ትውልዱ ከእመቤታችን ምን ይማራል?
Index
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!
ትውልዱ ከእመቤታችን ምን ይማራል?
መግቢያ
‹‹ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ›› በማለት አባ ሕርያቆስ በእመቤታችን ስም(ለእመቤታችን) በደረሰው የቁርባን ምስጋናው ስለ እመቤታችን ንጽሕናና ቅድስና፤ አካላዊቃልን በሥጋ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ለመውለድ መብቃት እንደቻለች፤ የአበው ተስፋ የነቢያትም ትንቢትና ምሳሌ በእርሱዋ እንዴት እንደተፈጸመ አምልቶ አስፍቶ ተናግሯል፡፡ ሊፈጽመውግን አልቻለም፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ጐሥዐ ልብየ… ልቤ በጎ ነገርን አፈለቀ እኔ የንጉሥን ሥራ እናገራለሁ››፤ ብሎ ቅድመ ዓለም ያለ ፍጡራን አምላክ፣ ያለ ተገዢ ጌታ፣ ያለ ሎላልት ንጉሥ የሆነ፤ ድህረ ዓለም በማኅፀነ ማርያም በተዋህዶ ኋላም በመስቀል የነገሠ የእግዚአብሔርን ሥራ እናገራለሁ ብሎ ቢጀምር ሊፈጽመው እንዳልቻለ የአባ ሕርያቆስም እንዲሁ ነው፡፡መዝ 44፥1
ስለ ምሥጢረ ሥላሴ(ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ልዩ ሦስትነት) በቅጥነተ ኅሊና ሊመረምሩ የወደዱ ብዙ ሊቃውንት፤ስለ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ፍጹም ሰው መሆን የማይወሰነው መወሰኑ ርቀትን ከግዘፍ፣ኃይልን ከድካም፣ባዕልነትን ከንድየት፣ሕያውነትን ከመዋቲነት ፍጹም በሆነ ተዋሕዶ ሳይቀላቀሉ ሳይለያዩ ሳይጠፋፉ አንድ ማድረግ፤ ጉምቱ ጉምቱ መንፈሳውያን ሊቃውንት ጠንቅቀው ሊጽፉ የሞከሩ ቢሆንም አንዳቸውም ግን ይህን ማድረግ ሳይቻላቸው ድካማቸው ስዒን በወለደው አንክሮ ተደምድሟል፡፡
የጌታ እግዚብሔርን ባሕርይ የመድኃኒታችንንም ሰው የመሆን ምሥጢር ጠንቅቆ ፈፅሞ መናገር እንዳይቻል፤ የአብ ሙሽራ የወልድ ማደሪያ የመንፈስ ቅዱስ ንጽሕት አዳራሽ ስለሆነች ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በእርሷ ስለተደረገ ነገርና ስለ ክብሯ ጠንቅቆ ፈጽሞ መናገር አይቻልም፡፡
‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር›› እንዳለ ነብዩ ዳዊት የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተከበረ(ድንቅ) ነገር ይባላል ሲል ነው፡፡ቃሉ ቃለ አንክሮ ነው፡፡‹‹ድንቅ›› የሚለው ቃለ አንክሮ ከአእምሮአችን በላይ ለሆነ የተከተተ መግለጫ ልንሰጠው ለማንችለው ጉዳይ የምንጠቀምበት ነው፡፡እመቤታችን ብሥራተ መልአኩን ከተቀበለች በኋላ ‹‹እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዐቢያተ››አብ ቢሉ በልጁ ወልድ ቢሉ በሥልጣኑ ምድራዊ ባይደለ ሰማያዊ፤ ተፈጥሯዊ ባይደለ አምላካዊ፤ ጊዜያዊ ያይደለ ዘላለማዊ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል ብላ መስክራለች፡፡መዝ 86፥3 ፤ሉቃ 1፥49
እንዚራ መንፈስ ቅዱስ የተባለ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ስለ እመቤታችን በጻፈው ድርሰቱ በብዙ ሕብረ አምሳል እየመሰለ ሲያወድሳት ቢቆይም የእርሷን ክብርና ገናናነት ተናግሮ መፈጸም እንደማይቻል ከተረዳው በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሰውነቱ‹‹መኑ ዘይክል ነቢበ ዕበየኪ ወአልቦ ዘይመስል ኪያኪ›› ትርጉም ‹‹ክብርሽን ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማነው? አንቺን የሚመስልሽ የለምና››ሲል መልካም ነገርን አፍልቋል፡፡
የምሥጋና አባቱ(መምህሩ)ነቢዩ ዳዊት ስለ ጌታ እግዚአብሔር‹‹መኑ ይመስለከ እምነ አማልክት እግዚኦ›› ‹‹አቤቱ ከአማልክት አንተን የሚመስልህ ማነው?›› ብሎ የልዑሉን ገናናነት እንደተናገረ፤ ከአማልክት የሚተካከለው ያይደለ የሚቀርበው፤የሚቀርበው ያይደለ የሚመስለው የሌለ የልዑሉ ዙፋን፤እርሱን በማኅፀኗ ተሸክማ በሥጋ ወልዳ ዓለማትን በረቂቅ በግዘፍ የሚመግበውን ጡቶቿን አጥብታ ያሳደገች የእርሷንም ክብር ገናንነት መናገር አይቻልም ሲል በምሥጢር መስሎታል፡፡ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ
ጨምሮም ‹‹ዕበያ ለድንግል ኢይትከሀል ለተነግሮ እስመ እግዚእ ኀረያ›› የድንግል ክብሯ ጠንቅቆ ይነገር ዘንድ አይቻልም ጌታ መርጧታልና፡፡አብ ቢሉ ለልጁ ማደርያ እንድትሆን ወልድ ቢሉ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ ሰው ይሆን ዘንድ መርጧታልና፡፡ መምረጡንም ቅድመ ሥጋዌ ቢሉ በነቢያት ትንቢት፤ ጊዜ ሥጋዌ ቢሉ በመልአክ ብሥራት፤ ድኅረ ሥጋዌ ቢሉ ሥጋን ነስቶ በመታየት፣ በሐዋርያት ትምህርት፣ በሊቃውንት መጻሕፍት አስረድቶናል፡፡ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ምዕመናን፤ እንዲሁም በእምነት በቀኖና የሚመስሏቸው ሌሎች የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ዳዊት በመዝሙሩ‹‹ወዘሕጎ ያነብብ መዐልተ ወሌሊተ ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ፤እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቈፅላኒ ኢይትነገፍ›› እንዳለ የነቢያትን ትንቢት፣የሐዋርያትን ትምህርት፣ የሊቃውንትን የትርጓሜ ድርሳናት፣ ከንፁሕ ምንጭ ስለ አምላካቸው ታላቅነት፤ ስለ እመቤታችንም ንፅሕና ቅድስና ክብርና አማላጅነት ሲጠጡ በመኖራቸው ልምላሜ ነፍስ ሳይለያቸው ሥራ ሊሠሩ በተሰጣቸው ጊዜ የንስሐ ፍሬ የመንፈስ ፍሬ በማፍራት በትሩፋት ላይ ትሩፋት እየጨመሩ የእርሷን ጸጋ ክንፈ ረድዔት በማድረግ እንደ ንስር በመንፈሳዊ ሕይወትና እውቀት ሲመጥቁ ይታያሉ፡፡መዝ 1፥2-3
ክርስቲያን ለመባልና የልጅነትን ክብር ለማግኘት የቻልነው አካላዊ ቃል ከእመቤታችን ተወልዶ የቤዛነትን ሥራ በመፈጸም ዓለምን ካዳነ በኋላ ነው፡፡‹‹በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው›› እንዲል፡፡ ወረደ ተወለደ መከራን ተቀበለ ተሰቀለ ሞተ ተነሣዐረገ ዳግመኛ በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ ይመጣል ብሎ ሥጋን ተዋሕዶ በፈፀመው ሥራና ስመ ሥጋዌውን ስመ ሥርየት ስመ ድኅነት ነው በማለት ማመን ነው፡፡ይህ ሁሉ የተፈፀመ ከእርሷ በነሳው ሥጋ ነው ብሎ የሚያምን በነገረ ድኅነት ውስጥ ያለውን የእመቤታችንን ሱታፌ መገንዘብ አይሳነውም፡፡