጤ ቀለጠች፡፡ ድንገት አንዱ ፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ ፍጠን ብሎ ቢረግጠው መስቀሉን እንደተሸከመ በግንባሩ ፍግም ብሎ ወደቀ፡፡ መስቀሉ ማጅራቱን ቀጥቅጦ ከዓለቱ ጋር ስላጣበቀው ፀጥ ብሎ ሲቀር ሁላችን በዋይታ ተሞላን፡፡

ወደ ማን እንጩኽ? ዕርዳታስ ከወዴት ይመጣ ዘንድ እንጣራ?

ወታደሮቹ ሁሉ ከመሰቀሉ በፊት የሞተ መስሏቸው ተደናገጡ፡፡ አንድ ዓይን ብቻ የነበረው የወታደሮች አለቃ በቁጣ ከጮኸ በኋላ ፣መስቀሉን ያነሱለት ዘንድ አዘዘ፡፡ ገልብጠው በጀርባው ሲያንጋልሉት ዓለቱ ከቀጠቀጠው አፍና አፍንጫው የእሾኽ አክሊል ከተጎነጎነበት ራስ ቅሉም ደም እንደ ውኃ ፈሰሰ፡፡ ፊቱም በደምና በአቧራ ተሸፍኖ ለማየት ተሳነው፡፡

አንዲት በነፍሷ የቆረጠች ብላቴና በወታደሮቹ መካከል አፈትልካ አጠገቡ በመድረስ መጠምጠሚያዋን ፈትታ ሰጠችው፡፡ ከመሳቀቋ የተነሳ ደፍራ ልትጠርግለት እንኳ አልቻለችም፡፡ እርሱም ፊቱ ላይ ያለውን ደሙን ጠርጎ አንዳች ነገር ካናገራት በኋላ ለመነሳት መታገል ጀመረ፡፡

ውሎአችንን የሚሰሙ በጊዜው ያልደረሱ ወይም ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ያልቀረቡ ራሳቸው እስኪፈርስ ሲያለቅሱ ሳጋቸው ይሰማኛል፡፡

በመካከል አንዲት ልጅ እግር ብላቴና በደም የተታታ ጨርቅ አቅፋ እያነባች ‹‹አባባ ናታን እነሆ ጌታችን ደሙን የጠረገበት ጨርቅ፡፡ አሁን እስኪያነሱት ድረስ የሆነውን ሁሉ ለማስታወስ የሚችል አቅል አልነበረኝም፡፡ እያንዳንዷ የደም ጠብታ ከሰማይና ከምድር የገዘፈ ዋጋ አላትና ለብርሃን እናት ወይም አእማድ ለሚመስሉ ደቀመዛሙርቱ አግኝተን እስክንሰጣቸው እነሆ›› አለችኝ፡፡

ጨርቁን ስቀበላት ያቀድሞ የማውቀው መዓዛ ሲያውደኝ ይታወቀኛል፡፡ እጀቼ እየተንቀጠቀጡ ቀስ አድርጌ የደከሙ ጉልበቶቼ ላይ ስዘረጋው ለማመን የሚከብድ ትዕይንት ገጠመን፡፡ ሁላችንም አፋችንን ከፍተን ዕንባ ባቆረዘዙ ዓይኖቻችን ለረዥም ሰዓት በአድናቆት ስናስተውለው ቆየን፡፡

መከራውን እንድናስብ የደሙን ዋጋ እንድንረዳ መልእክት ትቶልናል፡፡ ልክ መልካም ሰዓሊ እንደሚሥለው ሥዕል የመከራው ሰዓት መልኩ ጨርቁ ላይ በደሙ ታትሞበታል፡፡

ብላቴናይቱ‹‹ወንድሞቼና እህቶቼ ጌታ ይህን ጨርቅ ፊቱን ጠርጎ ሲመልስልኝ፤ ዓይኖቹን ትኩር ብዬ አየኋቸው ደም ጎርሰው ለማየት እንኳ እስኪቸግረው ቢደርስም እስከመጨረሻው ለመሔድ የነበረውን ጽናት እንድረዳው አደረገኝ በቃሉም ‹‹እናንተ የኢየሩሳሌም ሴቶች ስለ ራሳችሁ እንጂ ስለ እኔ አታልቅሱ፡፡ ያልወለዱ ማኅፀኖችና ያላጠቡ ጠቶች የተባረኩ ናቸው የሚባልበት ዘመን ይመጣልና፡፡ በእርጥቡ እንጨት ይህን ያደረጉ በደረቁማ እንዴት ይሆን?›› አለኝ ብላ በዚያች የመከራው ወቅት እንኳ ስለ መንጋው እንጂ ስለ ራሱ እንዳልተጨነቀ የፍቅሩን ጽናት አስታወሰችን፡፡

ጥግ ላይ ግዙፍ ሰውነቱን የሀዘን እሳት እንደ ጅማት ያኮማተረው አንድ ጎልማሳ መሬቱን በእጁ እየጫረ ካቀረቀረበት ቀና ሳይል ድምፁን ሳግ እያነቀው‹‹ወታደሮቹ አጠገብ ስለነበርኩ የጭካኔያቸውን መጠን አይቼዋለሁ፡፡ ከእርሱ መከራ ይልቅ የስጨንቃቸው የነበረ ከቁማራቸው ላይ ተነስተው እርሱ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ለመፈጸም ያባከኑት ጊዜ ነው፡፡ጌታ ኢየሱስ ፊቱን በጨርቅ ካበሰ በኋላ ከወደቀበት ተነስቶ መስቀሉን ለመሸከም ረዥም ጊዜ ወሰደበት፡፡አንዳቸው እንኳ መስቀሉን አንስተው ለማሸከም ርኅራኄ አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንም ቆሎ በል እያሉ ባለ ኃይላቸው በአለንጋ ይገርፉት ነበር፡፡ እያንዳንዱ ግርፋት ሲያርፍበት ከሕመሙ የተነሳ ሰውነቱ ሲንቀጠቀጥ ይታየኝ ነበር፡፡ትንሽ ፋታ እንኳ ሳይሰጡ ያጣድፉታል፡፡ ጌታ ግን መስቀሉን ሊሸከም የሚችልበት አቅም ስላልነበረው ሰውነቱን ለአለንጋችው ትቶ ተንጋለለ፡፡ያለ ህኅራኄ ሲገርፉት አለንጋው ስለሚያርፍበት ቦታ እንኳ አይጨነቁም ነበር፡፡ ሰውነቱ ደም በሚተፋ ሰምበር ተዥጎርጉሮ ደም ግባቱም ጠፋ፡፡

ቀስ ብዬ ወደ ወታደሮቹ አለቃ ስቀርብ በዚህች ምድር ላይ ለመኖር አንዳች ፍላጎት ስላልነበረኝ ሞትን በደሰታ ለማቀፍ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ምድር ለአራዊት ለመሰጠቷ ከዚያ በላይ ምስክር አላስፈለገኝም፡፡

የወታደሮቹን አለቃ‹‹ፍርዱ ሳይፈጸም እዚሁ ከሚሞትባችሁ መስቀሉን ለመሸከም እንድረዳው ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡ እርሱም በቀረች አንድ አይኑ ውስጥ ያልጠበኩት የርኅራኄ ጥላ ውልብ ብሎ ፈቀደልኝ፡፡

መስቀሉ እንኳን በድካም ለዛለና በዱላ ብዛት ለደቀቀ ቀርቶ ጤነኛ ሰው ሊሸከመው ከሚችል በላይ ክብደቱ አስጨናቂ ነበር እንዴት ቻለው?

እንደምንም መስቀሉን አንስቼ ስቆም ከክብደቱ የተነሳ ጎኔን ውጋት ቀስፎ መተንፈስ አቃተኝ፡፡ከህዝቡ መካከል ሀዘን ያደቀቃት የጌታችን እናት በትኅትና እየተራመደች ሔዳ አጠገቡ በርከክ አለች፡፡እጆቹን አንስታ ደረቷ ላይ ስታደርገው ቀና ብሎ ሲያያት እርሱን በመውለዷ ስላገኛት መከራ ፊቱ በሀዘን ተመቶ ዕንባው ኮለል እያለ ወረደ ዕንባዎቹን ቀስ ብላ በጣቷ እየጠረገች በከንፈሮቿ መጠጠቻቸው ግንባሯ ቅጭም አድርጋ ራሷን ከፍ ዝቅ እያደረገች በዓኖቿ ስታናግረው አንደምንም አንገቷን አቅፎ ተነሳ፡፡ሀዘን ያደቀቀው መከራ የሰበረው ልብ ሰይፍ ያለፈባትም ነፍስ ምን እንደምትመስል እርሷ ፊት ላይ አነበብኩኝ፡፡

እኔ በስተቀኙ ሆኜ ትከሻ ለትከሻ ገጥመን መስቀሉን ለመሸከም ክንዶቻችን ሲቆላለፉ መስቀሉ ዓለት እንደወደቀበት ቁልቁል አጠፈኝ፡፡ይህ መስቀል ከእርሱ በቀር ፍጡር ሊሸከመው የማይችል መሆኑ የገባኝ ያኔ ነበር፡፡ ለካስ የተሸከመው ዓለምን ነበር፡፡ለካስ ጫንቃው ላይ የወደቀው መለኮታዊው ፍርድ ነበር ተሸክሞ እየቃተተ ኮረብታውን የሚወጣው የሰውን ልጆች ሁሉ ሸክም ነበር፡፡

መንቀሳቀስ ሲያቅተኝ ዘወር ብዬ ተመለከትኩት ወደ እኔ ሲዞር ፊታችን ስንዝር ያህል ርቀት ነበረው፡፡በምራቅ የተበከለ ፊቱ ፍቅርን፤ደም የጎረሱ ዓይኖቹም ርኅራኄን ሲረጩ አየኋቸው፡፡

ጌታ ሆይ ለዚህ የተገባሁ አይደሉምና ይቅር በለኝ፡፡ይህን መስቀል መሸከም የሚችል መቼም መች ካንተ በቀር አይኖርም፡፡ በልቤ ቅንነት ያደረግሁትን ተመልከት፤ላግዝህ እንደማልችል ባውቀውም እስከ ፍጻሜው ግን አብሬህ ልሒድ ሸክሜ በአንተ ጫንቃ እንደኖረ መተላለፌንም እንደተሸከምክ አሁን አወቅሁ፡፡ እባክህ ጌታ ሆይ ከጌታ ጋር መስቀሉን የተሸከመ ተብዬ እቆጠር ዘንድ የታሪኬም ፍጻሜ ካንተ ጋር ይሆን ዘንድ ይቺን ብቻ ፍቀድልኝ›› አልኩት፡፡

ያን ጊዜ መስቀሉ የርግብ ላባ ያህል ሲቀለኝ ክፋቴ ሁሉ ግን በእርሱ ሸክም ሲሆንበት ታወቀኝ፡፡ በጸጥታ እያነባሁ እስከዚህ ያደረስከኝ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ በፊትህ ምንድር ናት?እያልኩ መጨረሻው ድረስ አብሬው ተጓዝኩ፡፡

በዓይኖቹ ትኩር ብሎ ሲያየኝ ወደ ሞት እየሄደ መሆኑን ባውቅም አልተሰናበተኝም፡፡ይልቁንም ይበልጥ ሊቀርበኝ ከርሱም ጋር ፈፅሜ ስጣበቅ ተሰማኝ፡፡

ችንካሩን ስመለከት ሰውነቴ በፍርሃት ራደ ልበሶቹን ሲገፉት መከራ ያልደረሰበት አንዳች ሰውነት አልቀረውም፡፡በጎኑና በጀርባው ያሉ አጥንቶቹ እስኪቆረጡ ድረስ ፈጠዋል፡፡ሲቸነክሩት ያሰማ የነበረው የጣዕር ድምፅ የሕይወት ዘመኔ ሲቃ እንደሚሆን ታወቀኝ፡፡ጌታ ሆይ! ለምን?ሌላ መንገድ አልነበረምን? ለምን ይህን የጭንቅ መንገድ ትመርጥ ዘንድ ፈቃድህ ሆነ?

ሆዴ ሲገላበጥ አፌን ደም ደም ሲለኝ የብርሃናት ጌታን ዕርቃን ለማየትም ስላልደፈርኩ ፊቴን ሸፈንኩ፡፡ ግን አሁንም ይታየኛል፡፡ መከራው ሊረሱት ከሚችሉት በላይ ነበርና፡፡

ጎልማሳው ይህ ሲነግረን የነበረውን መቀጠል አልቻለም ፡፡ የተመለከተው ነገር የዕድሜ ዘመኑ ሸክም የሕይወቱም እንጉርጉሮ እንደሚሆን ከእኛ የተጠራጠረ አልነበረም፡፡

የአይሁድ መምህር የሆነው ኒቆዲሞስ ‹‹ወንድሞቼ እህቶቼ የሆነውን ሁላችን ዓይተናል፡፡ጌታችን ነፍሱን በሠጠባት ሰዓት ፀሐይ ስትጨልም፣ጨረቃ ደም ስትሆን፣ ከዋክብት ሲረግፉ፣የቤተመቅደሱ መጋረጃ ሲቀደድ፣የመሬት መናወጥ ሆኖ መቃብራት ሲከፈቱና ሙታን ሲነሱ ስመለከት በመጽሐፍ የተባለው የነብያቱ ሁሉ ጩኸታቸው የአበው ተስፋቸው እንደተፈፀመ አወቅሁ፡፡ እርሱ እውነተኛው መሲሕ የሕያው አምላክ የባሕርይ ልጁ የዓለሙ ቤዛ እንደሆነ ፍጹም አመንሁ፡፡

ጲላጦስ ቤተመንግሥት ስደርስ የካህናት አለቆች የአይሁድ ሽማግሌዎች ጲላጦስ ስላደረገላቸው ምስጋና ሊያቀርቡ ተሰብስበው ነበር፡፡ሁሉም በዓይነ መዓት ተመለከቱኝ፡፡ጥርሳቸውን የሚያፋጩም ነበሩበት፡፡

ገዥውን የጌታን ሥጋውን እንዲሰጠኝ ስለምን በቁጣ መንጫጫት ጀመሩ፡፡ አስቀድሜ ስለተዘጋጀሁበት ነገ ሰንበት ነው ሰንበት ከመግባቱ በፊት ሥጋው ከመስቀል መውረድ አለበት ብዬ ስናገር የአርማትየሱ ዮሴፍም ሰንበት ሊሻር አይገባም ብሎ ደገፈኝ አይሁድ ስለ ሰንበታቸው እንጂ ስለጌታ ሥጋ ግድ ያልሰጠን ስለመሰላቸው ተስማሙ፡፡

ገዥው ሥጋውን እንዲሰጡን ፈቀደ፡፡አስቀድመን ግን መሞቱን እንድናረጋግጥ ጻፈበት፡፡ለወታደሮቹ አለቃ ትዕዛዙን ስንሰጠው ጠጋ ብሎ በጦር ጎኑን ወጋው፡፡ያልተቀላቀለ ውኃና ደም ከጎኑ ሲወጣ የወታደሮቹ አለቃ ጦሩን ጥሎ በምስጋና መጮኽ ጀመረ፡፡በዚያ ቅጽበት ጠፍቶ የነበረው አንድ ዓይኑ እንደተፈወሰ ተመለከትን፡፡መስቀሉ ሥር ተንበርክኮ ‹‹መስማትንስ ድምጽህን ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ›› ብሎ ሲያመሰግን እኔም የወጉትን ያዩታል የሚለውን የመጽሐፉን ቃል እያሰብኩ ነበር፡፡

ከመስቀሉ ስናወርደው እናቱ ከእኛ ጋር አብራ በእቅፏ ተቀበለችው፡፡ እኛ የግንዘቱን ሥርዓት ስናደርስም ራሱን ጭኗ ላይ አሳርፋ ዕንባዋ ሰውነቱ ላይ እየወረደ ያለማቋረጥ የተቸነከሩትን እጆቹ ትስማቸው ነበር፡፡ሥጋውን ያሸንበትን በደም የተነከረ ጨርቅ ከእጄ ስትቀበል ዓይኖቿ ውስጥ በቃላት የማይገለፅ ምስጋና ተመለከትሁ::

ወደ መቃብሩ ከመሄዳችን በፊት መስቀሉ ላይና መስቀሉ ሥር የፈሰሰ ደሙን በመጎናጸፊያዋ አብሳ ያዘችው፡፡

መቃብሩ በጲሊጦስ ማኅተም ሲዘጋ ከዮሐንስ ጋር ቁልቁል መውረድ ጀምሩ በየጥቂት እርምጃዎቿ ዘወር እያለች መቃብሩን ታየው ነበር፡፡ ልቧ በዚያ እንደቀረ እስከ ሕይወቷ ፍጻሜም ከዚያ እንደማትለይ ያያት ሁሉ በቀላሉ እርግጠኛ ይሆናል፡፡

ወንድሞቼና እህቶቼ‹‹ጌታ በሕይወቱ ገና ሳለ የነገረን ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ የቀረን በሦስተኛው ቀን እነሳለው ያለንን ቃል በእምነትና በተስፋ ጸንተን መጠበቅ ነው፡፡ ለቃሉ የታመነ ነውና፡፡ በዚያ ያሉ አርድእት ሁሉ በስቅለቱና በመከራው ሰቆቃ እንደተዋጡ ትንሣኤውን በተስፋ ሊጠብቁ በቃሉ ፀኑ፡፡

‹‹ እሁድ ማለዳ ››

ዜናው ሰማን፡፡መላእክት ወደ መቃብሩ ለሔዱ ሴቶች ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትሹታላችሁ? እንደተናገረው ተነሥቷል፡፡ ወደ ገሊላም ይቀድማችኋል›› እንዳሏቸው አበሰሩን፡፡

መግደላዊት ማርያም እንዳየችው እንዳናገራትም ተረከችልን፡፡ ኬፋና ዮሐንስም መግነዙንና መጠምጠሚያውን ከመቃብሩ ይዘው መጡ፡፡

ወደ ገሊላ ስንሔድ ዓርብ በሀዘን የተቃጠሉ ዓይኖቻችን ዛሬ በትንሣኤው ደስታ ያነቡ ነበር፡፡

በዝግ ቤቶቻችን ሳለን‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› የሚለውን የእረኛችንን ድምጽ ዳግመኛ መስማት በዚያ ለነበርን ሁሉ ከአእምሮ ባለይ ነበር፡፡

እንዲህ ያለ ትኅትና እንደምን ያለ ትኅትና ነው፡፡

እንዲህ ያለ ትዕግሥት እንደምን ያለ ትዕግሥት ነው፡፡

እንዲህ ያለስ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፡፡ሰውን እስከሞት መውደድህ ከማለት በቀር ሌላ ልንለው የምንችል ነገር አልነበረንም፡፡

ጌታ በተደጋጋሚ ለእኛ በታየባቸው አርባ እለታት ያውደኝ የነበረ ያ የማውቀው መዓዛ በዕለተ ዓርብ ኒቆዲሞስ ሲቀርበኝ ለምን እንዳወደኝ አሁን ተገለጠለኝ፡፡ እስከሞቱ ተከትሎታል ቅዱስ ሥጋውንም ገንዞ ለመቅበር ተመርጧል፡፡ የቅድስናው መዓዛም በእርሱ ላይ የመቅረቱ ምሥጢር ያ ነበር፡፡ ተሰብስበን በአንድነት በዳዊት ቃል አመሰገንን "በምሽት የለቅሶ ዋይታ ከበበን ሲነጋ ደግሞ ፍስሐ፤ ክፉን ባየንበት ሕማምንም በተቀበልንበት ዘመን ፋንታ ደስታ በዛልን፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን ከሠራ ከእርሱ ነውና"፡፡

 

ከነገድን ከቋንቋ ከሕዝብም ለአባቱ መንግሥት የተባገባን እንሆን ዘንድ በደሙ የዋጀን የፍጥረታት ሁሉ ጌታ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይግባው አሜን !





ሚያዝያ 2007

ዘመነ ሉቃስ

ቀሲስ ታምራት ውቤ

 

 



1 comment

  • kaymaruff
    kaymaruff Wednesday, 27 May 2015 22:33 Comment Link

    Hello to every single one, it's really a nice for me to pay a
    quick visit this website, it contains priceless Information.

Leave a comment

Make sure you enter the (*) required information where indicated. HTML code is not allowed.

back to top

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ