Login
Main menu

መሻገር

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን !

 

የጳጉሜን ወር ከኖርንበት ለመኖር ተስፋ ወደ ምናደርግበት፤ ከሸኘነው ያለፈ ዓመት ወደ ምንቀበለው አዲስ ዓመት መሻገሪያ ናት፡፡ በባህላችንም በአዲስ ዓመት መባቻ ስንገናኝ የምንለዋወጠው መልካም ቃል ‹‹እንኳንከዘመንዘመንአሸጋገረን››   የሚል ነው ለመሆኑ ከዘመን ወደ ዘመን መሻገር ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ወደ አዲስ ዘመን ተሻገረ የምንለው እንዴት ነው? ወይስ ከዘመን ዘመን መሻገር ማለት ለዘመናት መቁጠሪያነት ጌታ እግዚአብሔር በጠፈር ላይ ያኖራቸውን ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ ወርኅ እና ዐውደ ከዋክብት ተጠቅመን የቀመርነውን የቀን አቆጣጠር አንድ ዐውድ ጨርሰን ሌላውን መጀመር ነው? 

 

ጌታ እግዚአብሔር ፍጥረታትን በጊዜ እየሠፈረ የፈጠረበት ምክንያት ፊት ያልነበሩ ኋላም ኃላፊ መሆናቸውን ሲያመለክተን ነው፡፡ ፍጥረታትን የሚሰፍር ጊዜ ባይኖር ኖሮ ሁሉ በቅድምና ነበረ ኋላም አያልፍም ለማለት የተመቸ ይሆን ነበር፡፡ ስለሆነም ፍጥረት መለወጥ ማርጀት እንዳለበት ለማጠየቅ ይህን ሂደት የሚሰፍርና የሚያሳውቅ መለኪያ ተሠራለት፡፡ በተጨማሪም ፍጥረታት በጊዜ ውስጥ መገኘታቸው፣ መኖራቸውና ኋላም ማለፋቸው ሠራዒ መጋቢ እንዳላቸው  በማመልከት ፍጥረት ሀለወተ እግዚአብሔርን ጮኾ እንዲመሠክር ያስገድዳል፡፡ ሥሉስ ቅዱስ ግን በባህርያቸው ውላጤ በዘመናቸው ብልየት የለበትምና ጊዜ ይሰፍረው ዘንድ አይችልም፡፡ ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው፡፡ እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጎናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤ ይለወጡማል፡፡ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም” እንዳለ፡፡ መዝ 101(102)፡ 25-27

 

በመሆኑም ከጌታ እግዚአብሔር ለፍጥረት የተቸረ የመጀመሪያ ሥጦታ ጊዜ መሆኑ የጊዜን ክብር የሚያሳይና የሰጪውንም ፍፁም ሥልጣን የሚገልጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜን እንደ ሰጠ የመንሳት ሥልጣንም የእርሱ ነውና፡፡ ኢሳ 38፡1-5 ፤ዳን 2፡21፤ የሐዋ.ሥራ 1፡7 ጌታ እግዚአብሔር ጊዜ የማይወስነው የፈቀደውን ለማከናወንም የጊዜ መስፈሪያነት የማያስፈልገው ቢሆንም ሥራውን(ልደተ ፍጥረትን) በጊዜ ውስጥ በማከናወን ጊዜ የተሰጠን ለሥራ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ጊዜ የማይወስነው በጊዜ ውስጥ ከሠራ ጊዜ የሚወስነንማ እንግዲያው እንደምን ልንጠቀምበት ይገባ? ዘፍ 1፡1

 

ጌታ እግዚአብሔር ጊዜን ምሳሌ በማድረግ የፍጥረትን ህልውና ሂደትና ግብ አሳይቶናል፡፡ በመጀመሪያ ጊዜንና በጊዜ ውስጥ ፍጥረትን በማምጣት ካለ መኖር ወደ መኖር፤ ካለ መታወቅ ወደ መታወቅ ዘመን አሻገረን፡፡ በዚህም ከጊዜ በፊት የነበረው ዘመን የማይቆጠርለት ጥንቱ በዚህ ጊዜ ነው ተብሎ በዘመን የማይሰፈረው ዘመንን የሚሰፍረው ለመኖሪያ ዓለም (space) የማያስፈልገው ራሱን ዓለም አድርጎ የሚኖር እርሱ የነበረበት ነው፡፡ ከዚያ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት የጊዜና የፍጥረት ልደት በአንዲት ቅጽበት ተበሠረ፡፡ ጊዜ ፍጥረትን ፍጥረትም ጊዜን ሳይቀድም ተገኙ፡፡ ኗሪና መኖሪያው፤ ተሰፋሪና መሥፈሪያው፤ ተቆጣሪና መቁጠሪያው በአንዲት ቅጽበት ተገኙ፡፡ ከዚያ አንስቶ ጊዜ ለፍጥረት መሥሪያ ሆኖ እያገለገለ ፍጥረትም በጊዜ ውስጥ እየሰራ ወደ ፍጻሜያቸው ይጓዛሉ፡፡ በመጨረሻም በአንድ ተጠቅልለው ፍጥረትም ጊዜም ያልፋሉ፡፡ ጊዜ ያለ ፍጥረት ፍጥረትም ያለ ጊዜ አልነበረም አይኖርምም፡፡

ያም ሆኖ ግን ከፍጥረታት መካከል በጊዜ ውስጥ እንደሚኖር የሚያውቅ(time concsuessness) ያለው ሰው ብቻ ነው፡፡

 

ከዚህ የመሥሪያ ጊዜ ቀጥሎ የምንሻገር በጊዜ ወደማይሰፈር የዕረፍት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን እምነት በጥርጣሬ፣ ዕውቀት በድንቁርና የማይፈተኑበት መበላለጥ፣ መቀዳደም፣ የሌለበት ሁሉ በትምህርት ሳይሆን በባህሪያዊ ዕውቀት ወደ ፈጣሪው የሚቀርብበት ዘመን ነው፡፡ በሌላ አገላለጥ የመጀመሪያው ዘመን እንደታወቅን የማናውቅበት፤ ሁለተኛው ዘመን መታወቃችንን በማመን በመጠራጠርና በመካድ ውስጥ የምንዋልልበት፤ ሦስተኛው ዘመን ደግሞ ንዴተ ህላዌ ፈጽሞ ጠፍቶልን እንደታወቅን የምናውቅበት ዘመን ነው፡፡ ቆሮ 13 ይህ በመለኮታዊው ዕቅድ ፍጥረት የሚያልፍበት የዘመን ሽግግር ነው፡፡ አሁን ባለንበት የመሥሪያ ዘመን ባጋጠመን መታለል ልንሆን የሚገባንን ለመሆን ስላልቻልን ይኸኛውም ዘመን ለሁለት ተከፍለ፡፡ የድንቁርና፣ የድካም፣ የጉስቁልና፣ የልቅሶ የጩኸት የፍዳ ንዑስ ዘመን እና የዕውቀት፣ የኃይል፣ የተሐድሶ፣ የምስጋና፣ የምህረት ንዑስ ዘመን ሆነ፡፡ ይህንንም ማድረግ የቻለ የዘመናት ባለቤት የሆነ እርሱ በሥጋ ልደት የዘመን አካፋይ ሆኖ በመገለጥ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው አሻገረን፡፡ የምህረት ዘመን ነው ስንል ግን አዋጅ በአዋጅ መለወጡ ለማጠየቅ እንጂ የሥራ(የተጋድሎ) ዘመን አብቅቷል ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” ቀን በማለት የአሁኑን የተጋድሎ ዘመን ፤ በሌሊት መስሎ ደግሞ የሚቀጥለው(ከሞት በኋላ) ሃይማኖት አጽንቼ የትሩፋት ሥራ ሠርቼ ዋጋ አገኛለሁ የማይባልባትን ዘመን አመልክቶናል፡፡ ዮሐ 9፡4   

 

በዚህ መሠረት ከዓመት ዓመት ስንሸጋገር ልብ ልንለው የሚገባ ዐቢይ ነጥብ ቢኖር ባለፈው ዓመት ምን ሠራሁ? በሚመጣውስ ምን ልሠራ ይገባኛል? የሚለውን ነው፡፡ ባለፈው ካልሠራን፤ ለሚመጣውም የኅሊና ዝግጁነትና ትንሳኤ ከሌለን ዘመን አልተሻገርንም፡፡ መሻገር ውስጥ ምን ጊዜም ለውጥ አለ፡፡ የሚታይ፣ የሚወራለት፣ የሚመሰከርለት፣ በቀጣይ ዘመን ውስጥ ሀልዎት እንዲኖረን የሚያስችል(የሚያበቃ) ሂደት አለ፡፡ በአጭሩ አንድ ሰው በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ሥራ ካልሠራ አልኖረም( ህልውና አልነበረውም) ማለት ነው፡፡ በጊዜ ውስጥ ለመሥራት ወይም ላለመሥራት ሥልጣን ተሠጥቶት የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው፡፡ ተጠየቅ ያለበትም ለዚህ ነው፡፡ ሌላው ፍጥረት ሁሉ የተገኘበትን ምክንያት በሥርዓተ ተፈጥሮ ፈጽሞ ያልፋል፡፡ ይህን የሚያደርጉ በፈቃድ ሳይሆን በቅድመ ውሳኔ ስለሆነ ምስጋናም ሆነ ወቀሳ የለባቸውም፡፡ ሰው ግን ይለያል፡፡ ምክንያተ ሀልዎቱን ዘንግቶ ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅና፣ ዐውደ ዓመትን በመቁጠር ብቻ ተወስኖ ከኖረ በቁሙ ሳለ ቁጥሩ ከሙታን ነው፡፡ ሙታናቸውን  እንዲቀብሩ ሙታንን ተውአቸው እንዳለ መጽሐፉ፡፡

 

በመሆኑም አንድ ሰው ከዓመት ዓመት፣ ከወር ወር፣  ከሳምንት ሳምንት፣ ከቀን ወደ ቀን ተሸጋገረ የምንለው ምክንያተ ተፈጥሮውን አክብሮ ወደ ቀጣዩ የፍጥረት ዐቢይ ዘመን የሚያሻግረውን የተወደደ ሥራ ሲሠራ፤ በሕይወቱ ላይ ለውጥ ታይቶ ለሌሎችም የለውጥ ምክንያት ሲሆን ነው፡፡ ምክንያተ ፍጥረቱን ዘንግቶ ከፈጣሪው ተለይቶ ከፍጥረተ ዓለም ተጣልቶ የምድርን ጸጋ እንደ ተምች በልቶ ለኖረባትና የሰው ዘር ለሚቀጥልባት የአዳም ማኅጸን ምንም ሳያበረክት፤ እየኖረ እንደሆነ የሚያስብ ከሆነ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ንግግር ከሰውነት ደረጃ ወርዶ የምግብ ማመላለሻ ቱቦ ሆኗል ማለት ነው፡፡

 


እንግዲያውስ ሰውነቱን ያመነ ራሱን በሚሸኘው ዓመት ምን ሠርቶ እንዳሳለፈ በአዲሱ ዓመት ደግሞ ምን ሊሠራ እንዳሰበ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ሰው ሆይ! ያለፈው ዓመት በስንፍና ማለት መማር ያለብህን ሳትማር፣ መሥራት ያለብህን ሳትሠራ፣ መወሰን ባለብህ ጉዳይ ሳትወስን፣ መለየት ከሚገባህ ሳትለይ፣ ኅብረት ማድረግ ካለብህ ጋር ሳታብር፤ መጀመር ያለብህን ሳትጀምርና ማቆም ያለብህን ሳታቆም ካለፈህ፤ ዘንድሮም ይኸው የሚደገም ከሆነ ዘመን የተሻገርከው እንዴት ነው? የአምና ትኩረትህ ምን ነበር? ፍቅር ወይስ ጥላቻ፣ ይቅርታ ወይስ ቂም፣ ምህረት ወይስ በሌሎች መፍረድ፣ ትጋት ወይስ ሀኬት፣ ቅንነት ወይስ ጥመት፣ ትህትና ወይስ እልከኝነት፣ ንፅህና ወይስ ርኵሰት፣ ንቃት ወይስ ድንዛዜ፣ ትጋት ወይስ ትካዜ፣ እኛ ማለት ወይስ እኔነት…. የቱ ነበር? አሁንስ ወደ አዲስ ዓመት የምትሻገር ይኸንኑ ይዘህ ነው?

 

ዛሬም መሆን የሚገባኝን የምሆነው፤ ማድረግ የሚገባኝንም የማደርገው፤ ከስንፍና ምንጣፍ የምነሳው፤ ካለመወሰን አዚም የምወጣው፤ ከማስመሰል ሕይወት የምላቀቀው መቼ ነው? እያልክ ከራስህ ጋር ትጣላለህ? ራስህን ትጠየፋለህ፣ ትንቃለህ? በራስህ ትማረራለህ? ውስጥህ የተፈጠረውን ሽንፈት የተቀረፀብህን ትንሽነት ለመደበቅ ዙሪያህ ያሉትን ሰላም ትነሳለህ?

 

እስኪ ራስህን ጠይቅ አጠገብህ ላሉት የሰላም፣ የዕረፍት፣ የብርታት፣ የደስታ፣ የስኬት፣ የመልካምነት፣ ምንጭ ነህ ወይስ በተቃራኒው? ከሆድህ የሚፈልቀው የሕይወት ውሃ ነው ወይስ የሞት መርዝ? ወንድሜ ሆይ! ሚስትህ ወደ ግድግዳ ዞራ መኝታዋን በዕንባዋ እንዳራሰች ለማልቀስ እንኳ ተሳቅቃ እንደ ተጨነቀች፤ እህቴም ባልሽ ከባልንጀሮቹ ተለይቶ በትካዜ የወንድ ምጥ እንዳማጠ ስሜቱ ከነገርሽ የተነሳ እንደቆመጠጠ ነው ዘመን የምንሻገረው? ልጆችህ በትናንሽ ዓይኖቻቸው አውሬ እንዳየ ተጨንቀው መሔጃ አጥተው ሲቸገሩ ትንሽ የማይራራ አንጀት ይዘህ መኖር እውነት ዘመን መሻገር ነው? በምቀኝነት ተመርዘህ፣ ቂም አርግዘህ፣ በጥላቻ ተገንዘህ፣ በአዲስ ጨርቅ ላይ አሮጌ ቅዳጅ ለመጣፍ እየዛበርህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ? መሆን ለምትችለው ለመትጋት ሀሞት ስታጣ ፈልገህ መርጠህ ባልሆንከው ተቧድነህ ልዩነትን እየሰበክህ፤ ከረገፈ የአባቶችህ አፅም በለስ ከመሰብሰብ ይልቅ ኩርንችት ለመልቀም እያደምህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ? ሌት አብራህ የተኛችውን ቀን ዘማ ብለህ እየወገርህ፤ አምኖህ ለክብርህ ከፊት የቆመውን በሥውር ጦማር እያስገደልህ፤ ለጽድቅህ ሚቃትተውን ደሙን መሠዊያው መሃል እያፈሰስህ ምኑን ዘመን ተሻገርህ?

 

ዘመን መሻገር ማለት አዲስ ማንነት መያዝ ነው፡፡ አርዌ ምድር ቆዳው ሲያረጅ ራሱን መሬት ውስጥ ይቀብርና አሮጌውን አውልቆ ጥሎ አዲስ ቆዳ ለብሶ ይወለዳል፡፡ የጌታን ቃሉን የምንሰማ የመንፈስ ቅዱስ ምክር በልባችን አድሮ አሮጌ ማንነታችንን አውልቀን አዲሱን ሰው ለመልበስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” እንዳለ፡፡ ኤፌ 4፡24 ዘመን መሻገር ማለት ከክፋት ወደ በጎነት፣ ከሀኬት ወደ ትጋት፣ ከድንቁርና ወደ ማይሻረው እውቀት መወለድ ነው፡፡ እስራኤል ከባርነት ወደ ነጻነት ዘመን እንዲሻገሩ በልዑሉ ክንድ በሙሴ መሪነት ከግብጽ በእግረ ሥጋ ቢወጡም ለአዲሱ ዘመን የተዘጋጀ ልቡና ስላልነበራቸው ዘመን ባለፈበት የኮመጠጠ የግብጽ እርሾ ቦክተው በበረሀ ሻግተው ቀርተዋል፡፡ የዘመናት ባለቤት የሆነውን ይዞ ዘመንን ዋጅቶ መኖር ከሁሉ ይጠበቃል፤ ለትዕግስት ዘመን እንዳለ ሁሉ ለመተፋትም ዘመን አለና፡፡ ምክንያተ ፍጥረትን ሳያውቁ የሕይወት ብርሃን ከሆነው ከእርሱ ተለይቶ መኖር ኑሮ አይባልም፡፡ አባቶች ጌታ ከተወለደባት ጊዜ ጀምሮ አንድ ብለው የቆጠሩ ከእርሱ ጋር ያልነበርንበትን ዘመን እንዳልኖርንበት መቁጠራቸውን ያሳያል፡፡ “አማኑኤል” እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ በኋላ የሰው ልጅን ዕድሜ ከፈጣሪው ዕድሜ ጋር አንድ ብለን መቁጠር ጀመርን፡፡ ወደ ዘላለም ከገባው ጋርም ወደ ዘላለም ጊዜን ተሻግረን እንገባለን፡፡

 

ሦስተኛዋ ዘመን በኃጢአት የረከሰ ሰውነት፣ በቂም በጥላቻ የተሞላ ልቡና፣ በእኔ ባይነት የተቀሰፈ ኅሊና የያዘ ተሻግሮ ሊገባባት የሚችል አይደለችም፡፡ ሲያይ የማይታየውን ያልፈራች ሰውንም ያላፈረች ዓይን በሶስተኛው ዘመን ያለውን የሚያስደንቅ ክብር ማየት አይቻላትም፡፡ ሐሜትና ከንቱ ነገርን የጠገበች ዦሮም አዲሱን የበጉን ቅኔ ለመስማት አትታደልም፡፡ ባልንጀራዋን በመሸንገል በመሰሏም በመፍረድ በስድብና በእርግማን የተሞላች አንደበትም የቅዱሱን ስም በህያዋን ምድር ለማመስገን አይፈቀድላትም፡፡ አዲሲቷ ሰማይና አዲሲቷ ምድር ኃጢአት ሊፈፀምባቸው አይደለም ሊታሰብባቸው እንኳ የሚቻልባቸው አይደሉም፡፡ በዚህች ምድር የሚኖሩም ዕረፍት ወደ ሆነችው ሦስተኛዋ ዘመን መሻገር የቻሉ ንፁሐን ብቻ ናቸው፡፡ 

 

የባህረ ሐሳብ ሊቃውንት የጳጉሜን የመጨረሻ ቀን “ምርያ” ብለው ይጠሯታል፡፡ አእዋዲት፣ መድኃኒት ማለት ናት፡፡ አእዋዲት ማለት የምታዘዋውር ማለት ሲሆን፤ መድኃኒት የተሰኘች ጌታ የተወለደባትን ቀን ስለ ምታሳይ ነው፡፡ ዕለተ ምርያ እና የጌታ ልደት የሚውሉ አንድ ዕለት ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ዕለተ ምርያ ሰኞ ትውላለች የጌታ ልደት ታህሣስ 29 የሚውለውም ሰኞ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በምሥጢር ዘመን አሻጋሪያችን እርሱ መድኃኒታችን መሆኑን ያመለክታል፡፡ መድኃኒታችን “ኑ ወደ ባህሩ ማዶ እንሻገር” ይለናል፡፡ እንደ ሊቃውንቱ ትርጓሜ ባህር የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ የሚያሻግረንን አምነን ከእርሱም ጋር ኅብረት ኖሮን የዓለምን ሥራ ትተን በትንሣኤ ኅሊና ዘመን መሻገር ይኖርብናል፡፡ ሉቃ 8፡22-5 ከዚህም በተጨማሪ የብሉይ ኪዳን መካተቻ እና የአዲስ ኪዳን መባቻ ላይ የነበረውን ንጹሑን፣ ቅዱሱን፣ እውነተኛውን ነቢይና ሐዋርያ፣ ካህንና ሰማዕት፣ ባህታዊና ድንግል ዮሐንስ መጥምቅን ሕይወት አብነት እንድናደርግ በሄሮድስ ታሥሮ የቆየባትን የጳጉሜን ወር እና ምትረተ ርዕሱን እንድናስብ አበው መሥራታቸው ዘመን ከምሥጢር ጋር ያለቸውን ዝምድና እንድናውቅ ለመጠቆም ነው፡፡ ዮሐንስ ሦስተኛውን ዘመን እውን ወደ ሚያደርገው ሙሽራ ሙሽራይቱን ለማድረስ መንገዱን ጠርጓል፡፡ የፈቀዱትን አዘጋጅቷል፣ ደስታውም ተፈጽሞለታል፡፡ የሰሙትም ወደ ምህረት ዘመን ተሻግረው የአባቶቻቸውን ተስፋ ፍጻሜ ዐይተዋል፡፡  አባቶቻችን ከቃል ትምህርት ባለፈ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በሚከሰተው ዓውደ ዓመታችን ታላቅ ምልክትን ትተውልን አልፈዋል፣ እኛ ግን አላስተዋልንም፡፡ ጌታ “ሰማዩ አቀላልቷል ዛሬ ይዘንማል ትላላችሁ፤ የሰማዩን ፊት ታውቃላችሁ የዘመኑን ምልክት መለየት እንዴት አቃታችሁ” እንዲል፡፡ ዘመን ሳንሻገር ስንት ዘመን እንዳሻገርን ማን ይቁጠር? ለማንኛውም . . . 

 

 

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

 

                                           ቀሲስ ታምራት ውቤ                                             2011 ዓ.ም

Read more...

ጠቃሚ አድራሻዎች

መጻሕፍት ቢያነቧቸው

  • * ​ፍቅር 
  • ፍና ቅዱሳን
  • * የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱ እና ትምህርቱ 
  • * ዝጎራ