Login
Main menu

ሆሣዕና

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሆሣዕና፡- በዚህ ዕለት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ቀን እናስባለን፡፡ በዓለ ሆሣዕና ከጌታችን ፱ቱ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን ከሌሊት ጀምሮ በታላቅ መንፈሣዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በሌሊቱና በዑደቱ ሥርዓት ላይ ብቻ ከዘጠኝ ያላነሱ ምስባኮች ስለሚደርሱ ሁሉን መተርጐምን ለጊዜው ታግሠን የትኞቹ እንደሆኑ እንድናውቅ ብቻ ማመላከቻ እንሰጣለን፡፡

ምስባክ፡-መዝ፹፥፫፤መዝ፻፲፯፥፳፮፤መዝ፻፳፩፥፩፤መዝ፻፵፯፥፩፤መዝ፻፲፯፥፳፯፤መዝ፱፥፲፩፤መዝ ፰፥፪፤መዝ፵፱፥፩፤መዝ፷፯፥፴፬

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ አራቱም ወንጌላውያን ተባብረው ጽፈውታል፡፡ በማቴ 21፥1-17፤በማር11፥1-10፤ሉቃ19፥29-38፤በዮሐ12፥12-19 በመሆኑም አንዱ ወንጌላዊ የመዘገበውን ብቻ የጽሑፋችን መነሻ ከማድረግ ይልቅ ሁሉንም ወንጌላት መዳሰስን መርጠናል፡፡

ጌታችን ራሱን ለዓለም ገልጦ ማስተማር ከጀመረ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይኽ ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚሁም ጊዜ ቤዛነትን ፈጽሟል፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ በአህያናበውርንጫዋ ላይ ተቀምጦ፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈፀም ነው፡፡

ትንቢቱ “ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ትን.ዘካ 9፥9

ምሳሌውም፡- በብሉይ ኪዳን ነቢያት ዘመነ ጸብዕ(ጦርነት) መምጣቱን ለማመልከት በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታዩ፤ ዘመነ ሰላም መምጣቱን ለማመልከት ደግሞ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታችን በዚህ ወደ ኢየሩሳሌም ለአራተኛ ጊዜ የመጣው በደሙ የጥልን ግድግዳ አፍርሶ በመካከላችን ፍፁም ሰላምን(ዕርቅን) ለማድረግ ነውና ይህንኑ ሲያመለክት ነው፡፡ በመከራዬ፣ደሜን በማፍሰሴ፣በስቅለቴ፣በሞቴ ሰላም የሚሆንላችሁ ጊዜ ቀርቧል ሲለን ነው፡፡

“ፈትታችሁ አምጡልኝ ለጌታ ያስፈልጉታል”

ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ወደምትባል መንደር ሲደርስ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ሲልክ የሰጣቸው ትዕዛዝ ነው፡፡ የታሠሩ አህያና የአህያይቱን ግልገል ሲያገኙ የሚያደርጉትንና ለሚጠይቋቸው የሚሠጡት መልስ፡፡

ነባቢት ነፍስ ያለችው ሰውም ሆነ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሆኑ ፍጥረታት መታሠርን አይወዱም፡፡ምክንያቱም በተፈጥሮ ያገኙትን የመንቀሳቀስ መብት ይፃረራልና ነው፡፡መታሠር ነፃነትን፣ መታሠር ፈቃድን ይጋፋል፡፡ እኒያ እንስሳት የታሠሩበት የራሱ ምክንያት ይኖራል፡፡ እንስሳት እንዳይጠፉ፣ሌባ እንዳይሠርቃቸው ወይም የሚያጠፉት ነገር ሲኖር እንዳይደርሱበት ለማድረግ ይታሠራሉ ወይም በሌላ አነጋገር ነፃነታቸው ይገደባል፡፡

ሰውንም እንደአስፈላጊነቱ ከጥፋት ለመጠበቅ በሕግና በደንቦች ይታሠራል፡፡ አስተዋይ የሆነ በኅሊና ህግ ይጠበቃል፡፡ እኒህን ሁሉ ያልተጠቀመባቸው በቦታ እንዲገደብ ያደረጋል፡፡በሰው ላይ በጫና ሳይሆን በስምምነት የሚወጡ አብዛኛዎቹ ሕጎች ነፃነቱን አይነጥቁትም፡፡ በኅሊናው ሕግ የሚመራ ግን በአፍአ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ከሚኖርበት ሙግት ነፃ ስለሚሆን ፍፁም ሰላም ይኖረዋል፡፡ ከራሱ ከመሰሎቹ፣ከተፈጥሮና ከኒህ ሁሉ ገዢ ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ህብረት፣ስምምነት፣ፍቅር፣አንድነት ይኖረዋል፡፡

ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ሲልክ “ ፈታችሁ አምጡልኝ” ማለቱን መተርጉማን ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት(ከኃጢአት ማሠርያ) የሚፈታበት ጊዜ እንደደረሠ ለማጠየቅ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል ተመልከት)

ከእስራታቸው ተፈትተው ለጌታ ያስፈልጉታል እንደተባለ ጌታ ተቀመጠባቸው፡፡

- አዳምና ዘሩ ከሞት እስራት ነፃ ወጥተው የትንሣኤ ጌታ የሆነው የእርሱ ማደርያ ሆኑ፡፡

-አዳምና ዘሩ ሞትን ከሚያስከትል የሕግ እስራት ተለቀው፤ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ላወረደው አምላክ ዙፋን ሆኑ፡፡ በኦሪት የተሠጡን ትዕዛዛት ደገኛ ነበሩ፡፡ በማናቸውም ምክንያት እነዚያን ትዕዛዛት የሚተላለፍ ቢኖር ቅጣቱ በሞት ይፈፀማል፡፡ ይህም ሰውን ከሕጉ መልካምነት ይልቅ የቅጣቱን ክፋት እያሰበ በባርነት መንፈስ እንዲኖር አድርጎታል፡፡

ሰውም የእግዚአብሔርን አሳብ መረዳት ስላልቻለ ግንኙነታቸውን በፍርሃትና በሕግ ላይ የተመሠረተ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሰብረው መውጣት የቻሉ እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ብትወዱኝስ ትዕዛዜን ጠብቁ” በማለት ሕጉን መተላለፍ በድንጋይ መወገርና በእሳት መቃጠልን ሳይሆን ከፍቅሩ መለየትን እንደሚያስከትል አስተማረ፡፡ አሁን ሕጉን የምንጠብቀው የሞት ቅጣትን በመፍራት ሳይሆን የአባታችንን ፍቅር ላለማጣት ነው፡፡ ሕጎቹ አልተሻሩም ቀድሞም ደገኛ ሕግ ነበሩና፡፡ ጌታችን ያሻሻለው እኛ ለሕግጋቱ ያለንን ግንዛቤ ነው፡፡ ሕጉን የምንፈፅምበትን መንፈስ ነው በውስጣችን ያደሰው፡፡ሕጉ በፍቅር ይጠብቀናል እኛም ሕጉን በፍቅር እንፈፅማለን፡፡ የአዲስ ኪዳን መንፈስ የወንጌል የምስራች ይኸው ነው፡፡ ዮሐ 14፥15፣ዮሐ15፥9-11 ሮሜ 7፥1-20

ዮሐንስ ወንጌላዊም በመልእክቱ “እግዚአብሔርን ስንወድ ትዕዛዛቱን ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድበዚህ እናውቃለን፡፡ ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፡፡ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” 1ዮሐ 5፥2-4

ፈታችሁ አምጡልኝ በማለቱ የእስር ሠንሰለታችን ተቆረጠ፡፡ ሞት በሰው ላይ የሠለጠነው ኃጢአትን ምክንያት አድርጎ ነበር፡፡ ዲያብሎስ ደግሞ ዓለምን የገዛው ኃጢአትንና ሞትን መውጊያው በማድረግ ነበር፡፡ ጌታችን የሰውን ሥጋ ተዋህዶ ኃጢአትን ባለመስራት ኃጢአትን፤ በሥጋ ሞቶ በመነሣት ሞትን፤በደመሰሰ ጊዜ የዲያብሎስ ግዛት ፈረሰ፡፡ ምክንያት የሚያደርግ ኃጢአትን ነበርና ጌታችን ግን “የዚህ ዓለም ገዢ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች የለውም” በማለቱ የሰው ልጅ ለባርነት ምክንያት የሆነው የኃጢአት መርዝ እንደተወገዱለት አረጋገጠልን፡፡ ይህን የተናገረ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ የሚጠራ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ዮሐ14፥30፤1ቆሮ 15፥54-57

ይህ ብቻ ያይደለ በጸሎት በተመስጦ ከዚህ ዓለም ጭንቅና ፈተና፤በፆምና በተጋድሎ ከፍትወታትና ከእኩያት፤እውነትን በማወቅ ከወግና ከልማድ ትብታብ መፈታትን አደለን፡፡ ጥንትም ሰው የተፈጠረ በገዢነት መንፈስ እንጂ በተገዢነት ሁኔታ አልነበረም፡፡ሰው ሁሉን ይገዛል እርሱ የሚገዛው ግን ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መገዛትም ነፃነት ነው፡፡  ለጌታ እግዚአብሔር ከመገዛት በራቅን ቁጥር ራሳችንን መግዛት አቃተንና ከእንስሳት እንኳ በግብር አንሰን እስክንታይ ተዋረድን፡፡ ሕግጋት ይመሩን ይደግፉን ዘንድ ቢሰጡንም ለመፈፀም አቅም አጣን፡፡ በመሆኑም ሕግጋቱ ኃጢአታችንን እየገለጡ እንደገና ዕዳ ሆኑብን፡፡ ቅ.ጳውሎስ “ነገር ግን በህግ ባይሆን ኃጢአትን ባለወቅሁም ነበር” እንዳለ ሮሜ 7፥9-10

ጌታችን ሰውነታችንን በወደዳትና በተዋሀዳት ጊዜ ከጸጋው ብዛት የተነሣ ከሕግ በላይ አደረግን፡፡ ከጌታችን ጋር ፍፁም ህብረት ያደረጉ ሁሉ ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋው በታች ይሆኑ ዘንድ ተባለላቸው፡፡ በሕግ ቢኖሩም ሕግ እንዳለባቸው አያስቡም በጸጋው ይደነቃሉ እንጂ፡፡

ይህ ሁሉ ነፃ የመሆን የመፈታት ማሳያ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህን ሲያይ ነው “በነፃነት እንድንኖር ክርስቶስ ነፃ አወጣን” ያለው፡፡ ሮሜ 3፥21-31፤ሮሜ 6፥12-19፤ገላ 5-1

አስተውሉ “ፈትታችሁ ልቀቋቸው” አላለም “ፈትታችሁ አምጡልኝ፤ ማንም አንዳች ቢላችሁም ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ”አለ እንጂ፡፡ ከኃጢአት፣ከዓለም፣ከምኞት፣ከወግና ከልማድ ወዘተ…መፈታትን ወደርሱ ቀርበን ማደርያው ለመሆን ከእርሱ ጋር ለመሆን እንጂ ልንባዝን አይደለም፡፡

ወደ ሕይወታችን የተላኩ ካህናት ከእስራት የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡የሚፈቱን ወደ ጌታችን ለማቅረብ ነው፡፡ ከጌታችን ጋር የምንዋሃደውም ቅዱስ ሥጋውንና ክብሩ ደሙን በመቀበል ነው፡፡ ማንም በራሱ ሥልጣን ከኃጢአት እስራት መፈታት አይችልም፡፡ በራሴ ወደ ጌታ እቀርባለሁ በማለት የድፍረት ቃል መናገርም የተገባ አይደለም፡፡ እነሆ ሂዱ በማለት የሚፈቱንን የመንግስቱን ካህናት ልኳል፡፡ እነርሱም ከኃጢአት የምንፈታበትን ትምህርት ሥርዓት ጸሎትና ሥልጣን ይዘው እንፈታ ዘንድ ይጋብዙናል፡፡ ለምን? ለሚል መልሳቸው ለጌታ ታስፈልጉታላችሁ! ነው፡፡ ማቴ 18፥18፤ዮሐ 20፥23

ሰው ሆይ የተሰጠህን ክብር ተመልከት፡፡ ፍጡር ሳይኖር በፈጣሪነቱ፤ተገዢ ሳይኖር በአምላክነቱ፣ አመስጋኝ ሳይኖር በአኰቴቱቅድመ ዓለም ነግሦ ለሚኖር፤እልፍ አእላፋት ወትልፊት አእላፋት መላእክት፤የሚታየውና  የማይታየው ሁሉ ለሚገዛለት ለእርሱ ታስፈልጉታላችሁ መባላችን እንዴት ያለ ክብር ነው?፡፡ ፈጣሪነቱ በእኛ ታወቀ አንል ከእኛ ይልቅ ብዙ ፍጥረት ተዘርግቷል፤ያለእኛ ተገዢነት ጌትነቱ አይሟላም እንዳንል ሳንፈጠርም በጌትነቱ ኑሯል፤ ታዲያ “ለጌታ ያስፈልጉታል”መባላችን ስለ ምንድር ነው?/ቅዳሴ ዲዮስቆርስ/


 

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ስለ ልዑሉ ሲናገር “የእኛ ሕዝብህ መሆን ላንተ አያስፈልግህም ያንተ ጌትነት ለእኛ ያስፈልገናል እንጂ፤የእኛ ልጅነት ላንተ አይጠቅምህም ያንተ አባትነት ለእኛ ይጠቅመናል እንጂ” በማለት ገልፆታል፡፡ አባትነቱ በእኛ ልጅነት አይደነቅም፤ጌትነቱም በእኛ ተገዢነት አይከብርም፡፡ ዛዲያ “ታስፈልጉኛላችሁ” መባሉ ስለምንድር ነው?

እንመርምረው ዘንድ አይቻለንም! መልስ እናገኝለት ዘንድም ቅጥነተ አእምሯችን አይወስነውም! እንዲህ ያለ ፍቅር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፤ እንዲህ ያለ ርኅራኄስ እንደምን ያለ ርኅራኄ ነው ብለን ከማድነቅ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?/ ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ/

ጌታ ሆይ ልትፈልገን መጥተሃልና፤ታስፈልጉኛለችሁ ብለህም በክብር ጠርተኸናልና፤በአፈ አበው ቀደምት፣በልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት፣ጻድቃን ወሰማዕታት፣አእሩግ ወሕፃናት፤በአኰቴተ መላእክት ወሊቃናት እናመሰግንሃለን፡፡ ምስጋናና ክብር ኃይልና ባለጠግነት ጌትነትም በመታረዱ ለፈለገን ለበጉና ለአባቱ ለመንፈስ ቅዱስም ይገባል መቼም መች ለዘላለሙ አሜን! ራዕይ 4፥6-14

ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ ይመጣል

ለጽዮን ንጉሷ እንዲሚመጣ በአፈ ነቢያት ተነግሯታል፡፡ የሚመጣው ግን እንደነ ሰሎሞን በዝሆን ጥርስ በብርና በወርቅ ባጌጠ፤በሀምራዊ ግምጃ በተሸፈነ ሠረገላ ሳይሆን በአህያና በውንጫይቱ ላይ ተቀምጦ የዋህ ሆኖ ነው፡፡

የዋህ የሚለው ኀዳጌ በቀል መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጌታችን የመጣው አንገተ ደንዳና ወደ ሆነ የነቢያቱንና የካህናቱን ደም ወዳፈሰሰ ሕጉንም በወግና በልማድ  ወደ አፈረሰ ሕዝብ ነው፡፡ መጻሕፍቱን የነቢያቱንም ቃል ያነባሉ ለመቀበል ግን አይፈልጉም፡፡ ምንም እንኳ ሰይፈ በቀል በእጁ ቢሆንና ፍርድ ቢገባቸውም ሰው የመሆኑ ዓላማ ሁሉን ለማዳን እንጂ በአንድ ስንኳ ለመፍረድ ስላልሆነ በየዋህነት ተገለጠ፡፡ የነቢያትን ደም ባፈሰሰ እጃቸው የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ በመስቀል ሰቅለው ጽዋቸውን ቢሞሉም “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለቱ የምህረት እንጂ የበቀል ጊዜ አለመሆኑን አሳያቸው፡፡ የምህረት የይቅርታ ጊዜ አለ፤ከወዳጆቹ ከነቢያት ጀምሮ ላፈሰሱት ደም የበቀል ጊዜ ደግሞ ይኖራል፡፡ ዮሐ 3፥16፤ማቴ21፥33-46፤ማቴ 23፥29-36

“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው”

ሆሣዕና በዕብራውያን ቋንቋ “አሁን አድን” ወይም “መድኃኒት” የሚል ትርጉም አንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ደግሞ ሆሣዕና የሚለው ቃል ሰው ሲደነቅ ወይም ሲደሰት ከሚያወጣው ድምፅ ጋር በማመሳሰል በሌላ ቋንቋ የተለየ ትርጉም ሊሠጠው እንደማይቻል ያብራራሉ፡፡ ሁለቱም ትርጓሜ አይጣላም፡፡

አሁን አድን ወይም መድኃኒት ማለት ነው ቢሉ ጉዞው ወደ መስቀል ነበርና እውነተኛ መድኃኒትም እርሱ ነውና የተገባ ምስጋና ነው፡፡

ቃለ አንክሮ ቃለ ትፍስሕት ነው ቢሉም በዚያ የተሰበሰቡ አብዛኞቹ ያደረገውን ተዐምራቶች እያወሱ ይመሰክሩም ስለነበር፡፡ አንድም ከነበረው የአቀባበል ሁኔታ አንድም እንደ ኢትዮጵያ ሊቃውንት ትርጓሜ የፊቱ ብርሃን ፀሐይን ሲበዘብዛት ይታይ ነበርና አድናቆቱ የተገባ ነው፡፡

ሆሣዕና እያሉ የሚያመስግኑት ሁሉ“የዳዊት ልጅ” እና “ጌታ” ብለው ጠርተውታል፡፡ በዚህም የዳዊት ልጅ በማለታቸው ፍፁም ሰው መሆኑን አንድም“እግዚአብሔር ማለ አይፀፀትም ከወገብህ ከሚወጣ ከዘርህ በዙፋንህ አኖራለሁ” የተባለው ትንቢት መፈፀሙን ያጠይቃል፡፡አይሁድም በገዛ አፋቸው ክርስቶስ ማነው? ብሎ ሲጠይቃቸው የዳዊት ልጅ ነው ማለታቸውን ያስታውሷል፡፡ አሁን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ላለማመን ምክንያት አይኖራቸውም፡፡ 2ሳሙ7፥12-14፤ማቴ22፥41-46

በ“ጌታ” ስም የሚመጣ ማለት እግዚአብሔር አባቴ ነው ብሎ የሚመጣ የተባረከ ነው ብለዋል፡፡ አይሁድ “YHWH” የሚለውን በአብዛኛው የሥነ-መለኮት ሊቃውንት “ያህዌ” የሚል ግምት የሚሠጠውን በኮሬብ ለሙሴ የተገለጠ ስመ አምላክ ለመጥራት ሰለማይደፍሩ “Adonai” ወይም “ጌታ” በሚል ቀይረውታል፡፡ በመሆኑም ይህ ጌታ የሚለው ቅፅል በቀጥታ ለእስራኤል አምላክ የሚነገር በመሆኑ “በጌታ ስም” “የሚመጣ” በማለታቸው ፍጹም አምላክነቱን ገልፀዋል፡፡ ማቴ 22፥41-46

ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው መሆኑን በዕለተ ሆሣዕና ይመሰክሩ የነበሩ መጻሕፍት አንብበው ከሊቃውንት አፍ ተምረው ትንቢት የተረጎሙ ሱባዔ የቆጠሩ አረጋውያን ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናት ጭምር ነበሩ፡፡ አይሁድንም ይበልጥ ያስቆጣው ህፃናቱ ያመሰገኑበት መንፈስ ነበር፡፡ ይህ በራሱ ታላቅ ተዐምር ነውና፡፡

ምንጊዜም ንፁህ ምስጋና ፣ ንፁህ ጸሎት፣ንፁህ መሥዋዕት፣ንፁህ ልቡና፣ ንፁህ አገልግሎት ይበልጡንንፁህ ሕይወት አጋንንትን፣ ክፍዎችን፣ ተንሎለኞችን፣ ተረፈ አይሁድን፣መናፍቃንን፣ አረማውያንን ያስቆጣል፡፡ ይህ እንዲቋረጥ የማያኖሩት እንቅፋት የማይፈፅሙት ድርጊት አይኖርም፡፡ ንጹሐ ባህርይ ከሆነው ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ በንፁህ ህይወት የኖሩ በንፁህ አገልግሎት የፀኑ ሁሉ ተገፍተዋል ተዋርደዋል፤ለሞትም ወደ መታረጃቸው ተነድተዋል፡፡ ወደፊትም የሚሆነው ይኸው ነው፡፡ ንፁህ ሁን በዓለም ወደ ኋላ ትቀራለህ ትዋረድማለህ፤ በእግዚአብሔር መንግስት ግን ትቀድማለህ ትከብርማለህ፡፡ ማቴ 14፥1-4 ዮሐ15፥18-21

ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁሉ ይዘው የተቀበሉት የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም የሚገባ ወደ መስቀል የሚወጣ ለድል ነውና፡፡ ይህ ሁሉ የሰው አቀባበልና ምስጋና ጌታችንን ለአመል ከዓላማው አላዘናጋውም፤ ለመጣባት ለዚያች ሰዓት አዘጋጀው እንጂ፡፡ አድናቆት ሊያጅበን ምስጋና ሊነጠፍልን ይችላል፤ዓላማችን ምን መሆኑን ግን ልንረሳ አይገባንም፡፡ ከሰዎች ክብርን ብንቀበል ከእግዚአብሔር ከሆነው ክብር ከተጣልን ምን ይጠቅመናል፡፡ ሊጠቀምብህ የሚፈልግ ያወድስሃል ሊጠቅምህ የቆረጠ ግን ይገሥፅሃል፡፡ ወዳጀህን መምረጥ ያንተ ድርሻ ነው፡፡

የአይሁድ ሊቃናት እርስ በርሳቸው “አንድ ስንኳ ልታደርጉ እንዳይቻለችሁ ታያላችሁን? እነሆ ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል“ ይባባሉ ነበር፡፡ ቅንዐት ጥላቻን ይወልዳል ጥላቻ ደግሞ ሞትን፡፡ ጌታችን እንደቃሉ ወደ ትክክለኛዋ ሰዓት ቢመጣም በቁሙ ሲታይ ግን የሆሣዕና ትዕይንት በአይሁድ ሊቃናት ላይ ያሳደረው ቅንዐትና ቁጣ በሞቱ ላይ እንዲቆርጡ በከፍተኛ ሁኔታ አነሣስቷቸዋል፡፡እርሱ ግን “የሰው ልጅ ይከብር ዘንደ ሰዓቱ ደርሶአል፡፡እውነት እውነት እላችኋለሁ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ብትሞትም ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች”በማለት በሞቱ ይበልጡ ብዙዎችን እንደሚያድንና ወደ ራሱ እንደሚስብ ነግሯቸዋል፡፡

የእግዚአብሔር መንግስት ከጥንት ጀምሮ የሚጋፏት ብዙዎች ናቸው፡፡ ሕዝቡን ከመጨመር ልዑለ ባህርይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከመከተል አላስቆሙትም፡፡ ገና በሃይማኖቱ ጠንክሮ እየቆመ በኅሊና ትንሣኤ ኃጢአትን ድል አድርጎ እየዘመረ ይከተለዋል፡፡ የታመነ መሪ ነውና፡፡“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ ይከተሉኝማል” ማለቱ ለዚህ ነው፡፡ መከተል ማለት በግብር መምሰል በአርአያነቱ መጽናት ነው፡፡ በህይወታችን በኑሮአችን ከመሰልነው በሞቱ እንመስለዋለን በሞቱ ከመሰልነውም በትንሣኤው እንመስለዋለን፡፡ ክርስትና ማለት ቅሉ ይኸው ነውና፡፡ የበዓሉ ጌታ ቸርነቱ ይደረግልን! ማቴ11፥12፤ዮሐ10፥1-18፤ሮሜ 6፥5

ይቆየን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር

ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት

ሚያዚያ፣2008 ዓ.ም

 

 

Read more...

ኒቆዲሞስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ኒቆዲሞስ፡- ጌታችን ኒቆዲሞስ ከሚባል የአይሁድ መምህር ጋር የነበረውን ቆይታ የምናስብበት ሰንበት ነው፡፡

ምስባክ፡- ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ

        አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመጻ በላዕሌየ

        ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለእመሕያው፡፡

ትርጉም፡- ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ

        ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም

        የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፡፡

- ክቡር ዳዊት ከንጉሡ ሳዖል ጋር በነበረው ጠብ የተናገረው ነው፡፡ ምንም እንኳ ሳዖል ቢከፋብኝም ካንዴም ሁለቴ በእጄ ጥለኽው ፈተንኸኝ፡፡ እኔ ግን እንደሆነብኝ ልሁንበት እንዳደረገብኝ ላድርግበት የሚል ክፋትን፣ ቂም፣ በቀልን በልቤ አላገኘኸብኝም፡፡ በአፌም እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሣም ከማለት በቀር ጠላትህን በእጅህ ጥሎልሃል ከሚሉ ጋር ተባብሬ አልተገኘሁም ሲል ነው፡፡

         ዳዊት ምን ያህል የዋህና ኃዳጌ በቀል መሆኑን መጽሐፍ “ዳዊት ከሳዖል ልብስ ዘርፉን በመቁረጡ አዘነ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ የስንት ወንድሙን አንገት በሰይፍ፣ የስንት ወገኑን አንጀት በረሃብ፣ የስንት ባልንጀራውን ተስፋ የተሞላ ሕይወት በመድኃኒት፣ስንቱን ትዳር በነገር ቆርጦ ሲጥል ቅንጣት የማይሠማው ጨካኝ በሞላበት ዓለም እንዲህ ዓይነት ልብ እንደምን ያለ ነው?

          ሊገድለው ሠራዊት አስከትሎ የወጣ በተደጋጋሚ ጦር ወርውሮ የሳተ ለመግደል ቁርጥ ህሊና ያለው ጠላት ላይ የማይጨክን ክንድ እንዴት የተባረከ ነው? በዚህ ዓለም ስንቱ በጠላቱ ያይደለ በወዳጁ፣ በባዕድ ያይደለ በዘመዱ፣በመጻተኛ ያይደለ በወገኑ ላይ ግፍ ሠራ፡፡ ዳቦ ሲጠብቅ ድንጋይ፣ ዓሣ ሲለምን እባብ አቀረበለት፡፡

         ቅዱስ እግዚአብሔር ማዕምረ ኅቡዓት ልብ የሠወረውን ኩላሊት የሸሸገውን ሁሉ የሚያውቅ ከኅሊና አስቀድሞ የሚመረምር ከሀሳብ አስቀድሞ የሚፈትን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሰው ከሰው ተሠውሮ እንዲሠራ አይደለም፡፡ጽድቃችን ይሁን ኃጢአታችን፣ነውራችን ይሁን ክብራችን በፊቱ የተገለጠ ነው፡፡ የቦታ ርቀት የጨለማ ጽናት ልዑሉን አይጋርደውም፡፡ ሁሉን ያያል ሁሉን ያውቃል ሁሉን ይመረምራል፡፡ ኪዳን ዘነግህ

         የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ “በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ” ያለ በግብፅም ምድር ሆነ በከነዓን የእግዚአብሔር ዓይኖች የተገለጡ መሆናቸውን በማወቁ ነው፡፡ በፍትወት ተቃጥላ በኃጢአት ሠክራ የነበረች የጲጥፋራ ሚስት ግን ይህን ማስተዋል የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ አልነበረችም፡፡ዘፍ 39፥7-11

        ሰው ኅሊናው በፍትወት ሲሸነፍ በኃጢአት ፍቅር ሲማረክ ጌታ እግዚአብሔር በሁሉ የሚገኝ መሆኑን ለማየት አዕምሮው ይጨልማል፡፡ ቅዱስ አምላኩን በሥራ ለመካድ ደግሞ የሚመርጠው ጨለማን ነው፡፡ ይህም ኅሊናው ከእግዚአብሔር በመለየቱ የወደቀበትን ጨለማ ያሳያል፡፡ ጌታም “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም” በማለት ኃጢአትንና ክፉ ሥራን የሚወዱ ከጨለማ ጋር ያላቸውን ዝምድና አስታውቋል፡፡ ዮሐ3፥20

        ህፃናት ጥፋት ሠርተው የሚቀጡ መሆናቸውን ሲያውቁ ከቤተሰብ ይደበቃሉ፡፡ሲደበቁ በዋናነት የሚሠውሩት ከሌላው ሰውነታቸው ይልቅ ፊታቸውን ነው፡፡ በእነርሱ የአስተሳሰብ ደረጃ እነርሱ የማያዩት ሁሉ ሊያያቸው አይችልም፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

        ነቢዩ ዳዊት ግን “ዓይንን የፈጠረ አያይምን ጆሮንስ የፈጠረ አይሰማምን…” በማለት ልዑሉን ይገልፀዋል፡፡ በእኛ አነጋገር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ፡፡ መዝ 93፥7-10 በቅዳሴም “እግዚአብሔር ያያል ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” በማለት ማወጁ ወደ ኅሊናችን እንድንመለስ አይደለምን? ቅዳሴ እግዚእ ቁ.፲፫

ስለ ኒቆዲሞስም “በሌሊት ፈተንኸኝ ዓመፃም አላገኘህብኝም” ማለቱ ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ በሌሊት ሲመጣ ሁሉን በሚያውቅ በእርሱ ፊት በተንኮል እንዳልቀረበ ያጠይቃል፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደጌታ የሄደ በተንኰል ሊያጠምደው ወይም እንደ ሌሎቹ ረበናተ አይሁድ በጥያቄ ሊፈትነው አልነበረም፡፡ የእስራኤል መጽናናት በእርግጥ ጊዜው እንደደረሰ ለማወቅ እንጂ፡፡

እንደሌሎችም “ይህ የጸራቢው የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? የሚል ቃል በአንደበቴ እናገር ዘንድ አልወደድሁም፡፡ ይልቁን “… እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን በማለት ከመመስከር በቀር፡፡ አመጣጡ መልካም ስለነበር ጌታችን ታላቅ የሆነ ከእግዚአብሔር ልጅነት የሚገኝበትን ምሥጢር ገልፆለታል፡፡ ዮሐ 3


 

ወንጌል ዘዮሐንስ ምዕራፍ፡- ፫

       እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደመራን መፍቀሬ ሰብዕ ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው ምሥጢር ላይ ቆይታ እናደርጋለን፡፡

            ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነበር፡፡ ስለጌታችን በሚያየውና በሚሰማው ነገር ልቡናው ስለተቀሰቀሰ በሌሊት ይመጣ ዘንድ መንፈሱ ግድ አለው፡፡ በቀን ያልመጣው ስለ ብዙ ምክንያት ነው፡፡

፩. በሌሊት ኅሊና በሚታዩና በሚሰሙ ነገሮች ስለማይታወክ ክት(ይሰሰባል) ይሆናል፡፡ ስለሆነም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በሚኖረው ቆይታ ኅሊናን በሚከፍሉ ነገሮች ላለመረበሽና በሚሠማው ለመጠቀም ሰዓተ ሌሊቱን መርጧል፡፡ አበው ለጸሎትም ቢሉ መጻሕፍት ለመመልከት የሌሊቱን ጊዜ መምረጣቸው ለዚሁ ነው፡፡ አንድም

፪. ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ነው፡፡ በዕድሜ ከሚያንሰውና ከማንኛው ረቢ(መምህር) የት እንደተማረ ከማይታወቀው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ቃልን ሊጠይቅ ሲሔድ የሚያዩት ሁሉ፤ይህ ሰው ትምህርት ሳይጠነቅቅ ቀርቶ ኑሯልን ብለው እንዳይተቹት ስሙን(ደረጃውን) ለመጠበቅ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይመስላል፡፡ ለባለስልጣኑም ሆነ ለተራው፤ለባለጠጋውም ሆነ ለድሀው፤ ለትንሹም ለትልቁም መለኮታዊው ጥሪ(ግብዣ) በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቀርቧል መልስ መስጠት የየራሳችን ድርሻ ነው፡፡ ማቴ 22፥1-8

         ስንቶችን የሥልጣን ደረጃቸው ወይም አዋቂዎች ተብለው የተሠጣቸው ወንበር ወደ ሕይወት ለመቅረብ ግድግዳ እንደሆነባቸው እናውቃለን፡፡ የተማረ ወይም ባለስልጣን ወይም ታዋቂ ከሆነ በእግዚአብሔር ቤት መገኘት በካህናት እግር ሥር ተቀምጦ መማርን ራስን ከማዋረድ እንደሚቆጥር ግልጽ ነው፡፡

       የምድራችን መሪዎችና ታላላቆች በምክረ ካህን ሲኖሩ በአደባባይ በፀሐይ ፊት ለጌታ እግዚአብሔር ሲሰግዱ ማየትን እንናፍቃለን፡፡ ይሾምና፣ ይሽር፣ያከብርና ያዋርድ ባለጠጋም ሆነ ነዳይ ያደርግ ዘንድ ሁሉን ቻይ ነውና፡፡ በእግዚአብሔር መታመናችን ከክብር ውርደት ወይም የፖለቲካ ክሰረት የሚያመጣብን አይደለም፡፡

        ባለመድኃኒት ራስህን ፈውስ ነውና በቤተክህነቱም ላሉ የሕዝብ አለቆች የሚበጅ የኒቆዲሞስ መንፈስ ነው፡፡ ትምህርት የማያስፈልገው ምክር የማያሻው ልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነውና፡፡ ወንበሩ ታላቅ ቢሆንም ተቀማጩ ሰው መሆኑን ያስብ፡፡

፫. አይሁድ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር(የሚያምን) ቢገኝ ከምኩራባቸው ሊያወጡት ተስማምተው ስለነበር፤ ኒቆዲሞስ በግልጥ ለመምጣት ያልደፈረው አንድም በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ዮሐ 9፡ 22

        ኒቆዲሞስ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከነበረው ቆይታ በኋላ በሕይወቱ ላይ የታየው ለውጥ በወንጌላቱ ተመስክሯል፡፡ የካህናት አለቆችና ፈሪሳዊያን የዳስ በዓል በሚከበርበት ዕለት ጌታችንን እንዲይዙት የላኳቸው ሎሌዎች በትምህርቱ ከመደነቃቸው የተነሣ የተላኩበትን መፈፀም ተስኗቸው በተመለሱ ወቅት ሲበሳጩ ኒቆዲሞስ “… ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” በማለት ተከራክሯል፡፡ ዮሐ7፥50-52

      ይህም በአይሁድ ሸንጎ ስለጌታችን የተከራከረ የመጀመሪያው ሰው ያደርገዋል፡፡ ከዚያም ባለፈ ጌታ በተሰቀለባት ዕለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ሥጋውን ከመስቀል አውርዶ የገነዘ ይህ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ በዚያች ደቀመዛሙርቱ እንኳ አይሁድን ፈርተው በተበተኑባት ዕለት በድፍረት የጌታን ሥጋ ገንዞ ለመቅበር መምጣቱ እርሱ መሢህ መሆኑን በፍፁም ልቡ አምኖ ለመቀበሉ ማረጋገጫ ነው፡፡ ዮሐ 19፥38-42

       ከአይሁድ ሊቃናት መካከል በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለማመንና በድፍረት ለመጋፈጥ የመጀመሪያ የሆነው ኒቆዲሞስ ከጌታችን ጋር በተነጋገረባት በዚያች ሌሊት “የእስራኤል መምህር ተብሎ መጠራቱ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

      ኒቆዲሞስ የመንግስተ ሰማያት ምሥጢር በግልፅ ከተነገራቸው መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህም ደረጃውን ከደቀመዛሙርት መካከል እንደ አንዱ ያደርገዋል፡፡ እግዚአብሔርን በንፁህ ልብ መከተል ምንኛ መልካም እንደሆነ በዚህ እናያለን፡፡

     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲነጋገር እንደሳምራዊቷ ሴት ወይም እንደ ስምዖን ፈሪሳዊ ወዘተ… በተለመደ ቃላትና ቀለል በሚል ሀሳብ አልጀመረም ታላቅ በሆነ ምሥጢርና ተሰምቶ በማያውቅ ቃል እንጂ፡፡ ይህም ከእኛ ወዲያ ላሳር ለሚሉ ፈሪሳውያን አላዋቂነታቸውን የገለጠ ነው፡፡

አንድም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፡፡ ነገር ግን የዚህችን ዓለም ጥበብ አይደለም፤የሚሻሩትን የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን ተሰውሮ የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን፡፡” እንዲል ከእውቀቱ ብስለት የተነሣ የአይሁድ ሸንጎ አባል የእስራኤል መምህር ለሆነ ለእርሱ ምስጢር መናገርን የተገባ ሆኖ ስላገኘው ነው፡፡ 1ቆሮ 2፡ 6


 

መድኃኒታችን “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ” በማለት በእግዚአብሔርና በምዕመናን ዘንድ የሚደረገውን የአዲስ ኪዳን ማሠሪያ ውል ነግሮታል፡፡ምሥጢሩም ከአእምሮው በላይ መሆኑ “እንዴት ሊሆን ይችላል?” በሚል ጥያቄው ይታወቃል፡፡ በቤተክርስቲያን ያሉ ምሥጢራት ምስጢር መባለቸው ቅሉ ከሰው አእምሮ በላይ በመሆናቸው እንጂ የተሸሸገ ነገር ኖሯቸው አይደለም፡፡

         በምሥጢረ ጥምቀት ሰው በካህኑ እጅ ጸሎት ተደርጎ ሲጠመቅ የሚታይ አገልግሎት ይፈፀማል በቅዱስ ቅባትም(ሜሮን) ይታተማል፡፡ በዚህ ወቅት በሚታይ አገልግሎት(ሥርዓት) የማይታይ ጸጋን እናገኛለን ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅነት ነው፡፡

        ከእግዚአብሔር መወለዳችንን በምን እናውቃለን ቢሉ በእምነት ነው፡፡ በሥጋ የወለዱንን በእምነት እንደተቀበልን መንፈሳዊውም ይኸው ነው፡፡ ወላጅ መውለዱን ያውቃል ልጅ መወለዱን ያምናል፡፡

          በእናቱ ማኅፀን ያለ ተወልዶ ካልሆነ በቀር የዚህን ዓለም ብርሃን ማየት አይችልም፡፡ወላጆቹን ዘመዶቹን ሁሉ ማወቅ መገናኘት አይሆንለትም፡፡ እኛም በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለድን የእግዚአብሔርን መንግስት ብርሃን ማየት አይቻለንም፡፡እንደ ወላጅ ሥሉስ ቅዱስን እንደ ዘመድ የእግዚአብሔር ምርጦች የሆኑ ቅዱሳንን መገናኘት አይሆንልንም፡፡ መወለድ ወደዚህ ዓለም መግቢያ በር እንደሆነ ሁሉ ጥምቀትም ለመንፈሳዊው ዓለም(ለእግዚአብሔር መንግሥት) መግቢያ በር ነው፡፡

      ጌታችን ይኽን ምሥጢር በነፋስም ምሳሌ ቢነግረው ሊረዳው ስላልቻለ “የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታቸንን አትቀበሉትም፡፡ ስለ ምድራዊው ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” የሚል ተግሣፅ ተነግሮታል፡፡ ኒቆዲሞስ በአእምሮው ሊገነዘበው ያልቻለን ነገር ለማመን አለመፈለጉን ጌታ አውቆበታል ሃይማኖት ግን ከሥጋዊ ደማዊ አእምሮ እጅግ የራቀና የረቀቀ ምሥጢር ስለሆነ ከእውቀቱ ማነስ የተነሣ ከማመን እንዳይዘገይ የተሠነዘረ ተግሣፅ ነው፡፡

      በልዑል እግዚአብሔር ባህርይና በሀልዎቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም በሃይማኖት የሚፈፀሙ ምሥጢራትና ተዐምራቶች ሁሉ ከአእምሮ በላይ ናቸው፡፡ በእኔ የእውቀት ልክ ስላልሆኑ አልቀበልም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ይህን የሚል የራሱን ሁኔታ ጭምር መካድ ውስጥ ይገባልና፡፡ ምክንያቱ የሰው ተፈጥሮና ማንነት በራሱ ከሰው አእምሮ በላይ ነውና፡፡

- ለኒቆዲሞስ የነፋስን ምድራዊ ምሳሌ አቅርቦ ሲያስረዳው ስላልገባው ከነፋስ ይልቅ ረቂቅ የሆነ የመንፈስን ነገር ቢነግረው እንደማያምን አስረግጦለታል፡፡ አንድም

በምድር የሚፈፀመውን የጥምቀት ሥርዓት አምነህ መቀበል ካልቻልክ ረቂቅ የሆነውን ሰማያዊና መንፈሣዊ ልደት አምነህ መቀበል እንዴት ይቻልሃል? ሲለው ነው፡፡ አንድም በአፈ ነቢያት በቃለ መፅሐፍት የተነገረውን በኅቱም ድንግልና የሆነ ምድራዊ ልደቴን ብነግራችሁ ካላመናችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያለመቀዳደም ያለመበላለጥ የሆነ ሰማያዊ ልደቴን ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ሲል ነው፡፡

          ለጥቆም “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ ማንም የለም፤እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” በማለት የሚነግረው ሁሉ እንደነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በሚል ከባህርይ እውቀት ባልመነጨ ሁኔታ ሳይሆን በባህርዩ የሚያውቀውን በጌትነቱ ያዘጋጀውን መሆኑን ነግሮታል፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ንግግር ሲጀምር “…እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” በማለት ወደ እስራኤል በተለያየ ጊዜ እንደሚላኩ ነቢያት ወይም መምህራን ቆጥሮት ነበርና ለዚያ የተሠጠ መልስ ነው፡፡ እኔ ነቢይ ወይም መምህር ብቻ ያይደለሁ የነቢያት ጌታ የመምህራን እውቀት ነኝ፡፡ እነርሱ በሰሙት ቃል በተገለጠላቸው ራዕይ ይናገራሉ እኔ ግን የሰማያት ምሥጢር ባለቤት እንደመሆኔ በባህርይ እውቀት እነግርሃለው፡፡ አንድም

ከሰማያት(ከልዕልና) በፈቃዱ ሰውን ለማዳን የወረደ፤ኋላም ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞ በሥልጣኑ በክብር ወደ ሰማይ የሚወጣ ከእኔ በቀር የለም ሲለው ነው፡፡ በውሱን አካል ቢገለጥም ምሉዕነቱ እንዳልተለወጠ ያጠይቃል፡፡ ውሱን የሰው አካል ምሉዕ ሆነ፤ምሉዕ(የማይወስነው) መለኮት በሥጋ ተወሰነ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ቦታውን ሳይለቅ ምድር ደርሶ ጨለማን እንደሚገልጥ፤በልቡና ያለም ሀሳብ ከልብ ሳይለይ በቃል በጹሑፍ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ መገለጥም እንዲሁ ነው፡፡

       አያይዞ “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ዘንድ ይገባዋል” በማለት ተናገረ፡፡ ኒቆዲሞስ በአጭር ቆይታ የአዲስ ኪዳን መልክ ምን እንደሚመስል ተስሎለታል ሁለቱ ቁልፍ ነገሮች በጥምቀት የእግዚአብሔር መንግስት ዜግነት የሚገኝበትንና፤በጌታችን ሞት የዓለም ድኅነት የሚፈፀም መሆኑን ገለጠለት፡፡

    ጌታችን እንደሚሞትና ሞቱም በምን ዓይነት መንገድ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጥ የተናገረው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡ የሞቱም ዓላማ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መሆኑን ጭምር አስረዳው፡፡

ወገኖቼ እነሆ የክርስትና መልክ፡- በክርስትና ምንጊዜም ማመንን መከራ፣ጥምቀትን ሞት፣ሞትን ትንሣኤ ይከተለዋል፡፡ ይህ ከሌለ መንገዱ ላይ አይደለንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የጥምቀትን ምንነት ሲገልጥ “…ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?... ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን፡፡” ብሎታል፡፡ በግልጥ በስሙ የተጠመቅን በሞቱ ልንመስለው ቃልኪዳን ገብተናል፡፡ በሞቱ ያልመሰሉት በትንሣኤው አይመስሉትምና፡፡ሮሜ 6፥1-23፤ቈላ 2፥8-15

በጥምቀት ለኃጢአት እንሞታለን፣አሮጌው ሰውነታችንን እንሰቅላለን፣በሕግ ከሚመጣ እርግማን ነፃ እንወጣለን፡፡ በአንፃሩ በሕይወት እንኖራለን፣አዲሱን ሰው እንለብሳለን፣ከጸጋው በታች እንሆናለን፡፡

      ቤተክርስቲያን ለዚያ ነው ወዲያው እንደተጠመቅን የጌታችንን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በማቀበል ሞቱን እንድናስብና በሞቱ መተባበራችንን እንድናትም የምታደርገን፡፡ ያልተጠመቀ የጌታን ሥጋውን ደሙን መቀበል እንደማይችል ሁሉ ተጠምቆም የጌታችን ሥጋና ደም ሳይቀበል የሚሄድ ክርስቲያን ሆኗል ልንል አንችልም፡፡ ሊነጣጠሉ አይችሉምና፡፡

          ይህንኑ ለማመስጠር ነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለጥምቀት ሲነግረው ከቆየ በኋላ አከታትሎም ስለ ስቅለቱ የነገረው፡፡ ለጥምቀታችን የሆነው ማየ ገቦና ለቁርባናችን የሆነ ደሙ የፈሰሰ በመስቀል ላይ በስቅለቱ ጊዜ ነውና፡፡ ከአዳም ጎን ሙሽራው ሔዋን እንደተገኘች ከዳግማዊው አዳም ከክርስቶስም ጎን ሙሽራው ቤተክርስቲያን ተገኘች፡፡ ዮሐ 19፥33-35

          ክርስቲያኖች ሆይ በወላጆቻችን ክንድ በዮርዳኖስ ለመጠመቅ ስንቀርብ ተቀብሎን ልጅነትን ሰጥቶናል፡፡ ቀጥሎ የሚጠብቀን የቀራንዮ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ቀራንዮ የሚኬደው ግን በራስ ጽናትና በፍፁም እምነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ተጠምቂያለሁ ብቻ ብለን የምንቆመው ለዚህ ነው፡፡ ክርስቶስን በፍፁም ኑሯችን ልንመስለው ግድ ነው፡፡ እኛን መስሎ የተገለጠ እርሱን በመምሰል እንከብር ዘንድ ነውና፡፡

        ወገኖች ሆይ የአንድ ሰው በጨለማ ወደ ጌታችን መሔድ ለስንቶች በሕይወት ብርሃን የሚሆን መንገድ እንደገለጠ ተመልከቱ፡፡ የአንድ ሰውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚያደርገው የልብ ግንኙነት ለዓለም ጥቅም እንደሚሆን አስተውሉ፡፡

በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት በክህደት፤ጽድቃችንን በኃጢአት፣ንፅሕናችንን በርኵሰት ሳናጎድፍ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሠጠች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጸንተን እንድንኖር የቅዱሳን አምላክ ይደግፈን! አሜን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Read more...

ገብር ሔር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ገብር ሔር፡-  ይህች ዕለት ከልዑል እግዚአብሔር የተለያያ ጸጋን(ሥጦታን) የተቀበልን ሁሉ  አንደየሥራችን ምንሞገስባት አልያም የምንወቀስባት ዕለት ናት፡፡ ሁለቱም ለጥቅማችን እንጂ ለጥፋታችን አይደለም፡፡ 

ምስባክ፡- ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ

        ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ

        ዜኖኩ ጻድቀከ በማኅበር ዐቢይ፤   መዝ ፴፱፡፰

ትርጉም፡- አምላኬ ሆይ ፈቃድህን እገልጥ(አደርግ) ዘንድ ወደድሁ

         ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፤

         በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ፡፡

- አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ቃል ከግብር አስማምቼ እገልጣት ዘንድ ወደድሁ፡፡ እንዲህ የተዋቡ ቃላትና ሀሳቦች ሊፈልቁ የሚችሉት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ህብረት ካደረጉ ልቦች(አልባብ)ብቻ ነው፡፡ከሁሉ አስቀድሞ የጌታ እግዚአብሔር ፍቃዱ ምን እንደሆነ አውቃ ትገዛለት ዘንድ ነፍስ በትህትና ወደ ቃሉ ማዕድ መቅረብ ያስፈልጋታል፡፡ ጌታም በመጽሐፍ በሊቃውንት(ካህናት) አፍ ፈቃዱ ምን እንደሆነ አስታውቋል፡፡

        ሰው መንፈሳዊ ሥራን መስራት የሚጀምረው ነፍሱ ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር መስማማት ስትጀምር ነው፡፡ ፈቃደ ነፍሳችን ለፈቃደ እግዚአብሔር ሲገዛ፤ፈቃደ ሥጋችን ደግሞ ለፈቃደ ለነፍስ ይገዛል፡፡

       ሰው በሥጋው ብቻ ሊፆም፣ሊጸልይ፣ሊሰግድ፣ሊያስቀድስ፣የጌታን ሥጋና ደም ሊቀበል በአጠቃላይ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሊፈፅም ይችላል፡፡ ኖረንበታልም፡፡ በዚህ ሁሉ ወስጥ ግን በነፍስ መማረክ በመንፈስ መንበርከክ ከሌለ የሚጠቅም አይደለም፡፡

       አንድ ሰው ራሱን ወይም ሌሎችን ከብርቱ ችግር ለማዳን ተጨንቆ፤ ወይም ለራሱም ሆነ ለሌሎች እጅግ የሚጠቅም ነገር አውቆ መልእክት ለማስተላለፍ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የእጅ ስልኩን(Cell Phone) ቢያወጣ ያለበት ሥፍራ ግን ኔትወርክ ባይኖረው ምን ሊያደርግ ይችላል? ሙከራው ሁሉ ፋይዳ ቢስ ሲሆን ጭንቀቱን ይበልጥ ቢያባብስበት እንጂ የስልኩን ቀፎ መያዙ መፍትሔ አያመጣለትም፡፡ አንዲህ ዓይነት የአንጎልን ንዝረት የሚጨምር ገጠመኝ ሊኖረን እንደሚችል ጸሐፊው ይገምታል፡፡ የዚያን ቀኑን ስሜት እንድታስታውስም በትህትና ይጠይቃል፡፡ የስልክ ቀፎ የያዘ ሁሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በኛም ቀፎው ሥጋችን ኔትወርኩ ነፍሳችን መንፈሳችን ነው፡፡  ወይም ዓይነ ሥውር ለሆነ ሰው የንባብ መነፅር ቢያደርጉለት እንደማይጠቅመው ነፍስ የእግዚአብሔርን ብርሃን ማየት ከተሳናት ለሥጋ ለብቻው አይቻለውም፡፡

         ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት የገለፀላትም ይህንኑ ነው፡፡ “…እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም(የሚያመልኩትም) በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት(ሊያመልኩት) ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዮሐ 4፥20-26

        የአዳም ዘር ትምክህት የክርስቶሳውያን ሁሉ እናት በምንም ምን ርኵሰት የሌለባት እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ራሷን ለዓለም ያስተዋወቀችው “ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤መንፈሴም በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” በማለት ነው፡፡ ሉቃ1 ፥47


 

       ኔትወርክ ስናገኝ ስልኬ ሠራ እንደምንል፤ነፍስ ለእግዚአብሔር በመገዛት ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር ህብረት ስታደርግ ሥጋም ይከተላታል፡፡ የነፍስም ቅድስናዋ በሥጋ ገዝፎ ይታያል፡፡ የባትሪ ብርሃን በውስጡ ካለው ድንጋይ እንጂ ከአምፖሉ እንደማይገኝ በነፍስ ላይ የሚገለጠው መለኮታዊ ኃይል በሥጋ ተገልጦ በረከት ይሠጣል ተዐምራት ይሠራል፡፡

      በሠለጠነው ዓለም Satelait phone የሚሉት ከሳተላይት ጋር የተገናኘ ተንቀሳቃሽ ስልክ አለ፡፡ እርሱን የያዘ ሰው በየትኛውም ስፍራ ቢሆን ወደፈለገበት መልእክቱን ማድረስ እንደሚችል ይታመናል፡፡ ይህም ከተራው ስልክ የተለየ ያደርገዋል፡፡

     በቅዱሳንም እንዲሁ ነው በዓሣ አንበሪ ሆድ ሆነ በምድር ጉድጓድ፤ በአድማስ ጫፍ ሆነ በበረሃ፤ በቤተመቅደስም ሆነ በዋሻና በፍርኩታ ውስጥ ቢሆኑ ከአምላካቸው ጋር ለመገናኘት የሚያግዳቸው ነገር የለም፡፡ በሁሉ ሥፍራ እርሱ ከእነርሱ ጋር እነርሱም ከእርሱ ጋር ናቸው፡፡ ትን.ዳን 6፥1-23፤ትን.ዮናስ 2፥1-11

     የቅዱስ እግዚአብሔርን ፈቃድ በነፍስ በሥጋ በመግለጥ ይኖር የነበረ የከበረ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ንግስቲቱን በሠራችው ግፍ አውግዞ በተጣላችው ሰዓት አማላጅነት የመጡ አባቶች የንግስቲቱን ቁጣ ሲነግሩት የሠጣቸው መልስ ወትረ ድንቅ የሚያሰኝ ነው፡፡ እኒያ ወርቅ ከናፍር እንዲህ አሉ “ ከቶ ምን አለቻችሁ? በምንስ ዛቻ ላከቻችሁ? ከቶ በእኔ ላይስ ምን ልታደርግ የምትችልበት ሥልጣን አላት? ምግብ በመከልከል በረሃብ እቀጣዋለሁ አለችን? ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር ከጌታዬ ሰምቻለሁ! በሰውነቱ መከራ አመጣለሁ አለችን? በሥጋዬ የጌታን መከራ ተሸክሜ እንድኖር አውቃለሁ! ግዞት፣ስደት ነውን? ዓለም በሞላው የእግዚአብሔር ነው! ሞት ነውን? ወደ ጌታዬ ለመሔድ በናፍቆት የምጠብቀው ሠረገላ ነው፡፡”

     እኒህ ናቸው ከነፍስ ውበት ከመንፈስ ቅድስና የሚፈልቁ ቃላት፤ከጌታ እግዚአብሔር ጋር በፈቃድ በመስማማት የሚቀዱ ምሥጢራት፡፡

- ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሲና ኮረብታ በድንጋይ ጽላት የተፃፉ ሕግጋቱን ለነቢዩ ሙሴ ሲሠጠው ዓላማው ትዕዛዛቱን ወደ ሰዎች የልብ ጽላት ለመገልበጥ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ስለህጉ መልካምነትና ሕዝቡ ግን በመንፈስ ደካሞች ከመሆናቸው የተነሣ እንዴት ይሻር እንደነበር ቅዱስ ጳውሎስ አብራርቷል፡፡ ሮሜ 7፥7-25፤2ቆሮ 3፥1-ፍፃሜ

          በመንፈስ ደካሞች ለሆኑ የእግዚአብሔር ሕግ ሸክም ነው፡፡ ለትጉዎች ግን ሕጉ ሰላምና ተድላቸው ነው፡፡ መዝ 118፥77 እና 165 እውነተኞችም የእግዚአብሔርን ሕግን የሚጽፉት በልባቸው ጽላት ነው፡፡ አስታዋሽ አያስፈልጋቸውም በቀንና በሌሊት ትዝታቸው ነውና፡፡ መዝ 1፥2፤ መዝ 118፥97

          ወገኖቼ ክርስቲያኖች ራስን መመርመር በዚህ አለ፡፡ በኑሮአችን የእግዚአብሔርን ህግጋት የምናያቸው እንዴት ነው?..ከባድና አስቸጋሪ ሊፈፅሙ የማይችሉ፤ አሰልቺና የመኖር ነፃነትን የሚጋፉ፤ሁሉን በማድረግ ውስጥ የሚገኝን ደስታ የሚነጥቁ ፤በጭንቀት፣በሀዘን፣በፀፀት፤ራስን በመውቀስ ባህር ውስጥ የሚደፍቁ፤ እድገትን ሥልጣኔን በኑሮ መሻሻልን የማይፈቅዱ ወዘተ…ወይስ በተቃራኒው ቀላልና በደስታ ሊፈፀሙ የሚችሉ፤ ተወዳጅና የአእምሮ ነፃነት የሚያጎናፅፉ፤ ሁሉን በማድረግ ውስጥ ካለ ፀፀት የሚያተርፉ፤በተስፋ፤በሀሴት በራስ እርግጠኛ በመሆን በመልካም ምርጫ ባህር ላይ የሚያንሳፍፉ፤ ስግብግብነት የሌለው እድገትን፤ክህደት ያልነገሠበት ሥልጣኔን፣ርኵሰት ያልበከለው የኑሮ መሻሻልን የሚደግፉ?...

እኛም ሆነን ልጆቻችን ህገ እግዚአብሔር ከልባችን እየደበዘዘ በሔደ ቁጥር ግብራችን ከእንስሳ፤ ጠባያችን ከአውሬ የከፋና ሌላ አጥፊ ሳይነሣብን እርስ በርሳችን ተባልተን እናልቃለን፡፡


 

       እንኳን በነፍስ በሥጋ ለሚያከብረን ሕገ እግዚአብሔር ቀርቶ ለሕገ መንግሥት፤ለማኀበራዊ ሕግ፣ለትራፊክ ሕግ፤ለመሥሪያ ቤት ሕግ፤ ለማኅበር ሕግ ፣ ለዕድር ሕግ ወዘተ…ስንገዛ አይደለም የምንኖር፡፡ ስንቱን አምነንበት ነው የተቀበልነው? ስንቱስ ጠቃሚያችን ነው? ግን ለግማሹ ጠቃሚ በመሆኑ ለግማሹ በይሉኝታ ስንገዛ እንኖራለን፡፡ ውጤታቸውን ስንመዝን ግን ሁሉ ጊዜያዊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ግን ዘላለማዊ ክብር የሚያስገኝ ነው፡፡ የሚገርመው ግን ለሰው ሕግ ስንል የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጣስ ቅንጣት የማይከብደን መሆኑ ነው፡፡ ለዕድር ስብሰባ ሲል የሳምንቱን ዕለታት በሰላምና በጤና ስለማለፉ የሚያመሰግንበትን ዕለተ ሰንበትን የሚሽር ክርስቲያንን ክርስቲያን ብዬ እጠራ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? ሕጉ በልባችን ሊቀረፅ ቀርቶ በጆሮአችን በቅጡ ላለማለፉ እልፍ ነጥቦች መጥቀስ ይቻላል፡፡ያለ ዕድር መኖር ትችላለህ ያለ እግዚአብሔር ግን ትጠፋለህ፡፡

በዘመኑ ፍፃሜ ከሰማያት የወረደው ከድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ የልብ ጸላቶችን ቀርፀን ወደ ተራራው ወደ እርሱ እንወጣ ዘንድ አዘዘን የፍቅርን ህግ ይፅፍብን ዘንድ በሚያስፈራና በሚያስደነግጥ ድምፅ አልተናገረንም፤ ልጆቼ እያለ በልዝብ ቃል ፍቃዱን አስታወቀን እንጂ፡፡ በነፋስና በጢስ በጭጋግና በጨለማ ውስጥ ተሰውሮ አልወረደም፤ ፊትለፊት ተናገረን እንጂ፡፡ በመለኮታዊው እሳት የቀራንዮ ኮረብቶች አንደ ደብረ ሲና አልቀለጡም በእኛ ልብ ላይ የተገሸረ የኃጢአት ድንጋይ ተወገደ እንጂ፡፡

በልባችን ከእግዚአብሔር ሕግ ይልቅ የሚዘከር ከፍቅሩም በላይ ትዝታ ሊሆን የሚችል የከበረ ምን ነገር ይገኛል?

- በታላቅ ጉባዔም ጽድቅህን አወራሁ፤- ፈቃዱን የሚወዱ ሕጉንም በልባቸው የጻፉ ሰዎች ለምስክርነት ይጠራሉ፡፡ እኒህ በእውነት የእግዚአብሔርን የፍቅሩን ጥልቀት የፈቃዱን መልካምነት የሕጉንም በጎነት በሕይወት ያውቃሉና ይመሰክሩ ዘንደ ይገባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቀምሳችሁ እዩት ለማለት ቅድሚያ መቅመስ ያስፈልጋል፡፡ የከንፈር መስካሪዎች በእግዚአብሔር መንግሰት ሥፍራ የላቸውም፡፡ በከንፈሩ የሚያከብር በልቡ የሚክድ በእርሱ ዘንደ የተነቀፈ ነው፡፡ ቃሉ “በልብህ አምነህ በአፍህ ብትመሠክር“ ማለቱን አንዘንጋ፡፡ ማቴ 15፥8 ፤ሮሜ 10፥9-10

        ታላቅ ጉባዔ ለተባለ የሰው ዘር የእግዚአብሔር ልጅ ከኃጢአትና ከሞት ሊያድነው እንደ ተገለጠ እንመሰክር ዘንድ ተመርጠናል፡፡ ጽድቃችን ሰላማችን ሕይወታችን እርሱ ነው፡፡ የሰውን ዘር በሙሉ በእርሱ በኩል ወደሆነ ጽድቅ መጥራት ለጳጳሳት፤ለካህናት፣ለመምህራን፣ለዲያቆናት ብቻ የተተወ ኃላፊነት ሳይሆን ክርስቲያን የሆንን ሁሉ ግዴታ ነው፡፡ በሰው ጉባዔ ፊት አምኖ ለሚመሰክር እርሱ ደግሞ በሰማይ መላእክት ጉባኤ ፊት ይመሰክርለታል፡፡ ማቴ 10፥32

       ምስክርነታችንም በሦስት ወገን ነው፡፡ በቃል በማስተማር፣በህይወት በመኖር፣አስከሞት ድረስ በመታመን፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በሰላምም ሆነ በመከራ የክርስትና ዘመን የምንፈፅማቻው ግዴታዎች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ግን ስለእርሱ ደምን ለማፍሰስና በሞታችን ለመመስከር የተገባን ሆነን ስንገኝ ነው፡፡

      የከንፈር ምስክሮችና የእውነት(የጽድቅ) ምሥክሮች በሥራቸው የተገለጡ ናቸው፡፡ እውነተኞቹ ሁሉ ሰው በመፈጠርና በመዳን ረገድ የተሰጠው ክብርና ትኩረት እኩል አንደሆነ ሰለሚያምኑ ለሰው ፊት አያደሉም፡፡ ለረብና ለጥቅም የሚሠሩ ምንደኞች፤ የመኳንንትና የወይዛዝርት የድግስ ጌጦች፤ በከንቱ ውዳሴ፤ኔሻን ያሸበረቁ ሞኞች አይደሉም፡፡ ሥልጣን ወጥመድ ዘርና ጎሳን መለየትም ደዌ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ሰውን ለማስደሰትም ሆነ ለማሳዘን ለማክበርም ሆነ ለማዋረድ ሆን ብለው አይናገሩም፡፡ አንደቃሉ ይመክራሉ እንደ ሕጉ ይገስፃሉ ይዘልፋሉ፡፡ የሚጠገን ይጠገናል የሚሰበርም ይሠበራል፡፡ ርኵሰትን የሚፈልግ ወደርኵሰቱ ጽድቅን የሚሻም ወደ ጽድቁ ይሔዳል፡፡

       በሰው ፊትም የሚታሰቡት ሞገደኞች፣ዕብዶች፣ጊዜን ያልዋጁ ቂሎች አንዳንዴም የሰውን ክብር የማያውቁ ዋልጌዎች ተደርገው ነው፡፡ በዚህ ግርዶሽ ስንት የእውነት መልእክተኞች አንደ ዋዛ አመለጡን፡፡ የእነርሱ ቃል ግን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዘት ይገባል” ሕይወት ተገለጠ ዓይተንማል፤ ዓይኖቻችን ያዩትን በጆሮአችን የሰማነውን እጆቻችንም የዳሰሱትን እርሱን እናወራላችኋለን” እያለ ለዘላለም ይጮኻል፡፡ የሐዋ ሥራ 4፥13-21፤1ዮሐ 1፥1-2 ፤ 2ቆሮ 6፥ 4-10


 

ወንጌል ዘማቴዎስ ፳፭፥፩፬-፴

      ጌታችን ባስተማረው በዚህ ማለፊያ ምሳሌ የሰው ዘርን በሁለት ወገን ከፍሏቸዋል፡፡ ገብር ሔር(መልካም አገልጋይ) እና ገብር ሀካይ(ሐኬተኛ አገልጋይ)፡፡

      በምሳሌው የተጠቀሰው ባለጠጋ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ባሮቹን ጠርቶ ከገንዘቡ ሰጣቸው እንዲሰጣቸው አልጠየቁትም፤አልደከሙም ዋጋም አልከፈሉም፡፡ በዚህ ዓለም ያለድካም ያለደጅ ጥናት ያለዋጋ ምን ልናገኝ እንችላለን? አርሱ ግን የባህሪይ ገንዘቡ የሆነ መልካምነትን እውቀትን ህይወትን ሁሉ እንዲሁ በለጋስነቱ ብቻ ያለዋጋ ሰጠን፡፡ለጋስነቱን መዘከር ቸርነቱንም ማድነቅ የሚቻለው ምን ህሊና ነው!

     ሕይወት፣እውቀት፣ሰውነት(ሕዋሳት)፣ጊዜ፣ዕድሜ፣ሰላም፣ክህሎት፣ወዘተ…ለአዳም ዘር ሁሉ የተሰጠ የለጋስነቱ በረከት ናቸው፡፡ ይህን ከሰጠን በኋላ ወደሌላ ሀገር ሄደ ማለቱ ነፃ ፈቃድን ሰጠን፡፡ ለመሥራትም ወይም ላለመሥራት ለማትረፍ ወይም ለመስነፍ ምርጫው የራስ ነው፡፡ አስገድዶ አያሠራም፡፡ኋላም የሚያስፈርድብን በነፃ ፍቃዳችን የሠራነው ሥራ ነው፡፡

     ለጋስነቱ ያሰደነቃቸው ተመልሶ መጥቶም እንደሚቆጣጠራቸው ያልተጠራጠሩ እነርሱ አምኖ በሠጣቸው ለማትረፍ ተግተው ተስማሩ፡፡ ደከሙ ድካማቸው ፍሬ አስገኘላቸው፡፡በተሠጣቸው እኩል ማትረፍ እንዴት ያለ ትጋት ነው?

    ለጋሱ ጌታ እንደተጠበቀው መጣና ተቆጣጠራቸው ተግተው ያተረፉትን ሥራቸውን አስታወቁ፡፡ እርሱ በሰጣቸው ሌላ ማንም ሊሰጣቸው በማይችለው ጸጋ ተጠቅመው ለወገኖቻቸው የሚበጅ ሥራ በመሥራታቸው ተመሰገኑ፡፡ እርሱ በፍቅሩ መልካም የሆነውን ሁሉ እንደሠጣቸው፤እነርሱም ለሌሎች መልካም በማድረግ ፍቅራቸውን ገለጡ፡፡ በጥቂቱ ስለታመኑ በበዙ እንደሚሾሙ ተባለላቸው፡፡

     በምድር ታምነዋልና በሰማያት ይሾማሉ፡፡በጊዜያዊው ታምነዋልና በዘላለማዊው ይሾማሉ፡፡ በውሱን እውቀት ታምነዋልና በፍፁም እውቀት ይሾማሉ፡፡ ክርስቲያኖች ባለን በጥቂቱ እንታመን፡፡ በምዕመንነት የታመነ በዲቁና፣በዲቁና የታመነ በቅስና፤ በቅስና የታመነ በጵጵስና መሾሙ አይቀሬ ነው፡፡

     ከተግባረ ዕለት፤ከትምህርት ከእንቅልፍ ጥቂት ጊዜ አስተርፈን የሚበጅ ሥራ ለመሥራት ብንታመን አብዝተን መልካም የምንሠራበት የበዛ ጊዜ ይሠጠናል፡፡

    አሥራት በማውጣት ብንታመን ስስትን አጥፍቶ የበለጠ የትሩፋትን ሥራ በምንሠራበት ሁኔታ ይሾመናል፡፡

     በድንግልና ዘመን ብንታመን በትዳር ወይም በምንኩስና ዘመናችን በታላቅ ክብር ይሾመናል፡፡ ወዘተ…

     በለጋሱ ጌታ ለትጉህ አገልጋይ የተሠጠው ዋጋ የሚያስደንቅ ነው ወደ ጌታህ ደስታ ግባ በማለት ከእርሱ ጋር አብሮ እንዲኖር የተሠጠውን ክብር አብስሮታል፡፡


 

- ሐኬተኛው አገልጋይ ግን የተሠጠውን ጸጋ ዋጋ ሳይሠጠው ለስንፍናውም ምክንያት እንኳ በቅጡ ሳያዘጋጅ ቆየ፡፡ ጌታው ሲጠይቀው የሰጠው መልስ ምን ያህል ደካማ መሆኑን የገለጠ ነው፡፡

ጌታ ሆይ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ መሆንህን አውቃለሁና ፈራሁ ስለዚህ መክሊትህን ወሰጄ ከምድር በታች ቀበርኩት አሁንም እነሆ መክሊትህ፤

        ይህ ሰው ስንፍናውን በምክኒያት ሊደብቅ ቢሞክርም አልሆነለትም፡፡ የልቡናው ክፋትም በለጋስነት የሚታወቀውን ጌታን ጨካኝ ብሎ በመጥራቱ ታወቀ፡፡ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበት የምትሠበስብ ማለት ጌትነቱን ሁሉን የያዘ ፣ሁሉን ያስገኘ ፣በሁሉ ላይ የሠለጠነ መሆኑን መካድ ነው፡፡ ቢያንስ እሱን የተቆጣጠረው በሠጠው ላይ ነው፡፡ ይህም ፍትሕ ርትዕ ዙፋኑ ሞገስ እንደሆነ ያሳያል፡፡

       ምንጊዜም የሚጠበቅባቸውን መወጣት የማይችሉ ሰዎች ስንፍናቸውን ለመሸፈን የሚጥሩት በቅደስናው የተፈራ በሆነ በሠራዊት ጌታ ላይ ያልተገባ ንግግር በመናገር ነው፡፡ ፍርሃታቸው በሰው ፊት አንዳይታወቅ መደበቂያቸው ያልተገራ አንደበታቸው ነው፡፡ በልዑሉ ላይ የፌዝ ቃል ካልተናገሩ አዋቂ የሆኑ ቅዱሱን ካልተገዳደሩ የተፈላሰፉ የማይመስላቸው የልቅነት አቀንቃኞች ብዙ ናቸው፡፡ አንዲህ ያሉት ተሳዳቢዎች፣ፈሪዎች፣ሐኬተኞች የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም፡፡የሚያደምጣቸው ጽሑፋቸውንም  የሚያነብ ሁሉ በክፉ መርዝ ይያዛል በጥፋት ሥራቸውም ይተባበራል፡፡ ስድብና ልዑሉን መገዳደር ከዲያቢሎስ መሆኑን እናውቃለን፡፡

ኢዮብ ፈተናው ሲበረታበት ሰይጣን በሚስቱ አድሮ የተናገረው “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ”በማለት ነው መጽሐፈ ራዕይም “አውሬው እግዚአብሔርንና ስሙን ማደሪያውንና በሰማይ የሚያድሩትን ይሰድብ ዘንድ አፍ ተሰጠው” ተብሎ ተጽፏል ኢዮብ 2፥7-10፤ራዕ 13፥5-6

      ይህ ሀኬተኛ ባሪያ መክሊቱን በምድር ውስጥ እንደቀበረ ስንቶች እንሆን የተሠጠንን ጸጋ ከምድራዊ ጉዳያችን ይልቅ ትኩረትና ቅድሚያ ባለመስጠት ያጠፋን፡፡ የሚያሳዝነው ዛሬ ህይወታችንን፣ጊዜያችንን፣እውቀታችን፣ገንዘባችን ወዘተ…ለእግዚአብሔር እንዳንሰጥ ተሸንፈናል፡፡ ምክኒያቱም እነኚህን ሁሉ ከተወሰዱብን ቆይተዋል፡፡ በህይወታችን በጊዜአችን በእውቀታችን፣በገንዘባችን ወዘተ…የሚያዝበት ሌላ ነው፡፡ “System” የሚባል ሠንሠለት ጠፍንጎናል፡፡ነፃ ነኝ የምንል ባርያ ሆነናል ለፈጠረን ሳይሆን ለፈጠርነው ለቀደመን ሳይሆን ለቀደምነው እኛ ህልው ለሆንበት ሳይሆን በእኛ ህልውና ላገኘው ተገዝተናል፡፡ ይህን ቀንበር ሰብረን ስንወጣ ብቻ ነው የኛ የሆነውን ብቻ ሳይሆን ራሳችንን መስጠት የምንችለው፡፡ በምድር የቀበርነው መክሊት ሳይሆን በምድራዊ ሀሳብ የተቀበርን እኛ ትንሣኤ ያስፈልገናል፡፡ ፍፁም የሆነ የለውጥ ትንሣኤ የነፃነት ትንሣኤ በራስ የማዘዝ ትንሣኤ፣ የፈቀድነውን ብቻ የማድረግ ትንሣኤ ያሻናል!!!

    ይህ የወንጌል ክፍል በገብር ሔር /በመልካም አገልጋይ/ መሰየሙም የተገባ ነው፡፡ ክፉዎች ስም የላቸውምና፡፡ ለአርአያነት አይበቁምና ሰሙን ሊያስጠራበት ይችል የነበረበትን መክሊት በምድር ውስጥ ቀብሯልና የርሱም ስም በክፋትና በሀኬተኛነት ውስጥ ተቀብሮ ቀርቷል፡፡

ለመልካሙ አገልጋይ ግን የክፉው ዕድል/ድርሻ/ ጭምር ተወስዶ ተጨምሮለታል መልካሞች በጸጋ ለይ ጸጋ በሀብት ላይ ሀብት፣በክብር ላይ ክብር ቢጨመርላቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም ይተርፋሉና፡፡

ይቆየን ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ቀሲስ ታምራት ውቤ ዘሰአሊተ ምህረት

 

Read more...

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ