መሻገር
እንግዲያውስ ሰውነቱን ያመነ ራሱን በሚሸኘው ዓመት ምን ሠርቶ እንዳሳለፈ በአዲሱ ዓመት ደግሞ ምን ሊሠራ እንዳሰበ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሰው ሆይ! ያለፈው ዓመት በስንፍና ማለት መማር ያለብህን ሳትማር፣ መሥራት ያለብህን ሳትሠራ፣ መወሰን ባለብህ ጉዳይ ሳትወስን፣ መለየት ከሚገባህ ሳትለይ፣ ኅብረት ማድረግ ካለብህ ጋር ሳታብር፤ መጀመር ያለብህን ሳትጀምርና ማቆም ያለብህን ሳታቆም ካለፈህ፤ ዘንድሮም ይኸው የሚደገም ከሆነ ዘመን የተሻገርከው እንዴት ነው? የአምና ትኩረትህ ምን ነበር? ፍቅር ወይስ ጥላቻ፣ ይቅርታ ወይስ ቂም፣ ምህረት ወይስ በሌሎች መፍረድ፣ ትጋት ወይስ ሀኬት፣ ቅንነት ወይስ ጥመት፣ ትህትና ወይስ እልከኝነት፣ ንፅህና ወይስ ርኵሰት፣ ንቃት ወይስ ድንዛዜ፣ ትጋት ወይስ ትካዜ፣ እኛ ማለት ወይስ እኔነት…. የቱ ነበር? አሁንስ ወደ አዲስ ዓመት የምትሻገር ይኸንኑ ይዘህ ነው?
ዛሬም መሆን የሚገባኝን የምሆነው፤ ማድረግ የሚገባኝንም የማደርገው፤ ከስንፍና ምንጣፍ የምነሳው፤ ካለመወሰን አዚም የምወጣው፤ ከማስመሰል ሕይወት የምላቀቀው መቼ ነው? እያልክ ከራስህ ጋር ትጣላለህ? ራስህን ትጠየፋለህ፣ ትንቃለህ? በራስህ ትማረራለህ? ውስጥህ የተፈጠረውን ሽንፈት የተቀረፀብህን ትንሽነት ለመደበቅ ዙሪያህ ያሉትን ሰላም ትነሳለህ?
እስኪ ራስህን ጠይቅ አጠገብህ ላሉት የሰላም፣ የዕረፍት፣ የብርታት፣ የደስታ፣ የስኬት፣ የመልካምነት፣ ምንጭ ነህ ወይስ በተቃራኒው? ከሆድህ የሚፈልቀው የሕይወት ውሃ ነው ወይስ የሞት መርዝ? ወንድሜ ሆይ! ሚስትህ ወደ ግድግዳ ዞራ መኝታዋን በዕንባዋ እንዳራሰች ለማልቀስ እንኳ ተሳቅቃ እንደ ተጨነቀች፤ እህቴም ባልሽ ከባልንጀሮቹ ተለይቶ በትካዜ የወንድ ምጥ እንዳማጠ ስሜቱ ከነገርሽ የተነሳ እንደቆመጠጠ ነው ዘመን የምንሻገረው? ልጆችህ በትናንሽ ዓይኖቻቸው አውሬ እንዳየ ተጨንቀው መሔጃ አጥተው ሲቸገሩ ትንሽ የማይራራ አንጀት ይዘህ መኖር እውነት ዘመን መሻገር ነው? በምቀኝነት ተመርዘህ፣ ቂም አርግዘህ፣ በጥላቻ ተገንዘህ፣ በአዲስ ጨርቅ ላይ አሮጌ ቅዳጅ ለመጣፍ እየዛበርህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ? መሆን ለምትችለው ለመትጋት ሀሞት ስታጣ ፈልገህ መርጠህ ባልሆንከው ተቧድነህ ልዩነትን እየሰበክህ፤ ከረገፈ የአባቶችህ አፅም በለስ ከመሰብሰብ ይልቅ ኩርንችት ለመልቀም እያደምህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ? ሌት አብራህ የተኛችውን ቀን ዘማ ብለህ እየወገርህ፤ አምኖህ ለክብርህ ከፊት የቆመውን በሥውር ጦማር እያስገደልህ፤ ለጽድቅህ ሚቃትተውን ደሙን መሠዊያው መሃል እያፈሰስህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ?
ዘመን መሻገር ማለት አዲስ ማንነት መያዝ ነው፡፡ አርዌ ምድር ቆዳው ሲያረጅ ራሱን መሬት ውስጥ ይቀብርና አሮጌውን አውልቆ ጥሎ አዲስ ቆዳ ለብሶ ይወለዳል፡፡ የጌታን ቃሉን የምንሰማ የመንፈስ ቅዱስ ምክር በልባችን አድሮ አሮጌ ማንነታችንን አውልቀን አዲሱን ሰው ለመልበስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” እንዳለ፡፡ ኤፌ 4፡24 ዘመን መሻገር ማለት ከክፋት ወደ በጎነት፣ ከሀኬት ወደ ትጋት፣ ከድንቁርና ወደ ማይሻረው እውቀት መወለድ ነው፡፡ እስራኤል ከባርነት ወደ ነጻነት ዘመን እንዲሻገሩ በልዑሉ ክንድ በሙሴ መሪነት ከግብጽ በእግረ ሥጋ ቢወጡም ለአዲሱ ዘመን የተዘጋጀ ልቡና ስላልነበራቸው ዘመን ባለፈበት የኮመጠጠ የግብጽ እርሾ ቦክተው በበረሀ ሻግተው ቀርተዋል፡፡ የዘመናት ባለቤት የሆነውን ይዞ ዘመንን ዋጅቶ መኖር ከሁሉ ይጠበቃል፤ ለትዕግስት ዘመን እንዳለ ሁሉ ለመተፋትም ዘመን አለና፡፡ ምክንያተ ፍጥረትን ሳያውቁ የሕይወት ብርሃን ከሆነው ከእርሱ ተለይቶ መኖር ኑሮ አይባልም፡፡ አባቶች ጌታ ከተወለደባት ጊዜ ጀምሮ አንድ ብለው የቆጠሩ ከእርሱ ጋር ያልነበርንበትን ዘመን እንዳልኖርንበት መቁጠራቸውን ያሳያል፡፡ “አማኑኤል” እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ በኋላ የሰው ልጅን ዕድሜ ከፈጣሪው ዕድሜ ጋር አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን፡፡ ወደ ዘላለም ከገባው ጋርም ወደ ዘላለም ጊዜን ተሻግረን እንገባለን፡፡
ሦስተኛዋ ዘመን በኃጢአት የረከሰ ሰውነት፣ በቂም በጥላቻ የተሞላ ልቡና፣ በእኔ ባይነት የተቀሰፈ ኅሊና የያዘ ተሻግሮ ሊገባባት የሚችል አይደለችም፡፡ ሲያይ የማይታየውን ያልፈራች ሰውንም ያላፈረች ዓይን በሶስተኛው ዘመን ያለውን የሚያስደንቅ ክብር ማየት አይቻላትም፡፡ ሐሜትና ከንቱ ነገርን የጠገበች ዦሮም አዲሱን የበጉን ቅኔ ለመስማት አትታደልም፡፡ ባልንጀራዋን በመሸንገል በመሰሏም በመፍረድ በስድብና በእርግማን የተሞላች አንደበትም የቅዱሱን ስም በህያዋን ምድር ለማመስገን አይፈቀድላትም፡፡ አዲሲቷ ሰማይና አዲሲቷ ምድር ኃጢአት ሊፈፀምባቸው አይደለም ሊታሰብባቸው እንኳ የሚቻልባቸው አይደሉም፡፡ በዚህች ምድር የሚኖሩም ዕረፍት ወደ ሆነችው ሦስተኛዋ ዘመን መሻገር የቻሉ ንፁሐን ብቻ ናቸው፡፡
የባህረ ሐሳብ ሊቃውንት የጳጉሜን የመጨረሻ ቀን “ምርያ” ብለው ይጠሯታል፡፡ አእዋዲት፣ መድኃኒት ማለት ናት፡፡ አእዋዲት ማለት የምታዘዋውር ማለት ሲሆን፤ መድኃኒት የተሰኘች ጌታ የተወለደባትን ቀን ስለ ምታሳይ ነው፡፡ ዕለተ ምርያ እና የጌታ ልደት የሚውሉ አንድ ዕለት ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ዕለተ ምርያ ሰኞ ትውላለች የጌታ ልደት ታህሣስ 29 የሚውለውም ሰኞ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በምሥጢር ዘመን አሻጋሪያችን እርሱ መድኃኒታችን መሆኑን ያመለክታል፡፡ መድኃኒታችን “ኑ ወደ ባህሩ ማዶ እንሻገር” ይለናል፡፡ እንደ ሊቃውንቱ ትርጓሜ ባህር የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ የሚያሻግረንን አምነን ከእርሱም ጋር ኅብረት ኖሮን የዓለምን ሥራ ትተን በትንሣኤ ኅሊና ዘመን መሻገር ይኖርብናል፡፡ ሉቃ 8፡22-5 ከዚህም በተጨማሪ የብሉይ ኪዳን መካተቻ እና የአዲስ ኪዳን መባቻ ላይ የነበረውን ንጹሑን፣ ቅዱሱን፣ እውነተኛውን ነቢይና ሐዋርያ፣ ካህንና ሰማዕት፣ ባህታዊና ድንግል ዮሐንስ መጥምቅን ሕይወት አብነት እንድናደርግ በሄሮድስ ታሥሮ የቆየባትን የጳጉሜን ወር እና ምትረተ ርዕሱን እንድናስብ አበው መሥራታቸው ዘመን ከምሥጢር ጋር ያለቸውን ዝምድና እንድናውቅ ለመጠቆም ነው፡፡ ዮሐንስ ሦስተኛውን ዘመን እውን ወደ ሚያደርገው ሙሽራ ሙሽራይቱን ለማድረስ መንገዱን ጠርጓል፡፡ የፈቀዱትን አዘጋጅቷል፣ ደስታውም ተፈጽሞለታል፡፡ የሰሙትም ወደ ምህረት ዘመን ተሻግረው የአባቶቻቸውን ተስፋ ፍጻሜ ዐይተዋል፡፡ አባቶቻችን ከቃል ትምህርት ባለፈ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በሚከሰተው ዓውደ ዓመታችን ታላቅ ምልክትን ትተውልን አልፈዋል፣ እኛ ግን አላስተዋልንም፡፡ ጌታ “ሰማዩ አቀላልቷል ዛሬ ይዘንማል ትላላችሁ፤ የሰማዩን ፊት ታውቃላችሁ የዘመኑን ምልክት መለየት እንዴት አቃታችሁ” እንዲል፡፡ ዘመን ሳንሻገር ስንት ዘመን እንዳሻገርን ማን ይቁጠር? ለማንኛውም . . .
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
ቀሲስ ታምራት ውቤ 2011 ዓ.ም